ታላቁ ተጋድሎ

29/45

ምዕራፍ ፳፮—የመታደስ ሥራ

በመጨረሻው ዘመን መከናወን ያለበት የሰንበት ተሐድሶ ሥራ በነብዩ ኢሳይያስ ተተንብዮአል፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ማዳኔ ሊመጣ ጽድቅም ሊገለጥ ቀርቦአልና ፍርድን ጠብቁ፤ ጽድቅንም አድርጉ። ይህን የሚያደርግ ሰው ይህንንም የሚይዝ የሰው ልጅ እንዳያረክሰው ሰንበትንም የሚጠብቅ እጁንም ክፋት ከማድረግ የሚጠብቅ ብፁዕ ነው።” “ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም ስም ይወድዱ ዘንድ ባሪያዎቹም ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትንም መፃተኞች እንዳያረክሱት ሰንበትን የሚጠብቁትን ቃል ኪዳኔንም የሚይዙትን ሁሉ ወደ ተቀደሰው ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፤ በፀሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ።” [ኢሳ 56÷1፣2፣6፣7]። GCAmh 327.1

[በሚቀጥለው ጥቅስ] ትርጉም እንደተመለከተው እነዚህ ቃላት ለክርስትና ዘመንም የሚገጥሙ ናቸው፦ “ከእሥራኤል የተበተኑትን የሚሰበስብ ጌታ እግዚአብሔር፦ ወደ ተሰበሰቡት ዘንድ ሌሎችን እሰበስባለሁ ይላል” [ኢሳ 56÷8]። በወንጌሉ አማካኝነት አሕዛብ እንደሚሰበሰቡ እዚህ ላይ ተተንብዮአል። ሰንበትን በሚያከብሩ በእነርሱ ላይ በረከት ተነግሯል። ስለዚህም አራተኛው ትዕዛዝ እንዲከበር የተሰጠው መጠይቅ ስቅለቱን፣ ከሞት መነሳቱን እንዲሁም የክርስቶስን እርገት አልፎ የእግዚአብሔር ባሪያዎች መልካሙን ዜና ለአሕዛብ ሁሉ እስኪሰብኩ ድረስ ይዘልቃል። GCAmh 327.2

እግዚአብሔር በዚሁ ነብይ አማካኝነት ሲያዝ፦ “ምስክሩን እሰር፣ በደቀ መዛሙርቴም መካከል ሕጉን አትም” [ኢሳ 8÷16] ይላል። የእግዚአብሔር ሕግ ማህተም የሚገኘው በአራተኛው ትዕዛዝ ውስጥ ነው። ከአሥርቱ ትዕዛዛት ውስጥ የሕግ ሰጪውን ስምና ማዕረግ ወደ እይታ የሚያመጣው ይህ ትዕዛዝ ብቻ ነው ። የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንደሆነ ያውጃል፤ በመሆኑም ከሌሎች ሁሉ በላይ ያለውን የመከበርና የመመለክ መጠይቅ ያሳያል። ከዚህ ትዕዛዝ በስተቀር ከአሥርቱ ትዕዛዛት ውስጥ ሕጉ በማን ስልጣን እንደተሰጠ የሚያሳይ ምንም ነገር የለም። በጳጳሳዊ ኃይል አማካኝነት ሰንበት ሲቀየር ማህተሙ ከሕጉ ላይ ተወስዷል። የፈጣሪ መታሰቢያና የስልጣኑ ምልክት የሆነውን የአራተኛውን ትዕዛዝ ሰንበት ወደሚገባው ደረጃ ከፍ ከፍ በማድረግ ያድሱት ዘንድ የየሱስ ደቀ መዛሙርት ተጠርተዋል። GCAmh 327.3

“ወደ ሕግና ወደ ምስክር።” በርካታ የሚጋጩ አስተምህሮዎችና ጽንሰ-ሃሳቦች ቢኖሩም የእግዚአብሔር ሕግ፣ ሁሉም መላምቶች፣ አስተምህሮዎችና ጽንሰ-ሃሳቦች የሚፈተኑበት የማይሳሳት መመሪያ ነው። ነብዩ ሲናገር “እንዲህም ያለውን ቃል ባይናገሩ ንጋት አይበራላቸውም” [እንደዚህ ቃል የማይናገሩ ከሆነ፣ ምክንያቱ ብርሐን በውስጣቸው ስለሌለ ነው/if they speak not according to this word, it is BECAUSE THERE IS NO LIGHT IN THEM. KJV] [ኢሳ 8÷20]። GCAmh 327.4

እንደገናም ትዕዛዙ ተሰጥቷል፦ “በኃይልህ ጩኽ፣ አትቆጥብም ድምጽህን እንደመለከት አንሳ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር” [ኢሳ 58÷1]። ለመተላለፋቸው የሚገሰፁት እግዚአብሔር ሕዝቦቼ ብሎ የሚጠራቸው እንጂ የረከሰው፣ ኃጢአተኛው ዓለም አይደለም። በመቀጠልም ሲናገር፦ “ነገር ግን እለት እለት ይሹኛል መንገዴንም ያውቁ ዘንድ ይወድዳሉ፤ ጽድቅን እንዳደረጉ የአምላካቸውንም ፍርድ እንዳልተው ሕዝብ እውነተኛውን ፍርድ ይለምኑኛል” [ኢሳ 58÷1፣2]። እዚህ ላይ ወደ እይታ የመጣው ራሳቸውን ፃድቅ አድርገው በመቁጠር በእግዚአብሔር አገልግሎትም ጥልቅ ፍላጎት እንዳላቸው ለማንፀባረቅ ስለሚሞክር መደብ ነው።ልብን የሚመረምረው የእርሱ ጠንካራና ከባድ ተግሳጽ ግን በመለኮታዊ መመሪያዎች ላይ እየተረማመዱ እንደሆነ ያረጋግጥላቸዋል። GCAmh 327.5

ነብዩ ስለተተወው አዋጅ እንዲህ ይጠቁማል፦ “ከድሮ ዘመን የፈረሱት ስፍራዎች ይሰራሉ፤ የብዙ ትውልድም መሰረት ይታነፃል፤ አንተም ሰባራውን ጠጋኝ፣ የመኖሪያ መንገድን አዳሽ ትባላለህ። ፈቃድህን በተቀደሰው ቀኔ ከማድረግ እግርህን ከሰንበት ብትመልስ፣ ሰንበትንም ደስታ፣ እግዚአብሔርም የቀደሰውን ክቡር ብትለው የገዛ መንገድህን ከማድረግ ፈቃድህንም ከማግኘት ከንቱ ነገርንም ከመናገር ተከልክለህ ብታከብረው በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል” [ኢሳ 58÷12፣13]። ይህ ትንቢት በእኛ ዘመንም ተግባራዊ የሚሆን ነው። የእግዚአብሔር ሕግ የተጣሰው በሮም ስልጣን ሰንበት በተቀየረ ጊዜ ነበር። ያ መለኮታዊ ተቋም ይታደስ ዘንድ ግን ጊዜው መጥቶአል። የተሰበረው ይጠገናል፤ የበርካታ ትውልድ መሰረትም ይታነፃል። GCAmh 328.1

በፈጣሪ እረፍትና ባርኮት ተቀድሳ፣ አዳም በንጽህናው በቅድስት ኤደን ውስጥ እያለ ሰንበት ተጠብቃለች። በደስታ ይኖርባት ከነበረው ይዞታው ሲወጣም፣ በወደቀው ሆኖም በፀፀት ውስጥ በነበረው አዳም ሰንበት ተጠብቃለች። ከአቤል እስከ ኖህ፣ ከአብርሃም እስከ ያዕቆብ በሁሉም አባቶች ተጠብቃለች። የተመረጡት ሕዝቦች በግብጽ በባርነት በነበሩበት ጊዜ፣ በተስፋፋው ጣዖት አምላኪነት መካከል ሆነው ብዙዎች የእግዚአብሔርን ሕግ እውቀት አጡ። ጌታ ግን እሥራኤልን በተቤዤ ጊዜ፣ ፈቃዱን ያውቁ ዘንድ ለዘላለምም ይፈሩትና ይታዘዙት ዘንድ በሚያስደንቅ ትዕይንት ሕጉን ለተሰበሰበው ሕዝብ አወጀ። GCAmh 328.2

ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ የእግዚአብሔር ሕግ እውቀት በምድር ቆይቶአል። የአራተኛው ትዕዛዝ ሰንበትም ተጠብቆአል። “የኃጢአት ሰው” [ጳጳሳዊ ሥርዓቱ] የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቀን ከእግሩ በታች ለመርገጥ ቢሳካለትም፣ ገናና በነበረበት ዘመን እንኳ፣ በምስጢራዊ ስፍራዎች ተደብቀው ሰንበትን የሚጠብቁ ታማኝ ነፍሳት ነበሩ። ከተሐድሶው ጀምሮ በእያንዳንዱ ትውልድ የሚጠብቁአት ጥቂት ሰዎች ነበሩ። ሁልጊዜም በነቀፋና በስደት መካከል ቢሆንም ለእግዚአብሔር ሕግ ዘላለማዊነትና ለፍጥረት ሰንበት ላለው የተቀደሰ ኃላፊነት (ግዴታ) ቋሚ ማረጋገጫ የሚሆን ምስክር ሆኖአል። GCAmh 328.3

እነዚህ በራእይ 14 “ከዘላለሙ ወንጌል” ጋር በተገናኘ የቀረቡ እውነቶች፣ በሚገለጥበት ጊዜ የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን የሚለዩ ይሆናሉ። ምክንያቱም የሶስትዮሹ መልእክት ውጤት እንደሆኑ ተደርጎ “የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁት የሱስንም በማመን የሚፀኑት” ተብሎ ታውጆአል። ይህ መልእክት ደግሞ ጌታ ከመምጣቱ በፊት የሚሰጥ የመጨረሻው መልእክት ነው። ልክ እንደ ታወጀ የምድር መከር ይሰበሰብ ዘንድ የሰው ልጅ በክብር ሲመጣ በነብዩ ታይቶአል። GCAmh 328.4

ቤተ መቅደሱንና መለወጥ የማይችለውን የእግዚአብሔርን ሕግ በተመለከተ ብርሐን የተቀበሉ እነርሱ ይረዱት ዘንድ የተሰጣቸውን የእውነት ተዋረድ፣ ስምምነትና ውበት ሲያዩ በመገረም በደስታ ተሞሉ። ለእነርሱ የተገለጠው ውድ ዋጋ ያለው ብርሐን ለሌሎችም ክርስቲያኖች ይሰጥ ዘንድ ተመኙ፤ በደስታ ተቀባይነት ያገኛል ብሎ ከማመን በቀር ሌላ የሚያስቡት አልነበረም። ነገር ግን ከዓለም የሚለዩአቸውን (ከዓለም ጋር ልዩነት እንዲፈጥሩ የሚያደርጓቸውን) እውነቶች የክርስቶስ ተከታዮች ነን ባዮች አልተቀበሏቸውም። አራተኛውን ትዕዛዝ ማክበር ለሚጠይቀው መስዋዕትነት አብዛኛዎቹ ወደኋላ አፈገፈጉ። GCAmh 328.5

የሰንበት መጠይቆች በቀረቡ ጊዜ ብዙዎች ከዓለማዊያን እይታ በመነሳት ምክንያት ሰጡ፤ እንዲህ ሲሉ፦ “ሁልጊዜም እሁድን ስንጠብቅ ነው የኖርነው፤ አባቶቻችን ጠብቀውታል። ብዙ መልካምና ሐይማኖተኛ ሰዎች ጠብቀውት በደስታ አልፈዋል። እነርሱ ትክክል ከነበሩ፣ እኛም ነን። አዲሱን ሰንበት [ቅዳሜን] መጠበቃችን ከዓለም ስምምነት ውጪ ያደርገንና በእነርሱ ላይ ተጽዕኖ እንዳይኖረን እንሆናለን። ሰባተኛውን ቀን የሚጠብቅ አንድ ትንሽ ቡድን፣ እሁድን የሚያከብረውን ዓለም በሞላ ተጋፍጦ ምን ሊያመጣ ነው?” አይሁዳዊያን የሱስን ያልተቀበሉበትን ምክንያት ለማብራራት ሲሞክሩ እነዚህን ተመሳሳይ መከራከሪያዎች አቅርበው ነበር። አባቶቻቸው መስዋዕት በማቅረባቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል፤ ልጆቻቸው ተመሳሳይ መንገድ ቢከተሉ ድነት ሊያገኙ የማይችሉት ለምንድን ነው? ብለዋል። በሉተር ጊዜም፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች በካቶሊክ እምነት ውስጥ ሆነው አልፈዋል፤ እናም ያ ኃይማኖት ለመዳን በቂ ነው እያሉ ጳጳሳዊያኑ ምክንያት ያቀርቡ ነበር። እንደዚህ ዓይነቱ ምክንያታዊነት ለእምነት ወይም ለተግባራዊነቱ መጎልመስ ውጤታማ መሰናክል እንደሆነ ያረጋግጣል። GCAmh 329.1

እሁድን መጠበቅ መሰረት የያዘ አስተምህሮ እንደሆነ፣ ለብዙ መቶ ዓመታትም ወሰኑን ያሰፋ የቤተ ክርስቲያን ባህል እንደሆነ ብዙዎች ተከራክረዋል። ነገር ግን ይህንን መከራከሪያ በሚቃረን ሁኔታ ሰንበት [ቅዳሜ]ና አከባበሩ [እነርሱ ከሚናገሩት ዘመን በፊት] አስቀድሞ እጅግ ጥንታዊና የተስፋፋ እንደነበረ፣ እንዲያውም ከምድር እድሜ ጋር አንድ እንደሆነ፣ የመላዕክትንና የእግዚአብሔርን ይሁንታ ያገኘ እንደሆነ፣ እንዲታይ ተደርጓል። የምድር መሰረቶች በተተከሉ ጊዜ፣ አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት በዘመሩ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ እልል ባሉ ጊዜ፣ ያኔ የሰንበት መሰረት ተጣለ [እዮብ 38÷6፣7፤ ዘፍ 2÷1-3]። ይህ ተቋም አክብሮታችን ቢጠይቅ የተገባው ነው፦ የተቋቋመው በፍጡር ስልጣን አይደለም፤ በፍጡር ወግና ባህል የተደገፈ አይደለም፤ ለዘመናት በሸመገለው የተቋቋመ፣ በዘላለማዊው ቃሉ የታዘዘ ነው። GCAmh 329.2

የሰዎች ትኩረት ወደ ሰንበት ተሐድሶ ርዕስ እንዲዞር ሲደረግ፣ እንደዚህ ዓይነቶቹን ማብራሪያዎች በምስክሩ ላይ እየጫኑ፣ የሚጠይቁ ህሊናዎችን በተሳካ ሁኔታ ፀጥ ለማሰኘት የሚችሉበትን መንገድ በመቆፈር፣ ተቀባነት ያተረፉ አገልጋዮች የእግዚአብሔርን ቃል አጣመሙ። መጽሐፍ ቅዱስን ራሳቸው ያልመረመሩ እነርሱ ከፍላጎቶቻቸው ጋር የሚሄዱትን መደምደሚያዎች መቀበል በቂያቸው ነበር። በክርክር፣ በተቀነባበረ ማታለያ፣ በአባቶች ባህልና ልማድ፣ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን ስልጣን እውነቱን ይገለብጡ ዘንድ ብዙዎች ማሰኑ። ደጋፊዎቹ ደግሞ ይከላከሉለት ዘንድ ወደ መጽሐፍ ቅዱሳቸው አመሩ። በእውነት ቃል ብቻ የታጠቁ ምስኪን ሰዎች የተማሩ ሰዎችን ጥቃት ተቋቁመው ቆሙ። እነዚህ የተማሩ ሰዎች በአንደበተ ርዕቱነት ያቀረቡዋቸው የተቀነባበሩ ማታለያዎቻቸው፣ በትምህርት ቤት መደለያዎች ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በተገነቡ፣ ግልጽና ቀጥተኛ ምክንያት በሚያቀርቡ ምስኪኖች መከራከሪያ ፊት አቅም ሲከዳው በመደነቅና በቁጣ ተመለከቱ። GCAmh 329.3

የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ድጋፍ ሳይኖራቸው ብዙዎች ያለመታከት ለፉ፤ ያው ተመሳሳይ መከራከሪያ ክርስቶስንና ሐዋርያቱን ለመቃወም ቀርቦ እንደነበረ ረስተው፦ “ታዲያ የዚህን ሰንበት ጥያቄ ታላላቅ ሰዎቻችን (ሊቆቻችን) ለምን አይረዱትም? እንደእናንተ የሚያምኑ በጣም ጥቂቶች ናቸው። እናንተ ትክክል ሆናችሁ በዓለም ያሉ የተማሩ ሰዎች ሁሉ ሊሳሳቱ አይችሉም”አሉ። GCAmh 330.1

እንደነዚህ ያሉ መከራከሪያዎችን ፉርሽ ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውንና በሁሉም ዘመናት እግዚአብሔር ከሕዝቦቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ታሪክ መጥቀስ ብቻ በቂ ነበር። እግዚአብሔር የሚሰራው ድምፁን በሚሰሙና በሚታዘዙ፣ አስፈላጊም ሲሆን የማይጣፍጡ እውነቶችን የሚናገሩ ተወዳጅ ኃጢአቶችን ከመንቀፍ ወደ ኋላ በማይሉ አማካኝነት ነው። አብዛኛውን ጊዜ የተሐድሶ እንቅስቃሴዎችን ይመሩ ዘንድ የተማሩና ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች የማይመርጠው፣ በእምነታቸው፣ በጽንሰ-ሃሳቦቻቸውና በሥነ-መለኮታዊ ጥናት መዋቅሮቻቸው በመደገፍ ከእግዚአብሔር ዘንድ መማር እንደማያስፈልጋቸው ስለሚሰማቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት ወይም መተንተን የሚችሉት ከጥበብ ምንጭ ጋር የግል ቁርኝት ያላቸው ብቻ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ትምህርት ቤት ገብተው ያልተማሩ ሰዎች እውነትን እንዲያውጁ ይጠራሉ፤ ምክንያቱ ደግሞ ያልተማሩ መሆናቸው ሳይሆን በራሳችን ብቁ ነን፣ ከእግዚአብሔር መማር አያስፈልገንም ስለማይሉ ነው። ከክርስቶስ ትምህርት ቤት ይማራሉ፣ ትህትናቸውና ታዛዥ መሆናቸው ታላቅ ያደርጋቸዋል። የእውነቱን እውቀት በአደራ ሲሰጣቸው፣ ከምድራዊ ክብርና ከፍጡር ታላቅነት ጋር ሲወዳደር ዓለማዊውን ክብር ወደ እርባና ቢስነት በሚያወርድ ማዕረግ ያከብራቸዋል። GCAmh 330.2

አብዛኛዎቹ አድቬንቲስቶች መቅደሱንና የእግዚአብሔርን ሕግ በተመለከተ እውነቶችን አንቀበልም አሉ፤ ብዙዎቹም በአድቬንት እንቅስቃሴ የነበራቸውን እምነት ክደው፣ በዚያ ሥራ ላይ የተነገሩትን ትንቢታት በተመለከተ የነበሩትን ምክንያታዊ ያልሆኑና የሚጣረሱ አመለካከቶችን ተቀበሉ። አንዳንዶች የክርስቶስን የመምጫ ጊዜ፣ ወደሚታወቅ ቀን፣ በተደጋጋሚ የመወሰን ስህተት ተመሩ። አሁን በቤተ መቅደሱ ርዕሰ-ጉዳይ ዙሪያ እየበራ የነበረው ብርሐን እስከ ሁለተኛው ምፅዓት የሚደርስ ትንቢታዊ ዘመን እንደሌለ፤ የዚህ ክስተት መፈፀሚያ ትክክለኛ ጊዜ እንዳልተተነበየ ያሳያቸው ነበር። ነገር ግን ከዚህ ብርሐን ፈቀቅ ብለው፣ የጌታ መምጫ ነው ብለው የወሰኑት ጊዜ ሲያልፍ ሌላ ጊዜ እየወሰኑ፣ በዚያው ልክ ቅር ይሰኙ ነበር። GCAmh 330.3

የተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን መምጣት በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት በተቀበለች ጊዜ፣ ተስፋቸውንና የወደፊት መጠባበቃቸውን በእግዚአብሔር ቃል አማካኝነት በጥንቃቄ እንዲመረምሩት ሐዋርያው ጳውሎስ መከራቸው። ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት የሚከናወኑትን ክስተቶች ወደሚገልፁት ትንቢታት በመጠቆም በእነርሱ ዘመን ይመጣል ብለው ለመጠበቅ የሚያስችል ምክንያት እንደሌለ አሳያቸው። “ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ” [2ኛ ተሰሎ 2÷3] ይላል የማስጠንቀቂያ ቃሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተደገፉ ተስፋዎችን ለመቀበል የሚቃጣቸው ከሆነ፣ ወደ ተሳሳተ መንገድ ይመራሉ፤ ቅሬታ ለማያምኑ ሰዎች ማላገጫ ያጋልጣቸውና ለተስፋ መቁረጥ እጅ ወደ መስጠት አደጋ ይደርሳሉ፤ ከዚያም ለመዳናቸው አስፈላጊ የሆኑትን እውነቶች የመጠራጠር ፈተና ይጋረጥባቸዋል። ሐዋርያው ለተሰሎንቄ ሰዎች የሰጠው ማስጠንቀቂያ በመጨረሻው ዘመን ለሚኖሩ ሰዎች አስፈላጊ የሆነ ትምህርት አዝሏል። ብዙ አድቬንቲስቶች፣ በተቆረጠ የጌታ መምጫ ቀን ላይ እምነታቸውን ካላደረጉ በስተቀር በመዘጋጀት ሥራ ላይ ቀናኢ እና ትጉህ መሆን የማይችሉ መስሎ ይሰማቸዋል። ነገር ግን ተስፋቸው አሁንም ቅድምም እየተነሳሳ ተመልሶ ሲንኮታኮት እምነታቸው ንዝረት እያጋጠመው፣ በትንቢት ታላላቅ እውነቶች ለመመሰጥ የማይቻላቸው እየሆነ ይሄዳል። የመጀመሪያውን መልእክት በመስጠት ውስጥ ስለተወሰነ የፍርድ ሰዓት መስበክ የታዘዘው በእግዚአብሔር ነበር። ያ መልእክት መሰረት ያደረገው የትንቢት ዘመናት ስሌት፣ ማለትም የ2300 ቀናትን ማብቂያ በ1844 ዓ.ም የመከር ወቅት ያደረገው ትንቢት፣ ያለ ክስ የሚቆም ነው። ለትንቢት ዘመናቱ መነሻና መደምደሚያ የሚሆን አዲስ ቀን የመፈለጉ ተደጋጋሚ ጥረት፣ እንዲሁም እነዚህን እይታዎች በእግር ለማቆም የሚደረገው ያልተብላላ (እውነትን መሰረት ያላደረገ) ምክንያት ነፍሳትን ከወቅታዊ እውነት ከማራቁም በተጨማሪ ትንቢቶችን ለማብራራት በሚደረገው ጥረት ሁሉ ላይ ንቀት የሚያሳርፍ ነው። ለዳግም ምፅዓቱ ተደጋጋሚ የሆነ የተቆረጠ ጊዜ ሲወሰንና በስፋትም ሲሰበክ፣ የሰይጣንን እቅዶች የበለጠ የሚስማማ ይሆናል። የተወሰነው ጊዜ ሲያልፍ በመልእክቱ ደጋፊዎች ላይ ሹፈትና ንቀት በማነሳሳት በ1843 እና በ1844 ዓ.ም በነበረው ታላቅ የአድቬንት ንቅናቄ ላይ ነቀፋን ያሰፍናል። በእንደዚህ አይነቱ ስህተት የሚቀጥሉ ሰዎች በመጨረሻ፣ የክርስቶስን መምጣት እጅግ እሩቅ በሆነ የወደፊት ቀን ላይ ወደ መወሰን ይደርሳሉ። ከዚያም በውሸት ደህንነት ላይ ይደገፋሉ፤ ሰዓቱ እስኪያልፍባቸው ድረስ ብዙዎች የማይታለሉ አይሆኑም። GCAmh 330.4

የጥንታዊት እሥራኤል ታሪክ፣ ያለፈው የአድቬንቲስት ተቋም ተሞክሮ እጅግ የሚቀራረብ ተምሳሌት ነው። እግዚአብሔር የእሥራኤልን ልጆች ከግብጽ እንደመራ ሁሉ በአድቬንት ንቅናቄ ውስጥም የነበሩ ሰዎችን መርቷል። የዕብራውያን እምነት በቀይ ባህር እንደተፈተነ ሁሉ የእነርሱም እምነት በታላቁ የቅሬታ ወቅት ተፈተነ። ባለፈው ልምምዳቸው አብሮአቸው የነበረውን፣ የመራቸውን እጅ ማመናቸውን ቢቀጥሉ ኖሮ የእግዚአብሔርን ማዳን ማየት በቻሉ ነበር። በ1844 ሥራ ላይ በአንድነት የለፉ ሁሉ የሶስተኛውን መልአክ መልእክት ተቀብለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አውጀውት ቢሆን ኖሮ ጌታ ከጥረታቸው ጋር እጅግ ባደረገ ነበር፤ የብርሐን ጎርፍ በዓለም ላይ በወረደ ነበር። ከዓመታት በፊት በዓለም የሚኖሩ ሁሉ ማስጠንቀቂያው በደረሳቸው፣ የማጠቃለያውም ሥራ ተጠናቆ ሕዝቡን ለመቤዠት ክርስቶስ በመጣ ነበር። GCAmh 331.1

እሥራኤል አርባ ዓመት በበረሃ ይቅበዘበዝ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም። በቀጥታ ወደ ከነዓን ምድር መርቷቸው፣ ቅዱስና ደስተኛ ሕዝብ አድርጎ በዚያ ስፍራ ይመሰርታቸው ዘንድ ወደደ። ሆኖም “ባለማመናቸው ጠንቅ ሊገቡ” አልቻሉም [ዕብ 3÷19]። በማፈግፈጋቸውና በክህደታቸው ምክንያት በበረሃ አለቁ፤ ወደ ተስፋዋ ምድር ይገቡ ዘንድ ሌሎች [ልጆቻቸው] ተወልደው አደጉ። በተመሳሳይ ሁኔታ የክርስቶስ መምጣት ለረጅም ዘመን ይራዘም ዘንድ፣ ሕዝቦቹ በኃጢአትና በሃዘን ዓለም ውስጥ ለብዙ ዓመታት ይኖሩ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም። ያከናውኑት ዘንድ የሰጣቸውን ኃላፊነት ለመፈፀም ፈቃደኛ ሳይሆኑ ሲቀሩ፣ መልእክቱን ያውጁ ዘንድ ሌሎች ተነሱ። ለዓለም ካለው ምሕረት የተነሳ፣ ኃጢአተኞች ማስጠንቀቂያውን የመስማት ዕድል አግኝተው፣ የእግዚአብሔር ቁጣ ከመውረዱ በፊት በእርሱ በኩል መሸሸጊያ ያገኙ ዘንድ የሱስ ምፅዓቱን ያዘገያል። GCAmh 331.2

አሁንም እንደ ቀድሞው ዘመናት ተቃውሞ ይቀሰቀሳል። “ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሐን ይጠላልና ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሐን አይመጣም” [የእንግሊዘኛው KJV “ሥራውም እንዳይነቀፍ”] ይላል። [ዮሐ 3÷20]። ሰዎች የያዙትን አቋም መጽሐፍ ቅዱስ አልደግፍላቸው ሲል፣ መፍጠር የሚችሉትን ሁከት ሁሉ ተጠቅመው ብዙዎች አቋማቸውን ሊያስጠብቁ ይወስናሉ፤ በተንኮለኛ መንፈስም፣ ተወዳጅ ያልሆነውን እውነት ደግፈው የሚቆሙትን ባህርይና ምክንያት ያጠቃሉ። ይህ በሁሉም ዘመናት ሲተገበር የኖረ ተመሳሳይ መርሃ-ግብር ነው። ኤልያስ የእሥራኤል ችግር ፈጣሪ፣ ኤርምያስ ከዳተኛ(ባንዳ)፣ ጳውሎስ ደግሞ የመቅደስ አርካሽ፣ ተብለዋል። ከዚያ ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ለእውነት ታማኝ ሆነው የሚቆሙ እነርሱ አሳማጺያን፣ መናፍቃን ወይም ከፋፋዮች ተብለው ተወግዘዋል። የትንቢትን እርግጠኛ ቃል ለመቀበል ብቁ እምነት የሌላቸው እነርሱ ተወዳጅ ኃጢአቶችን ለማውገዝ በሚደፍሩት ላይ የሚመጣውን ክስ ያለምንም ጥያቄ ይቀበላሉ። ይህ መንፈስ ወደፊት የበለጠ እየጨመረ ይሄዳል። የመንግሥት ሕግጋት ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር የሚጣሉበት ጊዜ እየቀረበ ስለሆነ፣ ሁሉንም የመለኮታዊ መመሪያዎች የሚከተል ማንም ቢኖር እንደ ክፉ-ሰሪ ተቆጥሮ የሚደርስበትን ነቀፋና ቅጣት በጀግንነት መቋቋም እንደሚኖርበት መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል። GCAmh 332.1

ከዚህ በመነሳት የእውነት መልዕክተኛ ኃላፊነት ምንድን ነው? ብቸኛ ውጤቱ ሁልጊዜም መጠይቁን እንዲያድበሰብሱ ወይም እንዲቃወሙ ሰዎችን የሚያነሳሳ በመሆኑ እውነቱ መነገር የለበትም ወደሚለው ድምዳሜ መድረስ አለበት? አይደለም፤ ተቃውሞን ስለሚያነሳሳ ብቻ የእግዚአብሔርን ቃል ምስክርነት ለማፈን የሚያስችለው፣ የቀደሙት ተሐድሶ አራማጆች ካደረጉት የተሻለ ምክንያት የለውም። በቅዱሳንና በሰማዕታት የተደረገው የእምነት ምስክርነት የተመዘገበው ለሚቀጥሉ ትውልዶች ጥቅም ነበረ። እነዚያ ሕያው የሆኑ የቅድስናና የፍፁም ሐቀኝነት ተምሳሌቶች፣ የእግዚአብሔር ምስክሮች ይሆኑ ዘንድ አሁን የተጠሩትን ለማበረታታት ችለዋል። እውነትና ፀጋ የተቀበሉት ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን፣ በእነርሱ አማካኝነት፣ የእግዚአብሔር እውቀት ምድርን እንዲያፈካ ነበር። እግዚአብሔር በዚህ ትውልድ ላሉ አገልጋዮች ብርሐን ሰጥቷል? እንኪያስ ወደ ዓለም ሊያበሩት ይገባቸዋል። GCAmh 332.2

በጥንት ጊዜ በስሙ ለተናገር ሰው ጌታ እንዲህ ተናገረ፦ “እኔንም መስማት እምቢ ብለዋልና የእሥራኤል ቤት አንተን አይሰሙም።” ቢሆንም እንዲህ አለ፦ “ቢሰሙ ወይም ባይሰሙ ቃሌን ትነግራቸዋለህ” [ሕዝ 3÷7፤ 2÷7]። ይህ ትዕዛዝ የተሰጠው በዚህ ጊዜ ላለ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነው፤ “ድምጽህን እንደ መለከት አንሳ ለሕዝቤ መተላለፋቸውን ለያዕቆብ ቤትም ኃጢአታቸውን ንገር።” [ኢሳ 58÷1]። GCAmh 332.3

እስከሚችለው ርቀት ሄዶ እድሎቹን በመጠቀም የእውነትን ብርሐን የተቀበለ እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እርሱ እንደመጣው እንደ የእሥራኤል ነብይ ሁሉ፣ በተመሳሳይ፣ በከባድና በአስፈሪ ኃላፊነት ሥር ነው። “አንተም የሰው ልጅ ሆይ ለእሥራኤል ቤት ጉበኛ አድርጌሃለሁ፤ ከአፌ ቃሌን ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። ኃጢአተኛውን፦ ኃጢአተኛ ሆይ በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁ ጊዜ ኃጢአተኛውን ከመንገዱ ታስጠነቅቅ ዘንድ ባትናገር ያ ኃጢአተኛ በኃጢአቱ ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። ነገር ግን ከመንገዱ ይመለስ ዘንድ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቀው እርሱም ከመንገዱ ባይመለስ በኃጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል።” [ሕዝ 33÷7-9]። GCAmh 332.4

እውነትን ለመቀበልና ለማወጅ፣ ለሁለቱም ታላቁ መሰናክል፣ አለመመቸትንና ነቀፋን የሚያካትት መሆኑ ነው። ይህ በእውነት ላይ የሚነሳ ትችት፣ የእውነቱ ደጋፊዎች ሊያስተባብሉት ፈጽሞ ያልቻሉት ብቸኛ መከራከሪያ ነው። ይህ ግን የክርስቶስን ትክክለኛ ተከታዮች አያስተጓጉላቸውም። እነዚህ ሰዎች እውነት ሕዝባዊ ተቀባይነት ያለው እስኪሆን አይጠብቁም። ያለባቸውን ኃላፊነት አምነው፣ አውቀውትና ተስማምተውበት መስቀሉን ይቀበላሉ። ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር “ቀላል የሆነ የጊዜው መከራችን የክብርን የዘላለም ብዛት ከሁሉ መጠን ይልቅ ያደርግልናልና” [2ኛ ቆሮ 4÷17] ይላሉ። ከጥንቱ ሰው ጋርም “ከግብጽም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንዲሆን” ይቆጥራሉ። [ዕብ 11÷26]። GCAmh 333.1

እምነታቸው ምንም አይነት ቢሆን በኃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ከመርህ ይልቅ መርሃ ግብርን የሚከተሉ ከልባቸው የዓለም-አገልጋይ የሆኑ ብቻ ናቸው። እውነት፣ እውነት ስለሆነ መርጠነው መዘዙን ለእግዚአብሔር እንተወው። በመርህ የሚመሩ፣ እምነተኞችና ደፋር ሰዎች ላስገኙት ታላቅ ተሐድሶ ዓለም ባለ እዳ ናት። በዚህ ዘመን የሚያስፈልገው የተሐድሶ ሥራ በእንደዚህ አይነት ሰዎች አማካኝነት ወደ ፊት መቀጠል አለበት። GCAmh 333.2

እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ጽድቅን የምታውቁ ህጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ ስሙኝ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፣ በስድባቸውም አትደንግጡ። እንደ ልብስም ብል ይበላቸዋል፤ እንደ በግ ጠጉርም ትል ይበላቸዋል። ጽድቄ ግን ለዘላለም ማዳኔም ለትውልድ ሁሉ ይሆናል።” [ኢሳ 51÷7፣8]። GCAmh 333.3