ታላቁ ተጋድሎ
ምዕራፍ ፲፯—የንጋቱ አብሳሪዎች
እጅግ ክቡር ብሎም እጅግ አንፀባራቂ ከሆኑ፣ ከተገለፁ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መካከል አንዱ፣ ታላቁን የመቤዠት ሥራ ለማጠናቀቅ የሚመጣበት የክርስቶስ ዳግም ምፅዓት ነው። “በሞት አገርና ጥላ”[ማቴ 4÷16] ይቀመጡ ዘንድ ለረጅም ዘመን ለተተውት የእግዚአብሔር የእምነት መንገደኛ ሕዝቦች፣ “ትንሳኤና ሕይወት” [ዮሐ 11÷25] የሆነው “የተሳደደውን እንደገና ወደ ቤቱ ይመልስ ዘንድ” [2ኛ ሳሙ 14÷13] ውድና ደስታን የሚያፋፍመው የመገለጡ ተስፋ ተሰጥቷል። የዳግም ምፅዓቱ አስተምህሮ የተቀደሱት መጻሕፍት አንኳር ጭብጥ ነው። የመጀመሪያዎቹ ጥንዶች የሃዘን እርምጃቸውን ከኤደን ካደረጉበት ቀን አንስቶ የአጥፊውን ኃይል ሰባብሮ ወደ ታጣችው ገነት እንደገና ያመጣቸው ዘንድ የእምነት ልጆች የክርስቶስን ምፅዓት ሲጠብቁ ኖረዋል። የመሲሁን በክብር መምጣት እንደ የተስፋቸው መደምደሚያ በማየት የጥንት ቅዱሳን ወደፊት ይመለከቱ ነበር። ኤደን ውስጥ ሲኖሩ ከነበሩት ጀምሮ ገና ሰባተኛ ትውልድ የነበረው ሄኖክ፣ ለሶስት መቶ ዓመታት በዚህ ምድር የተመላለሰው ይህ ሰው፣ የአዳኙን መምጣት ከሩቅ ይመለከት ዘንድ ተፈቅዶለት ነበር። “እነሆ” አለ “እግዚአብሔር ይመጣል ከአዕላፍ ቅዱሳን ጋራ በሁሉ ይፈርድ ዘንድ” [ይሁዳ 14፣15]። የኃይማኖት አባቱ እዮብ በስቃይ ሌሊቱ ውስጥ፣ በማይነቃነቅ እምነት “እኔ ግን የሚያድነኝ ሕያው እንደሆነ አውቃለሁ፤ በፍጻሜም ዘመን በምድር አፈር ላይ ይቆማል…. ከስጋዬ ጋራ አምላኬን አየዋለሁ፤ እኔ እራሴ አየዋለሁ ዓይኖቼም ይመለከቱታል ከእኔም ሌላ አይደለም።” [እዮብ 19÷25-27] ሲል ጮኸ። GCAmh 221.1
የጽድቅን መንግሥት ይጀምር ዘንድ የሚመጣው ክርስቶስ፣ ቅዱሳት ፀሐፊዎች እጅግ ማራኪና ስሜታዊ የሆኑ ቃላትን እንዲናገሩ አነሳስቶአቸዋል። የመጽሐፍ ቅዱስ ገጣሚዎችና ነብያት በዘላለማዊ ነበልባል በሚፈኩ ቃላት ድባብ ውስጥ ሆነው አስበውታል። መዝሙረኛው ስለ እሥራኤል ንጉሥ ኃይልና ግርማ ሲዘምር፦ “ከጽዮን ያማረ ጌጽ ወጣ፣ እግዚአብሔርም አበራ፤ አምላካችን ይመጣል ዝምም አይልም…. ከላይ ሰማይን ይፀራታል፣ ምድርንም፣ ሕዝቦቹን ለመፍረድ” [መዝ 50÷2-4]። “ሰማዮች ደስ ይበላቸው ምድርም ሐሴት ታድርግ።” “ይመጣልና አዎን በምድር ላይ ለመፍረድ ይመጣል። ዓለምንም በጽድቅ ይፈርዳል አሕዛብንም በእውነቱ።” [መዝ 96÷11፣13]። GCAmh 221.2
ነብዩ ኢሳይያስ ሲናገር፦ “እናንት በአፈር ውስጥ የምትኖሩ ንቁ ዘምሩም፤ ጠልህ የብርሐን [እንደ እፅዋት] ጠል ነውና፣ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና/awake and sing, ye that dwell in dust; for thy dew is as the dew of herbs, and the earth shall cast out the dead” “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ [ከእኔ ሬሳ ጋር አብረው] ይነሳሉ/Thy dead men shall live, together with my dead body shall they arise።” “ሞትን ለዘላለም [በድል/in victory] ይውጣል፤ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፤ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና። በዚያም ቀን፦ እነሆ አምላካችን ይህ ነው ተስፋ አድርገነዋል፤ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው ጠብቀነዋል፣ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሴትም እናደርጋለን ይባላል።” [ኢሳ 26÷19፤ 25÷8፣9]። GCAmh 221.3
እንባቆምም በቅዱስ ራዕዩ ተውጦ መገለጡን ተመለከተ፦ “እግዚአብሔር ከቴማን መጣ ቅዱሱም ከፋራን ተራራ፤ ክብሩም ሰማያትን ከደነ ምስጋናውም በምድር መላ። ብልጭታውም እንደ ብርሐን ነበር።” “ቆመ ምድርንም ሰፈራት። አየ አሕዛብንም አናወፀ። የዘላለም ተራሮች ተንቀጠቀጡ። ከጥንት የነበሩ ኮረብቶች ዝቅ አሉ። መንገዱ ከዘላለም ነው።” “በፈረሶችህ ላይ ተቀምጠሃልና በመድሃኒትህም ሰረገሎች ላይ።” “ተራሮች አዩህ ተንቀጠቀጡም…. ቀላይ ቃልዋን ሰጠች እጅዋንም ወደ ላይ አነሳች። ፀሐይና ጨረቃ በስፍራቸው ቆሙ። በፍላፃዎችህ ብርሐን ሄዱ በሚያንፀባርቀውም በጦርህ ፀዳል።” “ሕዝብህን ለማዳን ወጣህ የቀባኸውን ታድን ዘንድ።”[እንባቆም3÷3፣4፣6፣8፣10፣11፣13]። GCAmh 222.1
አዳኙ ከደቀ መዛሙርቱ ሊለይ በተቃረበበት ጊዜ እንደገና እመጣለሁ በሚለው ቃሉ ከሃዘናቸው አጽናናቸው፦ “ልባችሁ አይደንግጥ በአባቴ ቤት ብዙ ስፍራ አለ። እሄዳለሁ ቦታ አዘጋጅላችሁ ዘንድ። በሄድሁም ቦታም ባዘጋጀሁላችሁ ጊዜ ዳግም እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ።” [ዮሐ 14÷1-3]። “የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከራሱም ጋር ቅዱሳን መልአክቱ ሁሉ፤ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ።” [ማቴ 25÷31፣32]። GCAmh 222.2
ከክርስቶስ እርገት በኋላ በደብረ ዘይት ተራራ ይመላለሱ የነበሩት መላዕክት የመመለሱን ተስፋ ለደቀ-መዛሙርቱ ደገሙላቸው፤ “ይህ የሱስ ከላንት ወደ ሰማይ የወጣው እንዲሁ ይመጣል እንዳያችሁት ወደ ሰማይ ሲወጣ” [የሐዋ ሥራ 1÷11]። ጳውሎስም በመንፈስ ሆኖ ሲመሰክር፦ “እርሱ ጌታ በእልልታ [with a shout] በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳል” [1ኛ ተሰሎ 4÷16]። የፍጥሞ ነብይም ሲናገር፦ “እነሆ እርሱ በደመና ይመጣል አይንም ሁሉ ታየዋለች።” [ራዕይ 1÷7] ይላል። GCAmh 222.3
“እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ በቅዱሳን ነብያቱ አፍ የተናገረው ነገር ሁሉ እስከሚታደስበት” [የሐዋ ሥራ 3÷21] ጊዜ ያለው ክብር ሁሉ በመምጣቱ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው። ከዚያም ለረጅም ጊዜ የቀጠለው የክፋት አገዛዝ ይሰበራል፤ “የዓለም መንግሥት ለጌታችንና ለእርሱ ለክርስቶስ ሆነች ለዘላለምም እስከ ዘላለም ይነግሳል” [ራዕይ 11÷15]። “የእግዚአብሔርም ክብር ይገለጣል ስጋም የለበሰ ሁሉ በአንድ ያዩታል።” “እግዚአብሔር አምላክ ጽድቅንና ምስጋናን በአሕዛብ ፊት ያበቅላል።” እግዚአብሔር “የክብር አክሊል ይሆናል የትምክህት ዘውድ ለቀሩት ሕዝቡ ይሆናል።” [ኢሳ 40÷5፤ 61÷11፤ 28÷5]። GCAmh 222.4
ሰላማዊ የሆነውና ለረጅም ጊዜ ሲናፈቅ የነበረው የመሲሁ መንግሥት ከመላው ሰማይ በታች የሚመሰረተው ያኔ ነው። “እግዚአብሔር ጽዮንን ያጽናናልና። በእርስዋ የፈረሰውን ሁሉ ያጽናናል። ምድረ-በዳዋንም እንደ ገነት ያደርጋል፤ በረሃዋንም እንደ እግዚአብሔር አታክልት።” “የሊባኖስ ክብር ይሰጠዋል የቀርሜሎስና የሳሮን ደም ግባት።” “ከእንግዲህ ወዲያ የተጣለች አትባይም፤ ምድርሽም ደግሞ የተፈታች። ነገር ግን ደስታዬ የሚያድርባት ትባያለሽ ምድርሽም ያገባች።” “ሙሽራውም በሙሽራይቱ ደስ እንዲለው እንዲሁ አምላክሽ በአንቺ ደስ ይለዋል።”[ኢሳ 51÷3፤ 35÷2፤ 62÷4፣5]። GCAmh 222.5
የክርስቶስ መምጣት ለእውነተኛ ተከታዮቹ በዘመናት ሁሉ ተስፋቸው ሆኖ ኖሮአል። እንደገና እንደሚመጣ የተናገረበት፣ የአዳኙ የደብረዘይት የመሰናበቻ ተስፋ በፊታቸው ያለውን የደቀ-መዛሙርቱን ዘመን አፈካው፤ ሃዘን ሊያዳፍነው፣ ፈተና ሊያደበዝዘው በማይችል ሁኔታ ልባቸውን በደስታና በተስፋ ሞላው። በስቃይና በስደት መሃል “የታላቁ አምላካችንንና የመድሃኒታችንን የየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ” መጠባበቅ “የተባረከው ተስፋ” [ቲቶ 2÷13] ነበር። የክርስቶስን መምጣት በሕይወት እያሉ ማየት ይመኙ የነበሩትን ወገኖቻቸውን ሲቀብሩ የተሰሎንቄ ክርስቲያናት በሃዘን በትር ሲመቱ ሳለ መምህራቸው ጳውሎስ በክርስቶስ ምፅዓት ስለሚሆነው ትንሳኤ አመላከታቸው። ከዚያም በክርስቶስ የሞቱ ይነሳሉ፤ በሕይወት ካሉት ጋራም ሆነው ጌታን በአየር ይገናኙታል። “እንዲሁም” አለ “ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ።” [1ኛ ተሰሎ 4÷16-18]። GCAmh 222.6
በድንጋያማዋ ፍጥሞ ተወዳጁ ደቀ-መዝሙር “አዎን ፈጥኜ እመጣለሁ” የሚለውን ተስፋ ይሰማል፤ የናፍቆት ምላሹም፣ በስደትዋ ዘመን ሁሉ ቤተ ክርስቲያን የፀለየችውን ፀሎት የሚያስተጋባ ነው፣ “አዎን ጌታ ሆይ የሱስ ና።” [ራዕይ 22÷20]። GCAmh 223.1
ቅዱሳንና ሰማዕታት ለእውነት ምስክር ከሆኑበት ከወህኒ ቤት፣ ከቃጠሎ ስፍራና ከመታረጃ ቦታ ዘንድ የእምነታቸውና የተስፋቸው ድምፅ ምዕተ ዓመታትን ተከትሎ ይፈሳል። “ስለ ክርስቶስ ከሞት መነሳት እርግጠኛ ሆነው እንደገና በሚመጣበት ጊዜም የራሳቸውን ትንሳኤ አምነው፤ በዚህ ምክንያት” አለ አንድ ክርስቲያን “ሞትን ናቁት፣ ከሞት ልቀው (በላይ ሆነው) ተገኙ”-Daniel T. Taylor, The Reign of Christ on Earth: or, The Voice of the Church in All Ages, ገጽ 33። “ነፃነታቸውን ተጎናጽፈው [ከሞት] ይነሱ” ዘንድ ወደ መቃብር ለመውረድ ፈቃደኞች ነበሩ።-Ibid., ገጽ 54። “ጌታ በደመና በአባቱ ክብር ከሰማይ ሲመጣ የመንግሥቱንም ዘመን ለጻድቃን ሲያመጣ”-Ibid., ገጽ 129-132። ለማየት ይናፍቁ ነበር። ዋልደንሶችም ይህንን እምነት ይጠብቁ ነበር። ዋይክሊፍ የአዳኙ መገለጥ የቤተ ክርስቲያን ተስፋ እንደሆነ አድርጎ ወደ ፊት በተስፋ ይመለከት ነበር።-Ibid., ገጽ 132-134። GCAmh 223.2
ሉተር ሲናገር፦ “የፍርድ ቀን እስኪመጣ ሶስት መቶ ዓመታት አይደፍንም ብዬ ራሴን አሳምኜዋለሁ። ይህን የኃጢአት ዓለም ከዚህ በላይ ይሰቃይ ዘንድ እግዚአብሔር አይተወውም፤ አያደርገውምም።” “የርኩሰት መንግሥት የሚገለበጥበት ታላቁ ቀን እየቀረበ ነው።”-Ibid., ገጽ 158, 134። GCAmh 223.3
“ይህ ያረጀ ዓለም መቋጫው ሩቅ አይደለም” አለ ሜላንክተን። “ከሁሉም ክስተቶች ሁሉ ይልቅ ተስፋ ያለውን የክርስቶስን መምጣት ያለመጠራጠር በብርቱ ይሹ ዘንድ” ካልቪን ክርስቲያኖችን በመማፀን “ታማኝ የሆነው መላው ቤተሰብ ያንን ቀን ይጠብቃል” በማለት ተናገረ። “ጌታችን የመንግሥቱን ክብር ሙሉ ለሙሉ የሚገልጥበት ያ ታላቅ ቀን እስኪደርስ ድረስ” አለ “ክርስቶስን ልንራብ፣ ልንፈልገው፣ እናሰላስለውም ይገባናል።”-Ibid., ገጽ 158-134። GCAmh 223.4
“ጌታ የሱስ ስጋችንን ተሸክሞ ወደ ሰማይ አላረገምን?” አለ የስኮትላንዱ ተሐድሶ አራማጅ ኖክስ፣ “እርሱስ አይመለስምን? ከአዕላፋት ጋራ እንደሚመለስ እናውቃለን።” ለእውነት ሕይወታቸውን የሰውት ሪድሌይ እና ላቲመር በእምነት የጌታን ምፅዓት ጠበቁ። ሪድሌይ ሲጽፍ “ይህንን አምናለሁ፣ እናም እለዋለሁ፣ ይህ ዓለም ያለ ምንም ጥርጥር፣ ወደ መጨረሻው ቀርቧል። ከእግዚአብሔር አገልጋይ ከዮሐንስ ጋር እኛም ወደ አዳኛችን ክርስቶስ ና፣ ጌታ የሱስ ሆይ ና፣ እያልን በልባችን እንጩህ።”-Ibid., ገጽ 151, 145። GCAmh 223.5
“ስለ ጌታ ምፅዓት የማስባቸው ሃሳቦቼ” አለ ባክስተር፣ “ከምንም በላይ ጣፋጭና ሃሴት የሚሰጡኝ ናቸው።”-Rechard Baxter, Works, vol. 17, ገጽ 555። “መገለጡን መውደድና ያንን የተባረከ ተስፋ መናፈቅ የእምነት የሥራ ውጤት፣ የቅዱሳኑም ባህርይ ነው።” “ከሞት መነሳት በሚከናወንበት ጊዜ የሚደመሰሰው የመጨረሻው ጠላት ሞት ከሆነ ይህ ድል ሙሉ ለሙሉ ለመጨረሻ ጊዜ ለሚተገበርበት ለክርስቶስ ዳግም መምጣት አማኞች ምን ያህል መናፈቅና መፀለይ እንዳለባቸው መማር እንችላለን።”-Ibid., vol. 17, ገጽ 500። “ይህን ቀን የድነታቸው ሥራ ሁሉ መቋጫ፣ የነፍሳቸው መሻትና ጥረት አድርገው በናፍቆትና በተስፋ ሊጠብቁት ይገባቸዋል።” “ኦ ጌታ ሆይ ይህንን የተባረከ ቀን እባክህን አፍጥነው!”-Ibid., vol. 17, ገጽ 182-183። በሐዋርያት ዘመን የነበረችው ቤተ ክርስቲያን፣ “በበረሐ የነበረችው ቤተ ክርስቲያን” እና የተሐድሶ መሪዎቹ ተስፋ ይሄ ነበር። GCAmh 224.1
ትንቢት የክርስቶስን አመጣጥና ዓላማውን ብቻ ሳይሆን፣ ቀኑ እንደቀረበ የሚያውቁበት ምልክቶችን ለሰዎች ይሰጣል። የሱስ “ምልክትም በፀሐይ ይሆናል በጨረቃም በከዋከብትም” [ሉቃስ 21÷25] አለ። “ፀሐይቱ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ የሰማይም ከዋክብት ይወድቃሉ፤ በሰማይም ያሉ ኃይላት ይናወጣሉ። የዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በደመና ሲመጣ ያያሉ ከብዙ ኃይል ከምስጋናም ጋራ” [ማር 13÷24-26]። ምፅዓቱን ከሚቀድሙ ምልክቶች ውስጥ ስለመጀመሪያዎቹ ገላጩ [የሱስ] ሲናገር ፦ “ታላቅም የምድር መናወጥ ሆነ ፀሐይም እንደ ጠጉር ጥቁር ሆነ፤ ጨረቃም በሞላው እንደ ደም ሆነ።” [ራዕይ 6÷12]። GCAmh 224.2
እነዚህ ምልክቶች የታዩት ይህ [19ኛው] ክፍለ ዘመን ከመጀመሩ በፊት ነበር። ይህንን ትንቢት በማሟላት ረገድም በ1755 ዓ.ም ከተመዘገቡት ሁሉ እጅግ አስደንጋጭ የሆነ የመሬት መናወጥ ሆነ። በተለምዶ የሊዝበን የመሬት መናወጥ በመባል ቢታወቅም ወደ አብዛኛው አውሮፓ፣ አፍሪካና አሜሪካ ድረስ የዘለቀ ነበር። በግሪላንድ፣ በዌስት ኢንዲስ፣ በማይዴራ ደሴት፣ በኖርዌይ፣ በታላቋ ብሪታንያና በአየርላንድ ድረስ ተሰምቷል። ከአራት ሚሊዮን ስኩየር ማይልስ [10,359,952 ካሬ ሜትር] ያላነሰ ስፋት ያካለለ ነበር። በአፍሪካ የነበረው ነውጥ አውሮፓ ከሆነው ብዙም የሚተናነስ አልነበረም። አብዛኛው አልጀርስ ወደመ፤ ከሞሮኮ አጭር ርቀት ላይ የነበረ ስምንት ወይም አሥር ሺህ ሰዎች የያዘ አንድ መንደር ተሰለቀጠ። በስፔንና በአፍሪካ ዳርቻዎች መጠነ ሰፊ ማዕበል ከተሞችን በማጥለቅለቅ ከፍተኛ ውድመት አደረሰ። GCAmh 224.3
መናወጡ አስከፊ ማንነቱን በይበልጥ ያሳየው በስፔንና በፖርቹጋል ነበር። ካዲዝን ያጥለቀልቅ የነበረው ማዕበል ስድሳ ጫማ [18 ሜትር ያህል] ከፍታ ነበረው። ከታላላቆቹ የፖርቹጋል ተራሮች መካከል “ከስር መሰረታቸው የመነጨ በሚመስል ፈጣን መናወጥ የተመቱ ነበሩ። አንዳንዶቹ ከአናታቸው በመከፈት በሚደንቅ ሁኔታ የመሰንጠቅና የመቀደድ ትንግርት አስተናገዱ፤ በአቅራቢያው ወደነበረው ሸለቆም እየተገመሱ ተወረወሩ። ከእነዚህ ተራሮች የእሳት ነበልባል እንደነበረም ይነገራል።”-Sir Charles Lyel I, Principles of Geology, ገጽ 495። GCAmh 224.4
በሊዝበን “የነጎድጓድ ድምጽ በከርሰ ምድር ተሰማ፤ ወዲያውም በመቀጠል ከባድ መናወጥ የዚያች ከተማ አብዛኛውን ክፍል አወደመው። በስድስት ደቂቃ ያህል ስድሳ ሺህ ሰው ረገፈ። መጀመሪያ ውቅያኖሱ ወደ ኋላ ሸሽቶ ዳርቻው ደረቅ ሆነ፤ እንደገና እየተምዘገዘገ መጥቶ በፊት ከነበረው ሃምሳ ጫማ ወደ ላይ ጨመረ።” “በመዓቱ ጊዜ በሊዝበን ከተከሰተው ሁሉ አስገራሚው በከፍተኛ ወጪ በእብነበረድ የተሰራው ወደብ መንሸራተቱ ነበር። እየተደረማመሰ ከሚወድቀው ስብርባሪ ለማምለጥ ብዙ ሕዝብ ወደ ወደቡ መጥቶ ተሰብስቦ ነበር። ነገር ግን በድንገት ወደቡ የነበረውን ሰው በሙሉ እንደያዘ ወደ ታች ሰጠመ፤ ከሞተው ሰው ሁሉ አንድ ሬሳ እንኳ ወደ ላይ አልሰፈፈም።”-Ibid., ገጽ 495። GCAmh 224.5
የመሬት መንቀጥቀጥ ንውጠቱን “ወዲያውኑ ተከትሎ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያንና ገዳም፣ ሁሉም ትላልቅና የመንግሥት ህንፃዎች ማለት ይቻላል፣ እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶች አንድ አራተኛ የሚሆነው ወደመ። ይህ ከሆነ ከሁለት ሰዓታት በኋላ በተለያዩ አካባቢዎች የእሳት ቋያ ተነስቶ ለሶስት ቀን ያህል በኃይል ሲንቀለቀል ቆይቶ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ምድረ-በዳ አደረጋት። የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት በሰው በሚታጨቁበት በበዓል ቀን ነበርና ያመለጡት በእጣት የሚቆጠሩ ነበሩ።”-Encyclopedia Americana, art. “Lisbon,” note (ed. 1831)። “የሰዎች ፍርሃት ሊገለጽ ከሚችለው በላይ ነበር። ማንም አላነባም፤ ከእንባ ያለፈ ነበር። በድንጋጤና በግርምት ቃዥተው ወዲያ ወዲህ እየተራወጡ፣ ፊታቸውንና ደረታቸውን እየደቁ፦ “የምሕረት ያለህ! የዓለም መጨረሻ ነው!” እያሉ ይጮሁ ነበር። እናቶች ልጆቻቸውን እረስተው የስቅለት ስዕሎቻቸውን (ቅርፃ ቅርፆቻቸውን) በብዛት ተሸክመው ወጡ። በሚያሳዝን ሁኔታ ለመጠለል የወጡት ወደ አብያተ ክርስቲያናት ነበር። ቅዱስ ቁርባን በከንቱ ተገለጠ፤ እነዚህ ምስኪን ፍጡሮች መሰዊያውን በከንቱ አቀፉ፤ ቅርፃ ቅርፆቹ፣ ቀሳውስቱና ሕዝቡ በአንድ ላይ ተቀበሩ። በዚያ የጥፋት ቀን ዘጠና ሺህ ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።” GCAmh 225.1
ከሃያ አምስት አመት በኋላ፣ ቀጣይ እንደሚሆን በትንቢት የተጠቀሰው፣ የፀሐይና የጨረቃ መጨለም ምልክት ታየ። ይህንን የበለጠ የተለየ የሚያደርገው ደግሞ የመፈፀሚያው ዘመን በትክክል መጠቆሙ ነው። በደብረ ዘይት ተራራ ላይ አዳኙ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ውይይት ሲያደርግ፣ ስለ 1260 የጳጳሳዊ የስደት ዓመታት በመጥቀስ የመከራው ቀናት እንደሚያጥሩ ተስፋ ሰጥቶ፣ የቤተ ክርስቲያንን ረጅም የፈተና ጊዜ ካብራራ በኋላ፣ ምፅዓቱን የሚቀድሙ ክስተቶችን ጠቆመ። ከእነዚህም መካከል የመጀመሪያው መቼ እንደሚሆን ጊዜውን ወስኖ ተናገረ፦ “ በዚያን ወራት ግን ከዚያ መከራ በኋላ ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሐንዋን አትሰጥም” [ማር 13፦24]። 1260ዎቹ ቀናት ወይም ዓመታት 1798 ዓ.ም ላይ አልቀዋል። ከሩብ ምዕተ ዓመት ቀደም ብሎ ደግሞ ስደት ሙሉ ለሙሉ ወደ መቆሙ ተቃርቦ ነበር። እንደ ክርስቶስ አገላለጽ በእነዚህ ጊዜያት መካከል ፀሐይ ትጨልማለች። በግንቦት 19 ቀን 1780 ዓ.ም. ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። GCAmh 225.2
“እጅግ ምስጢራዊ በመሆን ተወዳዳሪ የለውም ሊባል የሚችል፣ አምሳያ የሌለው፣ ሊብራራ የማይችል ክስተት…. የተፈፀመው በግንቦት 19 ቀን 1780 ዓ.ም. የሆነው የጨለማ ቀን ነበር - ምክንያት ሊቀርብለት በማይችል ሁኔታ፣ ሙሉ ለሙሉ የሚታዩት ሰማያትና ጠፈር በሙሉ በኒው እንግላንድ የጨለሙበት ክስተት” ነበር።-R. M. Devens, Our First Century, ገጽ 89። ጽልመቱ ከግርዶሽ የተነሳ አለመሆኑ ማስረጃ ደግሞ በዚያን ጊዜ ጨረቃ ሙሉ ልትሆን ተቃርባ የነበረች መሆኑ ነው። ክስተቱ የተፈጠረው በደመና ወይም በአየሩ መዳጎስ አልነበረም፤ ምክንያቱም ጽልመቱ በደረሰባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ሰማዩ ጥርት ከማለቱ የተነሳ ከዋከብት ይታዩ ነበር። ሳይንስ ለዚህ ክስተት አጥጋቢ የሆነ መንስኤ አለ ብሎ ለመፈረጅ አለመቻሉን የህዋ ተመራማሪው ሄርሻል ሲናገር፦ “በሰሜን አሜሪካ የሆነው የጨለማ ቀን ፍልስፍና ሊያብራራው የማይችል ከተፈጥሮ ድንቅ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው” ብሎአል። GCAmh 225.3
“የጽልመቱ ደረጃም ለየት ያለ ነበር። በኒው እንግላንድ በምሥራቃዊ ጠርዝ አካባቢዎች ነበር የታየው፤ በምዕራብ አቅጣጫ ደግሞ የኮኔክቲከት እሩቅ ስፍራዎች፣ በአልባ፣ ኒው ዮርክ፤ በደቡብ አቅጣጫ የውቅያኖሱን ዳርቻ ተከትሎ፤ በሰሜን ደግሞ በአሜሪካ ሰው የሰፈረባቸውን ስፍራዎች በሙሉ ያካተተ ነበር። እነዚያን ዳርቻዎች አልፎ እሩቅ ስፍራዎችን አካቶም ይሆናል። ትክክለኛ ወሰኑ ግን ሊታወቅ አልቻለም። የቆየውን ጊዜ በተመለከተ፣ በቦስተን አካባቢዎች ቢያንስ ለአሥራ አራትና አሥራ አምስት ሰዓታት ቆይቷል።”-William Gordon, History of the Rise, Progress and establishment of the Independence of the U.S.A., vol. 3, ገጽ 57። GCAmh 226.1
“ጠዋቱ ግልጽና አስደሳች ነበር፤ ሆኖም ሁለት ሰዓት ገደማ ያልተለመደ ገጽታ ፀሐይ ላይ ታየ። ደመና አልነበረም፤ አየሩ ግን ጥቅጥቅ ያለ የጭስ መልክ የያዘ ነበር፤ የፀሐይ ነፀብራቅ የገረጣ ቢጫማ ቀለም የያዘ ነበር። ሆኖም እየጠቆረ ሄዶ በመጨረሻ ከአይን ተሰወረ።” “የእኩለ ሌሊት ጨለማ በእኩለ ቀን” ተከሰተ። GCAmh 226.2
“ሁኔታው ለዕልፍ አዕላፋት ድንጋጤና ጭንቀት አስከተለ፤ ለእንስሳትም ስጋትን ፈጠረ፤ ዶሮዎች ግራ በመጋባት ወደ ማደሪያቸው ተንጋጉ፤ ወፎችም ወደ ጎጆአቸው በረሩ። ከብቶችም ወደ በረታቸው ተመለሱ። ጓጉንቸሮችና የሌሊት ጭልፊቶች ዝማሬያቸውን ጀመሩ። አውራ ዶሮዎችም ልክ ሲነጋጋ እንደሚያደርጉት ሁሉ ጮሁ። ገበሬዎች በመስክ የሚያከናውኑትን ሥራ ለመተው ተገደዱ። የንግድ ሥራም በአብዛኛው ተዘግቶ፣ በመኖሪያ ስፍራዎች ሻማዎች ተለኮሱ። የኮኔክቲከት ሕግ አውጪ ምክር ቤት በዚያን ጊዜ በሃርትፎርድ ተሰብስቦ ነበር። ሥራውን መቀጠል ስላልቻለ ተቋርጦ ሁሉም ነገር የሌሊትን ጽልመት መልክ የያዘ ሆነ።” GCAmh 226.3
ፀሐይ ከመግባቱ ከአንድ ሁለት ሰዓት በፊት፣ ከባዱ የቀን ጨለማ በከፊል ንፁህ ሰማይ ተተካ፤ በጥቁር ከባድ ጭጋግ ብትሸፈንም ፀሐይዋ ታየች። ሆኖም “ይህ ጊዜ ጥቅጥቅ ያለ ግርዶሽን አስከተለ፤ የሌሊቱ የመጀመሪያ አጋማሽ አንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆነው ሕዝብ አይቶት የማያውቅ ደጎጎን ታየ። ከፀሐይ ግባት በኋላ እስከ እኩለ ሌሊት ከጨረቃም ሆነ ከክዋክብት ህዋውን አልፎ የመጣ አንድም የብርሐን ነፀብራቅ አልነበረም። ‘የጽልመት ጥቁርነት!’ በመባል ተሰየመ።” ሁኔታውን በአይን ያየ ሲናገር፦ “እያንዳንዱ [በዩኒቨርስ ያለ] ብርሐን ሰጪ አካል ሊበሳ በማይችል ጽልመት ቢሸፈን ወይም ወደ አለመኖር ቢመጣ ጨለማው ከዚያ የባሰ ሊሆን አይችልም ብዬ ለማሰብ ተገድጃለሁ።” አለ። በዚያ ሌሊት ጨረቃ ሙሉ የሆነች ቢሆንም “ሞት የሚመስለውን ጥላ ለመግፈፍ ግን በጭራሽ አልተቻላትም።” ከእኩለ ሌሊት በኋላ ጽልመቱ ተወገደ፤ ጨረቃዋ ለመጀመሪያ ጊዜ መታየት ስትችል ደም ትመስል ነበር።” GCAmh 226.4
ገጣሚው ዊቲየር ስለዚህ ትውስታው ስለማይጠፋ ቀን ሲናገር፦ GCAmh 226.5
“በአበባውና በፀደይ ጣፋጭ ሕይወት ላይ፣ በለምለሙ ምድር ላይ በቀትር ሰማይ ላይ፣ አስደንጋጭ ጥቅጥቅ ጨለማ ወደቀ። በሩቁና በጥንቱ በ1780 ዓ.ም በሜይ-ደይ ተከሰተ።”
“ወንዶች ፀለዩ፣ ሴቶች አለቀሱ፤ የጥፋት ቀን—ፍንዳታ መለከቱ ጥቁሩን ሰማይ እስኪበታትነው
ለመስማት የሁሉም ጆሮ ቆሞ ነበር።”
GCAmh 226.6
ግንቦት 19፣ 1780 ዓ.ም በታሪክ “የጨለማው ቀን” በመባል ይታወቃል። ከሙሴ ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ጥቅጥቅ ያለ፣ መጠኑንና የቆየበትን ጊዜ የሚስተካከል ጽልመት ተመዝግቦ አያውቅም። በታሪክ አዋቂውና በገጣሚው የተገለፀው ይህ ክስተት ከመፈፀሙ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ አመት በፊት በነብዩ ኢዮኤል የተመዘገቡትን የጌታን ቃላት የሚያስተጋባ ነው። “ታላቁ የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ይመለሳል፣ ጨረቃም ደም ይሆናል።” [ኢዮኤ 2÷31]። GCAmh 227.1
ሕዝቦቹ የመምጣቱን ምልክቶች እንዲጠብቁ፣ የሚመጣውን ንጉሳቸውን ምልክቶች ሲያዩም ሐሴት እንዲያደርጉ ክርስቶስ መክሮአቸዋል። “ይህም ሊሆን ሲጀምር” አለ፦ “ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሱ።” ወደሚያቆጠቁጡት የፀደይ ዛፎች ተከታዮቹን እያመላከተ፦ “ሲያቆጠቁጡ ተመልክታችሁ በጋ አሁን እንደቀረበ እራሳችሁ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ ደግሞ እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደቀረበች እወቁ።” [ሉቃስ 21÷28፣30፣31]። GCAmh 227.2
ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን የነበረው የመዋረድና የፍቅር መንፈስ ለኩራትና ለወግ ቦታ በመልቀቁ ለክርስቶስ የነበረው ፍቅርና በእርሱ መምጣት ላይ የነበረው እምነት ቀዝቅዞ ነበር። በዓለማዊነትና ተድላን በመሻት ተውጠው የእግዚአብሔር ለመሆናቸው የተመሰከረላቸው ሕዝቦቹ የመገለጡን ምልክቶች በተመለከተ አዳኙ ለሰጠው ትምህርት የታወሩ ነበሩ። የዳግም ምፅዓት አስተምህሮ ቸል ተብሎ ነበር። በአብዛኛው ትኩረት እስኪያጣና እስኪረሳ ድረስ ስለ መምጣቱ የሚገልፁት ጥቅሶች በተጣመመ ትርጉም ተጋርደው ነበር። ይህ ክስተት በተለይ በአሜሪካ አብያተ ክርስቲያናት የሚንፀባረቅ ነበር። በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚጣጣመው ነፃነትና ምቾት፣ ለሃብትና ለድሎት የነበረው ጠንካራ ጉጉት፣ ገንዘብ የመሥራትን ፅኑ ፍላጎት እየወለደ፣ ሁሉም ሊደርስበትና ሊጨብጠው የሚችል ይመስል ለነበረው ለዝነኛነትና ለስልጣን የነበረው ሽኩቻ፣ የፍላጎቶቻቸውና የተስፋዎቻቸው ማዕከል የዚህ ዓለም ነገሮች እንዲሆኑ ሰዎችን በመምራት፣ የአሁኑ የነገሮች አደረጃጀት ሲያልፍ የሚመጣውን ያንን ክቡር ቀን ግን ወደፊት በመግፋት ገና ያልደረሰ የሩቅ ዘመን ክስተት አደረጉት። GCAmh 227.3
አዳኙ ለተከታዮቹ ስለመመለሱ ምልክቶች ሲጠቁማቸው ልክ ዳግም ከመምጣቱ አስቀድሞ ሊሆን ስላለው ወደ ኋላ የመንሸራተት ክስተት ተናግሮአል። በኖህ ዘመን እንደነበረ የዓለም ንግድ እንቅስቃሴና ትርምስም እንዲሁም ደስታ ፍለጋ - መግዛት፣ መሸጥ፣ መትከል፣ መገንባት፣ ማግባት፣ መጋባት - እግዚአብሔርንና የወደፊቱን ሕይወት መርሳት ይሆናል። በዚህ ዘመን ለሚኖሩ ለእነርሱ የክርስቶስ ማስጠንቀቂያ ይህ ነው፦ “በነፍሳችሁ ግን ተጠንቀቁ በስስትም በስካርም እንዳይደነድን፣ ስለ ትዳርም በማሰብ ያም ቀን በድንገት እንዳይደርስባችሁ።” “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትፀልዩ ሁልጊዜ ትጉ።” [ሉቃስ 21÷34፣36]። GCAmh 227.4
በዚህ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የምትገኝበት ሁኔታ በአዳኙ ቃል በራዕይ ተጠቅሷል፦ “ሕያው እንደመሆንህ ስም አለህ ሞተህማል” [ራዕይ 3÷1፣3]። ከምን-ግዴ ደህንነታቸው ለመቀስቀስ አሻፈረኝ ላሉ ለእነርሱ ከባድ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል፦ “እንግዲያስ ባትነቃ እንደሌባ እመጣብሃለሁ፣ በማናቸውም ሰዓት እንድመጣብህ ከቶ አታውቅም።” [ራዕይ 3÷1፣3]። GCAmh 228.1
ሰዎች ለተጋረጠባቸው አደጋ ይነቁ ዘንድ አስፈላጊ ነበር፤ ከምሕረት ዘመን መዘጋት ጋር ለተያያዙ አስፈላጊ ክስተቶች ዝግጁ ይሆኑ ዘንድ እንዲነቁ መደረግ አለባቸው። የእግዚአብሔር ነብይ ሲናገር፦ “የእግዚአብሔርም ቀን ታላቅና እጅግም የሚያስፈራ ነውና ማንስ ይችለዋል?” ይላል [ኢዮኤ 2÷11]። “አይኖችህ ክፉ እንዳያዩ ንፁሃን ናቸው” [እንባቆም 1÷13] የተባለለት ሲገለጽ ማን መቆም ይችላል? “አምላክ ሆይ እኛ አወቅንህ” ብለው ለሚጩሁ ሆኖም ቃል ኪዳኑን ለጣሱ ፈጥነውም ሌላ አማልክት ለተከተሉ [ሆሴዕ 8÷2፣1፤ መዝ 16÷4]፤ አመጽን በልባቸው ደብቀው የኃጢአትን መንገድ ለሚወዱ፣ ለእነዚህ “የጌታ ቀን ብርሐን ሳይሆን ጨለማ አይደለምን? ፀዳል የሌለው ድቅድቅ ጨለማ ነው” [አሞጽ 5÷20]። “በዚያን ዘመን” አለ ጌታ፣ “የሩሳሌምን በመብራት እመረምራለሁ፤ በአተላቸውም ላይ የሚቀመጡትን በልባቸውም እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፣ ክፉም አያደርግም የሚሉትን እቀጣለሁ” [ሶፎን 1÷12]። “ዓለሙን ስለክፋታቸው፣ ክፉዎችንም ስለ በደላቸው እቀጣለሁ፤ የትዕቢተኞችንም ኩራት አዋርዳለሁ” [ኢሳ 13÷11]። “ብራቸውና ወርቃቸውም በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ሊያድናቸው አይችልም። ብልጥግናቸውም ለምርኮ ይሆናል፤ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ” [ሶፎን 1÷18፣13]። GCAmh 228.2
ነብዩ ኤርምያስ ይህንን አስፈሪ ቀን ወደፊት ሲመለከት፦ “በውስጤም ልቤ ታውኮብኛል ነፍሴ ሆይ የመለከትን ድምጽ የሰልፍን ውካታ ሰምተሻልና ዝም እል ዘንድ አልችልም።” “መከራ በመከራ ላይ ተጠርቶአል” [ኤር 4÷19፣20]። GCAmh 228.3
“ያ ቀን የመዓት ቀን የመከራና የጭንቀት ቀን፤ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፤ የጨለማና የጭጋግ ቀን፤ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፤ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን” [ሶፎን 1÷15፣16]። “እነሆ ምድሪቱን ባድማ ሊያደርግ ኃጢአተኞችዋንም ከእርስዋ ዘንድ ሊያጠፋ….የእግዚአብሔር ቀን ይመጣልና።” [ኢሳ 13÷9]። GCAmh 228.4
በዚያ ታላቅ ቀን እይታ ውስጥ ሆኖ ከመንፈሳዊ ልፍስፍስነታቸው ነቅተው፣ በንስሐና ራሳቸውን በማዋረድ ፊቱን እንዲፈልጉ የእግዚአብሔር ቃል በከበረና ግሩም በሆነ ቋንቋ ሕዝቦቹን ይጠራቸዋል፦ “የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና እርሱም ቀርቦአልና በጽዮን መለከት ንፉ፣ በቅዱሱም ተራራ ላይ እሪ በሉ፤ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ ይንቀጥቀጡ የእግዚአብሔር ቀን መጥቶአልና” “በጽዮን መለከት ንፉ፣ፆምንም ቀድሱ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሕዝቡን አከማቹ ማህበሩንም ቀድሱ፣ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፤ ህፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ….ሙሽራው ከእልፍኙ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ። የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናት ከወለሉና ከመሰውያው መካከል ያልቅሱ።” “አሁንስ ይላል እግዚአብሔር በፍጹም ልባችሁ፣ በጾምም በልቅሶና በዋይታ ወደኔ ተመለሱ። ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሃሪ ቁጣው የዘገየ ምህረቱም የበዛ ነውና….ወደ እርሱ ተመለሱ።” [ኢዮኤ 2÷1፤15-18፣ 12፣13]። GCAmh 228.5
በእግዚአብሔር ቀን መቆም የሚችል ሕዝብ ይዘጋጅ ዘንድ፣ ታላቅ የተሐድሶ ሥራ ይከናወን ዘንድ ነበረው። ብዙ የእርሱ [ነን ባይ] ሕዝቦቹ ለዘላለም የሚሆን [ህንፃ] እየገነቡ እንዳልሆነ እግዚአብሔር ተመለከተ፤ ከፍዘታቸው ይነቁ ዘንድ፣ ለሚመጣው ጌታቸው እንዲዘጋጁ ይመራቸው ዘንድ ከምህረቱ የተነሳ የማስጠንቀቂያ መልእክት ሊልክላቸው ነበር። GCAmh 229.1
ይህ ማስጠንቀቂያ በራዕይ 14 እንዲታይ ተደርጓል። ልክ “የምድሪቱን መከር ለማጨድ” [ራዕይ 14÷15] የሚመጣው የሰው ልጅ መገለጥ ክስተት ከመከናወኑ በፊት የሚነገረው፣ በሰማያዊ ፍጡራን እንደታወጀ ተደርጎ የተወከለው ሶስት እጥፍ መልእክት እዚህ ይገኛል። ከእነዚህ ማስጠንቀቂያዎች ውስጥ የመጀመሪያው እየቀረበ ያለውን ፍርድ ይለፍፋል። “በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር” ነብዩ ተመለከተ። “በታላቅ ድምጽም፦ የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባህርንም የውኃውንም ምንጮች ለሰራው ስገዱለት አለ።” [ራዕይ 14÷6፣7]። GCAmh 229.2
ይህ መልእክት፣ “የዘላለሙ ወንጌል” አካል ተደርጎ ታውጆአል። ወንጌሉን የመስበክ ሥራ ለመላእክት አልተሰጠም፤ በአደራ የተሰጠው ለሰው ልጆች ነው። ይህን ሥራ ይመሩ ዘንድ ቅዱሳን መላእክት ተመድበዋል። ለሰው ልጅ መዳን የሚደረጉትን ታላላቅ ንቅናቄዎች ይቆጣጠራሉ። ወንጌሉን የማወጁ ሥራ የሚከናወነው ግን በምድር በሚኖሩ በክርስቶስ አገልጋዮች አማካኝነት ነው። GCAmh 229.3
ለእግዚአብሔር መንፈስ ጉስጎሳና ለቃሉ ትምህርት ታዛዥ የነበሩ ታማኝ ሰዎች ይህንን ማስጠንቀቂያ ለዓለም ማወጅ ነበረባቸው። “ምድርም እስኪጠባ ድረስ የንጋትም ኮከብ እስኪወጣ ድረስ”፣ “ለፀና የትንቢት ቃል” ጆሮአቸውን ያዘነበሉ ሰዎች ነበሩ [2ኛ ጴጥ 1÷19]። ከተደበቀ እምቅ ኃብት ይልቅ እግዚአብሔርን ማወቅ ያስበለጡ ” በብርና በወርቅ” ከመነገድ ይልቅ [ምሳሌ 3÷14] የተሻለ አድርገው በመቁጠር እግዚአብሔርን የሚሹ ነበሩ። ጌታም የመንግሥቱን ታላላቅ ነገሮች ገለፀላቸው። “እግዚአብሔር ለሚፈሩት ኃይላቸው ነው፤ ቃል ኪዳኑንም ያስታውቃቸዋል።” [መዝ 25÷14]። GCAmh 229.4
የዚህ እውነት መረዳት የነበራቸውና ያንን እውነት በማወጅ ተግባር ላይም የተሰማሩት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ መሪዎች አልነበሩም። እነዚህ [መሪዎች] ታማኝ ጠባቆች ቢሆኑ፣ በትጋትና በፀሎት ውስጥ ሆነው መጽሐፍ ቅዱስን የሚመረምሩ ቢሆኑ ኖሮ፣ የሌሊቱን ሰዓት ባወቁት ነበር፤ በቅርብ ሊሆኑ ያላቸውን ክስተቶች ትንቢቶቹ ይገልጡላቸው ነበር። ይህንን ደረጃ ግን አልያዙም ነበርና መልእክቱ የተላለፈው በሌላ መደብ ነበር። የሱስ እንዲህ አለ፦ “ጨለማ እንዳይደርስባችሁ ብርሐን ሳለላችሁ ተመላለሱ” [ዮሐ 12÷25]። እግዚአብሔር ከሰጠው ብርሐን ራሳቸውን የሚያገሉ፣ ወይም ሊደርሱበት በሚችሉበት ደረጃ ሆነው ሳለ ቸል የሚሉት እነርሱ በጨለማ ውስጥ ይተዋሉ። አዳኙ ግን እንዲህ አለ፣ “የሚከተለኝ የሕይወት ብርሐን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” [ዮሐ 8÷12]። የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ብቻ አላማዬ ያለ፣ ለተሰጠውም ብርሐን በትጋት ትኩረት የሚሰጥ እርሱ ታላቅ ብርሐን ይቀበላል። ወደ እውነት ሁሉ ይመራው ዘንድ፣ ለዚያ ነፍስ፣ ባለሰማያዊ ነፀብራቅ ኮከብ ይላክለታል። GCAmh 229.5
በክርስቶስ የመጀመሪያ ምፅዓት ጊዜ የእግዚአብሔር መዛግብት በአደራ የተሰጣቸው የቅድስትዋ ከተማ ካህናትና ፃፎች የዘመኑን ምልክቶች ሊረዱና የተስፋውን ልጅ [የየሱስን] መምጣት ሊያውጁ ይችሉ ነበር። የሚወለድበትን ቦታ (የትውልድ ስፍራውን) የሚክያስ ትንቢት ጠቁሞ ነበር [ሚክ 5÷2]። ዳንኤል የሚመጣበትን ዘመን ለይቶ አስቀምጧል [ዳን 9÷25]። እነዚህን ትንቢቶች እግዚአብሔር ለአይሁድ መሪዎች በኃላፊነት ሰጥቶ ነበር። የመሲሁ መምጣት በደጅ እንደሆነ ባያውቁና ለሕዝቡም ባይናገሩ የሚያላክኩበት ሰበብ አልነበራቸውም። ድንቁርናቸው በኃጢአት የተሞላ ቸልተኝነታቸው ውጤት ነበር። አይሁዳዊያን፣ ለምድር ታላላቅ ሰዎች የተለየ ትኩረት በመስጠታቸው ለሰይጣን ባርያዎች ክብር እየለገሱ፣ ለተሰዉት የእግዚአብሔር ነብያት ደግሞ ኃውልቶች ይገነቡ ነበር። በሰዎች መካከል በነበራቸው የደረጃና የስልጣን ፅኑ ፍላጎት ተውጠው ሲነታረኩ በሰማይ ንጉሥ የተሰጣቸውን መለኮታዊ ክብር ማየት ተሳናቸው። GCAmh 230.1
የእሥራኤል ሽማግሌዎች፣ በከበረና ጥልቅ በሆነ ፍላጎት በዓለም ታሪክ ተወዳዳሪ የሌለውን የሰውን ልጅ የማዳን ሥራ ሊፈጽም የሚመጣውን የእግዚአብሔርን ልጅ መገለጥ ክስተት፣ ቦታውን፣ ጊዜውንና ሁኔታውን በአንክሮ ማጥናት ነበረባቸው። የዓለምን አዳኝ እንኳን መጣህ ከሚሉት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች መካከል ይሆን ዘንድ ሕዝቡ በጥንቃቄ መከታተልና መጠበቅ ነበረበት። ነገር ግን እነሆ ከናዝሬት ኮረብታማ ስፍራ የመጡ ሁለት በመንገድ የዛሉ መንገደኞች ጠባቡን መንገድ ይዘው እስከ ምሥራቃዊ የከተማ ዳርቻ ድረስ ማደሪያ ፍለጋ ቢንከራተቱም አላገኙም። ይቀበላቸው ዘንድ የተከፈተ በር አልነበረም። በመጨረሻ ለከብቶች ማደሪያ በተዘጋጀ ደሳሳ ጎጆ መጠጊያ አገኙ። በዚያም የዓለም አዳኝ ተወለደ። GCAmh 230.2
ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የእግዚአብሔር ልጅ ከአባቱ ጋር የሚጋራውን ክብር ሰማያዊ መላዕክት አይተዋል። እናም ለሁሉም ሕዝቦች ተወዳዳሪ የሌለው ደስታ እንደሚፈጥር አድርገው፣ በምድር ላይ መገለጡን በጥልቅ ፍላጎት ወደፊት ይጠብቁት ነበር። ሊቀበሉት ለተዘጋጁ፣ የምድር ነዋሪዎችም ያውቁት ዘንድ ዜናውን በደስታ ለሚያሰራጩት ሰዎች የምሥራቹን የማብሰር ሥራ ለመላዕክት ተሰጥቶ ነበር። ክርስቶስ የሰውን ተፈጥሮ ሊወስድ ራሱን ዝቅ አድርጎ ነበር። ነፍሱን ለኃጢአት መስዋዕት አድርጎ ሲያቀርብ መጠን የለሽ የመከራ ጭነት ይሸከም ዘንድ ነበረው፤ ያም ሆኖ ግን በዚህ ውርደት ውስጥ እንኳ ቢሆን የልዑል ልጅ በሰው ልጆች ፊት ሲገለጥ ባህርይውን በሚመጥን ማዕረግና ክብር እንዲሆን የመላዕክት ጠንካራ ፍላጎት ነበር። መምጣቱን ይቀበሉ ዘንድ የምድር ኃያላን በእሥራኤል መዲና ይሰበሰቡ ይሆን? የመላዕክት ጭፍሮች ለሚጠብቀው ሕዝብ ህፃኑን ያስረክቡ ይሆን? GCAmh 230.3
የሱስን እንኳን ደህና መጣህ ለማለት የተዘጋጄ እንዳለ ለማየት አንድ መልአክ ምድርን አሰሰ። የመጠባበቅ ምልክት ግን ማየት አልተቻለውም። የመሲሁ መምጣት ዘመን በደጅ እንደሆነ የሚገለጽ፣ የምስጋናና የድል ዝማሬ መስማት አልቻለም። የመለኮት መገኘት ለዘመናት በተገለፀባት፣ በተመረጠችው ከተማና ቤተ መቅደስ ላይ መልአኩ ለተወሰነ ጊዜ አንዣበበ። ሆኖም በዚህ ቦታ እንኳ ያው ተመሣሣይ ቸልተኝነት ነበር። ካህናት በኩራትና በትዕቢት ተኮፍሰው የረከሰ መስዋዕት በማቅረብ ላይ ነበሩ። ፈሪሳዊያን በታላቅ ድምጽ ለሕዝቡ እየተናገሩ፣ ወይም በመንገዶቹ ጠርዝ የጉራ ፀሎታቸውን በመፀለይ ላይ ነበሩ። በቤተ-ነገሥታት፣ በፈላስፋዎች ጉባኤ፣ በራቢዎች ትምህርት ቤቶች፣ ሁሉም በተመሣሣይ ሆኔታ፣ ሰማይን ሁሉ በደስታና በምስጋና የሞላውን፣ በምድር ላይ ሊገለጥ ያለውን የሰው ልጆችን ነፃ አውጪ አስገራሚ እውነት ፈጽሞ ዘንግተውታል። GCAmh 230.4
ክርስቶስ ይመጣል ተብሎ እየተጠበቀ እንደሆነ የሚያስረዳ ምንም ፍንጭ የለም፤ ለሕይወት ልዑል ምንም ዝግጅት አልተደረገም። ሰማያዊው መልዕክተኛ በመደነቅ ተሞልቶ አሳፋሪውን ዜና ይዞ ወደ ሰማይ ሊሄድ ሲል በሌሊት መንጎቻቸውን የሚጠብቁ እረኞች፣ ከዋክብት ወደተሞሉ ሰማያት አንጋጠው ወደ ምድር የሚመጣውን መሲህ ትንቢት እያሰላሰሉ የዓለም አዳኝ የሚገለጥበትን ጊዜ ሲናፍቁ ተመለከተ። ሰማያዊውን መልእክት ለመቀበል የተዘጋጀ አካል እዚህ ተገኘ። ታላቁን ደስታ እያበሰረ የጌታ መልአክ በድንገት ተገለጠ። ሰማያዊ ክብር መስኩን እንዳለ አጥለቀለቀው፤ ለመቁጠር የሚያዳግት የመላዕክት ሰራዊት ተገለጠ፤ ይህንን ያህል ደስታ አንድ መልአክ ከሰማይ ብቻውን ይዞ መምጣት የማይቻለው በሚመስል ሁኔታ፣ አንድ ቀን የዳኑ ሕዝቦች የሚዘምሩትን “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” [ሉቃስ 2÷14] የሚለውን መዝሙር አዕላፋት ድምፆች በአንድ ላይ አስተጋቡ። GCAmh 231.1
ኦ! ይህ የቤተልሔም አስደናቂ ታሪክ ምን አይነት ትምህርት ነው! አለማመናችን፣ ኩራታችንና አንዳች-አይጎድለኝም ባይነታችንን እንዴት አድርጎ ይወቅሳል! በሚያስከስሰው ቸልተኝነታችን፣ የዘመኑን ምልክቶች ማወቅ ተስኖን የመጎብኘታችን ቀን ሳናውቀው እንዳንቀር፣ ጥንቁቅ እንድንሆን እንዴት አድርጎ እጅግ ያሳስበናል! GCAmh 231.2
መላዕክት የመሲሁን መምጣት የሚጠብቁ ሰዎችን ያገኙት በይሁዳ ኮረብታዎች፣ በምስኪን እረኞች መካከል ብቻ አልነበረም። በአሕዛብ መካከልም እርሱን የሚጠብቁ ነበሩ፤ የጥበብ ሰዎች፣ ሃብታሞችና የተከበሩ፣ የምሥራቅ ፈላስፋዎች ነበሩ። የተፈጥሮ ተማሪዎቹ ሰብዓ ሰገሎች (ማጅዎች) እግዚአብሔርን በእጅ ሥራው አይተውት ነበር። ከያዕቆብ የሚወጣውን ኮከብ ከዕብራውያን መጽሐፍ ቅዱሳት ተምረው “የእሥራኤል መጽናናት” ብቻ ሳይሆን “ለአሕዛብ ሁሉ የሚገለጥ ብርሐን”፣ “እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን” [ሉቃስ 2÷25፣ 32፤ የሐዋ ሥራ 13÷47] የሚመጣውን፣ የእርሱን መገለጥ በጽኑ ፍላጎት ይጠብቁ ነበር። ብርሐን ፈላጊዎች ነበሩ፤ ከእግዚአብሔር ዙፋን የወጣ ብርሐን ለእግራቸው መብራት ሆነ። እውነትን እንዲጠብቁና እንዲያብራሩ የተወከሉት የየሩሳሌም ካህናትና የአይሁድ መምህራን በጽልመት ተውጠው ሳለ፣ እነዚህን አሕዛብ እንግዶች የሰማይ-ልዑክ ኮከብ ወደ ተወለደው ንጉሥ የትውልድ ቦታ መራቸው። GCAmh 231.3
ክርስቶስ “ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት” የሚገለጥላቸው “ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት” ነው [ዕብ 9÷28]። የሁለተኛው ምፅዓት መልእክት እንደ አዳኙ የመወለድ ዜና ለኃይማኖት መሪዎች አደራ አልተሰጠም። እነርሱ ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ቁርኝት አስጠብቀው ማስቀጠል አልቻሉም። ከሰማይ የመጣውን ብርሐን አሻፈረኝ ብለዋል፤ ስለዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ ከገለፃቸው ቁጥር ውስጥ አልተካተቱም። “እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ ቀኑ እንደ ሌባ ይደርስባችሁ ዘንድ በጨለማ አይደላችሁም። ሁላችሁ የብርሐን ልጆች የቀንም ልጆች ናችሁና። እኛ ከሌሊት ወይም ከጨለማ አይደለንም።” [1ኛ ተሰሎ 5÷4፣5]። GCAmh 231.4
የጽዮን ቅጥር ጠባቂዎች የአዳኙን መምጣት የምሥራች በመቀበል የመጀመሪያዎቹ መሆን ነበረባቸው። ምፅዓቱ እንደቀረበ ድምጻቸውን አንስተው የሚያስተጋቡ የመጀመሪያዎቹ፣ ለመምጣቱም ይዘጋጁ ዘንድ ሕዝቡን በማስጠንቀቅ ቀዳሚዎቹ ሊሆኑ ይገባ ነበር። ሕዝቡ በኃጢአት ውስጥ አንቀላፍቶ እያለ እነርሱ ዘና ብለው ሰላምና ደህንነት ያልሙ ነበር። የሱስ፣ ቤተ ክርስቲያኑ በአስመሳይ ቅጠል ተጀቡና ወርቃማ ፍሬ ግን እንዳልነበራት እንደ መካንዋ የበለስ ዛፍ ሆና ተመለከታት። የኃይማኖት ወግና ሥርዓት በኩራት ሲጠበቅ ሳለ፣ አንድን አገልግሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያደርገው የእውነተኛ ትህትና፣ የታጋሽነትና የእምነት መንፈስ ግን አልነበረም። ከመንፈስ ቅዱስ ፀጋዎች ይልቅ ኩራት፣ ወግ አጥባቂነት፣ ግብዝነት፣ ራስ ወዳድነትና ጭቆና ይንፀባረቁ ነበር። ወደኋላ ይንሸራተቱ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ለዘመኑ ምልክቶች ዓይናቸውን ጨፈኑ። እግዚአብሔር አልጣላቸውም፤ ታማኝነቱም ይሸረሸር ዘንድ አልፈቀደም። ሆኖም እነርሱ ከእርሱ ተለዩ፤ ከፍቅሩም ራሳቸውን ነጠሉ። ቅደመ ሁኔታዎቹን ለማሟላት አሻፈረኝ ሲሉ ተስፋዎቹ ሳይፈፀሙላቸው ቀሩ። GCAmh 232.1
እግዚአብሔር የሚሰጠውን ዕድልና ብርሐን ለማሳደግና ዋጋ ለመስጠት ቸል ማለት የሚያመጣው እርግጠኛ ውጤት ይህ ነው። ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውን ዕድል (አቅርቦት) በመጠቀም እያንዳንዱን የብርሐን ጮራ ተቀብላ፣ የሚገለፀውን እያንዳንዱን ኃላፊነት ካላከናወነች በስተቀር ኃይማኖት ቀስ በቀስ ወደ ወግና ሥርዓት መጠበቅ ማሽቆልቆሉ አይቀሬ ነው፤ እጅግ አስፈላጊው እግዚአብሔርን የመምሰል መንፈስም ይጠፋል። የዚህ እውነትነት ደግሞ በቤተ ክርስቲያንዋ ታሪክ በተደጋጋሚ ተረጋግጧል። እንደተሰጡት በረከቶችና እድሎች መጠን እግዚአብሔር ከሕዝቦቹ የእምነት ሥራንና መታዘዝን ይፈልጋል። መታዘዝ መስዋዕትነትን ይጠይቃል፤ መስቀልንም ያካትታል። የክርስቶስ ታማኝ ተከታይ ነን የሚሉ በርካቶች ከሰማይ የመጣውን ብርሐን ያልተቀበሉት፣ እንደ ጥንታዊ አይሁዳዊያንም የመጎብኘታቸውን ወራት ያላወቁት በዚህ ምክንያት ነበር [ሉቃስ 19÷44]። በኩራታቸውና ባለማመናቸው ምክንያት እግዚአብሔር ባጠገባቸው አለፋቸው፣ ለተቀበሉት ብርሐን ሁሉ ጀሮ ለሚሰጡ እንደ ቤተልሄም እረኞችና የምሥራቅ ማጂዎች ላሉት፣ ለእነርሱ እውነቱን ገለፀ። GCAmh 232.2