ታላቁ ተጋድሎ

41/45

ምዕራፍ ፴፰—የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ

“ታላቅ ስልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሳ ምድር በራች። በብርቱም ድምጽ፦ ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፣ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፣ የርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች።” “ከሰማይም ሌላ ድምጽ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ ሕዝቤ ሆይ በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ፣ ከመቅሰፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።” [ራዕይ 18÷1፣2፣4]። GCAmh 436.1

ያ መልእክት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው በ1844 የበጋ ወራት በመሆኑ፣ ባቢሎንን በሚወክሉ የተለያዩ ድርጅቶች ዘንድ ያለውን ብልሹነት በተጨማሪነት በመግለጽ ይህ ጥቅስ ወደፊት የሚጠቁመው፣ በራዕይ 14 በሁለተኛው መልአክ እንደተነገረው [ራዕይ 14÷8]፣ የባቢሎን ውድቀት አዋጅ የሚደገምበትን ዘመን ነው። የኃይማኖታዊው ዓለም አሰቃቂ ገጽታ ሁኔታ እዚህ ላይ ተገልፆአል። ካለማመን የድፍረት ምሽግ ውስጥ እስኪገቡ ድረስ በእያንዳንዱ እውነትን አልቀበልም-ባይነት የሰዎች አዕምሮ እየጨለመ፣ ልባቸው የበለጠ ደንዳና እየሆነ ይሄዳል። እግዚአብሔር በሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች ባለመበገር፣ ቅዱስ አድርገው የሚጠብቁትን ወደማሳደድ እስኪመሩ ድረስ ከአሥርቱ ትዕዛዛት መርሆዎች በአንዱ ላይ መረማመዳቸውን ይቀጥላሉ። በቃሉና በሕዝቦቹ ላይ በተሰነዘረው ንቀት ሳቢያ ክርስቶስ እንደ ምንም (ዋጋ-ቢስ) ይሆናል። የመናፍስታዊ ትምህርቶች በአብያተ ክርስቲያናት ተቀባይነት ሲያገኙ በስጋም ልብ ላይ የተጣለው መግቻ ይወገድና የኃይማኖት ሞያ (ሥመ ኃይማኖተኛነት)፣ እጅግ የረከሰ ኃጢአትን የሚሸፍን ብልኮ ይሆናል። በመንፈሳዊ መገለጦች ያለው እምነት ለሚያታልሉ መናፍስትና ለአጋንንት አስተማሪዎች በር ይከፍታል፤ ከዚያም የርኩሳን መላእክት ተጽዕኖ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይንፀባረቃል። GCAmh 436.2

ስለ ባቢሎን፣ በዘመኑ ወደ እይታ የመጣው በዚህ በትንቢት ያለው እንዲህ ተነግሯል፦ “ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና እግዚአብሔርም አመጽዋን አሰበ” [ራዕይ 18÷5]። የኃጢአትዋን ስፍር ሞልታለች፤ ውድመት ሊወድቅባት ደርሶአል። እግዚአብሔር ግን አሁንም በባቢሎን ሕዝብ አለው፤ ከፍርዱ መጎብኘት በፊትም፦ “በኃጢአቷ እንዳይተባበሩ፣ ከመቅሰፍትዋም እንዳይቀበሉ” እነዚህ ታማኞች መጠራት አለባቸው። እንቅስቃው፣ ከሰማይ በወረደው፣ ምድርን በክብሩ ባበራው፣ በታላቅ ድምጽ የባቢሎንን ኃጢአቶች ባወጀው መልአክ የተመሰለው ለዚህ ነው። ከመልእክቱ ጋር ተያይዞ የሚሰማ ጥሪ አለ፦ “ሕዝቤ ሆይ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ።” እነዚህ እወጃዎች ከሶስተኛው መልአክ መልእክት ጋር ተዳምረው ለምድር ነዋሪዎች የሚሰጡ የመጨረሻዎቹን ማስጠንቀቂያዎች የያዙ ናቸው። GCAmh 436.3

ዓለም ይደርስበት ዘንድ ያለው ጉዳይ አስፈሪ ነው። የምድር ኃይላት፣ የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ይዋጉ ዘንድ ተባብረው “ታናናሾችና ታላላቆችም፣ ባለ ጠጋዎችና ድሆችም፣ ጌቶችና ባርያዎችም” [ራዕይ 13÷16] ሁሉ ሐሰተኛውን ሰንበት በመጠበቅ ከቤተ ክርስቲያንዋ ልማዶች ጋር መስማማት አለባቸው ብለው ያውጃሉ። ይህንን ለመከተል እምቢ በሚሉ ላይ ሕጋዊ መቀጮዎች ይወሰዳሉ፤ ከዚያም በመጨረሻ ሞት የሚገባቸው እንደሆኑ ይታወጃል። በሌላ በኩል ደግሞ የፈጣሪን የእረፍት ቀን የያዘው የእግዚአብሔር ሕግ ይከበር ዘንድ ይጠየቃል፤ መመሪያዎቹን የሚጥሱትም ሁሉ ቁጣ እንደሚደርስባቸው ያስጠነቅቃል። GCAmh 436.4

ስለዚህ ጉዳዩ በእንዲህ ሁኔታ በግልጽ በፊቱ ቀርቦ፣ የሰብአዊ ፍጡርን አዋጅ ይታዘዝ ዘንድ በእግዚአብሔር ሕግ ላይ የሚረማመድ ማንም ቢሆን እርሱ የአውሬውን ምልክት ይቀበላል፤ በእግዚአብሔር ፈንታ እታዘዘዋለሁ ብሎ ለመረጠው ኃይል ታማኝነቱን የሚገልጽበትን ምልክት ይቀበላል። ከሰማይ የሚመጣው ማስጠንቀቂያ፦ GCAmh 437.1

“ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግድ በግንባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር እርሱ ደግሞ በቁጣው ጽዋ ሳይቀላቀል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቁጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል” [ራዕይ 14÷9፣10] ይላል። GCAmh 437.2

እውነቱ ወደ አዕምሮው፣ ወደ ህሊናውም መጥቶ እንዲያስተውል ተደርጎ ተቀባይነት ከማጣቱ በፊት ግን አንድስንኳ በእግዚአብሔር ቁጣ የሚቃሰይ አይሆንም። ለዚህ ዘመን የሚሆኑትን የተለዩ እውነቶች ለመስማት ምንም ዕድል ያልነበራቸው ብዙዎች አሉ። የአራተኛው ትዕዛዝ ግዴታ በትክክለኛ ብርሃኑ በፊታቸው ፈጽሞ አልቀረበም። እያንዳንዱን ልብ የሚያነበው፣ እያንዳንዱንም ሐሳብ የሚፈትነው እርሱ፣ በተቃርኖው ጉዳዮች ዙሪያ ይታለል ዘንድ፣ የእውነትን እውቀት የሚሻን ማንንም አይተውም። አዋጁ [ሰንበትን በተመለከተ የሚሰራጨው መልእክት] ለህዝቡ በጭፍን የሚሰጥ አይሆንም። እያንዳንዱ ሰው በማስተዋል ውሳኔውን ያደርግ ዘንድ በቂ ብርሐን ይኖረዋል። GCAmh 437.3

ሰንበት የታማኝነት ታላቁ መፈተኛ ይሆናል፤ ምክንያቱም በተለየ ሁኔታ የተካደ የእውነት ነጥብ ነውና። የመጨረሻው ፈተና በሰዎች ላይ በሚሆንበት ጊዜ እግዚአብሔርን በሚያገለግሉና እርሱን በማያገለግሉ መካከል የልዩነት መስመር ይሰመራል። የመንግሥትን ሕግ በመታዘዝ፣ አራተኛውን ትዕዛዝ በመፃረር የሚከበረው ሐሰተኛው ሰንበት፣ እግዚአብሔርን ለሚቃወመው ኃይል ታማኝነትን በአደባባይ የሚገልጽ ሲሆን ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ እውነተኛውን ሰንበት መጠበቅ ደግሞ ለፈጣሪ ላለው ታማኝነት ማስረጃ ነው። አንዱ ወገን፣ ለምድራዊ ኃይላት መታዘዙን የሚያመለክተውን ምልክት በመቀበል የአውሬውን ምልክት ሲቀበል፣ ሌላው ደግሞ ለመለኮታዊ ስልጣን ታማኝ የሚሆንበትን ምልክት በመምረጥ የእግዚአብሔርን ማህተም ይቀበላል [በመግለጫ ስር ማስታወሻ 13ን ይመልከቱ]። GCAmh 437.4

እስከ አሁን ድረስ፣ የሶስተኛውን መልአክ መልእክት እውነቶች የሚናገሩ እነርሱ ተራ ደወል ደዋዮች (አስደንጋጮች) በመባል ተፈርጀዋል። የኃይማኖት አለመቻቻል በአሜሪካ የበላይነቱን ይይዛል፣ መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን ተባብረው የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትን ያሳድዳሉ፣ የሚለው ትንቢታቸው መሰረተ-ቢስና ትርጉም የለሽ ተብሏል። ይህ ምድር (አገር)፣ የኃይማኖት ነፃነት ጠበቃ ከሆነበት፣ ከእስካሁኑ ውጪ ሌላ ሊሆን ፈጽሞ እንደማይችል በልበ-ሙሉነት ሲታወጅ ቆይቷል። ሆኖም የእሁድን መከበር አስገዳጅ በማድረግ የሚቀርቡ ጥያቄዎች በስፋት ሲነሳሱ፣ ለረጅም ጊዜ በጥርጥር፣ አመኔታ ርቆት የነበረው ክስተት እየቀረበ እንደሆነ ይታያል፤ ሶስተኛው መልእክትም ከዚህ በፊት ሊኖረው ያልቻለውን ውጤት በዚህ ጊዜ ያስገኛል። GCAmh 437.5

በዓለምና በቤተ ክርስቲያን በሁለቱም ዘንድ ኃጢአትን ይገስጽ ዘንድ እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ትውልድ አገልጋዮቹን ልኳል። ሕዝቡ ግን እንዲነገራቸው የሚፈልጉት የማይጎረብጡ ነገሮችን ነው፤ ንፁሁና ቀጥተኛው (ያልተቀባባው) እውነት ተቀባይነት አያገኝም። ብዙ ተሐድሶ አድራጊዎች፣ ወደ ሥራቸው ሲገቡ የቤተ ክርስቲያንንና የአገሪቱን ኃጢአቶች በሚነቅሱበት ጊዜ ታላቅ ጥንቃቄ ለማድረግ ቁርጠኞች ነበሩ። በንፁህ የክርስቲያን ሕይወት ምሳሌ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎች ሕዝቡን ይመልሱ ዘንድ ተስፋ አደረጉ። ነገር ግን የእርጉም ንጉሥንና የከሃዲ ሕዝብን ኃጢአት ይገስጽ ዘንድ በኤልያስ ላይ ወርዶ እንዳንቀሳቀሰው ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ በላያቸው መጣ፤ ለማቅረብ ቸል ብለዋቸው የነበሩትን አስተምህሮዎች - የመጽሐፍ ቅዱስን ግልጽ ንግግሮች ከመስበክ ይታቀቡ ዘንድ አልተቻላቸውም። ለነፍሳት ስጋት የሆነውን አደጋ እና እውነትን በቅንነት ያውጁ ዘንድ ተገደዱ። ጌታ የሰጣቸውን ቃላት፣ የሚያመጡትን መዘዝ ሳይፈሩ ተናገሯቸው፤ ሕዝቡም ማስጠንቀቂያውን ይሰማ ዘንድ ተገደደ። GCAmh 437.6

የሶስተኛው መልአከ መልእክትም የሚታወጀው እንዲሁ ነው። መልእክቱ ተወዳዳሪ በሌለው ኃይል እንዲሰጥ ዘመኑ በደረሰ ጊዜ፣ ለእርሱ አገልግሎት ራሳቸውን የሚቀድሱትን፣ የእነርሱን አዕምሮ በመምራት፣ ራሳቸውን ባዋረዱ መሳሪያዎች በኩል ጌታ ሥራውን ይሰራል። እነዚህ ሰራተኞች ብቁ የሚሆኑት በስነ-ጽሁፍ ትምህርት ተቋማት ስልጠና ሳይሆን በመንፈሱ በመቀባት ይሆናል። እግዚአብሔር የሚሰጣቸውን ቃል እያወጁ በቅዱስ ቅንዓት ወደፊት ይራመዱ ዘንድ የእምነትና የፀሎት ሰዎች ይገደዳሉ። የባቢሎን ኃጢአቶች እርቃናቸውን ይቀራሉ። የቤተ ክርስቲያንን ስርዓቶች በመንግሥት ስልጣን አማካኝነት አስገዳጅ የማድረጉ አስፈሪ ውጤቶች፣ የመናፍስታዊነት ስኬቶች፣ በስውር የሚደረገው ሆኖም በፍጥነት የሚያድገው ጳጳሳዊ ኃይል፣ ሁሉም ይገለጣሉ። በእነዚህ ከባድና የከበሩ ማስጠንቀቂያዎች ሕዝቡ ይነቃነቃል። እንደዚህ አይነት ቃላት ፈጽሞ ሰምተው የማያውቁ እልፍ አዕላፋት ይሰማሉ። ከሰማይ የተላከላትን እውነት አሻፈረኝ በማለቷ ምክንያት ከስህተቶችዋና ከኃጢአቶችዋ የተነሳ የወደቀችው ቤተ ክርስቲያን ባቢሎን እንደሆነች ምስክርነቱን በመገረም ያዳምጣሉ። “እነዚህ ነገሮች እንደዚህ ናቸው እንዴ?” እያሉ ሕዝቡ ወደ ቀድሞ መምህሮቻቸው ሲሄዱ ፍርሃታቸውን ለማርገብ፣ የተነሳሳውንም ህሊና ለማዳከም አገልጋዮቹ ተረት ያቀርባሉ። ስለ መልካም ነገሮች ይተነብያሉ። ነገር ግን ብዙዎች በሰዎች ስልጣን ብቻ መርካት እምቢ በማለታቸው፣ ግልጽ የሆነውን “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” የሚለውን ያዩ ዘንድ አስረግጠው በሚጠይቁበት ጊዜ፣ ሕዝባዊው (ተወዳጁ) አገልግሎት፣ ልክ የጥንቱ ፈሪሳዊያን ስልጣናቸው ጥያቄ ውስጥ ሲገባ እንዳደረጉት ሁሉ በቁጣ ተሞልቶ፣ መልእክቱ የሰይጣን እንደሆነ በማውገዝ ኃጢአት ወዳድ የሆኑ እልፍ አዕላፍትን በማነሳሳት፣ ይህንን መልእክት የሚያወጁትን አጥብቀው እንዲያወግዙና እንዲያሳድዱ ያደርጋል። GCAmh 438.1

ተቃርኖው (ተጋድሎው) ወደ አዳዲስ ስፍራዎች ሲገባና የሰዎችም አዕምሮ ወደ ተረገጠው ህገ-እግዚአብሔር እንዲያተኩር ሲጠራ፣ ሰይጣን በመታወክ የራወጣል። መልእክቱን የሚያጅበው ኃይል የሚያደርገው ነገር ቢኖር የሚቃወሙትን የበለጠ ማበሳጨት ይሆናል። በመንጎቻቸው ላይ እንዳያንፀባርቅ ብርኃኑን ለመጋረድ የቤተ ክርስቲያን ባለስልጣናት (ካህናት) ከሰው አቅም በላይ ሊባል የሚችል ጥረት ያደርጋሉ። ማድረግ በሚችሏቸው መንገዶች ሁሉ የእነዚህን አስፈላጊ ጥያቄ ውይይቶች ለመጨቆን ይማስናሉ። ቤተ ክርስቲያን የመንግሥታዊ ኃይልን ጽኑ ክንድ [እርዳታ] ትጠይቃለች፤ በዚህም ተግባር ላይ ጳጳሳዊያኑና ፕሮቴስታንቶች ያብራሉ። እሁድን አስገዳጅ የሚያደርገው ንቅናቄ እየተባና የበለጠ ቆራጥ እየሆነ ሲመጣ [የእግዚአብሔርን] ትዕዛዛት በሚጠብቁ ላይ ሕጉ እንዲሰለጥን ይደረጋል። በቅጣትና በእስር ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል። አንዳንዶቹም እምነታቸውን እንዲክዱ ማባበያ ይሆን ዘንድ ተጽዕኖ ፈጣሪ እርከኖች፣ ሽልማቶችና ጥቅማ ጥቅሞች ይበረከቱላቸዋል። ነገር ግን የማያወላውለው መልሳቸው፣ ልክ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ሳለ፣ ሉተር ያቀረበው ጥያቄ (አቤቱታ) ይሆናል፦ “ስህተታችንን ከእግዚአብሔር ቃል ዘንድ አሳዩን።” በፍርድ ሸንጎዎች እንዲቀርቡ የሚደረጉ እነርሱ እውነትን ነፃ የሚያወጣ ጠንካራ መከራከሪያ ያደርጋሉ። ከሚሰሟቸው መካከል አንዳንዶቹም ሁሉንም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ጠብቀው እንደ እነርሱ ለመቆም ይመራሉ። በዚህ ሁኔታ እነዚህ እውነቶች በሌላ በምንም አይነት መንገድ ሊደርሳቸው የማይችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ብርሐን ይደርሳቸዋል። GCAmh 438.2

ከህሊና የመነጨ ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዝ እንደ አመጽ ይቆጠራል። በሰይጣን አይኑ ታውሮ፣ ወላጅ በሚያምን ልጁ ላይ ሸካራነትንና ጭቆናን ይተገብራል፤ ጌታው ወይም አለቃይቱ በእግዚአብሔር ትዕዛዛት አክባሪ አገልጋይ ላይ ጭቆና ይፈጽማሉ። ፍቅር ይርቃል፤ ልጆች ልጅነታቸው ተክዶ ከቤት ይባረራሉ። የጳውሎስ ቃላት እንዳሉ ቃል በቃል ተግባራዊ ይሆናሉ፦ “በእውነትም በክርስቶስ የሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” [2ኛ ጢሞ 3÷12]። የእውነት ደጋፊዎች የእሁድን ሰንበት ለማክበር እምቢ ሲሉ፣ አንዳንዶች ወደ ወህኒ ቤት ይወረወራሉ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ከአገር ይሰደዳሉ፤ አንዳንዶቹም እንደ ባርያ ይደረጋሉ። ለሰብአዊ ፍጡር ጥበብ፣ አሁን፣ ይህ ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ይመስላል፤ ነገር ግን የሚገድበው የእግዚአብሔር መንፈስ ከሰው በሚወሰድበት ጊዜ የመለኮትን መመሪያዎች በሚጠላው፣ በሰይጣንም ቁጥጥር ስር በሆኑ ጊዜ፣ እንግዳ የሆኑ ነገሮች ይከሰታሉ። የእግዚአብሔር ፍርሃትና ፍቅር በሚወገዱበት ጊዜ ልብ በጣም አረመኔ ሊሆን ይችላል። GCAmh 439.1

ማዕበሉ እየተቃረበ ሲመጣ፣ የሶስተኛውን መልአክ መልእክት እንደሚያምኑ የመሰከሩ፣ ነገር ግን እውነትን በመታዘዝ ያልተቀደሱ ሰፊ መደቦች አቋማቸውን ለቀው፣ የተቃዋሚውን ጎራ ይቀላቀላሉ። ከዓለም ጋር በመተባበር የመንፈሱም ተካፋይ በመሆን፣ ተመሳሳይ ሊባል በሚችል ብርሐን ነገሮችን ይመለከታሉ፤ ፈተናም በመጣ ጊዜ ቀላሉን፣ ሕዝባዊውን ጎራ ለመምረጥ የተዘጋጁ ናቸው። ተሰጥኦ ያላቸው፣ ባለግሩም ሞያ፣ በአንድ ወቅት በእውነቱ ሐሴት ያደርጉ የነበሩ እነርሱ ነፍሳትን ያታልሉና ያሳስቱ ዘንድ ኃይላቸውን ይተገብራሉ። የቀድሞ ወንድሞቻቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው እጅግ መራር ጠላቶች ይሆናሉ። ሰንበት ጠባቂዎች ስለ እምነታቸው ይናገሩ ዘንድ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ ያልሆኑትን እንደሆኑ በማድረግና በመክሰስ፣ በሐሰተኛ ዘገባዎችና በይሆናሎች ገዥዎችን የሚያነሳሱባቸው፣ ተወዳዳሪ የሌላቸው ስኬታማ የሰይጣን እንደራሴዎች የሚሆኑት እነዚህ ከሃዲዎች ናቸው። GCAmh 439.2

በዚህ የስደት ወቅት የእግዚአብሔር አገልጋዮች እምነት ይፈተናል። ወደ እግዚአብሔርና ወደ ቃሉ ብቻ በመመልከት ማስጠንቀቂያውን በታማኝነት ሰጥተዋል። የእግዚአብሔር መንፈስ በልባቸው ላይ በመንቀሳቀስ ይናገሩ ዘንድ አስገድዷቸዋል። በቅዱስ ወኔ ተነሳስተው፣ የመለኮት ትርታ በላያቸው ጠንክሮ፣ ጌታ የሰጣቸውን ቃል ለሕዝቡ በመናገራቸው የሚመጣውን መዘዝ ኩምሽሽ ብለው ሳያሰሉ ኃላፊነታቸውን ወደ መተግበር ገቡ። ምድራዊ ፍላጎቶቻቸውን አላጤኑም፤ ዝናቸውን ወይም ሕይወታቸውን ለመጠበቅም አልጣሩም። ሆኖም የተቃውሞና የነቀፋ ማዕበል በላያቸው ሲፈነዳ፣ አንዳንዶቹ በድንጋጤ ተሸንፈው “የንግግራችን ውጤት ምን እንደሚሆን መገመት ብንችል ኖሮ፣ ዝም እንል ነበር” ለማለት የተዘጋጁ ይሆናሉ። በችግር ታጥረዋል። ሰይጣን በጽኑ ፈተናዎቹ ያጠቃቸዋል። የጀመሩት ሥራ አቅማቸው ማከናወን ከሚችለው በላይ መስሎ ይሰማቸዋል። እናልቃለን ብለውም ይፈራሉ። የተነሳሱበት ግለት ከስሞአል፤ ሆኖም ግን መመለስ አይችሉም። ከዚያም ፈጽሞ ረዳት አልባነታቸውን ሲረዱ ጉልበት ያገኙ ዘንድ ወደ ኃያሉ አምላክ ይሸሻሉ። የተናገሯቸው ቃላቶች ማስጠንቀቂያውን ይሰጡ ዘንድ ያዘዛቸው የእርሱ እንደሆኑ እንጂ የራሳቸው እንዳልነበሩ ያስታውሳሉ። እግዚአብሔር እውነቱን በልባቸው አስቀመጠ፤ ከማወጅም ይቆጠቡ ዘንድ አልተቻላቸውም። GCAmh 439.3

ባለፉት ዘመናት የእግዚአብሔር ሰዎች እነዚህን ተመሳሳይ ፈተናዎች አልፈዋል። ዋይክሊፍ፣ ኸስ፣ ሉተር፣ ቲንዳል፣ ቤክስተር፣ ዌስሊ፣ ሁሉም አስተምህሮዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲፈተኑ ወትውተዋል፤ የሚወገዘውንም ሁሉ እንደማይቀበሉ ተናግረዋል። በማያባራ ንዴት፣ የስደት መዓት፣ በእነዚህ ሰዎች ላይ በረታ፤ ሆኖም እውነቱን ከመናገር ዝም አላሉም። በቤተ ክርስቲያንዋ የተለያዩ ዘመናት፣ በእያንዳንዳቸው፣ በዚያ ዘመን ለነበሩ የእግዚአብሔር ሕዝቦች፣ እንደ አስፈላጊነቱ ተስማሚ እንዲሆኑ የተደረጉ፣ የተለያዩ እውነቶች እንዲስፋፉ ተደርገዋል [ለአንድ ዘመን ከሌላው የሚለየው ለዚያ ጊዜ ገጣሚ የሆነ የተለየ እውነት ነበረው]። እያንዳንዱ አዲስ እውነት ጥላቻንና ተቃውሞን ተፋልሟል። በብርሃኑ የተባረኩ እነርሱ ተሰልለዋል፤ ተፈትነዋልም። በአስቸኳይ ጊዜ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የተለየ እውነት ይሰጣል። ታትሞ እንዳይወጣ ይቃወም ዘንድ የሚደፍር ማን ነው? የመጨረሻውን የምሕረት ግብዣ ለዓለም ያበረክቱ ዘንድ አገልጋዮቹን ያዛቸዋል። በነፍሳቸው ጥፋት ፈርደው ካልሆነ በስተቀር ዝም ይሉ ዘንድ አይቻላቸውም። የክርስቶስ አምባሳደሮች ስለሚያስከትለው ውጤት አያገባቸውም፤ ኃላፊነታቸውን ይወጡ፣ ውጤቱን ለእግዚአብሔር ይተዉ። GCAmh 440.1

ተቃውሞው ወደ ተጋጋለ ከፍታ በሚወጣበት ጊዜ፣ የችግሩ መንስኤ እነርሱ እንደሆኑ ስለሚሰማቸው የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንደገና ግራ ይጋባሉ። ነገር ግን ህሊናና የእግዚአብሔር ቃል አካሄዳቸው ትክክል እንደሆነ ያረጋግጡላቸዋል፤ ፈተናዎች ቢቀጥሉም ለመሸከም ይጠነክራሉ። ፉክክሩ እየቀረበና እየሰላ ይሄዳል፤ ነገር ግን እምነታቸውና ድፍረታቸው እንደ አደጋ ጊዜው መጠን ያድጋል። ምስክርነታቸው፣ የዓለምን ተቀባይነት ለማግኘት ስንል “ቅዱስ ሕጉን ከፋፍለን፣ አንዱን ክፍል አስፈላጊ፣ ሌላውን ደግሞ አላስፈላጊ ብለን ለመፈረጅ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ጣልቃ እንገባ ዘንድ አንደፍርም። የምናመልከው አምላካችን ያድነን ዘንድ ይችላል። ክርስቶስ የምድርን ኃይላት ድል አድርጓል፤ ድል የተነሳን ዓለም እንፈራ ዘንድ ይገባናልን?” የሚል ይሆናል። GCAmh 440.2

የተለያየ መልክ የያዘው መሳደድ፣ ሰይጣን በሕይወት እስካለ፣ ክርስትናም ህልውናውን የሚያስቀጥለው ኃይል እስካለው ድረስ የሚቀጥል የተነደፈ መርህ ነው። የጽልመት ሰራዊት ተቃዋሚ ሆኖ ራሱን ሳያስመዘግብ (ሳያስመለምል) ማንም እግዚአብሔርን ማገልገል አይችልም። ተጽዕኖው፣ ታዳኙን ከእጃችን እየወሰደው ነው ብለው በመስጋት ርኩሳን መላእክት ያጠቁታል። ሰዎችም ሳይቀሩ፣ በምሳሌነቱ ተገስፀው በሚያታልሉ ፈተናዎች አማካኝነት ከእግዚአብሔር ይለዩት ዘንድ ከእነርሱ [ከአጋንንት] ጋር ይተባበራሉ። እነዚህ ውጤታማ ሳይሆኑ ሲቀሩ ህሊናን ለማስገደድ ጠንካራ ኃይል በሥራ ላይ ይውላል። GCAmh 440.3

ሆኖም የሱስ በላይ ባለው ቤተ መቅደስ የሰው አማላጅ ሆኖ እስቀጠለ ድረስ፣ የሚገድበው የቅዱስ መንፈስ ተጽዕኖ በገዥዎችና በሕዝቡ ዘንድ ይታወቃል። [መንፈስ ቅዱስ] በተወሰነ ደረጃ እስከ አሁን ድረስ፣ የምድሪቱን ሕግጋት ይቆጣጠራል። እነዚህ ሕግጋት ባይኖሩ ኖሮ የዓለም ሁኔታ አሁን ካለው እጅግ የባሰ በሆነ ነበር። አብዛኛዎቹ መሪዎቻችን ንቁ (ሕያው) የሰይጣን ወኪሎች ቢሆኑም፣ በአገሪቱ ቀንደኛ ሰዎች መካከል እግዚአብሔር ተወካዮች አሉት። ጠላት በአገልጋዮቹ ላይ በመንቀሳቀስ የእግዚአብሔርን ሥራ በአያሌው ሊያደናቅፉ የሚችሉ ሐሳቦችን እንዲያቀርቡ ያደርጋቸዋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚፈሩ መንግሥታዊ መሪዎች እንደዚህ አይነቶቹን ሃሳቦች ሊመለሱ በማይችሉ ክርክሮች ይቃወሙ ዘንድ በቅዱሳን መላእክት ተጽዕኖ ይደረግባቸዋል። በእንዲህም ሁኔታ ጠንካራውን የክፋት ማዕበል ጥቂት ሰዎች ያስቆሙታል። የሶስተኛው መልአክ መልእክት ሥራውን ይሰራ ዘንድ የእውነት ጠላቶች ተቃውሞ ይገታል። የመጨረሻው ማስጠንቀቂያ በሚሰጥበት ጊዜ አሁን እግዚአብሔር ሥራውን ለመሥራት እየተጠቀመባቸው ያሉትን ቀንደኛ ሰዎች ቀልብ በመያዝ፣ የተወሰኑት ይቀበሉትና በመከራ ጊዜ ከእግዚአብሔር ሕዝቦች ጋር አብረው ይቆማሉ። GCAmh 441.1

በሶስተኛው መልአክ መልእክት እወጃ የሚሳተፈው መልአክ ምድርን በሙሉ በክብሩ ይሞላታል። ዓለም አቀፋዊ የሆነና ያልተለመደ ኃይል ሥራ እዚህ ላይ ተተንብዮአል። ከ1840 እስከ 1844 የተደረገው የአድቬንት (የዳግም ምጽዓት) እንቅስቃሴ የእግዚአብሔር ኃይል ግሩም መገለጫ ነበር፤ የመጀመሪያው መልአክ መልእክት በዓለም ባለው ወደ እያንዳንዱ የአገልግሎት ማዕከል ደርሶ፤ በአንዳንድ አገራትም፣ በአሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከነበረው ተሐድሶ ጀምሮ ያልታየ እጅግ ታላቅ ኃይማኖታዊ መነቃቃት ሆኖአል። በሶስተኛው መልአክ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የሚሆነው ኃያል እንቅስቃሴ ግን እነዚህን ሁሉ በሰፊ ልዩነት የሚበልጥ ይሆናል። GCAmh 441.2

ሥራው በጴንጤ ቆስጤ ቀን የተደረገውን የሚመሳሰል ይሆናል። የከበረው ዘር ይበቅል ዘንድ በወንጌሉ መክፈቻ በመንፈስ ቅዱስ መውረድ “የመጀመሪያው ዝናብ” እንደተሰጠ ሁሉ በመጨረሻ ደግሞ መከሩን ያጎመራ ዘንድ “የኋለኛው ዝናብ” ይሰጣል:: “እናውቃለን፣ እንከተልማለን እግዚአብሔርን። አወጣጡም እንደ ማለዳ ወገግታ ተዘጋጅቶአል። እንደ ዝናብ ይመጣልና ምድሩን እንደሚያጠጣ እንደ [የፊተኛና] እንደ ኋለኛም ዝናብ። [as the latter and former rain unto the earth.]” [ሆሴዕ 6÷3]። “እናንተ የጽዮን ልጆች፦ አምላካችሁ እግዚአብሔር የፊተኛውን ዝናብ በጽድቅ ሰጥቶአችኋልና እንደ ቀድሞውም የፊተኛውንና የኋለኛውን ዝናብ አዝንቦላችኋልና በእርሱ ደስ ይበላችሁ ለእርሱም እልል በሉ” [ኢዮኤ 2÷23]። “እግዚአብሔር ይላል፦ በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናልና ስጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ”፤ “የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል” [የሐዋ ሥራ 2÷17፣21]። የወንጌሉ ታላቅ ሥራ፣ ሲጀመር ከታየው የእግዚአብሔር ኃይል መገለጥ ባነሰ ሁኔታ የሚደመደም አይሆንም። በወንጌሉ መክፈቻ በፊተኛው ዝናብ መውረድ የተፈፀሙት ትንቢቶች በመጨረሻው ደግሞ በኋለኛው ዝናብ እንደገና ፍፃሜ ያገኛሉ። “እንግዲህ ከጌታ ፊት የመጽናናት ዘመን እንድትመጣላችሁ አስቀድሞም ለእናንተ የተመረጠውን የሱስ ክርስቶስን እንዲልክላችሁ፣ ኃጢአታችሁ ይፋቅ ዘንድ [በፍርድ ምርመራ] ንስሐ ግቡ ተመለሱም” በማለት ሐዋርያው ጴጥሮስ “የመጽናናት ዘመን/the time of refreshing” ብሎ የናፈቀው ይህ ነው [የሐዋ ሥራ 3÷19፣20]። GCAmh 441.3

የእግዚአብሔር አገልጋዮች በቅዱስ መቀደስ (consecration) ፊታቸው ፈክቶና እያንፀባረቀ ከሰማይ የመጣውን መልእክት ለማወጅ ከቦታ ቦታ ይራወጣሉ። በምድር ሁሉ በሺዎች በሚቆጠሩ ድምፆች መልእክቱ ይሰጣል። ተዓምራት ይደረጋሉ፣ ህሙማን ይፈወሳሉ፣ ድንቅና ተዓምራት አማኞችን ይከተሏቸዋል። በሰዎች ፊት እሳት ከሰማይ እስኪያወርድ ድረስ ሰይጣንም ሐሰተኛ ተዓምራትን ይሰራል [ራዕይ 13÷13]። በእንዲህም ሁኔታ የምድር ነዋሪዎች አቋማቸውን እንዲወስዱ ይደረጋሉ። GCAmh 442.1

መልእክቱ፣ ለመንፈስ ቅዱስ በጥልቅ በመሰጠት የሚራመደውን ያህል በክርክር ወደ ፊት አይገፋም። መከራከሪያዎቹ (አመክንዮዎቹ) ከወዲሁ ቀርበዋል። ዘሩ ተዘርቷል፣ አሁን ያድግና ፍሬ ያፈራል። በሚስዮናዊያኑ የተበተኑት ህትመቶች ተጽዕኖአቸውን አሳርፈዋል፤ ሆኖም ብዙ አዕምሮአቸው [በወንጌሉ] የተነካ እውነቱን ሙሉ ለሙሉ ከማስተዋል ወይም ለመታዘዝ እሽ ከማለት ተገድበው ቆይተዋል። አሁን የብርሐን ጮራ በሁሉም ስፍራ ይሰርጋል፤ እውነት በግልጽነቱ ይታያል፤ የእግዚአብሔር ልጆችም ያሰሯቸውን ገመዶች ይበጣጥሳሉ። የቤተሰብ ትስስሮች፣ የቤተ ክርስቲያን ግንኙነቶች፣ አሁን ያስቀሯቸው ዘንድ ኃይል-አልባ ይሆናሉ። ከሌላው ነገር ሁሉ ይልቅ እውነት የከበረ ነው። እውነትን የሚፃረሩ ወኪሎች ቢተባበሩም፣ አያሌ ቁጥር ያላቸው በእግዚአብሔር ጎራ ይቆማሉ። GCAmh 442.2