ታላቁ ተጋድሎ

19/45

ምዕራፍ ፲፮—የኃይማኖት መንገደኞቹ አባቶች

የእንግሊዝ ተሐድሶ አድራጊዎች፣ የሮማዊነትን አስተምህሮ የተዉ ቢሆንም ብዙ መልኮቹን ግን እንደያዙአቸው ነበር። ስለሆነም የሮም ስልጣንና እምነት ተቀባይነት ቢያጣም ጥቂት የማይባሉ ልማዶችዋና ክብረ በዓላቶችዋ ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ ሥርዓት ጋር ተዋህደው ነበር። እነዚህ ጉዳዮች የህሊና ጉዳይ አይደሉም፤ ይደረጉ ዘንድ በመጽሐፍ ቅዱስ ያልታዘዙ ብሎም አስፈላጊ ናቸው የሚባሉ ባይሆኑም ያልተከለከሉ በመሆናቸው በውስጠ-ባህርያቸው ኃጢአት አይደሉም ይባል ነበር። እነዚህን ልማዶች ማክበር የተሐድሶዋ ቤተ ክርስቲያን ከሮም ጋር የለያትን ሰላጤ ለማጥበብ የሚረዳ ሲሆን፣ ሮማዊያን የፕሮቴስታንት እምነትን እንዲቀበሉ ያበረታታል በማለት ግፊት ይደረግበት ነበር። GCAmh 213.1

በጥንቱ ወግ ለሚፀኑትና የግልግል ሃሳብን ለሚያቀበሉ፣ እነዚህ መከራከሪያዎች እውነት መሰሉአቸው። ይህንን እይታ ያልተቀበለ ሌላ መደብ ግን ነበር። እነዚህ ልማዶች በሮምና በተሐድሶው መካከል ባለው ክፍተት እንደ ድልድይ ሆነው ማገልገላቸው ራሱ ሊወገዱ እንደሚገባቸው የሚያረጋግጥ በቂ ምክንያት ነው ብለው የሚያምኑ ነበሩ። አርነት የወጡባቸው፣ ሊመለሱባቸውም ፍፁም ፍላጎት የሌላቸው የባርነት አርማዎች እንደሆኑ አድርገው ቆጠሩአቸው። ምክንያት ሲያቀርቡም አምልኮ እንዴት መሆን እንዳለበት እግዚአብሔር በቃሉ የደነገገው በመሆኑ ሰዎች የመጨመርም ሆነ የመቀነስ መብት እንዳልተሰጣቸው ተናገሩ። የታላቁ ክህደት መጀመሪያ ድርጊት የቤተ ክርስቲያን ስልጣን የእግዚአብሔር ስልጣን ማሟያ ለማድረግ የተሞከረበት ሂደት ነበር። ሮም እግዚአብሔር ያልከለከለው ነገር እንዲደረግ በማዘዝ ጀመረች፣ ይተገበር ዘንድ በግልጽ ያዘዘውን በመከልከል ጨረሰች። GCAmh 213.2

ብዙዎች በንጽህናውና ያልተወሳሰበ በመሆን ወደሚታወቀው ወደ ጥንቱ ቤተ ክርስቲያን የመመለስ ልባዊ ፍላጎት ነበራቸው። መሰረት የጣሉትን ብዙዎቹን የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ልማዶች እንደ ጣዖት አምልኮ መታሰቢያ ኃውልት በመቁጠር በአምልኮዋ ይተባበሩ ዘንድ ህሊናቸው አልፈቀደላቸውም። በመንግሥት ኃይል የምትደገፈው ቤተ ክርስቲያን ግን በሥርዓትዋ ላይ ተቃውሞ የሚያስነሱትን በዝምታ ታልፋቸው ዘንድ አልተቻላትም። በአምልኮዋ ጊዜ መገኘት የሕግ አስገዳጅነት ነበረው፤ ፈቃድ ያልተሰጠው ኃይማኖታዊ ስብሰባም እስር፣ ስደትና ሞት የሚያስከትል ነበር። GCAmh 213.3

በአሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ወደ ስልጣን የመጣው ንጉሠ ነገሥት፣ ፒዩሪታኖች (የእንግሊዝ ፕሮቴስታንቶች) “እንዲስማሙ፣ ወይም ከምድሪቱ እንደሚያባርራቸው ያለዚያም የከፋ ነገር” እንደሚገጥማቸው በቁርጠኝነት አወጀ። -George Bancroft, History of the United States of America, pt. 1, ch. 12, par. 6። እየታደኑ፣ እየተሳደዱና እየታሰሩ፣ ወደፊት የተሻሉ ቀናት ይመጣሉ የሚል ተስፋ ሊኖራቸው አልቻለም፤ አዕምሯቸው እንደመራቸው እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ለሚሹ ሁሉ “እንግሊዝ መኖሪያቸው ከመሆን ለዘላለም ቀርታለች” የሚለው ሃሳብ ብዙዎቹን አሸነፋቸው።-J. G. Palfrey, History of New England, ch. 3, par. 43። በስተመጨረሻ አንዳንዶቹ በሆላንድ መጠጊያ ለመሻት ወሰኑ። ችግሮች፣ ማጣትና እሥራት ገጠማቸው። አላማቸው ተሰናክሎ በጠላቶቻቸው እጅ ተላልፈው ተሰጡ። ሆኖም የማይወዛወዝ ጽናት በስተመጨረሻ አሸናፊ ሆነ፤ በሰላማዊ የደች ሪፐብሊክ ዳርቻዎች መጠለያ አገኙ። GCAmh 213.4

ሲሰደዱ፣ ቤቶቻቸውን፣ ቁሳቁሶቻቸውንና ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ትተው ወጡ። የተለየ ቋንቋና ባህል ባለው ሕዝብ መካከል በእንግዳ አገር ወዘ-ልውጦች ነበሩ። ዳቦ ማግኘት ይችሉ ዘንድ አዳዲስና ያልተፈተኑ ሙያዎችን መሞከር ተገደው ነበር። እድሜያቸውን ሙሉ መሬት ሲያርሱ የኖሩ ጎልማሶች አሁን ሜካኒካዊ ንግድ መማር ነበረባቸው። ነገር ግን ለስንፍናና ለማማረር ጊዜ ሳይሰጡ ሁኔታውን በፀጋ ተቀበሉት። ሁልጊዜ በድህነት ቢቆነጠጡም እግዚአብሔር ለሰጣቸው በረከቶች አመስጋኞች ነበሩ፤ በማይረበሸው መንፈሳዊ አምልኮአቸውም ደስታ ያገኙ ነበር። “የኃይማኖት ተጓዦች መሆናቸውን ያውቁ ነበር፤ በእነዚያ ነገሮች ላይ ልባቸውን መጣል ትተው ዓይናቸውን ወደ ውድዋ አገራቸው ወደ ሰማይ በማንሳት መንፈሳቸውን ያረጋጉ ነበር።”-Bancroft, pt. 1, ch. 12, par, 15። GCAmh 214.1

በስደትና በመከራ ውስጥ ሆነው ፍቅራቸውና እምነታቸው ጠነከረ። የእግዚአብሔርን ተስፋዎች አመኑ፤ በሚያስፈልጋቸውም ጊዜ አላሳፈራቸውም፤ ያግዟቸውና ያበረታቱዋቸው ዘንድ መልአክቱ ከጎናቸው ነበሩ። የእግዚአብሔር እጅም ከባህር ባሻገር የሚጠቁማቸው ሲመስል፣ ለራሳቸው አገር ወደሚያገኙበት፣ ለልጆቻቸውም ውድ የሆነውን የኃይማኖት ነፃነት ውርስ ትተው የሚያልፉበት አገር ሲጠቁማቸው፣ መለኮት ባቀረበው መንገድ ሳይሸማቀቁ ወደፊት ገሰገሱ። GCAmh 214.2

በእነርሱ ላይ ያለው ታላቅ አላማው ይፈፀም ዘንድ፣ ሊያዘጋጃቸው በሕዝቦቹ ላይ ፈተና ይመጣባቸው ዘንድ እግዚአብሔር ፈቀደ። ከፍ ከፍ ትደረግ ዘንድ ቤተ ክርስቲያንዋ ዝቅ አለች። በእርሱ የሚያምኑትን ፈጽሞ የማይጥል እንደሆነ ዓለም እንደገና ሌላ መረጃ ይሆነው ዘንድ ስለ እርስዋ እግዚአብሔር ኃይሉን ሊያሳይ ተቃርቦ ነበር። የሰይጣን ቁጣና የክፉ ሰዎች ሴራ ክብሩን ያሰፉ ዘንድ፣ ሕዝቦቹንም አደጋ ወደሌለበት ስፍራ ያመጡ ዘንድ እግዚአብሔር ክስተቶችን ገለበጠ። እንግልትና ስደት ለነፃነት በር እየከፈቱ ነበር። GCAmh 214.3

ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን እንዲለያዩ መጀመሪያ ሲገደዱ ፒዩሪታውያኖቹ እንደ እግዚአብሔር ነፃ ሕዝብ “ያወቋቸውን ወይም ወደፊት የሚያውቋቸውን መንገዶቹን ሁሉ ጠብቀው ይራመዱ ዘንድ”-J. Brown, The Pilgrim Fathers, ገጽ 74። ራሳቸውን በቃል ኪዳን አስተሳስረው ነበር። የተሐድሶ ትክክለኛ መንፈስ፣ የፕሮቴስታንትም አስፈላጊው መርህ ይህ ነበር። በአዲሱ ዓለም መጠለያ ያገኙ ዘንድ የኃይማኖት ስደተኞቹ ይህንን አላማ አንግበው ከሆላንድ ለቀቁ። በመልካም ምሪት አብሮአቸው እንዳይሄድ የተከለከለው ፓስተራቸው ጆን ሮቢንሰን ለስደተኞች የደህና ሁኑ ንግግር ሲያደርግ፦ GCAmh 214.4

“ወንድሞች ሆይ አሁን ልንለያይ ነው፤ እንደገና ፊታችሁን ለማየት በሕይወት እኖር እንደሆነ የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው። ጌታ ያ እንዲሆን አቅዶ ቢሆንም ባይሆንም ግን እኔ ክርስቶስን ከተከተልኩት ሳትርቁ እንድትከተሉኝ በእግዚአብሔርና በመልአክቱ ፊት እለምናችኋለሁ። እግዚአብሔር በራሱ መሳሪያ አንዳች ነገር ሊገልጥላችሁ ቢፈልግ በእኔ አገልግሎት እንደተቀበላችሁት እውነት እርሱንም (የሚገልጥላችሁን ነገር) ለመቀበል ዝግጁ ሁኑ፤ ጌታ ይገልጥላችሁ ዘንድ ያለው ተጨማሪ እውነትና ብርሐን እንዳለው በጣም እርግጠኛ ነኝ።-Martyn, vol. 5, ገጽ 70። በኃይማኖት መራመድ ስላቆሙት፣ ከተሐድሶ አድራጊዎች አልፈው መሄድ ስላልቻሉት አብያተ ክርስቲያናት ሁኔታ ያለኝን ጥልቅ ሃዘን ልገልጽላችሁ አልችልም። ሉተራዊያን ሉተር ካየው በቀር ወደፊት ሊራመዱ አልቻሉም። አያችሁ፣ ካልቪኒስቶችም ያ ሁሉም ያልተገለጠለት ታላቅ የእምነት ሰው ትቶ ካለፈበት ላይ ቆመው ቀርተዋል። ይህ እጅግ የሚታዘንበት ሰቆቃ ነው። ምክንያቱም በጊዜያቸው የሚንቀለቀሉና የሚያንፀባርቁ ብርሃናት የነበሩ ቢሆንም ወደ ሁሉም የእግዚአብሔር ምክር ግን ዘልቀው አልደረሱም፤ አሁን በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ ግን ልክ መጀመሪያ እንደተቀበሉት ሁሉ ተጨማሪ ብርሐን ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆኑ ነበር።-D. Neal, History of the Puritans, vol. 1, ገጽ 269። GCAmh 214.5

“በታወቀውና ሊታወቅ ባለው፣ በእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ትራመዱ ዘንድ የተስማማችሁበትን የቤተ ክርስቲያናችሁን ቃል ኪዳን አስታውሱ። ታውቁት ዘንድ ከተፃፈው ቃሉ የሚመጣውን ማንኛውንም ብርሐንና እውነት ልትቀበሉ ለእግዚአብሔርና ለእርስ በርሳችሁ የገባችሁትን የተስፋ ቃል ኪዳን አስታውሱ። ነገር ግን እለምናችኋለሁ እውነት ብላችሁ ስለምተቀበሉት ነገር ተጠንቀቁ። መርምሩት፣ አሰላስሉት፣ ከመቀበላችሁ በፊት ከሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር አመሳክሩት፤ የክርስትና ዓለም ገና በቅርቡ ጥቅጥቅ ካለው፣ የክርስቲያን ተቃዋሚ ከሆነው ጨለማ ወጥቶ በአንድ ጊዜ የእውቀት ፍጽምና ሊያመጣ የሚችል አይደለምና ነው።”-Martyn, vol. 5, ገጽ 70, 71። GCAmh 215.1

ረጅሙን አደገኛ የባህር ላይ ጉዞ እንዲያደርጉ ያጀገናቸው፣ የበረሃውን አደጋና እንግልት እንዲቋቋሙ፣ ብሎም በእግዚአብሔር እርዳታ የታላቅ አገርን መሰረት በአሜሪካ ዳርቻዎች እንዲጥሉ የእምነት መንገደኞቹን ያነሳሳቸው ለህሊና ነፃነት የነበራቸው ጥማት ነበር። ታማኞችና ፈሪሃ-እግዚአብሔር የነበራቸው ቢሆኑም እነዚህ የእምነት መንገደኞች ታላቁ የኃይማኖት መቻቻል መርህ በውል አልገባቸውም ነበር። ለራሳቸው ያገኙት ዘንድ እጅግ መስዋዕት የከፈሉበትን ነፃነት ለሌሎች በእኩል ለመለገስ ዝግጁዎች አልነበሩም። “በአሥራ ሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ ሊቆችና የስነ-ምግባር ምሁራን ጭምር፣ የሰብአዊ ፍጡር እምነት ብቸኛ ፈራጅ እግዚአብሔር እንደሆነ እውቅና የሚሰጠውን ከአዲስ ኪዳን የሚያድገውን ታላቅ መርህ በውል የተረዱት እጅግ ጥቂቶቹ ነበሩ።”-Ibid., vol. 5, ገጽ 297። የሰዎችን አዕምሮ ትቆጣጠር ዘንድ፣ ኑፋቄ ምን እንደሆነ ለማብራራትና ቅጣትም ለመበየን ትችል ዘንድ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን መብት ሰጥቷል የሚለው አስተምህሮ እጅግ ስር ከሰደዱት የጳጳሳዊው ሥርዓት ስህተቶች አንዱ ነበር። ተሐድሶ አራማጆቹ የሮምን አስተምህሮ ባይቀበሉም ከአለመቻቻል መንፈስዋ ግን ሙሉ ለሙሉ የተላቀቁ አልነበሩም። ለረጅም ዘመን በዘለቀው አገዛዝዋ፣ መላውን የክርስትና ዓለም በደጎጎን ሸፍኖ የኖረበት የጳጳሳዊው ሥርዓት ጽልመት እንኳ ገና ሙሉ ለሙሉ አልተገፈፈም ነበር። በማሳቹሴትስ ባህር ዳርቻ መንደር ውስጥ ከነበሩት ዋና አገልጋዮች አንዱ ሲናገር፦ “ዓለምን የክርስቲያን ተቃዋሚ ያደረገው መቻቻል ነበር፤ መናፍቃንን በመቅጣትዋም ቤተ ክርስቲያን አልተጎዳችም።”-Ibid., vol. 5, ገጽ 335። በመንግሥታዊ አስተዳደር ውስጥ ድምጽ የሚኖራቸው የቤተ ክርስቲያን አባላት ብቻ እንደሆኑ ቅኝ ገዥዎች ደንግገው ነበር። የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር (ካህናትን) ለመደገፍ ሁሉም ሰዎች እንዲያዋጡ የሚገደዱበት፣ አጥቢያ ፈራጆችም ኑፋቄን የሚጨቁኑበት ስልጣን የተሰጠበት መንግሥታዊ መሰል ቤተ ክርስቲያን ተቋቁሞ ነበር። ስለዚህም መንግሥታዊ ስልጣኑ በቤተ ክርስቲያን እጅ ነበር። አነዚህ እርምጃዎች ወደማይቀረው ውጤት — ወደ ስደት - ያመሩት ብዙም ሳይቆይ ነበር። GCAmh 215.2

የመጀመሪያው መንደር ከተቋቋመ ከአሥራ አንድ አመት በኋላ ሮጀር ዊሊያምስ ወደ አዲሱ ዓለም መጣ። እንደ ቀደምቶቹ የኃይማኖት ተጓዞች ኃይማኖታዊ ነፃነትን ሊቀምስ መጣ፤ ሆኖም ከሌሎቹ በተለየ፣ በጊዜው የነበሩ ማየት ያልቻሉትን ተመለከተ። ኃይማኖታቸው የትኛውም አይነት ቢሆን፣ ይህ ነፃነት ሊወሰድ የማይችል የሁሉም መብት እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ከእግዚአብሔር ቃል የሚመጣው ብርሐን ሁሉ ተገልጦ ያለቀ ሊሆን አይችልም የሚለውን የሮቢንሰንን አቋም በመያዝ እውነትን በቅንነት የሚፈልግ ሰው ነበር። ዊሊያምስ “የህሊና ነፃነትን አስተምህሮ ከነግዙፍነቱ የመሰከረ፣ አመለካከቶች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን የተናገረ የአዲሱ ክርስትና ዓለም ብቸኛ ሰው ነበር።”-Bancroft, pt. 1, ch. 15, par. 16። የፈራጆች ሥራ ወንጀልን መከላከል እንጂ ህሊናን መገደብ በጭራሽ እንዳልሆነ ተናገረ። “ሕዝቡ ወይም ፈራጆቹ” አለ፣ “ሰዎች ለሰዎች ያለባቸውን ኃላፊነት ሊወስኑ ይችላሉ። ሰው ለእግዚአብሔር ያለበትን ኃላፊነት ለማዘዝ ሲሞክሩ ግን ቦታቸውን ለቀዋል፤ በዚያ ደህንነት የለም። ምክንያቱም ፈራጁ እንደዚህ የማድረግ ስልጣን ካለው ዛሬ የተወሰነ አስተያየትና እምነት ካወጀ በኋላ ነገ ደግሞ ሌላ ሊናገር ይችላል፤ በእንግሊዝ አገር በተለያዩ ነገሥታትና ንግሥታት፣ በሮም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ ሊቀ ጳጳሳትና መማክርት፣ እንዲሁ ይደረጋል፤ ይህ ደግሞ እምነት የድንግርግር ክምር እንዲሆን ያደርጋል።”-Martyn, vol. 5, ገጽ 340። GCAmh 216.1

በተቋቋመችው ቤተ ክርስቲያን አምልኮ መሳተፍ በቅጣት ወይም በእስር አስገዳጅነት ይተገበር ነበር። “ዊሊያምስ ይህንን ሕግ አልተቀበለውም። ከእንግሊዝ ሕግ በጣም መጥፎው መመሪያ ሰዎች በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ እንዲሳተፉ የሚያስገድደው ነበር። የተለየ እምነት ካላቸው ጋር ህብረት እንዲፈጥሩ ሰዎችን ማስገደድ ተፈጥሮአዊ መብታቸውን በአደባባይ መጣስ እንደሆነ በማመን፣ እምነት የሌላቸውንና ፈቃደኛ ያልሆኑትን ወደ ሕዝባዊ አምልኮ መጎተት ግብዝነትን የመሻት ያህል ነበር። ‘ማንም’ አለ፣ ‘ያለ ራሱ ፍላጎት እንዲያመልክ ወይም አምልኮ እንዲቀጥል መገደድ የለበትም’። ‘ምን!’ አለ ተቃዋሚው በመመሪያዎቹ ተገርሞ፣ ‘የቀን ሰራተኛው የቅጥሩን ዋጋ ማግኘት የተገባው አይደለምን?’ ‘አዎ’፣ ‘ከሚቀጥሩት ዘንድ’” ብሎ መለሰ።-Bancroft, pt. 1, ch. 15, par. 2። GCAmh 216.2

ሮጀር ዊሊያምስ የተከበረና የተወደደ፣ ታማኝ አገልጋይ፣ እጅግ ብርቅ ተሰጥኦ ያለው ሰው፣ የማይታጠፍ ስብዕና ያለው፣ እውነተኛ ለጋስ ነበረ። ሆኖም ፈራጆች ቤተ ክርስቲያን ላይ አለን የሚሉትን ስልጣን በጽኑ መቃወሙና ለኃይማኖታዊ ነፃነት ጥያቄ ማቅረቡ በቸልታ የሚታለፍ ጉዳይ አልነበረም። የዚህ አዲስ አስተምህሮ መተግበር እጅግ ጠቃሚ የሆነውን “የአገሪቱን መዋቅርና አስተዳደር የሚገለብጥ” እንደሆነ ተደርጎ እንዲታይ ግፊት ታከለበት።-Ibid., pt. 1, ch. 15, par. 10። ከቅኝ ግዛቶቹ እንዲወገድ ከተደረገ በኋላ፣ በመጨረሻም እስርን ለማምለጥ ሲል ቀዝቃዛና ማዕበል በሞላበት ክረምት ጥቅጥቅ ወዳለው ጫካ ለመሰደድ ተገደደ። GCAmh 216.3

“ለአሥራ አራት ሳምንታት” አለ፣ “እንጀራ ወይም አልጋ ምን ማለት እንደሆነ ሳላውቅ በአስቸጋሪ ወቅት ተገፍትሬያለሁ” “ሆኖም ቁራዎች በበረሃ መገቡኝ።”-Martyn, vol. 5, ገጽ 349, 350። ውስጡ ክፍት የሆነ ዛፍ በአብዛኛው መጠለያው ሆነ። በዚህ ሁኔታ አስቸጋሪውን ሽሽት ዲካ በሌለው ጥቅጥቅ ጫካ በመቀጠል የወንጌልን እውነት ያስተምራቸው ዘንድ ሲጥር እምነታቸውንና ፍቅራቸውን ወዳተረፈባቸው ወደ አንድ የህንድ ጎሳ በመድረስ በዚያ መጠለያ ማግኘት ቻለ። GCAmh 217.1

ለወራት ስፍራ ሲለዋውጥና ሲንከራተት ከቆየ በኋላ በስተመጨረሻ ወደ ናራጋንሴት ዳርቻ በመሄድ፣ ለኃይማኖት ነፃነት መብት ሙሉ በሙሉ እውቅና የሰጠን የመጀመሪያውን ዘመናዊ አገር (ስቴት) መሰረት ጣለ። የሮጀር ዊሊያምስ መንደር አስተዳዳር ዋና መርህ “እያንዳንዱ ሰው አዕምሮው እንዳገኘው ብርሐን መጠን እግዚአብሔርን የማምለክ መብት ሊኖረው ይገባል” የሚል ነበር።-Ibid., vol. 5, ገጽ 354። ያቺ ትንሽዋ ግዛቱ ርሆድ ደሴት የጭቁኖች የጥገኝነት ስፍራ ሆነች፤ መሰረትዋ የነበሩት መርሆች - መንግሥታዊና ኃይማኖታዊ ነፃነት - የአሜሪካ ሪፐብሊክ የማዕዘን ድንጋይ እስኪሆኑ ድረስ አደገች፤ በለፀገችም። GCAmh 217.2

ቅድመ አያቶቻችን እንደ የመብት ረቂቃቸው (bill of rights) አድርገው ባሰፈሩት — የነፃነት ሰነድ (declaration of independence) በዚያ ግዙፍ፣ የቆየ መዝገብ ላይ እንዲህ ሲሉ አወጁ። “ሁሉም ሰዎች ሲፈጠሩ እኩል እንደሆኑ፣ ሊነጠቁ የማይቻላቸው መብቶች ፈጣሪያቸው ያቀዳጃቸው መሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል ሕይወት፣ ነፃነትና የደስታ መሻት ሲሆኑ እነዚህንም እውነቶች የራሳቸው ምስክር መሆናቸውን እናምናለን።” ህገ መንግሥቱም ተወዳዳሪ በሌለው በማያወላውል ሁኔታ ህሊናን መጣስ ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን አስረገጠ። “በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በማንኛውም የሕዝብ አመኔታ የሚያሻው የሥራ ገበታ ለመቀጠር ኃይማኖት እንደመመዘኛ መስፈርት ሆኖ ሊቀርብ አይችልም።” “ምክር ቤቱ የኃይማኖት መቋቋምን ደግፎ ወይም የዚያን ኃይማኖት መከተልን ተቃውሞ ፈጽሞ ሕግ ሊያወጣ አይችልም።” GCAmh 217.3

“የህገ መንግሥቱ አርቃቂዎች፣ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ከሰብአዊ ፍጡር ሕግ በላይ እንደሆነ፣ የህሊና ነፃነቱም ሊወሰድበት የሚችል እንዳልሆነ፣ ለዘላለማዊው መርህ እውቅና ሰጥተዋል። ምክንያት ማቅረብ ይህንን እውነት ለማረጋገጥ የመቅረብ አስፈላጊነት አልነበረውም፤ እያንዳንዳችን በውስጣችን የምናውቀው ጉዳይ ነው። የሰብአዊ ፍጡርን ሕግ ለመገዳደር አያሌ ሰማዕታት ስቃይና እሳትን ችለው በጽናት እንዲቆሙ ያስቻላቸው ይህንን ያወቁበት ንቃተ ህሊናቸው ነው። ለእግዚአብሔር ያለባቸው ኃላፊነት ከሰው ሕግጋት የሚበልጥ እንደሆነና የሰው ልጅ ህሊናቸውን የመቆጣጠር ስልጣን ሊኖረው እንደማይችል ገብቷቸው ነበር። ምንም ነገር ሊያጠፋው የማይችል ተፈጥሮአዊ መርህ ነው።”-Congressional Documents (U.S.A.), serial No. 200, document No, 271። GCAmh 217.4

ዜናው አውሮፓ አገር ሲስፋፋ፣ ሁሉም በላቡ ፍሬ ደስ የሚሰኝበት፣ ህሊናውንም የሚታዘዝበት ምድር እንዳለ ሲሰማ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አዲሱ ዓለም ጎረፉ። መንደሮች በፍጥነት ተበራከቱ። “ማሳቹሴትስ በልዩ ሕግ አማካኝነት ‘ከጦርነትም ሆነ ከረሃብ ወይም የአሳዳጆቻቸውን ጭቆና ለማምለጥ’ አትላንቲክን አቋርጠው ለሚመጡ የማንኛውም አገር ዜጋ ለሆኑ ክርስቲያኖች፣ ወጪያቸውን በመሸፈን የነፃ እንኳን ደህና መጣችሁና እርዳታ ታደርግ ነበር። የተሳደዱ፣ የተረገጡ በፀደቀው ረቂቅ አማካኝነት የህብረቱ እንግዶች ተደረጉ።”-Martyn, vol. 5, ገጽ 417። የመጀመሪያው ስደተኛ በፕላይ ማውዝ ከሰፈረ ጀምሮ በሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የኃይማኖት ስደተኞች በኒው ኢንግላንድ ሰፈሩ። GCAmh 217.5

አላማቸውን ለማሳካት፣ የቁጥብነትና የፍጋት ኑሮ በመምራት ለመኖር ብቻ በሚበቃ ገቢያቸው ረክተው ይኖሩ ነበር። የራሳቸው ጥረት ውጤት የሆነውን ሚዛናዊ ምርት ከመጠበቅ በቀር ከመሬቱ አንዳች ነገር አይሹም ነበር። አንድም ወርቃማ ራዕያቸው የማታለያ አክሊል በመንገዳቸው አልወረወረም.… አዝጋሚ ሆኖም የማያቋርጥ መሻሻል በሚያሳየው ማህበራዊ መንግሥታቸው የረኩ ነበሩ። ስሩ መሬት ውስጥ በደንብ ጠልቆ እስኪይዝ ድረስ የነፃነትን ዛፍ በእንባቸውና ከግንባራቸው በሚንጠባጠበው ላብ እያጠጡ የምድረ በዳውን መራቆት በትዕግስት ይችሉት ነበር። GCAmh 218.1

መጽሐፍ ቅዱስ የእምነት መሰረት፣ የጥበብ ምንጭና የነፃነት ዶሴ ተደርጎ ይታይ ነበር። መርሆዎቹም በቤት፣ በትምህርት ቤትና በቤተ ክርስቲያን በጥንቃቄ ትምህርት ይሰጥባቸው ነበር፤ ፍሬዎቹም በቆጣቢነት፣ በአዕምሮ ችሎታ፣ በንጽህናና በራስን መግዛት በግልጽ ይታዩ ነበር። በፕዩሪታን ሰፈር አንድ ሰው ለዓመታት ቢኖርም “ሰካራም ላያይ፣ መኃላ ላይሰማ ወይም ለማኝ ላያገኝ” ይችላል።-Bancroft, pt. 1, ch. 19, par. 25። የመጽሐፍ ቅዱስ መርሆዎች ብሔራዊ ታላቅነትን በማስጠበቅ ተወዳዳሪ የሌላቸው መሆናቸውን አስመሰከሩ። ደካማና ለየብቻ ይኖሩ የነበሩ መንደሮች በመስፋፋት ኃያል አገራት ወደ መሆን አደጉ፤ “ያለ ሊቀ ጳጳስ ቤተ ክርስቲያን፣ ያለ ንጉሥ አገር” የሆነችውን ሰላምና ብልጽግና የተቀረው ዓለም በግርምት አስተዋላት። GCAmh 218.2

አሁንም ግን ወደ አሜሪካ ዳርቻ የሚጎርፉ ሰዎች ቁጥራቸው በቀጣይነት እየጨመረ ሄደ። ያነሳሳቸው ፍላጎት ግን መጀመሪያ ከመጡት የኃይማኖት ስደተኞች አላማ በአብዛኛው የተለየ ነበር። የጥንቱ ኃይማኖትና ንጽህና መጠነ-ሰፊ የመቅረጽ ኃይል ቢኖረውም ዓለማዊ ጥቅም የሚሹ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ሲሄድ ተጽዕኖውም እየቀነሰ ሄደ። GCAmh 218.3

በመጀመሪያዎቹ ሰፋሪዎች የወጣው ድምጽ መስጠት ወይም የሕዝብ አስተዳደር ቢሮ መያዝ የሚችለው ሰው የቤተ ክርስቲያን አባል የሆነ ብቻ ነው የሚለው ደንብ እጅግ ጉዳት ያለው ውጤት አስከተለ። ይህ እርምጃ የአገሪቱን ንጽህና ለመጠበቅ የሚያስችል መፍትሄ ተደርጎ ተቀባይነት ያገኘ ቢሆንም ውጤቱ ግን የቤተ ክርስቲያን መበላሸት ሆነ። አማኝ እንደሆኑ መመስከር፣ ለመምረጥና ስልጣን ለመያዝ ቅድመ ሁኔታ ሲሆን ብዙዎች በምድራዊው ፍላጎት ብቻ ተነሳስተው፣ ከልባቸው ሳይለወጡ የቤተ ክርስቲያን አባል ሆኑ። በመሆኑም ቤተ ክርስቲያንዋ አያሌ ቁጥር ያላቸው ያልተለወጡ ምዕመናንን ያቀፈች ሆነች፤ እንዲያውም በአገልግሎት ውስጥ ጭምር የተሳሳተ አስተምህሮ የያዙ ብቻ ሳይሆኑ፣ መንፈስ ቅዱስ ያለውን የማደስ ኃይል የማያውቁ ሁሉ ነበሩበት። በመሆኑም በተደጋጋሚ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደታየው፣ ከቆስጠንጢኖስ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የተንፀባረቀው፣ በመንግሥት እርዳታ አማካኝነት ቤተ ክርስቲያንን ለመገንባት የሚደረገው ሙከራ፣ “መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም” [ዮሐ 18÷36] ያለውን የጌታን ወንጌል በመንግሥታዊ ኃይል ለመደገፍ መጣር፣ አሁንም እንደገና መጥፎ ውጤቱን አስመሰከረ። የቁርኝቱ ጥልቀት አናሳ ነው ሊባል ፈጽሞ የማይችል ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ያላት ጥምረት፣ ዓለምን ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚያቀርብ መስሎ ቢታይም እውነታው ግን ቤተ ክርስቲያንን ወደ ዓለም የሚያስጠጋ ነው። GCAmh 218.4

እውነት ቀስ በቀስ የሚጨምር (እያደገ የሚሄድ) በመሆኑ ከእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል የሚወጣውን ሁሉንም ብርሐን ለመቀበል ክርስቲያኖች ተዘጋጅተው መቆም አለባቸው የሚለው፣ በሮቢንሰንና በሮጀር ዊሊያምስ በግሩም ሁኔታ ጠንካራ ድጋፍ የነበረው ታላቁ መርህ በዘሮቻቸው ተረሳ። የተሐድሶውን በረከቶች ይቀበሉ ዘንድ የተመረጡት የአሜሪካ ፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም የአውሮፓዎቹ ጭምር በተሐድሶ መንገድ ወደፊት መቀጠል ሳይችሉ ቀሩ። ከጊዜ ወደ ጊዜ አንዳንድ ታማኝ ባሪያዎች እየተነሱ አዲስ እውነትን ቢያውጁም፣ ለረጅም ጊዜ ተቀባይነት የነበራቸውን ስህተቶች ቢያጋልጡም፣ አብዛኛው ሕዝብ ግን ልክ እንደ ክርስቶስ ዘመን አይሁዶች፣ ወይም በሉተር ዘመን እንደነበሩ ጳጳሳዊያን አባቶቻቸው፣ ያምኑበት የነበረውን እውነት ብቻ በማመን፣ እነርሱ ይኖሩበት የነበረውን አንዋንዋር በመኖር የረኩ ሆኑ። ኃይማኖት እንደገና ወግ ወደ መሆን አሽቆለቆለ። ቤተ ክርስቲያንዋ በእግዚአብሔር ቃል ብርሐን ብትራመድ ኖሮ ወደ ጎን ተገፍትረው ይጣሉ የነበሩ ስህተቶችና አጉል እምነቶች ባሉበት እንዲቀጥሉና እንዲከበሩ ሆኑ። ከዚያም በተሐድሶው አማካኝነት ተነቃቅቶ የነበረው መንፈስ ሞቶ፣ ልክ በሉተር ጊዜ በነበረው የሮም ቤተ ክርስቲያን ያስፈልግ የነበረው ታላቅ ተሐድሶ በፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትም የሚያስፈልግ እስኪሆን ድረስ አሽቆለቆለ። ተመሳሳይ የሆነ ዓለማዊነትና መንፈሳዊ ፍዘት፣ ተመሳሳይ የሆነ ለሰዎች አስተያየት ክብር መስጠት እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቃል አስተምህሮ በሰዎች ጽንሰ-ሃሳብ መተካት ይካሄድ ነበር። GCAmh 219.1

በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ በስፋት የተሰራጨው መጽሐፍ ቅዱስ፣ በዚህም መክንያት ወደ ዓለም የመጣው ታላቅ ብርሐን፣ በዚያው ልክ፣ የተገለፁት እውነቶች እውቀት እመርታም ሆነ በተግባር የሚገለጽ ኃይማኖት እድገት አላስከተለም ነበር። እንደ አለፉት ጊዜያት ሰይጣን የእግዚአብሔርን ቃል መከልከል አልተቻለውም፤ ለሁሉም ሰው ተደራሽ ሆኖአል። አላማውን ለማሳካት ግን ብዙዎች ዋጋ እንዳይሰጡት መራቸው። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ቸል አሉ፤ በመሆኑም የተሳሳቱ ትርጓሜዎችን መቀበላቸውን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መሰረት የሌላቸውን አስተምህሮዎችም ማክበርን ቀጠሉ። GCAmh 219.2

በማሳደድ እውነትን መደቆስ እንደተሳነው ያስተዋለው ሰይጣን ወደ ታላቁ ክህደት የመራውን ብሎም ወደ ሮም ቤተ ክርስቲያን መመስረት ያደረሰውን የመቻቻል እቅድ እንገና ተግባራዊ አደረገ። ሰይጣን በዚህ ጊዜ ክርስቲያኖችን ህብረት እንዲፈጥሩ ያነሳሳቸው፣ ከጣዖት አምላኪዎች ጋር ሳይሆን፣ ለዚህ ዓለም ካላቸው ፍቅር የተነሳ፣ የተቀረፁ ምስሎችን የሚያመልኩ ሰዎችን ያህል፣ እነርሱም ጣዖት አምላኪዎች መሆናቸውን ካረጋገጡ ከሃዲዎች ጋር ነበር። የዚህ ጥምረት ውጤትም ጥፋት የማምጣት አቅሙ ከቀደምት ጊዜያት ያልተናነሰ ነበር። ክብርና ብክነት በኃይማኖት ካባ ስር ሆነው ይኮተኮቱ ነበር። አብያተ ክርስቲያናቱም ብልሹ ሆኑ። ሰይጣን የመጽሐፍ ቅዱስን አስተምህሮ ማጣመም ቀጥሎበት ሚሊዮኖችን ወደ ጥፋት የሚወስድ ልማድ ስር እየሰደደ ነበር። “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለ ተሰጠ ኃይማኖት” [ይሁዳ 1÷3] በመጋደል ፈንታ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ባህሎች ከፍ አድርጋና ጠብቃ ማቆየት መረጠች። በዚህ ሁኔታ የተሐድሶ መሪዎች የተገበሯቸውና ብዙ የተሰቃዩላቸው መርሆዎች ተቦረቦሩ። GCAmh 219.3