የአድቬንቲስት ቤት

26/88

ምዕራፍ ሃያ አምስት—እንክብካቤ ለሚያስፈልጋቸው ልጆች መጠንቀቅ

ወላጅ-አልባ ልጆች፦ በእግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ቃል-ኪዳን ተደግፈው በዕምነት እያሉ ያለፉ ብዙ አባቶች፣ ጌታ እንደሚንከባከባቸው በመተማመን የሚወዷቸውን ትተው ተሰናብተዋል። ጌታ ታዲያ እነዚህን [ያለረዳት የቀሩ] ሐዘንተኞች እንዴት ነው የሚረዳቸው? ከሰማይ መናን በማውረድ ተዓምር አይሠራም። ምግብ እንዲያመጡላቸው ቁራዎችን አይልክም። ነገር ግን ራስወዳድነትን በማስወገድና የተዘጉትን የበጎ አድራጊነት ምንጮች በመክፈት የሰዎች ልብ ላይ ተዓምር ይሠራል። ለተጎዱና በሐዘን ውስጥ ላሉ ምህረት ያደርጉ ዘንድ በመጋበዝ ታማኝ ተከታዮቹ ለእርሱ ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንዲያሳዩ ይፈትናቸዋል። የእግዚአብሔር ፍቅር ያላቸው ሁሉ ቤታቸውንና ልባቸውን ከፍተው እነዚህን ልጆች ይውሰዷቸው…. AHAmh 112.1

ጥንቃቄ የተሞላበትን የወላጅ ምሪት የተነፈጉ፣ እንዲሁም በሚያሸንፈው በክርስቲያን ቤት ተጽዕኖ ሥር ያላደጉ ልጆችን በመርዳት ለጌታ መሥራት ለሚፈልጉ ሁሉ ጠቃሚ የሆነ ሥራ የሚሠራበት ሰፊ ሜዳ አለ። ብዙዎቹ የክፋትን ባህርያት የወረሱ ናቸው፤ በዚህም ሁኔታ ቸል ተብለው ካደጉ ዝሙትንና ወንጀልን ወደመፈፀም የሚመሯቸውን ህብረቶች ይመሠርታሉ። እነዚህ ተስፋ የማይጣልባቸው የትም አይደርሱም የተባሉ ልጆች የእግዚአብሔር ይሆኑ ዘንድ ትክክለኛ ባህርይ እንዲቀረጽባቸው አመቺ የሆነ ቦታ መቀመጥና ማደግ ይኖርባቸዋል።1 AHAmh 112.2

የቤተ-ክርስቲያን ኃላፊነቶች፦ ወላጅ-አልባ የሆኑ ልጆች ወደ ቤተ-ክርስቲያን ክንድ ይወረወራሉ፤ ክርስቶስ ለተከታዮቹ እንዲህ ይላል:- “እነዚህን የተራቆቱ ልጆች ውሰዷቸው፤ ለእኔ አሳድጉልኝ፤ ደምወዛችሁንም ትቀበላላችሁ”። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እጅግ የሰፋ ራስ-ወዳድነት ሲንጸባረቅ አይቻለሁ። ልጆቹን በማደጎነት በመውሰዳቸው የሚያገኙት የተለየ ጥቅም ከሌለ በስተቀር ጀርባቸውን ሰጥተው እምቢ ይላሉ። እነዚህ ልጆች መጥፋታቸውን ወይም መዳናቸውን እንኳ አያውቁም፤ የማወቅ ፍላጎትም አያሳዩም። ይህ ኃላፊነት የእነርሱ ሥራ መስሎ አይታያቸውም። ከቃየልን ጋር እንዲህ ይላሉ “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” በእነዚህ ልጆች ምክንያት ምቾታቸው እንዳይጓደል ምንም ዓይነት መስዋዕትነት መክፈል አይፈቅዱም፤ በግድ-የለሽነትም ወደ ዓለም ይገፈትሯቸዋል። አንዳንድ ጊዜ ታማኝ ክርስቲያን ነን ከሚሉ ሰዎች ይልቅ እነዚህን መሄጃ ያጡ ልጆች ዓለማውያን እጃቸውን ዘርግተው ይቀበሏቸዋል። በእግዚአብሔር ቀን ያድኗቸው ዘንድ ሰማይ የሰጣቸውን ዕድል ምን እንዳደረጉበት ለእነዚህ ክርስቲያን ነን ባዮች ጥያቄ ይቀርብባቸዋል። ይህንን ኃላፊነት ባለመቀበላቸው ይቅርታ እንዲያደርግላቸው ተመኝተዋል፤ ትርፍ የሚሠሩበት ካልሆነ መልካሙን ሥራ ለመሥራት ግን አልፈለጉም። እነዚህን የሚሰጧቸውን ዕድሎች የሚገፉ ሁሉ ከክርስቶስ ምን እንደሚሰሙ አየሁ:- “ከለዚህ ከተናናሽ ወንድሞቼ ለአንዱ ያላደረጋችሁት ለእኔ አላደረጋችሁትም።” ኢሳ 58 ÷ [5-11] ያንብቡ።2 AHAmh 112.3

ልጅ ለሌላቸው ጥንዶች የቀረበ ተማጽኖ፦ የራሳቸው ልጆች የሌላቸው የሌሎቹን ሰዎች ልጆች መንከባከብና መውደድ ይችሉ ዘንድ እራሳቸውን ያስተምሩ። በባዕድ ምድር ሄደው እንዲሠሩ አይጠየቁ ይሆናል፤ በሚኖሩበት በራሳቸው አካባቢ እንዲሠሩ ግን ይጋበዛሉ። ለለማዳ የቤት እንስሣት ትኩረት ከመስጠት፤ ከመጠን ያለፈ ፍቅር ለዱዳ እንስሣት ከማፍሰስ፣ ሰማይን ለማትረፍ ሲኦልን ለማምለጥ ላላቸው የሰው ዘሮች ችሎታቸውን ይጠቀሙበት። ትኩረታቸውን ለትናንሽ ልጆች በመስጠት በመለኮታዊው ዱካ መሠረት ይቅረጹአቸው፤ ያብጇቸው። በዙሪያችሁ ባሉ ቤትአልባ በሆኑ ልጆች ላይ ፍቅራችሁን ጫኑ። ለሰው ዘር ቤተሰብ ልባችሁን በመዝጋት ፈንታ ቤት የሌላቸውን ስንት ህጻናትን በጌታ እንክብካቤና ተግሳጽ ሥር ማሳደግ እንደምትችሉ አስቡ። ሥራውን መሥራት ለሚፈልግ ሁሉ ሥራ በገፍ አለ። በእንደዚህ ዓይነት ክርስቲያናዊ ጥረት አባላት ይበዛሉ፤ ቤተ-ክርስቲያን በመንፈስ ትጎለብታለች። አባትና ቤት የሌላቸውን የማትረፍ ሥራ የእያንዳንዱ ሰው ጉዳይ ነው።3 AHAmh 113.1

ልጆች የሌሏቸው እግዚአብሔር በገንዘባቸው እንዲያገለግሉት የባረካቸው ሰዎች ፍቅርን፣ እንክብካቤን፣ ዳበሳንና የዚህ ዓለም ቁሳዊ እርዳታን ለሚፈልጉ ሁሉ ልባቸውን ቢከፍቱ፣ አሁን ካላቸው ደስታ ይልቅ እጅግ ደስተኞች በሆኑ ነበር። የአባት ሩኅሩኅ እንክብካቤና የእናት ሰፍሳፋ ፍቅር የተነፈጉ ወጣቶች፣ በዚህ በመጨረሻው ቀናት ባለው የጋጀ(የተበላሸ) ዓለም ተጽዕኖ ሥር ሆነው እንዳይበላሹ ከተፈለገ ከመካከላችን አንዳችን የእናትነት ወይም የአባትነት ቦታ ልንተካላቸው ግዴታ አለብን። ፍቅር፣ አሳቢነትና ርኅራኄ እንዴት እንደምታሳዩአቸውም ተማሩ። እንዲንከባከባቸው ተስፋ የሚጥሉበት፣ በመጨረሻም ለእነርሱ ወዳዘጋጀው ቤት እንደሚወስዳቸው የሚጠብቁት አባት በሰማይ እንዳላቸው የሚናገሩ ሁሉ ጓደኛ ለሌላቸው ጓደኛ፤ ወላጅ ለሌላቸው አባት፤ ባላቸው ለሞተባቸው ረዳት የመሆን እንዲሁም ለሰው ዘር ጥቅም የሚውል ተግባራዊ ሥራ የማከናወን ከባድ ሃላፊነት በላያቸው ላይ እንዳለ ሊሰማቸው ይገባል።4 AHAmh 113.2

የአገልጋዮች ባለቤቶች የራሳቸው ያልሆኑ ልጆችን ለማሳደግ መቀበል አለባቸው?፦ የአገልጋይ ሚስቶች ጨቅላ ልጆችን በማደጎነት መቀበል ይኖርባቸው እንደሆነ ተጠይቋል። የእኔ መልስ ከቤቷ ወጥታ ሚሲዮናዊ ሥራ የመሥራት ዝንባሌው ወይም ብቃቱ ከሌላት፣ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች የመንከባከቡ ኃላፊነት ከተሰማት ጥሩ ሥራ ልትሠራ ትችላለች። ሆኖም ቅድሚያ ሰንበትን ይጠብቁ ከነበሩ ወላጆች የተረፉ ልጆችን ለመንከባከብ ምርጫዋ ታድርግ ። በፈቃደኛ ልብ ቤታቸውን መኖሪያ ከሌላቸው ጋር የሚጋሩትን ሴቶችና ወንዶች እግዚአብሔር ይባርካቸዋል። የአገልጋይ ሚስት ሌሎችን በማስተማር ሥራ ላይ መሳተፍ የምትችል ከሆነ ግን እንደ ክርስቲያን ሠራተኛ ያላትን ኃይል ለእግዚአብሔር ቀድሳ ታቅርብ። ለባልዋ እውነተኛ ረዳት ትሆናለች፤ በሥራው ታግዘው፤ እውቀትዋን ታሻሽል፤ መልእክቱን ለሌሎች ለማበርከት የምትረዳ ትሁን። በእግዚአብሔር የተቀደሱና በክርስቶስ ፀጋ የከበሩ ሴቶች እርዳታ የሚፈልጉትን በመጎብኘት ተስፋ ለቆረጡ ነፍሳት ብርሃን መፈንጠቅ ይችላሉ። አብረው በመጸለይና ወደ ክርስቶስ በመመልከት የጎበጡትን ሊያቃኑ ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነት ሴቶች ለአንድ ረዳት-የለሽ ሟች ህፃን ትኩረትና እንክበካቤ ለመስጠት ሲሉ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን መግደል አይገባቸውም፤ በፈቃደኝነት እጃቸውን ማሰር የለባቸውም።5 AHAmh 113.3

ቤት ወላጅና ጓደኛ አልባ ለሆኑ ክፍት ይሁን፦ ለማድረግ አቅሙ እስካላችሁ ድረስ ቤት ለሌላቸው ቤት ሥሩ፤ እያንዳንዱ ይህንን ተግባር ከግብ ለማድረስ ተዘጋጅቶ የቆመ ይሁን። ጌታ ለጴጥሮስ እንዲህ አለው “ጠቦቶቼን መግብ”። ይህ ትዕዛዝ ለእኛም ተሰጥቷል፤ ቤታችንም ወላጅ ለሌላቸው በመክፈት ይህ ትዕዛዝ እንዲፈጸም እናግዛለን። ክርስቶስ ቅር እንዲሰኝባችሁ አታድርጉት። ለእነዚህ ልጆች ወላጆች በመሆን ውብ መዓዛ ያለው ሥጦታ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። እንዲባርካቸው ጠይቁት፤ ክርስቶስ እንዳዘዘም ቅረጹአቸው፤ አብጇቸውም። ህዝባችን ይህንን ቅዱስ አደራ ይቀበላል?6* AHAmh 114.1

የእግዚአብሔር ሕዝብ መፈተኛ፦ ቤት ለሌላቸው ቤት በመሥራት ረገድ የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደሚፈተኑ ከዓመታት በፊት አይቻለሁ። እውነትን በማመናቸው ብዙዎች ቤት አልባ ይሆናሉ። ተቃውሞና ስቃይ አማኞችን ከቤታቸው ያፈናቅላቸዋል። ለእነዚህ መጠለያ ለሌላቸው ክርስቲያኖች በራቸውን በሰፊው መክፈት ቤት ያላቸው ሰዎች ኃላፊነት ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ እግዚአብሔር ጠንካራ ተከታዮቹን እንደሚፈትናቸው በቅርብ አይቻለሁ። በድህነቱ ሀብታሞች እንሆን ዘንድ ክርስቶስ ለእኛ ሲል ድኃ ሆነ። ለኃይማኖት ተጓዦች፣ ወዘ-ልውጦችና የተሻለ አገር ለሚናፍቁ በዓለም ላሉ ሁሉ ቤት ያዘጋጅ ዘንድ ያውም - ሰማያዊ ቤት - ራሱን መሥዋዕት አደረገ።7 AHAmh 114.2