የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
ኤለን ኋይት የሞት ሀዘን በደረሰባት ጊዜ
በቅርቡ በደረሰብኝ ሀዘን ዘላለማዊነትን በቅርበት አይቻለሁ፡፡ በታላቁ ነጭ ዙፋን ፊት እንድመጣ ተደርጌ ሕይወቴ እዚያ ምን እንደሚመስል አይቻለሁ፡፡ ምንም ሊያኮራኝ የሚችል ነገር አላገኝም፣ ምንም አለኝ የምለው መልካም ነገር የለም፡፡ «አምላኬ ሆይ፣ ከአንተ ቸርነት ትንሽ እንኳን የሚገባኝ አይደለሁም» የሚለው ጩኸቴ ነው፡፡ ብቸኛው ተስፋዬ በተሰቀለውና በተነሳው አዳኝ ነው፡፡ የክርስቶስ ደም የሚያስገኘውን ጥቅም እጠይቃለሁ፡፡ ኢየሱስ በእርሱ የሚታመኑትን እስከ መጨረሻው ያድናቸዋል፡፡ Amh2SM 267.3
አንዳንድ ጊዜ ልቤ በሀዘን ሲቀደድ ደስተኛ ፊት ማሳየት ይከብደኛል፡፡ ነገር ግን ሀዘኔ ዙሪያዬን ሁሉ እንዲያደበዝዘው አልፈቅድም፡፡ ከልክ በላይ ማዘን ልማድ ስለሆነብን ብዙ ጊዜ የመከራና የሀዘን ጊዜያቶች መሆን ከሚገባቸው በላይ ሀዘንና ተስፋ መቁረጥን ያስከትላሉ፡፡ በኢየሱስ እርዳታ ይህን ክፉ ለመሸሽ ወሰንኩ፤ ነገር ግን ውሳኔዬ ክፉኛ ተፈትኖ ነበር፡፡ የባለቤቴ ሞት ድንገተኛ ስለነበር እጅግ የተሰማኝ ሲሆን ለእኔ ከባድ ምት ነበር፡፡ በፊቱ ላይ የሞት ማህተም በተመለከትኩ ጊዜ ስሜቶቼን ለመቆጣጠር ከባድ ነበር፡፡ ከሀዘኔ የተነሳ ለማልቀስ ተመኘሁ፡፡ ነገር ግን ይህ ውዴን ሊያድነው እንደማይችል ስላወቅኩ ራሴን ለሀዘን አሳልፌ መስጠት ክርስቲያናዊ እንዳልሆነ ተሰማኝ፡፡ ከላይ እርዳታንና መጽናናትን ፈለግኩ፣ የእግዚአብሔር ተስፋዎችም ተረጋገጡልኝ፡፡ የጌታ እጅ አቆመኝ፡፡ ከገደብ ያለፈ ማዘንና ማልቀስ ኃጢአት ነው፡፡ በክርስቶስ ጸጋ ከባድ በሆነ ፈተና ውስጥ እንኳን የተረጋጋንና ደስተኞች ልንሆን እንችላለን፡፡ Amh2SM 267.4
ክርስቶስ ለደቀመዛሙርቱ ካቀረበው ከመጨረሻው ቃለመጠይቅ የድፍረትንና የጽናትን ትምህርት እንማር፡፡ ለመለያየት ተቃርበው ነበር፡፡ አዳኛችን ወደ ቀራኒዮ ወደሚመራው በደም ወደተቀለመ መንገድ እየገባ ነበር፡፡ እሱ በቅርቡ ሊያልፈበት ካለው መንገድ የበለጠ ፈታኝ መንገድ የለም፡፡ ደቀመዛሙርቱ ክርስቶስ ስለሚደርስበት መከራና ሞት አስቀድሞ የነገራቸውን ቃላት ስለሰሙ ልቦቻቸው በሀዘን ከብደዋል፣ አእምሮዎቻቸውም በጥርጣሬና በፍርሃት ተሞልተዋል፡፡ ሆኖም ጮክ ያለ ጩኸት አልነበረም፤ ከሀዘን የተነሳ ከድቶ መሄድም አልነበረም፡፡ እነዚያ የመጨረሻዎቹ ከባድ፣ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሰዓታት ያለፉት አዳኛችን ለደቀ መዛሙርቱ የማጽናኛና የማበረታቻ ቃላት በመናገርና ሁሉም በዝማሬና በምስጋና አንድ በመሆን ነበር፡፡. . . . Amh2SM 268.1