ታላቁ ተጋድሎ

30/45

ምዕራፍ ፳፯—ዘመናዊ መነቃቃቶች

የእግዚአብሔር ቃል በታማኝነት በተሰበከበት በማንኛውም ስፍራ ሁሉ ምንጩ መለኮታዊ እንደሆነ የሚያረጋግጡ ማሳያዎች ይዞ የሚመጣ ውጤት አለው። የባሪያዎቹን መልእክት የእግዚአብሔር መንፈስ አጅቦት ነበር፤ ቃሉም ኃይል ነበረው። ኃጢአተኞች ንቃተ-ህሊናቸው ሲነቃቃ ተሰምቷቸዋል። “ለሰው ሁሉ የሚበራ ወደ ዓለም ለሚመጣው” የነፍሳቸውን ምስጢራዊ ክፍሎች አበራ፣ የተደበቁት የጽልመት ነገሮችም ይፋ ሆኑ። ጥልቅ እምነት አዕምሯቸውንና ልባቸውን ያዘው። ስለ ኃጢአት ስለጽድቅና ስለሚመጣው ፍርድ አመኑ። የእግዚአብሔርን ጽድቅ በመጠኑም ቢሆን ተረድተው ነበርና ልብን በሚመረምረው ፊት ከነኩነኔያቸውና ከነእድፋቸው መቆምን ሲያስቡት እጅግ አርበደበዳቸው። እየተሰቃዩም እንዲህ ጮሁ፦ “ለዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛ/[ና]ል?” [ሮሜ 7÷24] አሉ። የቀራንዮ መስቀል፣ ለሰው ልጅ ኃጢአት ከተከፈለው፣ የዋጋ ተመን ከሌለው መስዋዕት ጋር ሲገለጽላቸው ለመተላለፋቸው ስርየት ለማግኘት የሚበቃው የክርስቶስ ሥራ ብቻ እንደሆነ ተመለከቱ። በእምነትና ራስን በማዋረድ ውስጥ ሆነው የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግደውን የእግዚአብሔር በግ ተቀበሉ። በየሱስ ደም አማካኝነት “ስለ ቀደመችው ኃጢአት ስርየት” [ሮሜ 3÷25] ተደረገላቸው። GCAmh 334.1

እነዚህ ነፍሳት ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አፈሩ። አምነው ተጠመቁ፤ በየሱስ ክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ሆነው — በአዲስ ሕይወት ለመመላለስ ተነሱ። በቀድሞ ፍላጎቶቻቸው ላይቀረፁ፤ በእግዚአብሔር ልጅ እምነት ዱካውን ሊከተሉ፣ ባህርይውን ሊያንፀባርቁና እርሱ ንፁህ እንደሆነ እነርሱም ንፁህ ይሆኑ ዘንድ ነበራቸው። ይጠሏቸው የነበሩትን ነገሮች አሁን ወደዷቸው፤ ቀድሞ ይወዷቸው የነበሩትን ደግሞ አሁን ጠሉአቸው። ኩሩና በእኔነት የሚተማመነው ማንነት የዋህና የተዋረደ ሆነ። የተንቦጠረረና ግብዝ የነበረው ኮስታራና ምስኪን ሆነ። ኃይማኖትን ይንቅ የነበረው አክባሪ፣ ሰካራሙ የማይጠጣ፣ ምግባረ-ብልሹ የነበረው ንፁህ ሆነ። ከንቱ የሆኑት ዓለማዊ ፋሽኖች ተተው። ክርስቲያኖች የሚፈልጉት፣ “ጠጉርን በመሸረብና ወርቅን በማንጠልጠል ወይም ልብስን በመጎናፀፍ አይሁንላችሁ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው” መሆንን ሆነ [1ኛ ጴጥ 3÷3፣4]። GCAmh 334.2

መነቃቃቶች ጥልቅ የልብ ምርመራና መዋረድን አስከተሉ። ልባዊና የምር የሆኑ፣ በክርስቶስ ደም ዋጋ ለተገዛው ርኅራኄ የሚያሳዩ፣ ኃጢአተኛው ይመጣ ዘንድ የሚለምኑ ነበሩ። ወንዶችና ሴቶች ይፀልዩ፣ ለሰዎችም መዳን ከእግዚአብሔር ጋር ይታገሉ ነበር። የእንደዚህ አይነቶቹ መነቃቃቶች ውጤቶች ራስን ከመካድና ከመስዋዕትነት ያፈገፈጉ ሳይሆን ለክርስቶስ ሲሉ ፈተናና ነቀፋ ይገጥማቸው ዘንድ የተገባቸው ሆነው በመቆጠራቸው ሐሴት በሚያደርጉ ነፍሳት ይታይ ነበር። በየሱስ ስም ያመኑ እነርሱ ሕይወታቸው ሲቀየር ሰዎች ተመለከቱ። ማህበረሰቡ በተጽዕኖአቸው ተጠቃሚ ሆነ። ከክርስቶስ ጋር ሰበሰቡ፣ የዘላለም ሕይወትን ያጭዱ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ዘሩ። GCAmh 334.3

ስለ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ይባላል፦ “ለንስሐ አዝናችኋልና” “እንደ እግዚአብሔር የሆነ ሃዘን ጸጸት የሌለበት ወደ መዳንም የሚያደርሰውንም ንስሐ ያደርጋልና። የዓለም ሃዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን እንዴት ያለ ትጋት፣ እንዴት ያለ መልስ፣ እንዴት ያለ ቁጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሃት፣ እንዴት ያለ ናፍቆት፣ እንዴት ያለ ቅንዓት፣ እንዴት ያለ በቀል በመካከላችሁ አደረገ። በዚህ ነገር ንፁሐን እንደሆናችሁ በሁሉ አስረድታችኋል።” [2ኛ ቆሮ 7÷9-11]። GCAmh 335.1

ይህ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ ውጤት ነው። መለወጥን ወይም መታደስን ካላደረገ በስተቀር ለእውነተኛ ንስሐ ማስረጃ የለውም። ቃል ኪዳኑን ካደሰ፣ የዘረፈውን መልሶ ከሰጠ፣ ኃጢአቱን ከተናዘዘ፣ እግዚአብሔርንና ባልንጀሮቹን ከወደደ፣ ኃጢአተኛው ከእግዚአብሔር ጋር ሰላምን እንዳገኘ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። በቀደሙት ዓመታት፣ የኃይማኖት መነቃቃት ወራትን ተከትለው የመጡ ውጤቶች እንደዚህ ዓይነት ነበሩ። በፍሬያቸው ተመዝነው፣ በሰዎች ደህንነትና የሰው ዘርን ከፍ ከፍ በማድረግ በእግዚአብሔር የተባረኩ መሆናቸው የሚታወቅ ነበር። GCAmh 335.2

ነገር ግን በቅርብ ዘመናት የሚደረጉ መነቃቃቶች፣ ቀደም ባሉ ጊዜያት የእግዚአብሔር ባሪያዎችን ጥረት ተከትለው ከሚመጡት የመለኮታዊ ፀጋ ምልክቶች ጋር ሲነፃፀሩ ጉልህ ልዩነት ያለባቸው ሆነዋል። እርግጥ ነው መጠነ-ሰፊ ፍላጎት ተቀጣጥሏል፤ ብዙዎች መለወጥን ይመሰክራሉ፤ ብዙ ሕዝብም ወደ ቤተ ክርስቲያን ይጨመራል። ሆኖም ውጤቶቹ በዚያው ልክ እውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ስለመጨመሩ ዋስትና የሚሰጡ አይደሉም። ለተወሰነ ጊዜ የሚንቦገቦግ ብርሐን ብዙ ሳይቆይ ይጠፋል። ጨለማውም ከበፊቱ የባሰ ደጎጎን ይሆናል። GCAmh 335.3

ተወዳጅ መነቃቃቶች ብዙ ጊዜ የሚካሄዱት ምናብን በሚስብ፣ ስሜትን በሚቀሰቅስ፣ አዲስና አስገራሚ ለሆኑ ነገሮች ያለውን ፍቅር ለማርካት ነው። በዚህ ሁኔታ የተለወጡ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ለመስማት፣ ለነብያትና ለሐዋርያት ምስክርነት፣ ያላቸው ፍላጎት እጅግ አናሳ ነው። ኃይማኖታዊ አገልግሎቱ አንዳች የሚያስፈነድቅ (ስሜት የሚያስገነፍል) ባህርይ ከሌለው ለእነርሱ የሚስብ አይደለም። ስሜታዊ ያልሆነ ምክንያትን የሚጠቅስ መልእክት ለአፀፋ የሚጎተጉታቸው አይደለም። ዘላለማዊ ፍላጎቶቻቸውን በቀጥታ የሚመለከቱት የእግዚአብሔር ቃል ግልጽ ማስጠንቀቂያዎች ቸል ተብለዋል። GCAmh 335.4

በእውነት ለተለወጠ ነፍስ፣ ከእግዚአብሔርና ከዘላለማዊ ነገሮች ጋር ያለው ግንኙነት የሕይወት ዋና ርዕስ ነው። በዛሬዎቹ ተወዳጅ አብያተ ክርስቲያናት ለእግዚአብሔር የመቀደስ መንፈስ የት ነው ያለው? አዲስ የሚለወጡ ሰዎች ኩራታቸውንና ለዓለም ያላቸውን ፍቅር አይተውም። ራሳቸውን ለመካድ፣ መስቀሉን ለማንሳት፣ ትሁቱንና ራሱን ዝቅ ያደረገውን የሱስን ለመከተል ያላቸው ፍላጎት ከመለወጣቸው በፊት ከነበራቸው ፍላጎት የተሻለ አይደለም። ስሙን የተሸከሙ አያሌ ሰዎች የመርሆቹ መሐይም ከመሆናቸው የተነሳ ኃይማኖት የከሃዲዎችና የተጠራጣሪዎች መዝናኛ (ስፖርት) ሆኖአል። የእግዚአብሔር መሰልነት ኃይል ከብዙዎች አብያተ ክርስቲያናት ሙልጭ ብሎ ሊጠፋ ተቃርቧል። ሽርሽሮች፣ የቤተ ክርስቲያን ቲያትሮች፣ የቤተ ክርስቲያን ትርኢቶች፣ የሚያማምሩ ቤቶችና ታይታ ለእግዚአብሔር ያለውን ኃሳብ አጥፍተውታል። መሬቶች፣ ሸቀጣሸቀጦችና ዓለማዊ ሥራዎች አዕምሮን መስጠውታል። እናም የዘላለማዊ ጉዳዮች የአልፎ ሃጅ ትኩረት እንኳ የሚሰጣቸው ከስንት አንድ ነው! GCAmh 335.5

የተስፋፋ የእምነትና የቅድስና ማሽቆልቆል ቢኖርም የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች የሆኑ ሰዎች በእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አሉ። በመጨረሻ ምድር በእግዚአብሔር ፍርድ ከመጎብኘቷ በፊት ከሐዋርያት ጊዜ በኋላ ታይቶ የማያውቅ፣ እውነተኛ የሆነው የእግዚአብሔርን መሰልነት መነቃቃት በእግዚአብሔር ሕዝቦች መካከል ይሆናል። የእግዚአብሔር መንፈስና ኃይል በልጆቹ ላይ ይወርዳል። በዚያን ጊዜ የዚህ ዓለም ፍቅር የእግዚአብሔርንና የቃሉን ፍቅር ከተካባቸው (ቦታ ከወሰደባቸው) አብያተ ክርስቲያናት ብዙዎች ራሳቸውን ይነጥላሉ። ብዙዎች አገልጋዮችም ሆኑ ምዕመናን ለጌታ ዳግም ምፅዓት ሕዝብን ያዘጋጁ ዘንድ በዚህ ዘመን እግዚአብሔር እንዲታወጁ የሚፈልጋቸውን ታላላቅ እውነቶች በደስታ ይቀበላሉ። የነፍሳት ጠላት ይህንን ሥራ ለማደናቀፍ ይጥራል፤ ይህ አይነቱ ንቅናቄ የሚከሰትበት ጊዜ ከመምጣቱ በፊትም የሚመሳሰል ማታለያ በማቅረብ ሊገድበው ይጥራል። በአታላይ ሃይሉ ስር ሊያደርጋቸው በሚችለው አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የእግዚአብሔር የተለየ በረከት እየፈሰሰ እንደሆነ እንዲመስል ያደርጋል፤ ታላቅ የኃይማኖታዊ ፍላጎት መነሳሳት እንዳለ ሆኖ እንዲንፀባረቅ ያደርጋል። ሥራው የሌላ መንፈስ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር በግሩም ሁኔታ እያከናወነላቸው እንዳለ በማሰብ እልፍ አዕላፋት ይፈነድቃሉ። የኃይማኖትን መልክ ይዞ ሰይጣን ተጽዕኖውን ወደ ክርስቲያኑ ዓለም ሊያስፋፋ ይጥራል። GCAmh 336.1

ባለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት በተከናወኑት አብዛኛዎቹ መነቃቃቶች ዘንድ አንዳንዴ ጠና፣ አንዳንዴ ለስለስ የሚሉ ተመሳሳይ ተጽዕኖዎች በሥራ ላይ ነበሩ፤ ወደ ፊት በሚደረጉት መጠነ ሰፊ ንቅናቄዎችም የሚንፀባረቁ ይሆናሉ። ለማሳሳት እንዲያመች ሆኖ በደንብ የተስማማ፣ እውነትንና ሃሰትን ያቀላቀለ የስሜታዊ ፍንደቃ አለ። ሆኖም ማንም ሊታለል አይገባውም። በእግዚአብሔር ቃል ብርሐን አማካኝነት የነዚህን እንቅስቃሴዎች ባህርይ ለመለየት አስቸጋሪ አይደለም። ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምስክርነት ቸል ባሉበት፣ ዓለምን መተውንና ራስ መካድን ከሚጠይቁት ግልጽና ነፍስ-መርማሪ ከሆኑት እውነቶች በሚርቁበት በዚያ ስፍራ የእግዚአብሔር በረከት እንደማይወርድ እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ክርስቶስ ራሱ በሰጠው መመሪያም “በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” [ማቴ 7÷16] እንዳለው እነዚህ እንቅስቃሴዎች የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራዎች እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። GCAmh 336.2

በቃሉ እውነቶች ውስጥ እግዚአብሔር የራሱን መገለጥ ለሰዎች ሰጥቷል። እነዚህ እውነቶች ለተቀበሏቸው ሁሉ ከሰይጣን ማታለያዎች የሚከልሉ ጋሻዎች ናቸው። እነዚህ እውነቶች ቸል መባላቸው አሁን በአማኙ ዓለም ውስጥ በስፋት እየተንሰራፉ ለመጡት እርኩሰቶች በር እንዲከፈት ምክንያት ሆኖአል። የእግዚአብሔር ሕግ ተፈጥሮና አስፈላጊነቱ በአብላጫው ከእይታ ውጪ ሆኖአል። ስለ መለኮታዊ ሕግ ባህርይ፣ ዘላለማዊነትና ኃላፊነት ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ መለወጥንና ቅድስናን በተመለከተ ወደ ስህተት በመምራት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለው የመንፈሳዊነት ደረጃ ዝቅ እንዲል አድርጓል። በእኛ ዘመን በሚደረጉ መነቃቃቶች ውስጥ የመንፈስ ቅዱስና የእግዚአብሔር ኃይል አለመገኘት ምስጢር የሚገኘው እዚህ ነው። GCAmh 336.3

በተለያዩ የኃይማኖት ድርጅቶች ውስጥ በቅድስናቸው የታወቁ፣ ለዚህ ሃቅ እውቅና የሚሰጡና የሚያዝኑ ሰዎች አሉ። የተጋረጠበትን ወቅታዊ ሐይማኖታዊ አደጋዎች ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ፓርክ በጥሩ ሁኔታ ሲያስቀመጠው፣ “የአደጋ ምንጭ ከሆኑት አንዱ መለኮታዊውን ሕግ ለማስተግበር የመስበኪያ መድረኩ (ፑልፒቱ) የሚያሳየው ቸልተኝነት ነው። በቀድሞ ጊዜያት መድረኩ የህሊና ድምጽ ማሚቶ ነበር….በሥራቸው የተደነቁ ሰባኪዎቻችን የጌታን ምሳሌ በመከተል፣ ለሕጉ፣ ለመመሪያዎቹና ለማስጠንቀቂያዎቹ ከፍተኛ ዋጋ በመስጠት ለስብከቶቻቸው ግርማ ሞገስ ያላብሱ ነበር። ሁለት ታላላቅ አባባሎችን ይደጋግሙ ነበር፦ ሕጉ የመለኮታዊ ፍፁምነት ጽሁፋዊ መግለጫ እንደሆነና፣ ሕጉን የማይወድ ሰው ወንጌሉን የማይወድ እንደሆነ ይናገሩ ነበር፤ ምክንያቱም ሕጉም ሆነ ወንጌሉ እውነተኛውን የእግዚአብሔር ባህርይ የሚያንፀባርቅ መስታወት ስለሆነ ነው። ይህ አደጋ ደግሞ ወደ ሌላ ያመራል፤ የኃጢአትን አስከፊነት፣ ስፋትና መጠኑን እንዲሁም ጉድለቱን (ስህተትነቱን) ዝቅ ያደርገዋል። ሕጉን ያለመታዘዝ ስህተትነት ከሕጉ ትክክለኛነት ጋር የተመጣጠነ ነው።” GCAmh 337.1

“ከተጠቀሱት አደጋዎች ጋር አብሮ የሚሄደው ሌላው ደግሞ የእግዚአብሔርን ፍርድ ዝቅ የማድረግ አደጋ ነው። የዘመናዊው መድረክ መለኮታዊ ፍርድን ከመለኮታዊ ቸርነት ጨምቆ የማውጣት ዝንባሌ አለው። ይህም ቸርነት መርህ ሆኖ ከፍ ከፍ በመደረግ ፈንታ እንደ ስሜት ተቆጥሮ እንዲዘቅጥ የሚያደርገው ነው። የአዲሱ ስነ-መለኮታዊ ቅርፅ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን የሚለያይ ነው። መለኮታዊ ሕጉ መልካም ነው ወይስ ክፉ? መልካም ነው። ስለዚህ ፍርድም መልካም ነው፤ ምክንያቱም ሕጉን ተግባራዊ ለማድረግ የሚገለጽ ጠባይ ነውና። የመለኮታዊውን ሕግና ፍርድ፣ የሰብዓዊ ፍጡራንን ያለመታዘዝ መጠኑንና ስህተቱን ዋጋ ዝቅ ከማድረግ ልማድ የተነሳ፣ ሰዎች ለኃጢአት ስርየት የቀረበውን ፀጋ ዝቅ ያለ ግምት ወደመስጠት ልማድ ይንሸራተታሉ።” ከዚያም ወንጌሉ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ያለውን ዋጋና አስፈላጊነት ያጣና ብዙም ሳይቆዩ መጽሐፍ ቅዱስን ጭምር ለመጣል ዝግጁ ይሆናሉ። GCAmh 337.2

ብዙ ኃይማኖታዊ አስተማሪዎች ክርስቶስ በሞቱ ሕጉን እንደሻረውና በዚህም ምክንያት ሰዎች ከመጠይቁ ነፃ እንደሆኑ አስረግጠው ይናገራሉ። አንዳንዶች ከባድ ቀንበር እንደሆነ በማመልከት፣ ከሕጉ ባርነት በተቃራኒ በወንጌሉ ስር ሊጣጣም የሚገባውን ነፃነት ያስተምራሉ። GCAmh 337.3

ነብያትና ሐዋርያት ግን የእግዚአብሔርን ቅዱስ ሕግ በእንዲህ ሁኔታ አላዩትም ነበር። ዳዊት እንዲህ አለ፦ “ትእዛዛትህን ፈልጌያለሁና አስፍቼ [በነፃነት] እሄዳለሁ/And I will walk at liberty for I seek thy precepts” [መዝ 119÷45]። ከክርስቶስ ሞት በኋላ የፃፈው ሐዋርያው ያዕቆብ ስለ አሥርቱ ትዕዛዛት ሲናገር፦ “የንጉሥ ሕግ እንዲሁም ነፃ የሚያወጣውን ፍፁሙን ሕግ” በማለት ይገልፀዋል [ያዕ 2÷8፤1÷25]። ከስቅለት ግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ፣ ምስጢር ገላጩ [ክርስቶስ] “ትዕዛዛቱን የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው ስልጣናቸው በሕይወት ዛፍ ላይ ይሆን ዘንድ በደጅም ወደ ከተማ ይገባሉ” [ራዕ 22÷14] በማለት በረከትን ያውጅላቸዋል። GCAmh 337.4

ክርስቶስ በሞቱ የአባቱን ሕግ ሽሯል የሚለው አባባል መሰረተ-ቢስ ነው። ሕጉ ሊለወጥ ወይም ወደጎን ሊተው የሚቻል ቢሆን ኖሮ የሰውን ልጅ ከኃጢአት ቅጣት ለማዳን ክርስቶስ መሞት ባላስፈለገው ነበር። የክርስቶስ መሞት፣ ሕጉን ከመሻር በተቃረነ መልኩ፣ የሚያረጋግጠው ሕጉ መለወጥ የማይችል እንደሆነ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ “ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ” መጣ [ኢሳ 42÷21]። “ሕግን ለመሻር የመጣሁ አይምሰላችሁ” አለ “ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም” [ማቴ 5÷17፣18]። ራሱን አስመልክቶ ደግሞ ሲናገር፣ “አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” [መዝ 40÷8] አለ። GCAmh 337.5

የእግዚአብሔር ሕግ በተፈጥሮው (በባህርይው) መለወጥ የሚችል አይደለም። የፀሃፊው [የጌታ] የራሱ የፈቃድና የባህርይው መገለጥ ነው። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፤ ሕጉም ፍቅር ነው። ሁለቱ ታላላቅ መርሆዎች ፍቅር ለእግዚአብሔርና ፍቅር ለሰው ናቸው። “ፍቅር የሕግ ፍፃሜ” ነው [ሮሜ 13÷10]። የእግዚአብሔር ባህርይ ጽድቅና እውነት ነው፤ የሕጉ ተፈጥሮም እንዲሁ ነው። መዝሙረኛው፣ “ሕግህም እውነት ናት ትዕዛዛትህ ሁሉ ጽድቅ ናቸውና” [መዝ 119÷142፣172] ሲል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ ደግሞ ሲናገር፣ “ሕጉ ቅዱስ ነው ትዕዛዚቱም ቅድስትና ፃድቅ ናት” [ሮሜ 7÷12] ይላል። የእግዚአብሔር አዕምሮና ፈቃድ መገለጫ የሆነው እንዲህ ያለው ሕግ እንደ ራሱ እንደ ፀሐፊው ጽኑ መሆን አለበት። GCAmh 338.1

ከሕጉ መርሆዎች ጋር ስምሙ እንዲሆኑ በማድረግ ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ማስታረቅ፣ የመለወጥና የቅድስና ተግባር ነው። በመጀመሪያ ሰው የተፈጠረው በእግዚአብሔር አምሳል ነበር። ከእግዚአብሔር ማንነትና ከሕጉ ጋር ፍፁም መስማማት ያለው ነበር። የጽድቅ መርሆዎች በልቡ ላይ ተጽፈው ነበር። ኃጢአት ግን ከፈጣሪው ጋር አለያየው። መለኮታዊ አምሳሉን ከዚያ በኋላ ማንፀባረቅ አልቻለም። ልቡ ከእግዚአብሔር ሕግ መርሆዎች ጋር ጦርነት ላይ ነበር። “የስጋ ሀሳብ የእግዚአብሔር ፀላት ነውና ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛም፤ አይችልምና” [ሮሜ 8÷7]። ሆኖም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ይታረቅ ዘንድ “አንድ ልጁን እስኪለውጥ ድረስ እግዚአብሔር እንዲሁ ዓለምን ወዶአልና” [ዮሐ 3÷16] በክርስቶስ ሥራ አማካኝነት ከፈጣሪው ጋር ስምሙ ይሆን ዘንድ መታደስ ይችላል። ልቡ በመለኮታዊ ፀጋ እንደገና አዲስ መሆን አለበት፤ አዲስ ሕይወት ከላይ ሊኖረው ይገባል። ይህ፣ ያለዚያ ለውጥ፣ የሱስ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” ያለበት አዲሱ መወለድ ነው። GCAmh 338.2

ከእግዚአብሔር ጋር የመታረቅ የመጀመሪያው እርምጃ ኃጢአተኛ መሆንን ማወቅ ነው። “ኃጢአትም እርሱ ሕግን መተላለፍ ነው”፤ “ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና” [1ኛ ዮሐ 3÷4፤ ሮሜ 3÷20]። ኩነኔውን ማየት ይችል ዘንድ ኃጢአተኛው በእግዚአብሔር በታላቁ የጽድቅ ሚዛን ደረጃ ባህርይውን መፈተን አለበት። የጽድቅ ባህርይን ፍጽምና የሚያሳይ መስታዎት ነውና በራሱ ያለውን ጉድለት እንዲያስተውል ያስችለዋል። GCAmh 338.3

ሕጉ ለሰው ኃጢአቱን ይገልጽለታል፣ መድሃኒት ግን አያቀርብለትም። ለሚታዘዝ የሕይወት ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ ሳለ የሕግ ተላላፊው ዕጣ ፈንታ ሞት እንደሆነ ያውጃል። ከኃጢአት ኩነኔ ወይም በኃጢአት ከመበከል ነፃ የሚያደርገው የክርስቶስ ወንጌል ብቻ ነው። ያወጣው ሕግ ወደ ተጣሰበት ወደ እግዚአብሔር ንስሐ መግባት አለበት፤ የሚዋጅ መስዋዕት በሆነው ክርስቶስም እምነት ይኖረው ዘንድ ይገባዋል። በዚህም ሁኔታ “ስለቀደመችው ኃጢአት ስርየት” ያገኝና [ሮሜ 3÷25] የመለኮታዊ ባህርይ ተካፋይ ይሆናል። የልጅነት መንፈስ በመቀበል፣ የእግዚአብሔር ልጅ በመሆን “አባ አባት!” በማለት ይጣራል። [ሰው] አሁን የእግዚአብሔርን ሕግ ይተላለፍ ዘንድ ነፃ ነውን? ጳውሎስ እንዲህ ይላል፣ “እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም ሕግን እናፀናለን እንጂ”፤ “ለኃጢአት የሞትን እኛ ወደፊት እንዴት አድርገን በእርሱ እንኖራለን?” “ትዕዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና ትዕዛዛቱም ከባዶች አይደሉም” [ሮሜ 3÷31፤ 6÷2፤ 1ኛ ዮሐ 5÷3]። በአዲሱ መወለድ ልቡ ከሕጉ ጋር ወደ መስማማት ከመምጣቷ ጋር ከእግዚአብሔር ጋርም ስምሙ ትሆናለች። ይህ ኃያል ለውጥ በኃጢአተኛው ላይ ተግባራዊ ሲሆን ከሞት ወደ ሕይወት ተላለፈ፣ ከኃጢአት ወደ ቅድስና፣ ሕግን ከመተላለፍና ከአመጽ ወደ መታዘዝና ታማኝነት ተሸጋገረ። ከእግዚአብሔር ጋር ተለያይቶ የነበረበት የቀድሞው ሕይወት አብቅቷል፤ የመታረቅ፣ የእምነትና የፍቅር አዲስ ሕይወት ጀምሯል። ከዚያም “እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ስጋ ፈቃድ በማንመላለስ”፣ “የሕግ ጽድቅ በእኛ ይፈፀም ዘንድ” አለው [ሮሜ 8÷4]። የነፍስ መዝሙርም፣ “አቤቱ ሕግህን እንደ ምን እጅግ ወደድሁ ቀኑን ሁሉ እርሱ ትዝታዬ ነው” ይሆናል። [መዝ 119÷97]። GCAmh 338.4

“የእግዚአብሔር ሕግ ፍፁም ነው ነፍስንም ይመልሳል” [መዝ 19÷7]። ያለ ሕጉ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ንጽህናና ቅድስና እንዲሁም ስለ ራሳቸው ኃጢአትና እድፍ ትክክለኛ መረዳት አይኖራቸውም። እውነተኛ የኃጢአተኛነት ስሜት አይኖራቸውም፤ የንስሐም አስፈላጊነት አይታያቸውም። የእግዚአብሔርን ሕግ ተላላፊ ሆነው የጠፉ መሆናቸው ስለማይታያቸው የሚያስተሰርየው የክርስቶስ ደም እንደሚያሻቸው አያስተውሉም። የመዳን ተስፋ ያለ ፍፁም የልብ ለውጥ ወይም ያለ ሕይወት ተሐድሶ ተቀባይነት ያገኛል። በእንዲህ ሁኔታ የላይ ላይ መለወጦች በስፋት ይንሰራፋሉ፤ ከክርስቶስ ጋር ፈጽሞ ህብረት አድርገው የማያውቁ እልፍ አዕላፋት የቤተ ክርስቲያን አባል ይሆናሉ። GCAmh 339.1

መለኮታዊውን ሕግ ቸል ከማለት ወይም አሻፈረኝ ከማለት የተነሳ የተሳሳቱ የቅድስና ንድፈ ሃሳቦች በዚህ ጊዜ ባሉ ሐይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ዘንድ አብይ ቦታ ይዘዋል። እነዚህ ንድፈ ሃሳቦች በአስተምህሮ ረገድ የተሳሳቱ፣ በተግባራዊ ውጤታቸውም አደገኛ ናቸው። በአጠቃላይ በቀላሉ ተቀባይነት ማግኘታቸው ደግሞ በዚህ ነጥብ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ምን እንደሆነ ሁሉም ግልጽ መረዳት ይኖራቸው ዘንድ በእጥፍ አስፈላጊ ያደርገዋል። GCAmh 339.2

እውነተኛ ቅድስና የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን በፃፈው መልእክት ይህ “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና” ይላል፤ ሲፀልይም “የሰላም አምላክ ሁለንተናችሁን ይቀድስ” [1ኛ ተሰ 4÷3፤ 5÷23] ይላል። ቅድስና ምን እንደሆነ እንዴትስ ሊደረስበት እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል። አዳኙ ለደቀ መዛሙርቱ ሲፀልይ፣ “በእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነውና” [ዮሐ 17÷17፣19] አለ። አማኞች “በመንፈስ ቅዱስ መቀደስ” እንዳለባቸው ጳውሎስ ያስተምራል [ሮሜ 15÷16]። የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ምንድን ነው? የሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ሲነግራቸው፣ “የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል” [ዮሐ 16÷13] አላቸው፤ መዝሙረኛውም፣ “ሕግህ እውነት ነው” [መዝ 119÷142] ይላል። በሕጉ የታቀፉት ታላላቅ የጽድቅ መርሆዎች በእግዚአብሔር ቃልና በመንፈሱ አማካኝነት ለሰዎች ቀርበውላቸዋል። የመለኮት ፍጽምና መገለጫ የሆነው ሕጉ “ቅድስት ጻድቅት በጎም” ስለሆነ ያንን ሕግ በመታዘዝ የሚቀረፀው ባህርይም ቅዱስ ይሆናል ማለት ነው። ክርስቶስ የእንደዚህ አይነቱ ባህርይ ፍፁም ምሳሌ ነው። እንዲህ ይላል፣ “እኔ የአባቴን ትዕዛዝ እንደጠበቅሁ” “ደስ የሚያሰኘውን ነገር ዘወትር አደርጋለሁና” [ዮሐ 15÷10፤ 8÷29]። የክርስቶስ ተከታዮች እርሱን መምሰል ይኖርባቸዋል — በእግዚአብሔር ፀጋም ከቅዱስ ሕጉ መርሆዎች ጋር የሚስማሙ ባህርያትን መቅረጽ ይኖርባቸዋል። ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቅድስና ነው። GCAmh 339.3

ይህ ሥራ ሊከናወን የሚችለው በክርስቶስ ላይ ባለው እምነት፣ በውስጥ በሚኖረው የእግዚአብሔር መንፈስ ኃይል ብቻ ነው። ጳውሎስ አማኞችን ሲገስጽ “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ፤ ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም በእናንተ የሚሰራ እግዚአብሔር ነውና” [ፊልጵ 2÷12፣13] በማለት ይናገራል። ክርስቲያኑ የኃጢአት ጉትጎታዎች ይሰሙታል፤ ነገር ግን ቀጣይነት ያለው ውጊያ ያካሂዳል። የክርስቶስ ድጋፍ የሚያስፈልገው እዚህ ላይ ነው። የፍጡር ደካማነት ከመለኮት ኃይል ጋር ይቀናጅና፣ እምነት “በጌታችን በየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሳትን በሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” [1ኛ ቆሮ 15÷57] በማለት ይናገራል። GCAmh 340.1

የቅድስና ሥራ እያደገ የሚሄድ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። በመለወጥ ጊዜ በስርየት ደም አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም የሆነው ኃጢአተኛ የክርስትና ሕይወቱ ገና መጀመሩ ነው። አሁን “ወደ ፍጽምና [perfection]” መሄድ “የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ” ማደግ አለበት [ዕብ 6÷1፤ ኤፌ 4÷13]። ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ነገር አደርጋለሁ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ በክርስቶስ የሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ [ወደ] ምልክት እፈጥናለሁ” [ፊልጵ 3÷13፣14]። ጴጥሮስ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅድስና የሚደረስበትን መንገዶች በፊታችን ሲያስቀምጥ፦ “ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፣ በበጎነትም እውቀትን፣ በእውቀትም ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛትም መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፣ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማች መዋደድ፣ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ.…እነዚህን ብታደርጉ ከቶ አትሰናከሉምና።” [2ኛ ጴጥ 1÷5-10] ይላል። GCAmh 340.2

የመጽሐፍ ቅዱስን ቅድስና (sanctification) የሚለማመዱ እነርሱ የትህትና መንፈስ ያንፀባርቃሉ። ልክ እንደ ሙሴ የቅድስናን (Holiness) አስፈሪ ግርማ ሞገስ ተመልክተዋል፤ የዘላለማዊውን እግዚአብሔር ንጽህናና ከፍ ከፍ ያለውን ፍጽምና ሲያነጻጽሩ የራሳቸውን ዋጋ ቢስነት ያስተውላሉ። GCAmh 340.3

ነብዩ ዳንኤል የእውነተኛ ቅድስና ምሳሌ ነበር። ረጅም የሕይወት ዘመኑ ለጌታው በሚያከናውነው የከበረ ሥራ የተሞላ ነበር። በሰማይ “እጅግ የተወደደ” ሰው ነበረ [ዳን 10÷11]። ነገር ግን ንጹህና ቅዱስ እንደሆነ በመናገር ፈንታ በእግዚአብሔር ፊት ሲማፀን ሳለ፣ ይህ የተከበረ ነብይ፣ ራሱን ከእሥራኤል ኃጢአተኞች ጋራ ቆጠረ፦ “በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና”፣ “ኃጢአትን ሰርተናልና ክፋትንም አድርገናልና።” ሲናገርም፣ “ስናገርና ስፀልይም በኃጢአቴና በሕዝቤም በእሥራኤል ኃጢአት ስናዘዝ” ይላል። በኋላም የእግዚአብሔር ልጅ ትዕዛዝ ይሰጠው ዘንድ ሲገልጽለት እንዲህ ይላል፦ “ደም ግባቴም ለጥፋት ተለወጠብኝ፤ ኃይልም አልነበረኝም።” [ዳን 9÷18፣15፣20፤ 10÷8]። GCAmh 340.4

እዮብ የእግዚአብሔርን ድምጽ በአውሎ ነፋሱ ውስጥ ሲሰማ “ራሴን እንቃለሁ በአፈርና በአመድ ላይ ተቀምጬ እፀፀታለሁ” ይላል [እዮብ 42÷6]። የእግዚአብሔርን ክብር ሲያይ ኪሩቤሎቹም “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር” እያሉ ሲጮሁ ሲሰማ ነበር ኢሳይያስ “ጠፍቻለሁና ወዮልኝ!” ያለው [ኢሳ 6÷3፣5]። ጳውሎስ ወደ ሶስተኛው ሰማይ ተወስዶ ሰው ሊናገራቸው የማይችሉትን ነገሮች ሲሰማ ስለ ራሱ ሲናገር፣ “ከቅዱሳን ሁሉ ለማንስ ለእኔ” በማለት ይናገራል [2ኛ ቆሮ 12÷2-4፤ ኤፌ 3÷8]። የተወደደው ዮሐንስ፣ በየሱስ ደረት ላይ ተደግፎ ክብሩን ያየው ዮሐንስ፣ ነበር እንደሞተ ሰው ሆኖ በመልአኩ እግር ስር የወደቀው [ራዕይ 22÷8]። GCAmh 340.5

በቀራንዮ መስቀል ጥላ ስር ለሚራመዱ ለእነርሱ፣ ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ፣ ከኃጢአት ባርነት ነፃ ስለመውጣት የሚነዛ ጉራ ሊኖር አይችልም። የእግዚአብሔርን ልጅ ልብ በስቃይ ብዛት የሰነጠቀው ሰቆቃ መንስኤ ኃጢአታቸው መሆኑ ይሰማቸዋል፤ ይህ አስተሳሰባቸውም ራሳቸውን ወደ ማዋረድ ይመራቸዋል። ወደ የሱስ በጣም የተጠጉ ሰዎች የሰው ልጅ አቅመ-ቢስነትና ኃጢአተኝነት ምን ያህል እንደሆነ ጥርት አድርገው ያስተውላሉ፤ ብቸኛው ተስፋቸውም በተሰቀለውና በተነሳው አዳኝ በኩል ነው። GCAmh 341.1

አሁን በክርስቲያኑ ዓለም እውቅናው እየሰፋ የመጣው ቅድስና (sanctification) ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ መንፈስን ያዘለ፣ ለእግዚአብሔር ሕግም ቸልተኛ በመሆኑ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ኃይማኖት ባይተዋር መሆኑን የሚያመለክት ነው። ጠበቃዎቹ ሲያስተምሩ ቅድስና የቅጽበት ሥራ፣ በእምነት ብቻ ወደ ፍጹም ቅድስና (holiness) የሚደረስበት መሆኑን ይናገራሉ። “እመን ብቻ”፤ ከዚያም “በረከቱ ያንተ ነው” ይላሉ። በተቀባዩ በኩል ተጨማሪ ጥረት አያስፈልግም ይላሉ። ከዚህም ጋር አብሮ የእግዚአብሔርን ሕግ ይክዳሉ፤ ትዕዛዛትን ከመጠበቅ ባርነት ነፃ ወጥተናልም ይላሉ። ነገር ግን እርሱን ደስ የሚያሰኙት ምን እንደሆኑ ከሚያሳዩ፣ የባህርይውና የፈቃዱ መገለጫ ከሆኑት መርሆዎች ጋር ሳይስማሙ፣ ከእግዚአብሔር ፈቃድና ባህርይ ጋር በሚጣጣም መልኩ ሰዎች ቅዱስ ይሆኑ ዘንድ የሚቻላቸው ነውን? GCAmh 341.2

ጥረት ለማያሻው፣ ራስ መካድን፣ ከዓለም ከንቱነት መለያየትን ለማይጠይቅ ቀላል ኃይማኖት ያለው መሻት የእምነትንና የእምነትን ብቻ አስተምህሮ ተወዳጅ አስተምህሮ እንዲሆን አድርጎታል። ነገር ግን የእዚአብሔር ቃል ምን ይላል? ያዕቆብ ሲናገር፣ “እምነት አለኝ የሚል ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱ ሊያድነው ይችላልን?….“አንተ ከንቱ ሰው እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሰዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የፀደቀ አይደለምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደነበረ በሥራም እምነት እንደተፈፀመ ትመለከታልህን? ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ [በምግባሩ-KJV] እንዲፀድቅ ታያላችሁ” [ያዕ 2÷14-24] ይላል። GCAmh 341.3

የእግዚአብሔር ቃል ምስክር፣ ይህንን እንደ ወጥመድ የሚያንቀውን የእምነት ያለ-ሥራ አስተምህሮ ይቃወማል። ምሕረት ከሚያስገኙ ቅድመ ሁኔታዎች ጋር ሳይስማማ የሰማይን ተቀባይነት የሚጠይቅ እምነት፣ እምነት አይደለም። ይህ ግምታዊ ድፍረት ነው፤ ምክንያቱም እውነተኛ እምነት መሰረት ያደረገው በመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎችና አቅርቦቶች ላይ ነው። GCAmh 341.4

ከእግዚአብሔር መጠይቆች መካከል አንዱን በፈቃዱ እየጣሰ ሳለ ቅዱስ መሆን እችላለሁ በሚል እምነት ማንም ራሱን ማታለል የለበትም። የሚታወቅን ኃጢአት መፈፀም እየመሰከረ ያለውን የመንፈስ ድምጽ ፀጥ ያሰኘዋል፤ ነፍስንም ከእግዚአብሔር ይለያል። “ኃጢአት ሕግን መተላለፍ ነው።” “ኃጢአትን የሚያደርግ [ሕጉን የሚተላለፍ] ሁሉ አላየውም አላወቀውምም” [1ኛ ዮሐ 3÷6]። ዮሐንስ በመልእክቱ በሙላት የተናገረው ስለ ፍቅር ቢሆንም የእግዚአብሔርን ሕግ እየጣሰ እያለ ቅዱስ ነኝ ብሎ ስለሚናገረው መደብ እውነተኛ ባህርይ ግን ገለፃ ለማድረግ አላቅማማም። “አውቄዋለሁ የሚል ትዕዛዛቱን የማይጠብቅ እርሱ ሀሰተኛ ነው እውነትም በእርሱ ውስጥ የለም፤ ቃሉን ግን የሚጠብቅ ሁሉ በእርሱ የእግዚአብሔር ፍቅር በእውነት ተፈጽሞአል” [1ኛ ዮሐ 2÷4፣5]። የእያንዳንዱ ሰው ኃይማኖት መፈተኛ ይህ ነው። በሰማይና በምድር የእግዚአብሔር የቅድስና ደረጃ ብቸኛ መለኪያ ወደ ሆነው ሚዛን ሳናመጣው በፊት ማንንም ሰው ቅዱስ ነው ብለን መፈረጅ አንችልም። ሰዎች የግብረ-ገብነት ሕጉ (የአሥርቱ ትዕዛዛት) ክብደት ካልተሰማቸው፣ የእግዚአብሔርን መመሪያዎች ካጣጣሉና ካቀለሏቸው፣ ከእነዚህ ከታናናሾቹ ትዕዛዛቶች አንዱን ከጣሱ፣ ለሰዎችም እንዲሁ ካስተማሩ፣ በሰማይ እይታ ክብረ-ቢሶች ናቸው፤ መጠይቆቻቸውም መሰረተ-ቢስ እንደሆኑ እናውቃለን። GCAmh 341.5

ኃጢአት የለብኝም የሚለው አባባል በራሱ፣ ይህንን የሚናገረው ሰው ቅዱስ ከመሆን የራቀ እንደሆነ ማስረጃ ነው። ሰው ራሱን ቅዱስ አድርጎ የሚቆጥርበት ምክንያት፣ ተመን ሊወጣለት የማይችለው የእግዚአብሔር ንጽህናና ቅድስና ትክክለኛ መረዳት ስለሌለው፤ ወይም ከባህርይው ጋር ለመስማማት የሚፈልጉ እነርሱ ወደ ምን አይነት [ባህርይ] መለወጥ እንዳለባቸው ስለማያውቅ፣ የክርስቶስ ንጽህናና ከፍ ከፍ ያለው ማራኪነቱ ትክክለኛ ማስተዋል ስለሌለውና የኃጢአት ፀያፍነትና አስከፊነት ስላልገባው ነው። በእርሱና በክርስቶስ መካከል ያለው ርቀት እየጨመረ ሲሄድ፣ መለኮታዊውን ባህርይና መጠይቆቹን በበቂ ሁኔታ ያለመረዳቱ እየሰፋ ሲሄድ፣ ያኔ በራሱ እይታ የበለጠ ፃድቅ እየሆነ የሄደ ይመስለዋል። GCAmh 342.1

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተቀመጠው ቅድስና ሁለመናን - መንፈስን፣ ነፍስንና አካልን የሚያካትት ነው። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች ሲፀልይ “መንፈሳችሁም፣ ነፍሳችሁም፣ ስጋችሁም ጌታችን የሱስ ክርስቶስ በመጣ ጊዜ ያለነቀፋ ፈጽመው ይጠበቁ” [1ኛ ተሰ 5÷23] ብሎአል። እንደገናም ለአማኞች ሲጽፍ፣ “ወንድሞቼ ሆይ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው ቅዱስ መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ“[ሮሜ 12÷1] ይላል። በጥንት እሥራኤላዊያን ዘመን ወደ እግዚአብሔር የሚመጣው እያንዳንዱ መስዋዕት በጥንቃቄ ይፈተሽ ነበር። በቀረበው እንስሳ ላይ አንዳች እንከን ሲገኝበት ተቀባይነት ያጣ ነበር፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የሚቀርበው መባ ነውር የሌለበት መሆን ይገባዋል። ስለዚህ ክርስቲያኖችም አካሎቻቸውን “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስ መስዋዕት” አድርገው ያቀርቡ ዘንድ ታዘዋል። ይህንን ለማድረግ ይችሉ ዘንድ ሁሉንም ኃይሎቻቸውን ምርጥ በሚባል ሁኔታ መጠበቅ አለባቸው። የአካላዊንም ሆነ የአእምሯዊን ኃይል የሚያዳክም ማንኛውም ድርጊት፣ ሰው ለፈጣሪው የሚሰጠው አገልግሎት ብቁ እንዳይሆን ያደርገዋል። ልናበረክተው ከምንችለው ከላቀው ነገር ያነሰ ብናቀርብለት እርሱ ደስ ይሰኛልን? ክርስቶስ “ጌታ አምላክህን በፍፁም ልብህ ውደድ” [ማቴ 22÷37] ይላል። እግዚአብሔርን በፍፁም ልባቸው የሚወዱ እነርሱ ተወዳዳሪ የሌለውን የሕይወታቸውን አገልግሎት ሊሰጡት ምኞታቸው ነው፤ እያንዳንዱን ክህሎታቸውንም ፈቃዱን እንዲያደርጉ ከሚያስችሏቸው ሕግጋት ጋር ያጣጥማሉ። አምሮትን ወይም ፍላጎትን ለማርካት ሲሉ ለሰማያዊ አባታቸው የሚያቀርቡትን መባ አያኮስሱም፣ አያረክሱምም። GCAmh 342.2

ጴጥሮስ እንዲህ ይላል፦ “ነፍስን ከሚዋጋ ስጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እለምናችኋለሁ” [1ኛ ጴጥ 2÷11]። እያንዳንዱ ኃጢአት የሆነ እርካታ ተፈጥሯዊ ችሎታዎችን ያደነዝዛል፣ የአዕምሮና የመንፈስ ህዋሳቶችን ምውት ያደርጋል፤ የእግዚአብሔር ቃል ወይም መንፈስ በልብ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖም ደካማ ይሆናል። ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች ሲጽፍ “በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍፁም እያደረግን ስጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንፃ” [2ኛ ቆሮ 7÷1] ይላል። ራስን መግዛትን ከመንፈስ ፍሬዎች — ፍቅር፣ ደስታ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት ጋር ይመድበዋል። [ገላ 5÷22፣23]። GCAmh 343.1

እነዚህ መንፈሳዊ እወጃዎች ቢኖሩም እንኳ፣ ምን ያህል ታማኝ ክርስቲያኖች [ነን ባዮች] ናቸው ትርፍ በማጋበስ ወይም በፋሽን አምልኮ ኃይላቸውን የሚያደክሙት፣ ስንቶች ናቸው በቁንጣን፣ ወይን በመጠጣትና በተከለከለ ፌሽታ እግዚአብሔር መሰል ወንድነታቸውን የሚያረክሱት። ቤተ ክርስቲያንም በመገሰጽ ፈንታ፣ ለክርስቶስ ያለው ፍቅር ሊያቀርበው የማይችለውን ጎተራዋን እንደገና መሙላት ትችል ዘንድ፣ አምሮትን፣ ለሃብት ያለውን ፍላጎት ወይም ለፌሽታ ያለውን ፍቅር ታበረታታለች። ወደ ዛሬዎቹ አብያተ ክርስቲያናት የሱስ ቢገባና በኃይማኖት ስም የሚካሄደውን ያልተቀደሰ ንግድና ድግስ ቢመለከት ገንዘብ ዘርዛሪዎቹን ከቤተ መቅደስ እንዳባረረ ሁሉ እነዚህን አርካሾች አያስወጣቸውም ነበርን? GCAmh 343.2

ሐዋርያው ያዕቆብ ሲናገር የላይኛይቱ ጥበብ “በመጀመሪያ ንጽህት ናት” ይላል። በትንባሆ በረከሱ ከንፈሮቻቸው የከበረውን የየሱስን ስም የሚጠሩትን፣ ትንፋሻቸውና ሰውነታቸው በመጥፎ ሽታ የተበከለውን፣ የሰማይን አየር የሚበክሉትን በዙሪያቸው ያሉትን መርዝ ወደ ውስጥ እንዲተነፍሱ የሚያደርጉትን ያዕቆብ ቢገናኛቸው፣ ከወንጌሉ ንጽህና እጅግ ከሚቃረን ድርጊት ጋር ቢነካካ ሐዋሪያው፣ “የምድር ነው፣ የስጋም ነው፣ የአጋንንትም ነው” ብሎ አያወግዘውም ነበርን? የትንባሆ ባሪያዎች፣ የጠቅላላ ቅድስናን በረከት እንዳገኙ በመጥቀስ ስለ ሰማይ ስላላቸው ተስፋ ያወራሉ። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል በግልጽ ሲናገር “ፀያፍ ነገር ሁሉ ወደ እርስዋ ከቶ አይገባም።” [ራዕ 21÷27] ይላል። GCAmh 343.3

“ወይስ አታውቁምን ስጋችሁ በእላንት የሚያድረው የመንፈስ ቅዱስ መቅደስ እንደሆነ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት። ለራሳችሁም አይደላችሁም በዋጋ ተገዝታችኋልና፤ እንግዲህም እግዚአብሔርን አክብሩ በስጋችሁና በመንፈሳችሁ እሊህም ለእግዚአብሔር የሆኑት” [1ኛ ቆሮ 6÷19፣20]። አካሉ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ እርሱ ጎጂ የሆነ ልማድ ባሪያ አይሆንም። ኃይላቱ ሁሉ በደም ዋጋ የገዛው የክርስቶስ ናቸው። ንብረቱ ሁሉ የጌታ ነው። ይህንን በአደራ የተሰጠውን ንብረት (ካፒታል) እያባከነ እንዴት ከበደል ነፃ ይሆናል? ነፍሳት የሕይወት ቃል አጥተው ሲጠፉ ሳለ ታማኝ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ እነርሱ ጥቅመ-ቢስ፣ ጎጂ በሆኑ እርካታዎች ላይ፣ በየአመቱ፣ እጅግ ብዙ ገንዘብ ያጠፋሉ። የድሃውን ችግር ለማቃለል ወይም ወንጌሉን ለመደገፍ ከሚያወጡት በላይ ውድመት በሚያስከትል የምኞት መሰዊያ ላይ ሲበሉና ሲጠጡ ሳለ እግዚአብሔርን በአሥራትና በስጦታ ይመዘብራሉ። የክርስቶስ ተከታዮች ነን የሚሉ ሁሉ በእውነት ተቀድሰው ቢሆን ኖሮ ጥሪታቸው አስፈላጊ ላልሆነ እንዲያውም ለሚጎዳ ፍላጎት ማርኪያ በመዋል ፈንታ ወደ ጌታ ጎተራ በገባ፣ ክርስቲያኖችም የራስ መግዛትን ፣ ራስን የመካድንና ራስን መስዋዕት አድርጎ የማቅረብን ምሳሌነት ባሳዩ ነበር። GCAmh 343.4

ዓለም የራስን ፍላጎት ለማርካት ተላልፎ ተሰጥቷል። “የስጋ መመኘት፣ የዓይን መመኘት፣ የሰውም ትምክህት” [1ኛ ዮሐ 2÷16] አብዛኛውን ሕዝብ ተቆጣጥሮአል። የክርስቶስ ተከታዮች ግን የበለጠ ቅድስና ያለው መጠራት አላቸው። “ስለዚህም ጌታ ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኩስንም አትንኩ ይላል” [2ኛ ቆሮ 6÷17]። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው፣ ኃጢአት የተሞላባቸውን ፍላጎቶች ማሳደድንና የዓለም እርካታዎችን በጽኑ የማውገዝ ሥራ የማይፈጽም ቅድስና እውነተኛ ሊሆን እንደማይችል ብንመሰክር ትክክል ነን። GCAmh 344.1

ከዚህ ቅድመ ሁኔታ ጋር ለሚስማሙ ሁሉ፣ ከመካከላቸው ውጡ ከርሳቸውም ተለዩ፣ ርኩሱንም አትንኩ፤ የእግዚአብሔርም ተስፋ፦ “እኔም እቀበላችኋለሁ፣ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆኑኛላችሁ” የሚል ነው [2ኛ ቆሮ 6÷17፣18]። በእግዚአብሔር ነገሮች ጥልቅና የተትረፈረፈ ተሞክሮ ይኖረው ዘንድ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ዕድልና ኃላፊነት ነው። “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ይላል የሱስ “የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” [ዮሐ 8÷12]። “የፃድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ እየጨመረ ይበራል” [ምሳሌ 4÷18]። እያንዳንዱ የእምነትና የመታዘዝ እርምጃ ነፍስን “ጨለማ በሌለበት” የዓለም ብርሃን ከሆነው ጋር በቅርበት ያቆራኛታል። ድምቅ ያለው የጽድቅ ፀሃይ [የየሱስ] ጮራ በእግዚአብሔር አገልጋዮች ላይ ያንፀባርቃል፤ እነርሱም የእርሱን ጨረር እንደገና ማንፀባረቅ ይኖርባቸዋል። ከዋክብት ከክብሩ የተነሳ ብሩህ የሆኑበት አንድ ታላቅ ብርሐን በሰማይ እንዳለ እንደሚያስረዱን ሁሉ ክርስቲያኖችም በዓለማት ዙፋን ላይ የተቀመጠ ባህርይዉም ሊመሰገንና ሊወረስ የተገባው እግዚአብሔር እንዳለ ማንፀባረቅ ይገባቸዋል። የመንፈሱ ፀጋዎች፣ የባህርይውም ንጽህናና ቅድስና በምስክሮቹ ይንፀባረቃል። GCAmh 344.2

ጳውሎስ ለቆላስያስ ሰዎች በፃፈው ደብዳቤ ለእግዚአብሔር ልጆች ስለተሰጡ የተትረፈረፉ በረከቶች ይናገራል። እኛ “ይህንን ከሰማንበት ቀን ጀምረን የፈቃዱን እውቀት መንፈሳዊ ጥበብንና አዕምሮን ሁሉ እንዲሞላባችሁ እየለመንን ስለ እናንተ ፀሎትን አልተውንም፤ በበጎ ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁ፣ በእግዚአብሔርም እውቀት እያደጋችሁ፣ ከደስታም ጋር በሁሉ ለመጽናትና ለመታገስ እንደ ክብሩ ጉልበት መጠን በኃይል ሁሉ እየበረታችሁ” ይላል። [ቆላ 1÷9-12]። GCAmh 344.3

እንደገናም የክርስቲያንን ዕድል ከፍታ ወደ መረዳት ይመጡ ዘንድ ያለውን ፍላጎት በኤፌሶን ላሉ ወንድሞች ጽፏል። እጅግ በተሟላ፣ ጠቅለል ባለ ቋንቋ እንደ ታላቁ ንጉሥ ወንዶችና ሴቶች ልጅነታቸው ሊኖራቸው የሚችለውን ግሩም ኃይልና እውቀት በፊታቸው ይገልጥላቸዋል። “በመንፈሱ በውስጥ ሰውነታችሁ በኃይል እንድትጠነክሩ” “የእናንተ ስርና መሰረት በፍቅር ይፀና ዘንድ” “ከቅዱሳንም ሁሉ ጋር ስፋቱና ርዝመቱ ከፍታውም ጥልቀቱም ምን ያህል መሆኑን ለማስተዋል ከመታወቅም የሚያልፈውን የክርስቶስን ፍቅር ለማወቅ ትበረቱ ዘንድ” የእናንተ ዕድል ነው ይላቸዋል። ነገር ግን የሐዋርያው ፀሎት ተወዳዳሪ ወደሌለው የዕድል ከፍታ የሚደርሰው “እስከ እግዚአብሔርም ፍፁም ሙላት ደርሳችሁ ትሞሉ ዘንድ” ብሎ ሲፀልይ ነው። [ኤፌ 3÷16-19]። GCAmh 344.4

የእርሱን መጠይቆች ስናሟላ (ትዕዛዛቱን ስንፈጽም) የሰማዩ አምላካችን በሰጠን ተስፋዎች ላይ ባለን እምነት ልንደርስባቸው የምንችላቸው የስኬት ከፍታዎች እዚህ ላይ ተገልፀዋል። በክርስቶስ ብቁ ሥራዎች በኩል ወደማይለካ የኃይል ዙፋን መድረሻ አለን። “ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም?” [ሮሜ 8÷32]። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ያለ ልክ ለልጁ ሰጠው፤ እኛም የሙላቱ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ አለን። የሱስ እንዲህ አለ፦ “እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱስን አይሰጣቸው!” [ሉቃ 11÷13]። “ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ።” “ደስታችሁ ፍፁም እንዲሆን ለምኑ ትቀበሉማላችሁ።” [ዮሐ 14÷14፤ 16÷24]። GCAmh 345.1

የክርስቲያን ሕይወት በባህርይው ትህትናን የተላበሰ ቢሆንም በሃዘንና ራስን በማቆርቆዝ የሚታወቅ መሆን የለበትም። እግዚአብሔር አዎንታ የሚሰጠውና የሚባርከው ሕይወት መኖር የሁሉም ሰው ዕድል ነው። በውግዘትና በጽልመት ውስጥ እንኖር ዘንድ የሰማዩ አባታችን ፈቃድ አይደለም። ጭንቅላቱን ዝቅ ከሚያደርግና (ከሚያቀረቅርና)፣ ልቡ በራስ ሃሳብ ከተሞላ ጋር እውነተኛ ትህትና አብሮ ስለመሄዱ የሚያረጋግጥ መረጃ የለም። ወደ የሱስ ሄደን እንነፃለን፣ በሕጉ ፊትም ያለ ሃፍረትና ያለ ፀፀት መቆም እንችላለን። “እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ስጋ ፈቃድ ለማይመላለሱ እንግዲህ በክርስቶስ የሱስ ላሉ አሁን ኩነኔ የለባቸውም።” [ሮሜ 8÷1]። GCAmh 345.2

የወደቁ የአዳም ልጆች በክርስቶስ አማካኝነት “የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ፤” “የሚቀድሰውና የሚቀደሱት ሁሉ ሁለቱም ከአንድ ናቸውና ስለዚህም ምክንያት ወንድሞች ብሎ ሊጠራቸው አያፍርም” [ዕብ 2÷11]። የክርስቲያን ሕይወት የእምነት የድልና በእግዚአብሔር የሚገኝ ደስታ ያለው መሆን አለበት። “ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋል። ዓለምንም የሚያሸንፈው እምነታችን ነው” [1ኛ ዮሐ 5÷4]። የእግዚአብሔር ባሪያ ነህምያ በእውነት እንዲህ ሲል ተናግሮአል፦ “የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና” [ነህ 8÷10]። ጳውሎስም፦ “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜም እላለሁ ደስ ይበላችሁ።” “ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ ሳታቋርጡ ፀልዩ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ የሱስ ወደ እናንተ ነውና።” [ፊልጵ 4÷4፤ 1ኛ ተሰ 5÷16-18]። GCAmh 345.3

የመጽሐፍ ቅዱሳዊው መለወጥና መቀደስ (sanctification) ፍሬዎች እንደ እነዚህ ያሉ ናቸው፤ በእግዚአብሔር ሕግ የተቀመጡት ታላላቅ የጽድቅ መርሆዎች በክርስቲያኑ ዓለም በቸልተኛነት ስለሚታዩ፣ እነዚህ ፍሬዎች የሚገለጡት ከስንት አንድ ነው። ያለፉት ዓመታት መነቃቃት መገለጫ የሆነው፣ ጥልቅና ቋሚ የሆነ የእግዚአብሔር መንፈስ ሥራ መገለጥ [በዚህ ዘመን] እጅግ አናሳ የሆነው በዚህ ምክንያት ነው። GCAmh 345.4

በማየት እንለወጣለን። እግዚአብሔር የባህርይውን ፍጽምናና ቅድስና የገለጠባቸው፤ ለሰውም ያስታወቃቸው የተቀደሱ መርሆዎች ቸል ሲባሉ፣ የሰዎች አዕምሮም ወደ ፍጡር ትምህርቶችና ጽንሰሃሳቦች ሲሳብ፣ የተቀደሰ ሕይወት በቤተ ክርስቲያን ማሽቆልቆሉ አያስገርምም። ጌታ እንዲህ ይላል፦ “እኔን የሕይወት ምንጭ ትተውኛል የተቀደዱትንም ጉድጓዶች ውኃውንም ይይዙ ዘንድ የማይችሉትን ጉድጓዶች ለራሳቸው ቆፍረዋል።” [ኤር 2÷13]። GCAmh 345.5

“ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ….ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች ፍሬዋን በየጊዜው እንደምትሰጥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሰራውም ሁሉ ይከናወንለታል” [መዝ 1÷1-3]። በአማኞች መካከል የጥንቱ እምነት መነቃቃት ሊኖር የሚችለው የእግዚአብሔር ሕግ ወደሚገባው ደረጃው ተመልሶ ሲታደስ ብቻ ነው። “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፣ በመንገድ ላይ ቁሙ ተመልከቱም የቀደመችውንም መንገድ ጠይቁ፤ መልካሚቱ መንገድ ወዴት እንደሆነች እወቁ በእርስዋም ላይ ሂዱ ለነፍሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ።” [ኤር 6÷16]። GCAmh 346.1