የልጅ አመራር
ምዕራፍ 30—በራስ መደገፍ እና የአክብሮት ስሜት
እያንዳንዱ ልጅ በራስ መደገፍ እንዲችል ያሠለጥኑ—በተቻላው መጠን እያንዳንዱ ልጅ በራስ ስለ መደገፍ መሰልጠን አለበት። የተለያዩ ችሎታዎችን በመጠቀም ምን ላይ ጠንካራ እንደሆነ እና በምን ጉድለት እንዳለው ይማራል፡፡ ጥበበኛ መምህር ልጅ ሚዛናዊ እና የሚስማማ ባህሪይ ይኖረው ዘንድ ለደካማ ባህሪያት እድገት ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡275 CGAmh 148.1
እጅግ ብዙ ምቾት ልፍስፍስነትን ያደብራል—ወላጆች በሕይወት በሚኖሩበት ጊዜ፣ ልጆቻቸው ራሳቸውን እንዲረዱ ቢረዷቸው ኖሮ፣ ሲሞቱ ጠርቀም ያለ ሐብት ከሚተውላቸው ይልቅ የተሻለ በሆነ ነበር፡፡ በአብዛኛው በራሳቸው ጥረት እንዲደገፉ የተተው ልጆች የተሻሉ ወንዶችና ሴቶች ሲሆኑ በአባታቸው ንብረት ላይ ከሚደገፉ ልጆች በተሻለ ለተግባራዊ ሕይወት ብቁ ናቸው፡፡ በራሳቸው ንብረት እንዲደገፉ የተተው ልጆች በአጠቃላይ ለችሎታዎቻቸው ዋጋ ይሰጣሉ፣ አጋጣሚዎቻቸውን ያሻሽላሉ፣ እንዲሁም የሕይወት ዓላማን ለማሳካት ችሎታዎቻቸውን ያዳብራሉ፣ ያቀናሉም፡፡ በክርስትና ሕይወት ውስጥ ለስኬት መሠረት የሆነውን ታታሪነትን፣ የቁጠባን እና የግብረ-ገብ መልካም ባህሪያትን ዘወትር ያሳድጋሉ፡፡ ወላጆች ብዙ የሚያደርጉላቸው ልጆች ብዙውን ጊዜ ለእነርሱ አነስተኛ ግዴታ እንዳላቸው ይሰማቸዋል፡፡2 CGAmh 148.2
እንቅፋቶች ጥንካሬን ያመጣሉ—ሰዎችን የሚያጠናክሩ እንቅፋቶች ናቸው። የግብረ-ገብን ጥንካሬ የሚፈጥረው እርዳታ ሳይሆን ችግሮች፣ ግጭቶች፣ ጠንከር ያሉ ነቀፋዎች ናቸው፡፡ እጅግ በብዙ ምቾት መኖር እና ኃላፊነትን ማስወገድ የግብረ-ገብ ኃይል እና የመንፈሳዊ ጡንቻ ጥንካሬ ያላቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎችን ልፍስፍስ እና የቀጨጩ አድርጓቸዋል። 276 CGAmh 148.3
ወጣቶች ወደ ከፍተኛው የወንዶች እና ሴቶች አካለመጠን ደረጃ ላይ መድረስ እንዲችሉ ከልጅነት ዕድሜያቸው ጀምሮ ጽኑ የሐቀኝነት ባህሪይ መርሆዎች ላይ መጣመር አስፈላጊ ነው። በዋጋ የመገዛታቸውን ሐቅ ዘወትር ከእይታቸው መሰወር የለባቸውም፣ የእርሱ በሆነው ሰውነት እና መንፈሳቸውም እግዚአብሔርን ማክበር አለባቸው፡፡ ወጣቱ ዓላማዎቻቸው እና የሕይወት ተግባራቸው ምን እንደ ሆነ በጥልቀት ማሰብ እና ልማዶቻቸው ከማናቸውም ብልሹ ሥነ-ምግባር ነፃ በሚያሆን ሁኔታ መሰረትን መጣል አለባቸው፡፡ ሌሎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉበት ሁኔታ ላይ ቢሆኑ በራሳቸው የሚደገፉ መሆን አለባቸው፡፡ 277 CGAmh 149.1
ልጆች ችግሮችን በድፍረት መጋፈጥ እንዲችሉ አዘጋጇቸው—ከቤትና ከትምህርት ቤት ልምምድ ባሻገር፣ ሁሉም ከባድ የሕይወትን ልምምድ መጋፈጥ አለባቸው። ይህንን እንዴት በጥበብ መጋፈጥ እንደሚቻል ለእያንዳንዱ ልጅ እና ለእያንዳንዱ ወጣት ግልፅ መደረግ ያለበት ትምህርት ነው፡፡ እግዚአብሄር እንደሚወደን፣ ለደስታችን የሚሰራ መሆኑን እና ህጉን ሁል ጊዜ ብንታዘዝ ኖሮ ሥቃይን በጭራሽ አለማወቃችን እውነት ነው፤ እንዲሁም ስቃይ፣ ችግር እና ጫናዎች በእያንዳንዱ ነፍሳት ላይ የመጣው በኃጢያት ምክንያት መሆኑ ያነሰ እውነታ አይደለም፡፡ ልጆች እና ወጣቶች እነዚህን ችግሮች እና ሸክሞች በድፍረት እንዲጋፈጡ በማስተማር የዕድሜ ልክ መልካም ሥራዎችን ልንሰራ እንችላለን፡፡ ልናዝንላቸው ቢገባም እንኳ ፈጽሞ ለራሳቸው ማዘናቸውን በሚያበረታታ መልኩ መሆን የለበትም፡፡ እነርሱ የሚያስፈልጋቸው ደካማ ከሚያደርጋቸው ይልቅ የሚያነቃቃቸው እና የሚያበረታታቸው ነው፡፡ CGAmh 149.2
ይህ ዓለም የፈንጠዚያ ሜዳ ሳይሆን የጦር ሜዳ እንደሆነ መማር አለባቸው። ሁሉም እንደ መልካም ወታደሮች መከራን ለመቋቋም ተጠርተዋል፡፡ ራሳቸውም እንደ ሰው ጠንካራ እና ጽኑ መሆን አለባቸው። ምንም እንኳን ምድራዊ እውቅና ወይም ሽልማት የማያመጣ ባይሆንም እንኳ የባህሪይ እውነተኛ መፈተኛ ሸክሞችን ለመሸከም፣ አስቸጋሪ ሥፍራን ለመያዝ፣ ሊከናወን የሚገባውን ስራ ለመስራት ፈቃደኛ በመሆን እንደ ሆነ ይማሩ፡፡ 278 CGAmh 149.3
የአክብሮት ስሜትን ማጎልበት—ብልሁ አስተማሪ በተማሪዎቹ አያያዝ ላይ በራስ የመተማመን እና የአክብሮት ስሜትን ለማበረታታት ይሻል። ልጆች እና ወጣቶች እምነት ሲጣልባቸው ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ብዙዎች፣ ትንንሽ ልጆችም እንኳ፣ ከፍተኛ የአክብሮት ስሜት አላቸው፤ ሁሉም ምስጢርን በመጠበቅ እና በአክብሮት መያዝን ይፈልጋሉ፣ ይህም መብታቸው ነው፡፡ ክትትል ሳይደረግላቸው መውጣት ወይም መግባት እንደማይችሉ እንዲሰማቸው መመራት የለባቸውም፡፡ ጥርጣሬ በራሱ ለማስወገድ የሚሻውን ክፋት በመፍጠር ባህሪይን ያበላሻል…፡፡ ወጣቱ እምነት ሲጣልበት እንደሚታመን እና እምነት ሲጣልባቸው የማይታመኑ ጥቂቶች እንደሆኑ እንዲሰማቸው ምሯቸው።279 CGAmh 150.1