የልጅ አመራር

24/85

ምዕራፍ 22—ትጋት እና ጽናት

በተግባራት መጠናቀቅ የሚገኝ እርካታ—ልጆች ብዙውን ጊዜ በስሜት አንድን ሥራ ይጀምራሉ፤ ነገር ግን በሥራው ግራ ተጋብተው ወይም ተዳክመው ይቀይሩትና አዲስ ነገር ለመጀመር ይሻሉ፡፡ እንደዚሁም ብዙ ነገሮችን ሊነካኩ ይችላሉ፣ ትንሽ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሲገጥማቸው፣ ትተውትና ምንም ሳይፈጽሙ ከአንድ ነገር ወደ ሌላ ነገር ያልፋሉ፡፡ ወላጆች የመለዋወጥ ፍቅር ልጆቻቸውን እንዲቆጣጠር መተው የለባቸውም። በማደግ ላይ ያለውን አዕምሮ በትዕግስት ሥርዓታዊ ለማድረግ ጊዜ በማይኖራቸው ነገሮች መያዝ የለባቸውም፡፡ ጥቂት የማበረታቻ ቃላት ወይም በትክክለኛው ጊዜ የሚደረግ ጥቂት እገዛ፣ ችግሮቻቸውን እና ተስፋ መቁረጣቸውን ያሸንፉ ዘንድ ይረዳቸዋል፣ እናም ተጠናቅቆ የተሰራ ሥራ በማየታቸው የሚያገኙት እርካታ ለላቀ ጥረት ያነሳሳቸዋል፡፡ 219 CGAmh 121.1

ብዙ ልጆች የማበረታቻ ቃላትን እና በጥረታቸው ውስጥ ትንሽ እርዳታ ከማጣታቸው የተነሳ ተስፋ ቆርጠው ከአንድ ነገር ወደ ሌላ ነገር ይለውጣሉ። እናም ይህንን አሳዛኝ ጉድለት እስከ ጎልማሳነት ሕይወታቸው ድረስ ይዘው ይቆያሉ፡፡ ተስፋ በሚያስቆርጥ ሁኔታ ውስጥ ጸንተው መቆምን ስላልተማሩ በተሰማሩበት በማናቸውም ነገር ስኬትን ማግኘት ያቅታቸዋል፡፡ ስለሆነም ገና ወጣት በነበሩበት ጊዜ ተገቢ ትምህርት ስላልነበራቸው የብዙዎች መላ የሕይወት ዘመን ውድቀት እንደሆነ አስረግጧል፡፡ በልጅነት እና በወጣትነት የሚሰጥ ትምህርት መላ የጎልማሳነት ሕይወት ሥራ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል፣ እናም የሃይማኖታዊ ልምዳቸው ተጓዳኝ አሻራ ይኖረዋል፡፡ CGAmh 121.2

የስንፍና ባህሪያት እስከ ኋለኛው ዕድሜ ድረስ ይዘልቃል—የተሞላቀቁ እና ይህን የሚሹ ልጆች ሁልጊዜ ያንኑ ይጠብቃሉ፤ እናም የሚጠብቁት ነገር ሳይፈጸም ሲቀር ቅር ይሰኛሉ፣ ተስፋም ይቆርጣሉ። ይህ ተመሳሳይ ባሕርይ በመላው ህይወታቸው ይታያል፤ ሌሎች እንዲደግፏቸው እና እንዲረቱላቸው በመሻት፣ ረዳት አልባ፣ ለእርዳታ ሌሎች ላይ የሚደገፉ ይሆናሉ፡፡ ለአካለ መጠን ከደረሱ በኋላም እንኳ፣ ተቃውሞ የደረሰባቸው እንደሆነ፤ ጥቃት የደረሰባቸው ይመስላቸዋል፤ እናም በዓለም ውስጥ በሚያደርጉት ጉዞ ይጨነቃሉ፣ ሸክማቸውን ለመሸከም አቅቷቸው፣ አብዛኛውን ጊዜ ሁሉ ነገር ለእነርሱ አመቺ ስላልሆነ ያጉረመርማሉ ይጨነቃሉም፡፡ 220 CGAmh 121.3

ጠንቃቃነት እና የቅልጥፍና ልምዶችን ማካበት—ልጆት ከእናት የሥርዓታዊነትን፣ የጠንቃቃነትን እና የቅልጥፍና ልምዶችን መማር አለባቸው። አንድ ልጅ በግማሽ ሰዓት ውስጥ በቀላሉ ሊከናወን የሚችል አንድን ሥራ ለመስራት አንድ ወይም ሁለት ሰዓት እንዲወስድበት መፍቀድ የቀርፋፋነት ልምዶችን እንዲያዳብር መፍቀድ ነው፡፡ ለወጣቶች የታታሪነት እና የጠንቃቃነት ልምዶች እያጎለመሱ ሲሄዱ የሚገቡበት ይህ ነው የማይባል በረከት ያለው የህይወት ትምህርት ቤት ይሆናል፡፡ 221 CGAmh 122.1

ምክር በተለይም ለሴት ልጆች—ብዙ እንድጨነቅ እና እንድረበሽ ያደረገኝ ሌላው እንከን አንዳንድ ልጃገረዶች ምላሳቸውን ልቅ በማድረግ ውድ ጊዜያቸውን ዋጋ አልባ የሆኑ ነገሮችን በማውራት ማሳለፋቸው ነው፡፡ ልጃገረዶች ለወሬ ትኩረት ሲሰጡ ስራቸው ግን ወደ ኋላ ይጓተትባቸዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች እንደ ትናንሽ ነገሮች ተደርገው ታይተዋል። ብዙዎች ጥቃቅን ነገሮች ምን እንደ ሆኑ ባለማወቅ ተታልለዋል። ጥቀቅን ነገሮች ሊሰራ ከታሰበው ትልቅ ነገር ጋር አስፈላጊ የሆነ ግንኙነት አላቸው፡፡ እግዚአብሔር ከሰብአዊው ቤተሰብ ድነት ጋር የሚዛመዱትን እጅግ በጣም ጥቃቅን የሆኑ ነገሮችን አይንቅም፡፡ 4 CGAmh 122.2

የ“ጥቃቅን ነገሮች” አስፈላጊነት—ለጥቃቅን ነገሮች አስፈላጊነት በጭራሽ ዝቅተኛ ግምት አይስጡ። ትናንሽ ነገሮች ትክክለኛውን የህይወት ትምህርት ይሰጣሉ። ነፍስ ወደ ክርስቶስ አምሳያነት ለማደግ ወይም የክፉን ምሳሌ ለመያዝ የምትሰለጥነው በእነርሱ ነው፡፡ ከኢየሱስ ጋር መኖራችንን እና ከእርሱ መማራችንን ስለ እኛ ለሁሉም የሚመሰክውን የአስተሳሰብ፣ የቃል፣ የእይታ፣ እና የድርጊት ልምዶችን እንድናዳብር እግዚአብሔር ይርዳን! 222 CGAmh 122.3

ስህተቶችን እንደ መወጣጫ ድንጋይ ያድርጉ—ልጆች እና ወጣቶች ድል የነሷቸው እያንዳንዱ ስህተት፣ እያንዳንዱ ጥፋት፣ እያንዳንዱ ችግር ወደ ተሻለ እና ከፍ ወዳሉ ነገሮች የመወጣጫ ድንጋይ እንደሚሆኑ ይማሩ፡፡ ለሕያዋን ተገቢ የሆኑ የሕይወት ስኬቶች ሁሉ የተገኙበት በእነዚያ ልምዶች አማካይነት ነው፡፡ 223 CGAmh 123.1