የልጅ አመራር
ምዕራፍ 64—ቤት እና ራስን የመግዛት ክሩሴድ
ራስን መግዛት ችላ ተብሏል− ራስን አለመግዛት የውድመት ሥራውን ቀጥሏል፡፡ ኃጢአት በየትኛውም መልኩ የእውነት እና የጽድቅ ዕድገት ታላቅ መሰናክል ሆኖ ቆሟል፡፡ ድንቁርና እና ምግባረ ብልሹነት የወለዷቸው ማህበራዊ ስህተቶች ሊነገር ለማይቻል ስቃይ መንስኤ በመሆን በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም ላይ ክፉ ጥላቸውን በመጣል ላይ ይገኛሉ፡፡ በወጣቶች መካከል ሕገ-ወጥነት ከመቀነስ ይልቅ በመጨመር ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን አውዳሚ እርግማን ማስወገድ የሚችለው የላቀ ቆራጥነት፣ ያለማቋረጥ የሚደረግ ጥረት ብቻ ነው፡፡ ከፍላጎት እና ከምግብ አምሮት፣ ከክፉ ልማዶች እና ያልተቀደሱ ስሜቶች ጋር የሚደረግ ጦርነት የጦፈ እና የሞት ሽረት ነው፤ በዚህ ጦርነት ድልን የሚቀዳጁ ሰዎች በመርህ የሚመሩ ብቻ ናቸው፡፡ 778 CGAmh 381.1
ራስን አለመግዛትን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ቢሆንም እንኳ እያደገ ይገኛል፡፡ ዕድገቱን ለማስተጓጎል፣ የወደቁቱን ለማንሳት እና ደካሞችን ከፈተና ለመከለል በመሻት ረገድ የላቀ ቆራጥነት ያለን መሆን አንችልም፡፡ በደካማ የሰብአዊ እጆቻችን ጥቂት ነገር ብቻ ነው ማድረግ የምንችለው፣ ነገር ግን አስተማማኝ ረዳት አለን፡፡ የክርስቶስ ክንድ የሰብአዊ ዘር ሀዘን እና የመዋረድ ጥልቀት ድረስ መድረሱን መርሳት የለብንም፡፡ ይህን ራስን ያለመግዛትን ሰይጣን እንኳ እንድናሸንፍ እርዳታውን ይሰጠናል፡፡ 779 CGAmh 381.2
ሙሉ በሙሉ መታቀብ መልስ ነው− ማንኛውም ሰው ራስን ካለመግዛት ኃይል ደህንነቱ የተጠበቀ የሚሆንበት ብቸኛው መንገድ ሙሉ በሙሉ ከወይን፣ ከቢራ እና ከጠንካራ መጠጦች መታቀብ ነው፡፡ ጥሩ ሰው ለመሆን እነዚህ ነገሮችን መተው እንዳለባቸው ልጆቻችንን ማስተማር አለብን፡፡ እውነተኛ ጥሩነት ምን መያዝ እንዳለበት እግዚአብሔር አሳይቶናል፡፡ ክብር የሚያገኘው እና ስሙ ከሕይወት መጽሐፍ የማይወገደው ያሸነፈ ሰው ነው፡፡ 780 CGAmh 381.3
ወላጆች በላቀ ቆራጥነት፣ ትጋት በተሞላበት ጥረት፣ ተወዳጅ ለሆነው ሕይወት ባህል ዝበት ሳይኖራቸው፣ ራስን ባለመግዛት ከሚመጡ ስቃዮች እና ወንጀሎች ለመከላከል በልጆቻቸው ዙሪያ ግብረ ገባዊ ጋሻን መገንባት ይችላሉ፡፡ ልጆች ከልክ በላይ እንዳሻቸው በቀንበጥነቱ መቆንጠጥ የነበረበትን ባህሪይ ይዘው እንዲያድጉ መተው የለባቸውም፤ ነገር ግን በጥንቃቄ መገራት እና ከእውነት፣ ከተሃድሶ እና ራስን ከመካድ ጎን እንዲቆሙ ዘንድ መማር አለባቸው፡፡ በእያንዳንዱ አስጊ ሁኔታ ውስጥ እውነተኛ ተሃድሶን ደግፈው የሚቆሙትን በእርግጥ ሊገጥማቸው ያለውን የተቃውሞ ማዕበል ለመጋፈጥ የግብረ ገብ ነጻነት ይኖራቸዋል፡፡ 781 CGAmh 382.1
ራስን አለመግዛት አብዛኛውን ጊዜ አግባብነት የሌለውን ፍላጎት የማርካት ውጤት ነው— በአገራችን ራስን አለመግዛትን ለማስወገድ ታላቅ ጥረት ተደርጓል፣ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ ያደገውን አንበሳ ለማሸነፍ እና ለማሰር አስቸጋሪ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የዚህ ግማሽ ጥረት ወላጆች የልጆቻቸውን ልማዶች እና ባህሪያትን በመቅረጽ ረገድ ያላቸውን ኃላፊነት ለማሳወቅ ቢውል ኖሮ፣ አሁን ካለበት ሁኔታ ይልቅ አንድ ሺህ እጥፍ መልካም መሆን ይችል ነበር፡፡ ራስን በመግዛት ሥራ ውስጥ ያሉ ሠራተኞችን በሙሉ ስኬታማ እንዲሆኑ እንነግራቸዋለን፤ ነገር ግን የሚወጉትን ሥራ በጥልቀት እንዲመለከቱ እና በከፍተኛ ጥንቃቄ እና በጽኑነት ወደ ተሃድሶ እንዲሄዱ እንጋብዛቸዋለን፡፡ 782 CGAmh 382.2
ራስን ያለመግዛትን ሥሩ ጋር ለመድረስ አልኮል ወይም ትንባሆን ከመጠቀም ጠለቅ አድርጎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ስንፍና፣ ዓለማ ቢስነት፣ ወይም ክፉ ጓደኞች በግንባር ቀደምትነት አጋላጭ መንስኤዎች ናቸው፡፡ በጥብቅ ራስን መግዛትን እንደሚለማመዱ ራሳቸውን የሚቆጥሩ ቤተሰቦች ላይ አብዛኛውን ጊዜ ቤት ውስጥ ከሚገኝ የምግብ ጠረጴዛ ይጀምራል፡፡ የምግብ መፈጨትን የሚያዛቡ፣ የአዕምሮአዊ እና አካላዊ ኃይሎችን ሚዛን በማዛባት ከመጠን በላይ የሆነ የአዕምሮ መነቃቃትን የሚፈጥሩ ወይም በማንኛውም መንገድ የአካል ሥርዓትን የሚያዳክሙ ነገሮች፣ አዕምሮ አካል ላይ ያለውን ቁጥጥር በማዳከም ራስን ወደ አለመግዛት እንዲያዘነብል ያደርገዋል፡፡ የብዙዎች ተስፋ የተጣለባቸው ወጣቶች ውድቀት መንስኤው ለጤና ተስማሚ ባልሆነ ምግብ ሳቢያ የተፈጠረ ኢተፈጥሮአዊ የምግብ አምሮት ነው፡፡783 CGAmh 382.3
የአሜሪካ ሕዝባችን የምግብ ጠረጴዛ በአጠቃላይ ሰውን ሰካራም በሚያደርግ ሁኔታ የተዘጋጀ ነው፡፡ በብዙዎቹ የማሕበረተሰብ ክፍሎች መካከል የምግብ አምሮት ገዢ መርኾ ነው፡፡ ጥሩ ጥራት የሌላቸውን ምግቦችን በጣም በተደጋጋሚ በመመገብ የምግብ አምሮቱን የሚያረካ ማንኛውም ሰው የተሳሳቱ የአመጋገብ ልማዶች ዝንባሌዎችን በሚያጎለብትበት ጊዜ በሌላ አንጻር የምግብ አምሮት እና የስሜት ጩኸትን የሚቋቋመውን ኃይል እያደከመ ነው፡፡784 CGAmh 383.1
ሻይ እና ቡና አስተዋጽአ አድራጊ ምክንያቶች ናቸው— ቤት ውስጥ በተጀመረ ራስን አለመግዛት የማብላሊያ አካላት በመጀመሪያ ይዳከሙ እና ከዚያም ተራ ምግብ አምሮትን የማያረካ ይሆናል፡፡ ጤናማ ያልሆኑ ሁኔታዎች በመመስረት ለተጨማሪ አነቃቁ ምግብ ጉጉት ይፈጠራል፡፡ ሻይና ቡና ቅጽበታዊ ውጤት ይፈጥራሉ፡፡ በእነዚህ መርዞች ተጽዕኖ ሥር ነርቫዊ ሥርዓት ይሸበራል፤ በአንዳንድ ሁኔታዎችም የማሰብ ችሎታ የበረታ፣ አስተሳሰብም ይበልጥ ብሩህ የሆነ ይመስላል፡፡ እነዚህ አነቃቂዎች እንደዚህ አይነቶቹን ተስማሚ ውጤቶችን ስለሚፈጥሩ፣ ብዙዎች እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጓቸው ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፤ ነገር ግን ሁል ጊዜ አጸፋዊ ምላሽ ይኖራል፡፡ ነርቫዊ ሥርዓት ከመጪው ጊዜ ሐብቱ ላይ ለጊዜያዊ ጥቅም የሚውል ኃይል ይበደር እና ተጓዳኝ ድባቴ ይህንጊዜያዊ ብርታትን ተከትሎ ይመጣል፡፡ ከሻይ እና ቡና የሚገኘው ድንገተኛ እፎይታ ብርታት የሚመስለው ነርቫዊ ሽብር ብቻ እና ውጤቱም የአካል ሥርዓት መጎዳት ስለመሆኑ ማስረጃ ነው፡፡ 785 CGAmh 383.2
ትንባሆ፣ ብልሁ መርዝ— ትንባሆን መጠቀም አልኮልን ከመጠቀም በላቀ ኃይል አብዛኛውን ጊዜ ነርቫዊ ሥርዓትን የሚጎዳ ልማድ ነው፡፡ ከአስካሪ መጠጥም ይልቅ ሰለባውን በጠንካራ የባርነት ማሰሪያ የሚይዝ ነገር ነው፤ ልማዱን ለማሸነፍ ይበልጥ ከባድ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አካል እና አዕምሮ ከአስካሪ መጠጥ ይልቅ በትንባሆ የተመረዘ ይሆናል፣ ምክንያቱም ትንባሆ ብልህ መርዝ ነው፡፡786 CGAmh 384.1
ትንባሆ… አዕምሮ መንፈሳዊ ነገሮችን በተለይም እነዚህን እርኩስ እርካታዎችን የማረም ዝንባሌ ያላቸውን እውነቶችን በግልጽ ለይቶ እንዳያውቅ፣ አዕምሮን የሚጎዳ እና የስሜት ኃይሎችን የሚያደነዝዝ ነገር ነው፡፡ በማናቸውም አይነት ሁኔታዎች ትንባሆ የሚጠቀሙ ሰዎች በእግዚአብሄር ፊት ንፁሃን አይደሉም፡፡ በእንደዚህ አይነቱ እርኩስ ተግባር ላይ ሳሉ የእግዚአብሔር በሆነው አካላቸው እና በመንፈሳቸው እርሱን ማስከበር አይችሉም፡፡ 787 CGAmh 384.2
ትንባሆ አዕምሮን በማደከም ጥቃቅን የስሜት ኃይሎቹን ሽባ ያደርጋቸዋል፡፡ እርሱን መጠቀም ለከባድ መጠጥ የሚያነሳሳ እና በአብዛኛው ሁኔታ ለአስካሪ መጠጥ መሰረት ይጥላል፡፡ 788 CGAmh 384.3
የአነቃቂ እና የአደንዛዝ ዕፅ ተጽዕኖ— የአነቃቂ እና አደንዛዥ ዕፅ ተጽዕኖ አካላዊ ጥንካሬን ማዳከም ነው፣ አካልንም የሚጎዳ ነገር ሁሉ አዕምሮን ይጎዳል፡፡ አነቃቂ ለጊዜው ኃይሎችን በማነቃቃት አዕምሮአዊ እና አካላዊ እንቅስቃሴን ሊፈጥር ይችላል፤ ነገር ግን የአነቃቂው ተጽዕኖ ሲጠፋ፣ አዕምሮ እና አካል በፊት ከነበረበት ይልቅ የባሰ ሁኔታ ውስጥ ይሆናል፡፡ አስካሪ መጠጦች እና ትንባሆ አካልን ማዳከም እና አዕምሮን ግራ ማጋባት ብቻ ሳይሆን ግብረ ገብን በማዋረድ ለሰብአዊ ዘሮቻችን አስፈሪ እርግማን መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ የአመክንዮ ላይ ቁጥጥር የሚያደርገው ሲወገድ እንስሳዊ ስሜቶች ሥፍራውን ይይዛሉ፡፡ እነዚህ መርዞች ያለገደብ ጥቅም ላይ በዋሉ ቁጥር ተፈጥሮ ይበልጥ አውሬ ይሆናል፡፡12 CGAmh 384.4
አነቃቂ ዕፆችን እንዲጠሉ ልጆችን አስተምሯቸው— አነቃቂ ዕጾችን እንዲጠሉ ልጆቻችሁን አስተምሯቸው፡፡ ባለማወቅ የእነዚህ ነገሮችን አምሮት በውስጣቸው የሚያሳድጉ ስንቶች ናቸው! 789 CGAmh 385.1
እግዚአብሔር ወላጆች ልጆቻቸውን ከአምሮት በተለይም የአነቃቂ እና የአደንዛዥ ዕጾች አምሮትን ከማርካት እንዲጠብቋቸው ጥሪ ያደርግላቸዋል፡፡ የክርስቲያን የምግብ ጠረጴዛ ቅመማ ቅመሞች እና ማጣፈጫዎች በበዛበት ምግብ መሞላት የለበትም፡፡ ጨጓራን ከማንኛውም ጉዳት እንዴት መጠበቅ እንዳለባቸው ማጥናት አለባቸው፡፡ 790 CGAmh 385.2
በዚህ ፈጣን በሆነ ዘመን የምግብ አነቃቂነቱ ዝቅተኛ ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ በሁሉ ነገር ራስን መግዛት እና ጽኑ የምግብ አምሮት ክደት ብቸኛው አስተማማኝ ጎዳና ነው፡፡ 791 CGAmh 385.3
የወላጆች ተግዳሮት— ልጆች ጥብቅ በሆነ ሁኔታ ራሳቸውን የሚገዙ እንዲሆኑና ንጹህ እና መልካም ባህሪይ እንዲኖራቸው የማስተማር እና የማሰልጠን ሥራን አዳጋች የሚያደርገው ወላጆች የምግብ አምሮት እና ስሜቶች ዝንባሌዎችን ወደ ልጆቻቸው ማስተላለፋቸው ነው፡፡ ጤናማ ላልሆነ ምግብ እና ለአነቃቂ እና አደንዛዥ ዕጽ ያላቸው አምሮት ከወላጆቻቸው በውርስ ቢተላለፍባቸው፣ ለልጆቻቸው የሰጧቸውን ክፉ ዝንባሌዎችን ለመቀልበስ ወላጆች ላይ እንዴት ያለ አስፈሪ በሆነ ሁኔታ የከበረ ኃለፊነትን ተሸክመዋል! ወላጆች ዕድለኞች ላልሆኑ ዘሮቻቸው ግዴታቸውን ለመወጣት እንዴት በላቀ ቆራጥነት እና ትጋት መስራት ይኖርባቸው ይሆን! 792 CGAmh 385.4
ጣዕም እና አምሮት መገራት አለበት— ወላጆች በምግብ አዘገጃጀት ወይም በማናቸውም ልማዶች በልጆቻቸው ላይ የተሳሳተ ዝንባሌዎችን የሚያጎለብት ነገር እንዳይፈጽሙ የሕይወት እና የጤና ሕግን መረዳትን የመጀመሪያ ሥራቸው ማድረግ አለባቸው፡፡ የማብላሊያ አካላት እንዳይዳከም፣ ነርቫዊ ኃይሎች ሚዛናዊነትን እንዳያጡ እና በፊታቸው በሚቀርበው ምግብ ሳቢያ ለልጆቻቸው የሚሰጧቸው ትምህርቶች እንዳይቀለበሱ እናቶች እንዴት ባለ ጥንቃቄ እጅግ ቀላል፣ ጤናማ ምግብ ለማዘጋጀት ጥናት ማድረግ አለባቸው! ይህ ምግብ የጨጓራ አካላትን የሚያዳክም ወይም የሚያበረታ እና በእግዚአብሔር ደም የተገዙ ንብረቶች የሆኑ የልጆችን አካላዊ እና ግብረ ገባዊ ጤንነትን በመቆጣጠር ረገድ ብዙ የሚሰራ ይሆናል፡፡ 793 CGAmh 385.5
ወላጆች የልጆቻቸውን አካላዊ እና ግብረ ገባዊ መዋቅራቸውን ለመጠበቅ፣ ነርቫዊ ሥርዓትን እጅግ ሚዛናዊ ለማድረግ እና ነፍስ አደጋ ላይ እንዳትወድቅ እንዴት ያለ የተቀደሰ አደራ ተሰጥቷቸዋል! 794 CGAmh 386.1
እህቶቻችን የምግብ ጠረጴዛቸውን በጤናማ፣ አልሚ ምግብ ብቻ በመሙላት ለሌሎች በሚሰራ ታላቅ የድነት ሥራ ውስጥ ብዙ ሥራ መስራት ይችላሉ፡፡ የልጆቻቸውን ጣዕም እና አምሮት በመግራት፣ በሁሉ ነገር ራስን የመገዛትን ልማዶችን በመቅረጽ እና ለሌሎች ጥቅም ራስን መካድን እና በጎ ማድረግን በማበረታታት ረገድ ውድ ጊዜያቸውን ጥቅም ላይ ማዋል ይችላሉ፡፡ 795 CGAmh 386.2
ችላ ባይ ወላጆች ተጠያቂዎች ናቸው— አያሌ ወላጆች በትዕግስት ራስን የመካድ ልማዶችን ልጆቻቸውን ማስተማርን ለማስወገድ በፈለጉበት ጊዜ እንዲመገቡ እና እንዲጠጡ ያደርጓቸዋል፡፡ ጣዕምን የማርካት እና ዝንባሌን የመሙላት ምኞት ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ አይቀንስም፤ እናም እነዚህ የተሞላቀቁ ወጣቶች እየደጉ ሲሄዱ ለምግብ አምሮት ባሪያ በመሆን ለስሜት ተገዥ ይሆናሉ፡፡ በማሕበረተሰቡ ውስጥ መሆን ባለባቸው ሥፍራ ላይ ሲቀመጡ እና የራሳቸውን ሕይወት በሚጀምሩበት ጊዜ ፈተናን ለመቋቋም አቅም የሌላቸው ይሆናሉ፡፡ በሆዳሞች፣ የትንባሆ አምላኪዎች፣… እና ሰካራሞች ውስጥ የተሳሳተ ትምህርት ክፉ ውጤቶችን እንመለከታለን…፡፡ CGAmh 386.3
አስፈሪ በሆነው ራስን ያለመግዛት ክፋት ላይ የክርስቲያን ወንዶች እና ሴቶች አሳዘኝ ለቅሶ ስንሰማ፣ ወዲያው፡ ወጣቶቹን ማን አስተማራቸው? እነዚህን ፈር የለቀቁ የምግብ አምሮቶችን በውስጣቸው ማን አሳደገ? በምድራዊ ሕይወት እና በሚመጣው ሕይወት የሰማይ መልአክት ህብረት ውስጥ ፋይዳ ያላቸው የሚያደርጋቸውን ባህሪይ የመቅረጽን ክቡር ኃላፊትን ችላ ያለው ማን ነው? የሚሉ ጥያቆዎች ይነሳሉ፡፡ 796 CGAmh 387.1
ትክክለኛው ሥራ ከቤት መጀመር አለበት— ትክክለኛው ሥራ መጀመር ያለበት ቤት ውስጥ ነው፡፡ የወጣቶችን ባህሪይ በመቅረጽ ረገድ የማስተማር ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ትልቅ ሸክም ተሸክመዋል፡፡ ትክክለኛ ልማድ እና ንጹህ ጣዕምን ለመፍጠር፣ ግብረ ገባዊ ጥንካሬን ለማጎልበት፣ እውነተኛ ዋጋ ያለው ግብረ ገብ በመቅረጽ ረገድ የእናት ሥራ ይህ ነው፡፡ በሌሎች መማረክ እንደሌለባቸው፣ ለተሳሰቱ ተጽዕኖዎች እንዳይሸነፉ፣ ነገር ግን በመልካም ነገር ሌሎች ላይ ተፅዕኖ እንዲያደርጉ፣ ከእነርሱ ጋር የሚያብሩትን የከበሩ እና የላቁ እንዲያደርጓቸው አስተምሯቸው፡፡ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ካቆራኙ ከባድ ፈተና ለመቋቋም ከእርሱ ኃይል እንደሚያገኙ አስተምሯቸው፡፡797 CGAmh 387.2
ራስን መግዛት የሚፌዝበት ጉዳይ አይደለም— ብዙዎች ራስን መግዛትን የፌዝ ጉዳይ ያደርጉታል፡፡ እነርሱ ጌታ የምግብ እና የመጠጥ አይነት ጥቃቅን ጉዳዮቻችን አያሳስቡትም በማለት ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ጌታ እነዚህ ጉዳዮች የማያሳስቡት ከሆነ፣ ግልጽ መመሪያ እና ችላ እንዳትላቸውም ሁሉት ጊዜ በማስጠንቀቅ ትዕዛዝ ለመስጠት ለመኑሄ ሚስት ራሱን መግለጥ ባላስፈለገው ነበር፡፡ እነዚህ ነገሮች እንደሚያሳስቡት ይህ በቂ ማስረጃ አይደለም?798 CGAmh 387.3
ተሃድሶ የሚጀምረው ከእናት ነው— እናት የሕይወት ልማዶቿን መጠበቅ ያለበት አይነት ጥንቃቄ በቅዱስ መጽሐፍት ውስጥ ትምህርት ተሰጥቶበታል፡፡ 799 CGAmh 387.4
ተሃድሶ ልጆቿ ከመወለዳቸው በፊት ከእናት መጀመር አለበት፤ እንዲሁም ሰዎች የእግዚአብሔር መመሪያዎች በታማኝነት ቢታዘዙ ኖሮ ራስን አለመግዛት አይኖርም ነበር፡፡ 800 CGAmh 388.1
መልአኩ ለዕብራይስጥ ወላጆች በሰጠው መመሪዎች ውስጥ የእናት ልማዶች ብቻ ሳይሆን የልጆችም ሥልጠና ተካትቷል፡፡ እስራኤልን ነጻ ሊያወጣ የነበረ ልጅ ሳምሶን በሚወለድበት ጊዜ ጥሩ ውርስ እንዲኖረው ተገቢ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥልጠና መምጣት አለበት፡፡ ከጨቅላነቱ ጀምሮ ስለ ፅኑ ራስን መግዛት መሰልጠን ነበረበት…፡፡ CGAmh 388.2
ለዕብራውያን ወጣቶች በተሰጡ መመሪያዎች ላይ የልጅን አካላዊ ደህንነት የሚጎዱ ማናቸውም ነገሮች ችላ መባል እንደሌለባቸው ያስተምረናል፡፡ አላስፈላጊ የሆነ ምንም ነገር የለም፡፡ የአካልን ጤንነት የሚነካ እያንዳንዱ ተጽዕኖ ከአዕምሮ እና ከባህሪይ ጋር ያራሱ የሆነ ቁርኝት አለው፡፡ 801 CGAmh 388.3
ራስን የመግዛት እና ራስን የመቆጣጠር ትምህርት ከጨቅላነት ጀምሮ መሰጠት አለበት፡፡ ይህ ሥራ በአብዛኛው እናት ላይ የሚያርፍ ሸክም ሲሆን ከአባት እርዳታ በማግኘት በስኬት ወደ ፊት መጓዝ ትችላለች፡፡ 802 CGAmh 388.4
ትምህርቱ በእሳት መሞቂያ ሥፍራ እና በትምህርት ቤት ይቀጥል— ዕድሜ ልክ ያሳደግናቸውን እና የምግብ አምሮትን የገሩ ልማዶችን ማስወገድ እጅግ ከባድ ጉዳይ ነው፡፡ ራስን ያለመግዛት አጋንንት በቀላሉ ሊሸነፍ አይችልም፡፡ ግዙፍ ጉልበት ያለው እና ድል ለመንሳት ከባድ የሆነ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ወላጆች ልጆች ከጨቅላነታቸው ጀምሮ እንዲከተሉ እነርሱ ከሚያሰትምሯቸው መርኾዎች ራስን ያለመግዛትን የሚዋጋ ክሩሴድ በቤተሰቦቻቸው የእሳት መሞቂያ ሥፍራ ይጀምሩ እና ስኬትን ተስፋ ማድረግ ይችላሉ፡፡ እናቶች እግዚአብሔር የሰጣችሁን ውድ ሰዓቶቻችሁን የልጆቻችሁን ባህሪያትን በመቅረጽ፣ በማሳደግ እና በማሰልጠን እና በምግብ እና በመጠጥ ረገድ ራስን የመግዛትን መርኾዎችን በጥብቅ እንዲታዘዙ በማስተማር ቢጠቀሙባቸው ውጤቱን ታገኛላችሁ፡፡803 CGAmh 388.5
በዚህ ዘርፍ ውስጥ ያለ መመሪያ በእያንዳንዱ ትምህርት ቤት እና በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ መሰጠት አለበት፡፡ ወጣቶች እና ልጆች የአልኮል፣ የትንባሆ እና ሌሎች አካልን የሚያፈርሱ፣ አዕምሮን የሚያደነዝዙ እና የነፍስን ስጋዊ ፍላጎቶችን የሚያረኩ መርዞችን ጉዳት መረዳት አለባቸው፡፡ እነዚህ ነገሮችን የሚጠቀም ሰው አካለዊ፣ አዕምሮአዊ ወይም የግብረ ገብ ልዩ የተፈጥሮ ችሎታዎች ሙሉ ጥንካሬ እንደማይኖረው ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡28 CGAmh 389.1
የትንሽ ዝባትን ውጤት ግልጽ አድርጉ— መከልከል ያለበት የክፉ ጅማሮ ነው፡፡ ወጣቶችን በማስተማር ሂደት ውስጥ ከትክክለኛው ጎዳና በግልጽ የሚታይ ትንሽ የማፈንገጥን ውጤት እጅግ ግልጽ ሊደረግ ይገባል…፡፡ ወጣቶች ጌታ እንጂ ባሪያ ባለመሆን አስተሳሰብ ይቀረጹ፡፡ እነርሱ ጋር ባለው ግዛት ላይ እግዚአብሔር ገዥ አድርጓቸዋል፣ በመሆኑም ስዩመ ሰማይ የሆነውን ንጉስነታቸውን ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፡፡ እንደዚህ አይነቱ መመሪያ ሙሉ በሙሉ ሲሰጥ፣ ውጤቱ ከወጣቶቹ ልቆ ይሄዳል፡፡ ተጽዕኖዎቹ በጥፋት አፋፍ ላይ ያሉትን በሺዎች የሚቆጠሩ ወንዶች እና ሴቶችን እስከ ማዳን ድረስ ይዘልቃል፡፡ 804 CGAmh 389.2
ፈተናን ለመቋቋም ግብረ ገባዊ ብርታትን ይገንቡ— በማደግ ላይ ያለውን ራስን ያለመግዛት ክፋትን ለማሸነፍ በትክክለኛው ጎን ግላዊ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ አቤት፣ በአገሩ ያለውን የእያንዳንዱን ወላጅ ልብ የሚያቀልጥ እና መንገዳቸውን የሚያበራ ቃላትን ማግኘት በቻልን ነበር! 805 CGAmh 389.3
ወላጆች ለልጆቻቸው የጤናማ እና የደስተኛ ሕይወት መሰረት ሊመሰርቱላቸው ይችላሉ፡፡ ፈተናን ማሸነፍ በሚችል የግብረ ገብ ብርታት እና ከሕይወት ችግሮች ጋር ውጤታማ በሆኑ ሁኔታ ከሚታገሉበት ድፍረት እና ጥንካሬ ጋር ከቤቶቻቸው ሊልኳቸው ይችላሉ፡፡ በውስጣቸው ሕይወታቸውን ለእግዚአብሔር ክብር እና ለዓለም በረከት የሚያደርጉበትን ዓለማ መቀስቀስ እና ኃይልን ማሳደግ ይችላሉ፡፡ ወደ ላይኛው የክብር ከፍታ ጉዞ ላይ በብርሃን እና በደመና ውስጥ ለእግራቸው የቀና ጎዳና ማድረግ ይችላሉ፡፡ 806 CGAmh 389.4
እግዚአብሔር በመጠጥ፣ በአመጋገብ እና በአለባበስ ሰፊው ራስን የመግዛት መድረክ ላይ እንድንቆም ጥሪ ያደርግልናል፡፡ ወላጆች ሆይ እግዚአብሔር ለሰጣቸው ኃላፊነቶቻችሁ አትነቁምን? የጤና ተሃድሶ መርኾዎችን በማጥናት ራስን የመካድ ጎዳና ብቸኛው አስተማማኝ ጎዳና እንደሆነ ልጆቻቸውን አስተምሯቸው፡፡ 807 CGAmh 390.1