የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
በእውነት ታዛዥ የሆኑት አይወድቁም
ዓለም የእግዚአብሔርን ሕግ ስትጥስ ከእውነተኛ ልባቸው ታዛዥና ጻድቃን በሆኑት ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖራታል? ጠንካራ በሆነው የክፋት ማዕበል ተጠራርገው ይወሰዳሉን? ብዙዎች ራሳቸውን በጨለማው መስፍን ባንዲራ ሥር ስለሚያሰልፉ ትዕዛዛትን ጠባቂ የሆኑ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ለአምላካቸው ያላቸውን ታማኝነት ይለውጣሉን? በፍጹም አያደርጉም! በክርስቶስ ያለ አንድም ሰው ታማኝነቱን አይለውጥም ወይም አይወድቅም፡፡ የእሱ ተከታዮች ከማንኛውም ምድራዊ ገዥ ይልቅ ከፍ ላለው ባለሥልጣን በመታዘዝ ያመልኩታል፡፡ በእግዚአብሔር ትዕዛዝ ላይ የተፈጸመው ንቀት ብዙዎች እውነትን እንዲጨቁኑና ዝቅተኛ ክብር እንዲሰጡ ቢመራቸውም ታማኝ የሆኑት ሰዎች ከበፊቱ በበለጠ ትጋት የተለዩ እንዲሆኑ የሚያደርጉአቸውን እውነቶች ከፍ አድርገው ይይዛሉ፡፡ ራሳችንን በራሳችን እንድንመራ አልተተውንም፡፡ በመንገዳችን ሁሉ እግዚአብሔርን ማወቅ አለብን፤ እርሱም መንገዳችንን ያቀናልናል፡፡ ትሁት በሆነ ልብ ከቃሉ ምክር በመቀበል ከእግዚአብሔር ምክርን መጠየቅና ፈቃዳችንን ለፈቃዱ ማስገዛት አለብን፡፡ ያለ እግዚአብሔር ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ Amh2SM 368.2
እውነተኛው ሰንበት የእግዚአብሔር ሕዝብ ከዓለም እንዲለይ የሚያደርግ ምልክት ስለሆነ ዋጋ ለመስጠትና ከጥቃት ለመከላከል በቂ ምክንያት አለን፡፡ ዓለም የእግዚአብሔርን ሕግ ከመሻሩ የተነሳ የእግዚአብሔር ሕዝብ ለአምላካቸው ሕግ ከፍተኛ ክብር ይሰጣሉ፡፡ ከሃዲዎች ለእግዚአብሔር ሕግ ያላቸውን ንቀት የሚያሳዩበት ጊዜ ታማኝ ካሌቦች የሚጠሩበት ጊዜ ነው፡፡ የታይታ ሰልፍ ሳይሰለፉና ከነቀፌታ የተነሳ ሳይናወጡ በተመደቡበት ቦታ ጸንተው የሚቆሙት ያኔ ነው፡፡ እምነት ያልነበራቸው ሰላዮች ካሌብን ለማጥፋት ተዘጋጅተው ቆሙ፡፡ የሀሰት ዘገባ ይዘው በመጡት ሰላዮች እጅ ለመውገር ያዘጋጁትን ድንጋይ ተመለከተ፤ ነገር ግን ይህ ድርጊታቸው እውነትን ከመናገር አላገደውም፡፡ መልእክት ስለነበረው መልእክቱን ማስተላለፍ ነበረበት፡፡ ዛሬም ለእግዚአብሔር ታማኝ በሆኑ ሰዎች ላይ ተመሳሳይ የሆነ መንፈስ ይንጸባረቃል፡፡ Amh2SM 369.1
ዘማሪው እንዲህ ይላል፣ «ሕግህን ሻሩት፤ ስለዚህ ከወርቅና ከእንቁ ይልቅ ሕግህን ወደድሁት” (መዝ. 119፡ 126፣ 127)፡፡ ሰዎች ወደ ኢየሱስ ሲጠጉና ክርስቶስ በእምነት በልባቸው ሲያድር ዓለም በእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል ላይ የንቀት ናዳ ከሚያወርደው በበለጠ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ሕግጋት ያላቸው ፍቅር እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ ይህ ጊዜ እውነተኛው ሰንበት በቃልና በጽሁፍ ለሕዝብ መድረስ ያለበት ጊዜ ነው፡፡ አራተኛው ትዕዛዝ እና ይህንን ትዕዛዝ የሚጠብቁት ተቀባይነት ሲያጡና ሲናቁ እምነታቸውን የሚደብቁበት ሰዓት ሳይሆን የሶስተኛውን መልአክ መልእክት፣ የእግዚአብሔር ሕግጋትና የኢየሱስ ኃይማኖት የሚል ጽሁፍ ያለበትን ባንዲራ በማውለብለብ የያህዌን ሕግ ከፍ ከፍ የሚያደርጉበት ጊዜ ነው፡፡ Amh2SM 369.2