የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ የሚቀርቡ ጉድለት ያለባቸው አቀራረቦች
የመንፈስ ቅዱስ አስፈላጊነትን በተመለከተ ብዙ እየተባለ ሲሆን አንዳንዶች ይህን ጉዳይ ቤተ ክርስቲያናትን በሚጎዳ ሁኔታ እየተረጎሙት ነው፡፡ የዘላለም ሕይወት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን ሕያው የሆኑ መሠረታዊ ነገሮች መቀበልና የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ነው፡፡ ይህ የእግዚአብሔርን ልጅ ሥጋ መብላትና ደሙን መጠጣት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እውነትነት ያለው እና እውነት፣ መንፈስና ሕይወት ስለሆነ፣ ይህን ለሚያደርጉ በወንጌል አማካይነት ሕይወትና ሕያውነት ግልጽ ይሆኑላቸዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል መመገብ ልዩ መብት ነው፡፡ ያንን ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስን፣ ዘላለማዊ እውነትን፣ በጸሎት ለሚመረምር ሰው የመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ መንፈሳዊ ጅማትና ጡንቻ ይሰጠዋል፡፡ {2SM 38.4} Amh2SM 38.4
ክርስቶስ «እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱ ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው” ብሏል (ዮሐ. 5፡ 39)፡፡ አጥልቀው የሚቆፍሩ ሰዎች የተደበቁ የእውነት እንቁዎችን ያገኛሉ፡፡ ከልቡ ተግቶ ከሚመረምር ሰው ጋር መንፈስ ቅዱስ አብሮ አለ፡፡ የእሱ ብርሃን ለእውነት አዲስና ንጹህ የሆነ አስፈላጊነትን በመስጠት በአእምሮ ውስጥ ለማተም በቃሉ ላይ ይበራል፡፡ ቃሉን የሚመረምር ሰው ከዚህ በፊት በፍጹም ተሰምቶት በማያውቅ የሰላምና የደስታ ስሜት ይሞላል፡፡ የእውነት ክቡርነት ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ ግንዛቤ ያገኛል፡፡ እያንዳንዱ ፊደል ከወርቅ ጋር የተቀላቀለ እስኪመስል ድረስ በላዩ በማብራት አዲስ፣ ሰማያዊ ብርሃን በቃሉ ላይ ያበራል፡፡ ቃሉን መንፈስና ሕይወት በማድረግ እግዚአብሔር ራሱ ለአእምሮና ለልብ ተናግሯል፡፡ {2SM 39.1} Amh2SM 39.1
እያንዳንዱ እውነተኛ ቃሉን የሚመረምር ሰው የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ በመጠየቅ ልቡን ወደ እግዚአብሔር ያነሳል፡፡ ብዙም ሳይቆይ ደካማና እየተፍረከረኩ ያሉ ጽንሰ-ሀሳቦቹ በሕያው እግዚአብሔር ቃል ካልተደገፉና አስተማሪ ለመሆን ከሚሞክር ሰው ልበ-ወለድ ንግግሮች በላይ ያደረገውን ነገር ለይቶ ያውቃል፡፡ እነዚህ ንድፈ ሀሳቦች የእግዚአብሔር መንፈስና ሕይወት በቃሉ ውስጥ እንዳሉ የሚገልጸውን የመጀመሪያውን ታላቅ ትምህርት ባልተማሩ ሰዎች የተፈለሰፉ ናቸው፡፡ በልባቸው ውስጥ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ያለውን ዘላለማዊ የሆነ መሠረታዊ ነገር ተቀብለው ቢሆን ኖሮ ልዩ ስሜት ለመፍጠር ሲባል የሆነ አዲስ ነገር ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ ምን ያህል ደብዛዛ እና መግለጫ የሌላቸው እንደሆኑ ማየት ይችሉ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል የመጀመሪያዎቹን መርሆዎች መማር ያስፈልጋቸዋል፤ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተስፋ ቃል በሰጣቸው መሠረት ከዚያ በኋላ ለሕዝቡ የሕይወት ቃል ይኖራቸዋል፤ ሕዝቡም ስንዴውን ከገለባ ለይቶ ያውቃል፡፡ --Letter 132, 1900. {2SM 39.2} Amh2SM 39.2