ታላቁ ተጋድሎ
ምዕራፍ ፴፯—ከአደጋ መከለያው መጽሐፍ ቅዱስ
“ወደ ሕግና ወደ ምስክር ሂዱ እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም [በውስጣቸው ብርሐን ስሌለላቸው ነው/it is because there is no light in them]” [ ኢሳ 8÷20]። ከሐሰተኛ መምህራንና ከጨለማ መናፍስት አሳሳች ኃይል ተጽዕኖ መከለያቸው ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተመርተዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ንግግሮች ማጭበርበሪያዎቹን ስለሚገልጥበት፣ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዳያገኙ ለማገድ ሰይጣን ማግኘት የሚችለውን እያንዳንዱን መሳሪያ ይጠቀማል። በእያንዳንዱ የእግዚአብሔር ሥራ መነቃቃት፣ የክፋት ልዑል ለበለጠ ሥራ ይነሳሳል፤ ክርስቶስንና ተከታዮቹን በመቃወም ለሚያደርገው የመጨረሻ ፍልሚያ ለመዘጋጀት አሁን ተወዳዳሪ የሌለው ጥረቱን እያደረገ ነው። የመጨረሻው ታላቅ ማታለያው በቅርቡ በፊታችን ይከፈታል። የክርስቶስ ተቃዋሚ (antichrist) ግሩም ሥራዎቹን ሊሰራ በቅርቡ በፊታችን ሊገለጥ ነው። አስመስሎ የሚሰራው እውነትን እጅግ ስለሚመስለው፣ በቅዱስ መጻሕፍት ካልሆነ በስተቀር በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ የማይቻል ይሆናል። እያንዳንዱ አረፍተ ነገር፣ እያንዳንዱ ተዓምር በምስክሩ [በመጽሐፍ ቅዱስ] መፈተን አለበት። GCAmh 429.1
ሁሉንም የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት ለመጠበቅ ጥረት የሚያደርጉ እነርሱ ተቃውሞ ይገጥማቸዋል፣ ይፌዝባቸዋልም። መቆም የሚችሉት በእግዚአብሔር ብቻ ነው። በፊታቸው ላለው ፈተና ፀንተው ለመቆም ይቻላቸው ዘንድ፣ በቃሉ የተገለፀውን የእግዚአብሔር ፈቃድ [የግድ] መረዳት አለባቸው፤ በትክክል ሊያከብሩት የሚችሉት የባህርይው፣ የመንግሥቱና የአላማው ትክክለኛ መረዳት ሲኖራቸው፣ እነዚያንም በተስማማ ሁኔታ ሲተገብሩ ብቻ ነው። በመጨረሻው ታላቅ ጦርነት ፀንተው የሚቀሩት በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አዕምሯቸውን ያፈረጠሙ ብቻ ናቸው። የሚበረብረው ፈተና ወደ እያንዳንዱ ነፍስ ይመጣል። ከሰዎች ይልቅ እግዚአብሔርን ልታዘዝን? ወሳኙ ሰዓት ደርሶአል፤ እግሮቻችን በማይለወጠው በእግዚአብሔር ቃል ቋጥኝ ላይ ተተክለዋልን? የእግዚአብሔርን ትዕዛዛትና የየሱስን ኃይማኖት በመደገፍ ፀንተን ለመቆም ተዘጋጅተናልን? GCAmh 429.2
ከስቅላቱ በፊት፣ እንደሚሞት፣ ከመቃብርም እንደገና እንደሚነሳ አዳኙ ለደቀ መዛሙርቱ አብራርቶላቸው ነበር፤ በአዕምሮና በልብ ላይ የእርሱን ቃላት ያትሙ ዘንድ መላዕክት በዚያ ተገኝተው ነበር። ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ ሲጠብቁት የነበረው ከሮም ቀንበር ምድራዊ ነፃ መውጣት ነበርና የተስፋቸው ሁሉ ማዕከል የሆነው እርሱ በአሳፋሪ ሞት ይሞታል የሚለው ሃሳብ ይኖር ዘንድ መታገስ አልተቻላቸውም። ማስታወስ የነበረባቸው ቃላት ከአዕምሯቸው ጠፉ፤ ፈተና ሲደርስም ሳይዘጋጁ አገኛቸው። ልክ አስቀድሞ ያላስጠነቀቃቸው ይመስል የየሱስ ሞት ተስፋዎቻቸውን በሙሉ አንኮታኮተባቸው። በክርስቶስ ቃላት ለደቀ መዛሙርቱ በግልጽ እንደተከፈቱላቸው ሁሉ ለእኛም የወደፊቱ በትንቢታት ውስጥ ተከፍቶልናል። ከምሕረት ጊዜ መዝጊያ እንዲሁም ለመከራ ጊዜው ከሚደረግ የዝግጅት ሥራ ጋር የተያያዙት ክስተቶች በግልጽ ቀርበዋል። እልፍ አዕላፋት ግን ለእነዚህ አስፈላጊ እውነቶች ያላቸው መረዳት፣ [እውነቶቹ] ፈጽመው ባይገለፁ ኖሮ ከሚኖራቸው ማስተዋል የተሻለ አይደለም። ድነትን ያውቁ ዘንድ አስተዋዮች ሊያደርጋቸው የሚችለውን እያንዳንዱን አሻራ ለመንጠቅ ሰይጣን ይከታተላቸዋል፤ የመከራ ጊዜም ሳይዘጋጁ ያገኛቸዋል። GCAmh 429.3
እጅግ አስፈላጊ ከመሆናቸው የተነሳ በሰማይ መካከል በሚበሩ ቅዱሳን መላእክት እንዲወከሉ ያደረጋቸውን ማስጠንቀቂያዎች እግዚአብሔር ወደ ሰዎች ሲልክ የማመዛዘን ኃይል የተቸረው እያንዳንዱ ሰው መልእክቱን እንዲሰማ ይጠብቅበታል። ለአውሬውና ለምስሉ በሚሰግዱ ላይ የተነገሩት አስፈሪ ቅጣቶች [ራዕይ 14÷9-11] የአውሬው ምልክት ምን እንደሆነ ይማሩ ዘንድ፣ እርሱንም ላለመቀበል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ይገነዘቡ ዘንድ ሁሉንም ሰው ትንቢታትን በትጋት ወደ ማጥናት ሊመሩአቸው ይገባቸዋል። አብዛኛው ሕዝብ ግን እውነትን ከመስማት ጆሮውን ይመልሳል፣ ወደ ተረትም ዘወር ይላል። ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት ሐዋርያው ጳውሎስ አቆልቁሎ ሲያይ እንዲህ ይላል፦ “ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጣልና” [2ኛ ጢሞ 4÷3] ያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ደርሶአል። የኃጢአተኛውን፣ የዓለም አፍቃሪውን ልብ መሻቶች ስለሚያውክ፣ እልፍ አዕላፋት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች አይፈልጉም፤ ሰይጣንም የሚያፈቅሯቸውን ማታለያዎች ያቀርብላቸዋል። GCAmh 430.1
ነገር ግን የተሐድሶዎች ሁሉ መሰረት፣ የአስተምህሮዎች ሁሉ ደረጃ መለኪያ አድርጎ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ የሚጠብቅ ሕዝብ እግዚአብሔር በምድር ይኖረዋል። የምሁራን አስተያየቶች፣ የሳይንስ ድምዳሜዎች፣ እንደሚወክሏቸው አብያተ ክርስቲያናት በቁጥር በርካታ የሆኑትና የሚጋጩት የመንፈሳዊ ጉባኤ እምነቶችና ውሳኔዎች፣ የአብላጫ ድምጽ — እነዚህ ሁሉ፣ ማንኛቸውም ቢሆኑ አንድን ኃይማኖታዊ ጉዳይ ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል እንደመረጃ ሆነው ሊወሰዱ አይገባቸውም። ማንኛውንም አስተምህሮ ወይም መመሪያ ከመቀበላችን በፊት፣ ድጋፍ የሚሆነው፣ ግልጽ የሆነ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል” የሚል [ቃል] መጠየቅ ይገባናል። GCAmh 430.2
በእግዚአብሔር ፈንታ በሰው ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ ለመሳብ ሰይጣን ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ነው። ያለባቸውን ኃላፊነት ራሳቸው እንደ መሪያቸው አድርገው መጽሐፍ ቅዱስን ከመመርመር ይልቅ ወደ ጳጳሳት፣ ወደ ፓስተሮች፣ ወደ ስነ-መለኮት ፕሮፌሰሮች እንዲመለከቱ ሕዝቡን ይመራቸዋል። ከዚያም የእነዚህን መሪዎች አዕምሮ በመቆጣጠር፣ እንደ ፈቃዱ በእልፍ አዕላፋት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይቻለዋል። GCAmh 430.3
የሕይወትን ቃል ይናገር ዘንድ ክርስቶስ ሲመጣ ተራ ሰዎች በደስታ አዳመጡት፤ ብዙዎች፣ ካህናትና ገዥዎች ሳይቀር በእርሱ አመኑ። ነገር ግን የካህናት አለቆችና የአገሪቱ ቀንደኛ ሰዎች ትምህርቶቹን ለማውገዝና ለመካድ ወሰኑ። ጥፋት ያገኙበት ዘንድ ባደረጓቸው ጥረቶች ሁሉ ግራ ቢጋቡም፣ ከቃሉ የሚወጣውን የመለኮታዊ ኃይልና የጥበብ ተጽዕኖ ስሜት ማስወገድ ባይችሉም፣ እነርሱ ግን ራሳቸውን በጥላቻ አሸጉት፤ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ይሆኑ ዘንድ እንዳይገደዱ መሲህ ስለመሆኑ የሚያረጋግጠውን ፈጽሞ ግልጽ የሆነውን መረጃ አንቀበልም አሉ። እነዚህ የየሱስ ተቃዋሚዎች፣ ሕዝቡ ገና ከጨቅላነቱ ጀምሮ እንዲያከብራቸው የተማረ፣ ለስልጣናቸውም ያለምንም ጥያቄ የማጎብደድ ልምድ ያለው፣ ሰዎች ነበሩ። “አለቆቻችንና ፃፎቻችን በየሱስ የማያምኑት እንዴት ነው?” “ክርስቶስ ቢሆን ኖሮ እነዚህ ፃድቅ ሰዎች አይቀበሉትም ነበርን?” አሉ። የአይሁድ ሕዝብ ተቤዥያቸውን አንቀበልም እንዲሉ ያደረጋቸው የእንደዚህ አይነት መምህራን ተጽዕኖ ነበር። GCAmh 430.4
እነዚያን ካህናትና አለቆች ያነሳሳው መንፈስ፣ ኃይማኖተኛነትን እንደ ትልቅ ሙያ በሚቆጥሩ ብዙዎች ዘንድ አሁንም ይንፀባረቃል። ለዚህ ዘመን የተሰጡትን የተለዩ እውነቶች በተመለከተ የመጽሐፍ ቅዱስን ምስክርነት ለመመርመር እምቢ ይላሉ። ወደ ቁጥራቸው ብዛት፣ ሐብትና ተወዳጅነት እየጠቆሙ፣ የእውነት ደጋፊዎችን፣ ጥቂቶች፣ ድሆችና በብዙሃን ዘንድ የማይወደዱ፣ ከዓለም የነጠላቸውን እምነት የያዙ፣ አድርገው በንቀት ይመለከቷቸዋል። GCAmh 431.1
በፃፎችና በፈሪሳውያን ዘንድ የነበረው ከመጠን ያለፈ ስልጣን ባለቤት መሆን፣ በአይሁዳዊያን መበተን እንደማያበቃ ክርስቶስ ቀደም ብሎ ተገንዝቦ ነበር። በዘመናት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አሰቃቂ መርገም የሆነው፣ ህሊናን ይገዛ (ይቆጣጠር) ዘንድ የሰብአዊ ፍጡርን ስልጣን ከፍ የማድረግ ሥራ ትንቢታዊ እይታ እርሱ ነበረው። በፃፎችና በፈሪሳዊያን የሰነዘረው አስፈሪ ውግዘትና እነዚህን እውር መሪዎች እንዳይከተሉ ሕዝቡን ያስጠነቀቀበት [ንግግሮቹ] በጽሁፍ የሰፈሩት ለወደፊት ትውልዶች ተግሳፅ ይሆኑ ዘንድ ነበር። GCAmh 431.2
የሮማዊት ቤተ ክርስቲያን፣ ለመሪዎችዋ መጽሐፍ ቅዱስን የመተርጎምን መብት ትጠብቅላቸዋለች። ሐይማኖታዊ መሪዎች ብቻ ናቸው የእግዚአብሔርን ቃል ለማብራራት ብቃት ያላቸው በሚለው መሰረተ ሐሳብ በመደገፍ [ቃሉ] ከተራው ሕዝብ ይታገዳል። ተሐድሶው መጽሐፍ ቅዱስን ለሁሉም ቢሰጥም፣ በሮም ተጠብቆ የኖረው ያው ራሱ መርህ በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት ያሉትን እልፍ አዕላፋት፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለራሳቸው እንዳይመረምሩ ያግዳቸዋል። እንደ ቤተ ክርስቲያንዋ አቋም] የተተረጎሙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እንዲቀበሉ ይማራሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፍንትው ብሎ የተገለፀ ቢሆንም፣ ከእምነታቸው ጋር የሚቃረን ወይም የኖረውን የቤተ ክርስቲያናቸውን ትምህርት የሚፃረር ከሆነ ምንም ነገር ላለመቀበል የማይዳዳቸው በሺዎች የሚቆጠሩ አሉ። GCAmh 431.3
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሐሰተኛ መምህራን በማስጠንቀቂያ የተሞላ ቢሆንም እንኳ፣ ነፍሳቸውን ለኃይማኖታዊ መሪዎች ጥበቃ በአደራ ለመስጠት ብዙዎች የተዘጋጁ ናቸው። ዛሬ ለያዟቸው የእምነት አቋሞች፣ እንደዚያ እንዲያደርጉ በኃይማኖታዊ መሪዎቻቸው እንደታዘዙ ከመናገር በቀር ሌላ ምንም ምክንያት ማቅረብ የማይችሉ ኃይማኖተኞች ነን የሚሉ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። የአዳኙን ትምህርቶች ትኩረት ሳይሰጡ ያልፏቸውና በአገልጋዮች ቃላት ላይ የማያወላውል መታመን ያደርጋሉ። ነገር ግን አገልጋዮች ስህተት መሥራት የማይቻላቸው ናቸውን? ብርሐን ተሸካሚ መሆናቸውን ከእግዚአብሔር ቃል ካላረጋገጥን በስተቀር የእነርሱን ምሪት አምነን እንዴት ነፍሳችንን እንስጣቸው? ዓለም ከሚነጉድበት መንገድ ገለል ለማለት የሚያስችል የግብረ ገብነት ድፍረት አለመኖር፣ የተማሩ ሰዎችን ዱካ እንዲከተሉ ብዙዎችን ይመራቸዋል፤ ለራሳቸው ለመመርመር ባላቸው ቸልተኝነትም ተስፋ በሚያስቆርጥ መልኩ በስህተት ሰንሰለት እየተጠፈሩ ናቸው። ለዚህ ዘመን የሚሆነው እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ወደ እይታ በግልጽ እንደመጣ ያስተውላሉ፤ በአዋጆቹም ላይ የቅዱስ መንፈስ ኃይል መገኘት እንዳለ ይሰማቸዋል፤ ሆኖም የቤተ ክርስቲያን ሹማምንት ተቃውሞ ከብርሐኑ ዘወር እንዲያደርጋቸው ይፈቅዳሉ። ምክንያትና ህሊና ያመኑ ቢሆኑም እነዚህ የተሞኙ ነፍሳት ከአገልጋዩ የተለየ ነገር ማሰብን አይሞክሯትም፤ ግላዊ ሚዛናቸው፣ ዘላለማዊ ፍላጎቶቻቸው ለሌላው እምነት የለሽነት፣ ኩራትና ጥላቻ ይሰዋሉ። GCAmh 431.4
ሰይጣን ምርኮዎቹን ለመጠፈር በሰው ተጽዕኖ በኩል የሚሰራባቸው መንገዶች በርካታ ናቸው። የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ከሆኑት ጋር በሃር የፍቅር ገመድ በማቆራኘት ሰይጣን እልፍ አዕላፋትን የራሱ ያደርጋቸዋል። ቁርኝቱ ምንም አይነት ቢሆን፣ የወላጅ፣ የልጅ፣ የጋብቻ ወይም የወዳጅነት ቢሆን፣ ተጽዕኖው ተመሳሳይ ነው፤ የእውነት ጨቋኞች ህሊናን ለመቆጣጠር ኃይላቸውን ይጠቀማሉ፤ በቁጥጥራቸው ሥር ያሉ ነፍሳትም የራሳቸው ህሊና የሚያምበትን ለመታዘዝ በቂ ወኔ ወይም ግላዊ-ነፃነት የላቸውም። GCAmh 432.1
እውነትና የእግዚአብሔር ክብር የሚነጣጠሉ አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስን ማግኘት እየቻልን በተሳሳቱ አመለካከቶች እግዚአብሔርን እናከብረው ዘንድ አይቻለንም። ሕይወቱ ፃድቅ (ትክክለኛ) እስከሆነ ድረስ አንድ ሰው የሚያምነው ምንም ቢሆን ችግር የለውም ይላሉ ብዙዎች፤ ሕይወት ግን ቅርጽ የሚወጣለት በእምነት ነው። ብርሐንና እውነት መድረስ የምንችልባቸው ሆነው፣ ያንን የመስማትና የማየት ዕድል እናጎለብት ዘንድ ቸል ብንል ልክ እንዳልተቀበልነው ይቆጠራል፤ ከብርሐን ይልቅ ጨለማን እየመረጥን ነው። GCAmh 432.2
“ለሰው ቅን የምትመስል መንገድ አለች፣ ፍፃሜዋ ግን የሞት መንገድ ነው” [ምሳ 16÷25]። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማወቅ የሚያስችል ሁሉም ዕድል እያለ፣ ድንቁርና ለስህተት ወይም ለኃጢአት ማሳበቢያ ምክንያት አይሆንም። አንድ ሰው በጉዞ ላይ እያለ ወደ ብዙ አቅጣጫ የሚያመሩ መንገዶች ወዳሉበት፣ እያንዳንዱም መንገድ ወደየት እንደሚወስድ የሚጠቁም ሰሌዳ ወዳለበት ስፍራ ቢደርስና፤ አቅጣጫ ጠቋሚውን ሰሌዳ ቸል ብሎ፣ ትክክል የመሰለውን መንገድ ቢመርጥ፣ ምኑንም ያህል እጅግ ቅን ቢሆን፣ በተሳሳተ መንገድ ላይ ራሱን የማግኘቱ ዕድል እጅግ የሰፋ ነው። GCAmh 432.3
ከትምህርቶቹ ጋር እንተዋወቅ ዘንድ፣ እርሱ ከእኛ ምን እንደሚፈልግም ለራሳችን እናውቅ ዘንድ እግዚአብሔር ቃሉን ሰጠን። የሕጉ ሰው “የዘላለምን ሕይወት እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ?” በሚለው ጥያቄ ወደ የሱስ ሲመጣ “በሕግ የተፃፈው ምንድን ነው እንዴትስ ታነበዋለህ?” [ሉቃስ 10÷25-26] በማለት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መራው። የዚያ ሕግ፣ የመመሪያዎቹና መጠይቆቹ ሁሉ የታመነ አቅርቦት በእጃቸው ውስጥ ስላለ፣ ድንቁርና ለወጣትም ሆነ ለዕድሜ ባለፀጋው ማሳበቢያ ሊሆን ወይም የእግዚአብሔርን ሕግ ለሚጥሱ ከተዘጋጀው ቅጣት ሊያስመልጣቸው አይችልም። መልካም አመለካከት መኖሩ በቂ አይደለም፤ አንድ ሰው ትክክል የመሰለውን ወይም አገልጋዩ ትክክል ነው ብሎ የነገረውን ማድረጉ በቂ አይደለም። የነፍሱ መቤዠት አደጋ ላይ ነውና መጽሐፍ ቅዱስን ራሱ መመርመር አለበት። እምነቶቹ ምንም ያህል ጠንካራ ቢሆኑ፣ አገልጋዩ እውነት ምን እንደሆነ እንደሚያውቅ ምንም ያህል መተማመን ቢኖረው፣ ይህ የእርሱ መሰረት አይደለም። ወደ ሰማይ የሚያደርገውን ጉዞ እያንዳንዱን አቅጣጫ የሚጠቁም ካርታ አለው፣ ምንም ነገር ላይ መገመት አያስፈልገውም። GCAmh 432.4
እውነት ምን እንደሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይማር ዘንድ፣ በብርሃኑም ይመላለስ ዘንድ፣ ምሳሌውንም እንዲከተሉ ሌሎችን ያበረታታ ዘንድ፣ የእያንዳንዱ አመዛዛኝ ፍጡር ተቀዳሚና ተወዳዳሪ የሌለው ኃላፊነቱ ነው። ጥቅስን ከጥቅስ እያነፃፀርን፣ እያንዳንዱን ሃሳብ እየመዘንን፣ ቀን በቀን መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት አለብን። በመለኮት እርዳታ አመለካከቶቻችን ለራሳችን ማበጀት አለብን፤ በእግዚአብሔር ፊት መመለስ የሚኖርብን ስለራሳችን ነውና። GCAmh 433.1
መጽሐፍ ቅዱስ በተፃፈበት ቋንቋ ሊስተዋል (በቀላሉ ሊታይ) የማይችል ረቂቅ፣ ምስጢራዊና መንፈሳዊ ትርጉም እንዳለው በሚያስተምሩ ታላቅ ጥበብ እንዳላቸው በሚያስመስሉ ምሁራን ምክንያት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ፍንትው ብለው የተገለፁት እውነቶች በጥርጣሬና በጽልመት እንዲወሳሰቡ ሆነዋል። እነዚህ ሰዎች ሐሰተኛ መምህራን ናቸው። የሱስ “መጻሕፍትንና እግዚአብሔርን አታውቁምና” ብሎ የተናገረው ለእንደዚህ አይነት መደቦች ነው [ማር 12÷24]። ምሳሌ ወይም ምልክት ጥቅም ላይ ካልዋለ በስተቀር የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ በግልጽ እንደተቀመጠው እንደዚያው ትርጉሙም መብራራት አለበት። “ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ቢሆን ያውቃል” በማለት ተስፋውን ሰጥቷል [ዮሐ 7÷17]። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንደተፃፈው አድርገው ራሱን ቢቀበሉ፣ አዕምሮአቸውን የሚያደናግሩና የሚያስቱ ሐሰተኛ መምህራን ባይኖሩ፣ መላእክትን የሚያስደስት፣ አሁን በስህተት ውስጥ የሚቅበዘበዙትን ሺህ በሺህ የሆኑትን ወደ ክርስቶስ መንጋ የሚያመጣ ሥራ በተከናወነ ነበር። GCAmh 433.2
ሟች ፍጡር እስከሚችልበት አቅም ጥግ ድረስ የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገሮች እንረዳ ዘንድ የአዕምሮን ኃይላት ሁሉ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማዋል፣ ለመረዳት ችሎታችንም የማስተዋልን ኃላፊነት መስጠት፣ ይገባናል፤ ሆኖም የህፃን ታዛዥነትና ተሸናፊነት የተማሪው እውነተኛ መንፈስ እንደሆነ መዘንጋት የለብንም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከባድ የሆኑ ነገሮችን፣ የፍልስፍናዊ እክሎችን ለመፍታት የምንታገልባቸውን አይነት ዘዴዎች በመጠቀም ፈጽሞ መረዳት አይቻልም። አያሌ ሰዎች የሳይንስን ክፍለ ወሰን ለማጥናት በሚገቡበት አይነት፣ በራስ በመደገፍ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የለብንም፤ በፀሎት በተሞላ አምላካዊ ድጋፍ፣ ፈቃዱንም ለመማር በእውነተኛ መሻት እንጂ። ከታላቁ እኔ ነኝ (I AM) እውቀት እናገኝ ዘንድ ትሁትና መማር የሚችል መንፈስ ይዘን መምጣት አለብን። ያለበለዚያ ክፉ መላእክት አዕምሮዎቻችንን ያሳውሩአቸውና፣ ልቦቻችንንም ያደነድኑአቸውና በእውነቱ መመሰጥ ሳይሆንልን ይቀራል። GCAmh 433.3
የተማሩ ሰዎች ምስጢራዊ ናቸው የሚሏቸው ወይም አስፈላጊ አይደሉም ብለው የሚያልፏቸው ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በክርስቶስ ትምህርት ቤት ለተማረ ለእርሱ በማጽናኛና በምሪት የተሞሉ ናቸው። በርካታ የስነ-መለኮት ሊቆች የእግዚአብሔር ቃል የተሻለ መረዳት የሌላቸው አንዱ ምክንያት ሊተገብሯቸው ለማይፈልጓቸው እውነቶች ዓይናቸውን ስለሚጨፍኑ ነው። [ቃሉን] ለመመርመር የሚውለው የማሰብ ችሎታ(የአዕምሮ) ኃይል፣ አንድ አላማ የመያዝንና ጽድቅን ከልብ የመጠማትን ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ለመረዳት አያግዝም። GCAmh 433.4
መጽሐፍ ቅዱስ ያለ ፀሎት ፈጽሞ መጠናት የለበትም። በቀላሉ የምንረዳቸው ነገሮች አስፈላጊነት እንዲሰማን ወይም ለመረዳት አስቸጋሪ ከሆኑት እውነቶች ጋር ግብግብ እንዳንገጥም ለማድረግ የሚቻለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው። በውበቱ እንማረክ ዘንድ፣ በማስጠንቀቂያው እንገሰጽ ዘንድ ወይም በተስፋዎቹ ሕይወት ይዘራብን እና እንጠነክር ዘንድ ልብ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያስተውል የማዘጋጀት ሥራ የሰማያዊ መላእክት ኃላፊነት ነው። የመዝሙረኛውን ተማጽዕኖ የራሳችን ልናደርገው ይገባናል፦ “አይኖቼን ክፈት፣ ከሕግህም ተአምራትህን አያለሁ” [መዝ 119÷18]። አብዛኛውን ጊዜ ፈተናዎች መቋቋም የማይቻሉ ይመስላሉ፤ ምክንያቱም ፀሎትንና የመጽሐፍ ቅዱስን ጥናት ቸል በማለቱ ተፈታኙ ሰው የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ወዲያውኑ አስታውሶ በመጽሐፍ ቅዱስ [ጥቅስ] መሳሪያዎች ሰይጣንን መፋለም ስለማይችል ነው። በመለኮታዊ ነገሮች ለመማር ፈቃደኛ በሆኑት በእነርሱ ግን መላእክት በዙሪያቸው ናቸው፤ እጅግ አስፈላጊ በሆነው ሰዓትም፣ አስፈላጊ የሆኑትን፣ ለዚያ ጊዜ ገጣሚ የሆኑትን እውነቶች እንዲያስታውሱ ያደርጋቸዋል። ስለዚህም “ጠላት እንደጽኑ ፈሳሽ ሲመጣ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በእርሱ ላይ ምልክቱን ያነሳበታል” [ኢሳይያስ 59÷19]። GCAmh 434.1
የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ተስፋ ሲሰጥ እንዲህ አላቸው፣ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” [ዮሐ 14÷25]። በአደጋ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲያስታውሰን፣ የክርስቶስ ትምህርቶች አስቀድመው በአዕምሮ ውስጥ መከዘን (መጠራቀም) አለባቸው። “አንተን እንዳልበድል” አለ ዳዊት “ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” [መዝ 119÷11]። GCAmh 434.2
ለዘላለማዊ ፍላጎቶቻቸው ዋጋ የሚሰጡ ሁሉ የጥርጥርን ጣልቃ ገብነት ለመከላከል በተጠንቀቅ መሆን አለባቸው። የእውነት ምሰሶዎች ኃይለኛ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ከዘመናዊ ክህደት የአሽሙር እና የውሸት ክርክር፣ ሳይታወቅ ውስጥ ውስጡን ከሚበላ ቸነፈራዊ ትምህርት መዳረሻ ውጭ መሆን ፈጽሞ የሚቻል አይደለም። ሰይጣን ፈተናዎቹን ለሁሉም መደቦች እንዲስማሙ ያደርጋቸዋል። በሁለቱም ወገን በተመሳሳይ ሁኔታ በተሰላ አካሄድ አለመተማመንን ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ንቀትን ለማነሳሳት፣ ያልተማረውን በፌዝና በንቀት ሲያጠቃ፣ የተማረውን ደግሞ በሳይንሳዊ ተቃውሞዎችና በፍልስፍና አመክኔዎች ይገናኛቸዋል። እዚህ ግባ የማይባል ልምድ ያላቸው ወጣቶች እንኳ መሰረታዊ የክርስትና መርሆዎችን በተመለከተ የጥርጥር አግቦአዊ አነጋገር ለመሰንዘር ይዳዳቸዋል። ይህ የወጣት ክህደት፣ ጥልቀት የሌለው ቢሆንም ተጽዕኖ አለው። በዚህም ምክንያት ብዙዎች በአባቶቻቸው እምነት ላይ እንዲቀልዱ፣ በፀጋ መንፈስ ላይም ንቀት እንዲፈጽሙ ይመራሉ [ዕብ 10÷29]። ለእግዚአብሔር ክብር፣ ለዓለም ደግሞ በረከት ይሆናሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው ብዙ ነፍሳት በክህደት የሚሸት ትንፋሽ ዋግ ተመተዋል። በሰብአዊ አመክንዮ ኩራተኛ ውሳኔዎች ላይ የሚተማመኑ፣ መለኮታዊ ምስጢራትን መተንተን እንደሚችሉና፣ ያለ እግዚአብሔር ጥበብ እርዳታ እውነት ላይ እንደርሳለን ብለው የሚያልሙ እነርሱ በሰይጣን ወጥመድ የተተበተቡ ናቸው። GCAmh 434.3
ያለነው በዚህ ዓለም ታሪክ እጅግ ከባድ በሚባለው ዘመን ውስጥ ነው። እየተትገለገለ ያለው የዓለም እልፍ አዕላፍ መዳረሻ ሊወሰን ነው። የራሳችን የወደፊቱ ደህንነት፣ የሌሎች ነፍሳት ድነት ጭምር አሁን በምንራመደው መንገድ የሚወሰን ነው። በእውነት መንፈስ መመራት ያስፈልገናል። እያንዳንዱ የክርስቶስ ተከታይ፣ “ጌታ ሆይ ምን አደርግ ዘንድ ትወዳለህ” ብሎ መጠየቅ አለበት። በፆምና በምልጃ፣ በተለይም በፍርዱ ትዕይንት ላይ በሚያተኩረው ቃሉ ላይ እየተመሰጥን በእግዚአብሔር ፊት ራሳችንን ማዋረድ ያስፈልገናል። በእግዚአብሔር ነገሮች ላይ ጥልቅና ሕያው የሆነ ልምምድ አሁን መሻት ይገባናል። የምናባክነው አንድ ሰኮንድ እንኳ የለንም። እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ክስተቶች በዙሪያችን እየተከናወኑ ነው፤ በሰይጣን የድግምት ምድር ላይ ነን። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሆይ አትተኙ፤ ጠላት በአቅራቢያው አድፍጦ እያደባ ነው። ግድ የለሽና የምታንቀላፉ ከሆናችሁ፣ በማንኛውም ጊዜ ተዘጋጅቶ፣ ተስፈንጥሮ ሊከመርባችሁና መብሉ ሊያደርጋችሁ ጠላት በአቅራቢያችሁ አድፍጦ እያደባ ነው። GCAmh 434.4
በእግዚአብሔር ፊት ስላሉበት ትክክለኛ ሁኔታ ብዙዎች ተታለዋል። ያደርጓቸው ዘንድ ቸል ያልዋቸውን፣ ያከናውንዋቸው ዘንድ እግዚአብሔር የሚፈልግባቸውን መልካምና የተከበሩ ተግባራት መቁጠር ረስተው፣ ስላልፈፀሟቸው የስህተት ተግባራት ራሳቸውን እንኳን ደስ ያለህ ይላሉ። በእግዚአብሔር የአትክልት ስፍራ ዛፎች መሆናቸው በቂ አይደለም። ፍሬ በማፍራት ለሚጠብቅባቸው መልስ መስጠት ይኖርባቸዋል። ፀጋው እያበረታቸው ያከናውኑአቸው ዘንድ ይቻላቸው ስለነበሩት፣ ነገር ግን ስላላደረጓቸው መልካም ነገሮች ሁሉ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። በሰማይ መጻሕፍት የእርሻው መሰናክሎች ተብለው ይመዘገባሉ። ነገር ግን የዚህ መደብ ጉዳይ እንኳ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አስቆራጭ አይደለም። የእግዚአብሔርን ምሕረት ባቃለሉ፣ ፀጋውንም ባጎሳቆሉ ዘንድ የታጋሽ (ጽኑ) ፍቅር ልብ አሁንም ይማፀናል። “ስለዚህ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሳ ክርስቶስ ያበራልሃል።” “እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ።” [ኤፌ 5÷14-16]። GCAmh 435.1
ፈታኙ ሰዓት በደረሰ ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል የሕይወታቸው መመሪያ ያደረጉ እነርሱ ይገለጣሉ። በበጋ ወራት ሁሌም አረንጓዴ በሆኑ ዛፎችና በሌሎቹ መካከል በቀላሉ የሚታይ ልዩነት የለም፤ የክረምቱ ኃይለኛ ነፋስ በመጣ ጊዜ ግን፣ ሁሌም አረንጓዴዎቹ ዛፎች ምንም ሳይለወጡ ሲቀሩ፣ ሌሎች ዛፎች ግን ቅጠላቸው ይረግፋል። እንደዚሁም ሐሰተኛ ልብ ያለው አማኝ አሁን ከትክክለኛው ክርስቲያን አይለይ ይሆናል፤ ልዩነቱ ገሃድ የሚሆንበት ጊዜ ግን በላያችን ነው። እስኪ ተቃውሞ ይነሳ፣ አክራሪነትና አለመቻቻል ቦታ ይሰጣቸው ስደትም ይቀጣጠል፤ ባለ-ከፊል ልቦችና ግብዞች ተንገዳግደው እምነታቸውን ይተዋሉ፤ ነገር ግን ከብልጽግና ዘመናቱ ይልቅ፣ እምነቱ ጠንክሮና ተስፋው ፈክቶ እውነተኛው ክርስቲያን እንደ ቋጥኝ ሳይነቃነቅ ይኖራል። GCAmh 435.2
መዝሙረኛው እንዲህ ይላል፦ “ምስክርህ ትዝታዬ ነውና [Thy testimonies are my meditation]” “ከትዕዛዛትህ የተነሳ አስተዋልሁ” “ስለዚህ የሐሰትን መንገድ ጠላሁ።” [መዝ 119÷99፣104]። GCAmh 435.3
“ጥበብን የሚያገኝ ሰው ምስጉን ነው” “በውኃ አጠገብ እንደተተከለ በወንዝም ዳር ስሩን እንደሚዘረጋ ሙቀትም ሲመጣ እንደማይፈራ ቅጠሉም እንደሚለመልም በድርቅ ዓመትም እንደማይሰጋ ፍሬውንም እንደማያቋርጥ ዛፍ ይሆናል።” [ምሳ 3÷13፤ ኤር 17÷8]። GCAmh 435.4