የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ሃያ ስድስት—የወላጆች ጥሪት ለልጆች
በዘር የመተላለፍ ተፈጥሮአዊ ሕግ፦ የወላጆች የአካልና የአዕምሮ ሁኔታ በልጆች ቀጣይነት ያገኛል። ይህ ጉዳይ በአንክሮ የሚጤን ጉዳይ አይደለም። የወላጆች ልማድ ከስነ-አካል ህግ ጋር የሚቃረን በሚሆንበት ጊዜ በራሳቸው ላይ የመጣው ጉዳት በወደፊት ትውልዱም የሚደጋገም ይሆናል…. AHAmh 115.1
በአካል፣ በአዕምሮ እንዲሁም በግብረ-ገብነት ልማድ ሁሉም የክርስቶስ የሥራ ጓደኛ መሆን ይችላሉ። አብዛኛው የሚወሰነው በወላጆች ነው። በረከት ወይም እርግማን የሚሆኑ ልጆች ወደዚህ ምድር የመምጣታቸው ኃላፊነት በእነርሱ ላይ የተጣለ ነው።1 AHAmh 115.2
የላቀ እቅድ ማስቀመጥ ከፍተኛ የአዕምሮና የመንፈስ ሥጦታ ያስገኛል፤ የወላጆች አካላዊ ጥንካሬ በተሻለ ሁኔታ የዳበረ ከሆነም የላቀ የሕይወት መሣሪያ ለልጆቻቸው መለገስ ይችላሉ። በራሳቸው ውስጥ ያለውን ወደር የሌለውን ሀብታቸውን በማጎልመስ ወላጆች ህብረተሰብን የሚቀርፅ፣ ተተኪውን ትውልድ ክፍ ከፍ የሚያደርግ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ።2 AHAmh 115.3
ብዙ ወላጆች በአሳዛኝ ሁኔታ ዕውቀት ይጎድላቸዋል፦ በአምሳሉ የተፈጠሩትን የእግዚአብሔርን ንብረቶች አካላቸውንና ነፍሳቸውን በኃላፊነት ከእርሱ የተቀበሉ ሁሉ፣ የሺዎችን አካላዊና ግብረ-ገባዊ ጤና ካሳጣው፣ ይህንን ዓለም ከተጠናወተው፣ የስሜት እርካታ ጥማት አጥር ሊያበጁላቸው ይገባቸዋል። በዚህ ጊዜ እየተፈጸሙ ያሉት ወንጀሎች ወደ ኋላ መለስ ተብሎ መንስኤያቸው(ምንጫቸው) ቢጠና፣ መሠረቱ ለእንደዚህ ዓይነት ነገር ቁብ የማይሰጡ፣ ድንቁርና የወረሳቸው እናቶችና አባቶች መሆናቸው በግልጽ ይታይ ነበር። AHAmh 115.4
ጤና እንዲሁም ራሱ ሕይወት ጭምር ለዚህ አሳዛኝ ድንቁርና መሥዋዕት እየሆነ ይገኛል። ወላጆች ሆይ እግዚአብሔር ልጆቻችሁን እንድታስተምሯቸው የጣለባችሁን ግዴታ መወጣት ከተሳናችሁ፣ በመርህና በምሣሌነት ማሳደግ ካልቻላችሁ፣ ለሚመጣው መዘዝ በቀጥታ ለእግዚአብሔር መልስ መስጠት መገደዳችሁ አይቀርም። እነዚህ ውጤቶች በልጆቻችሁ ላይ ተወስነው አይቀሩም፤ ብዙ ትውልድን ይደርሳሉ። በመስክ ውስጥ እንዲያድግ የተተወ አንድ ኮሸሽላ ዘሩን እንደሚያበዛ ሁሉ በቸልተኝነታችሁ ምክንያት የሚዘራው ኃጢአት በተጽዕኖው ወሰን ሥር የሚመጡትን ሁሉ የሚያጠፋ ይሆናል።3 AHAmh 115.5
እራስን ያለመግዛት ጥፋቶች ይተላለፋሉ፦ የምቾት ኑሮ እንዲሁም ወይን መጠጣት ደምን ያበላሻሉ፤ ፍላጎትን ያቀጣጥላሉ፤ ሁሉንም ዓይነት በሽታ ይወልዳሉ። ክፋቱ ግን እዚያ ላይ አያበቃም። ወላጆች በሽታዎችን በቅርስነት ለልጆቻቸው ትተው ያልፋሉ። እንደ ሕግ ሆኖ እያንዳንዱ ራሱን መቆጣጠር የማይችል ልጅ-አሳዳጊ አባት ያሉትን ዝንባሌዎችና የክፋት ባህርያት ወደ ልጆቹ ያስተላልፋል። ከነደደውና ከተበላሸው ደሙ በሽታን ይሰጣቸዋል። ልቅነት፣ በሽታና ልፍስፍስነት የስቃይ ውርስ ሆነው ከአባት ወደ ልጅ፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋሉ። ይህ መከራንና ጭንቀትን ወደ ዓለም የሚያመጣ ጥፋት የመጀመሪያውን የሰው ልጆች ውድቀት ከመድገም የማይተናነስ ነው…. AHAmh 115.6
ሆኖም ቅንጣት ታክል ሐሳብ ወይም ጥንቃቄ ሳያደርጉ፣ ወንዶችና ሴቶች (ያሁኑ ትውልድ) በስካርና በቁንጣን ያልተቆጠበ ፍላጎታቸውን ያረካሉ። ለሚቀጥለው ትውልድም እንደ ቅርስ በሽታን፣ የላሸቀ አዕምሮንና የተበከለ ሥነ-ምግባርን አውርሰው ያልፋሉ። 4 AHAmh 116.1
ለጥልቅ ማስተዋልና ለትዕግሥት በቂ ምክንያት አለ፦ አባቶችና እናቶች የራሳቸው ባህርይ ምን ዓይነት እንደሆነ ከልጆቻቸው ማየት ይችላሉ። ብዙ ጊዜ የራሳቸው ጎደሎዎች በወንድና በሴት ልጆቻቸው ሲንፀባረቁ ሲያዩ አሳፋሪ ትምህርት ያገኛሉ። ልጆቻቸው የወረሷቸውን ዝንባሌዎችና የክፋት ባህርያት ለመጨቆንና ለማስተካከል በሚጥሩበት ጊዜ እጥፍ ትዕግሥት፣ ጽናትና ፍቅር ያስፈልጋቸዋል።5 AHAmh 116.2
አንድ ልጅ ከወላጆቹ የወረሳቸውን የተሳሳቱ ባህርያት ቢያንፀባርቅ፣ የራሳቸው ግድፈት ውጤት በሆነው ላይ መደንፋት አለባቸው? የለም አይደለም! እነዚህ ባህርያት እንደገና በልጆቻቸው ላይ እንዳይደገሙ ወላጆች ራሳቸውን በጥንቃቄ ተቆጣጥረው ጠጣርነትንና ሸካራነትን ከራሳቸው ያስወግዱ።6 AHAmh 116.3
ክርስቶስ በጥባጭ ለሆኑት ህፃናት ያሳየውን ቸርነትና ርኅራኄ አንፀባርቁ። ጠማማነታቸውን ከእናታቸው ወይም ከአባታቸው የወረሱት መሆኑን ምንጊዜም አትርሱ። የራሳችሁን ባህርይ በወረሱት ልጆቻችሁ ላይ አትጨክኑ።7 AHAmh 116.4
ወላጆች፣ ወደ ልጆቻችሁ የተላለፉትን የክፋት ዝንባሌዎች የክርስቶስ ኃይል ሊለውጣቸው ጉልበት እንዳለው እምነታችሁን በግልጽ ማሳየት ይኖርባችኋል። የድሮው ቸልተኝነታችሁ ምንጊዜም ያሁኑን ሥራችሁን ያከብደዋል፤ ሆኖም በእርሱ ካመናችሁ እግዚአብሔር ብርታት ይሰጣችኋል። በለሰለሰና ጥበብ በሞላበት አኳኋን ልጆቻችሁን አሳድጉ።9 AHAmh 116.5