የአድቬንቲስት ቤት

86/88

ክፍል ፲፰—ትካሳላችሁ

ምዕራፍ ሰማንያ አምስት—የዚህና የሚመጣው ዓለም ሽልማት

ታማኝ ወላጆችን የተትረፈረፈ ሽልማት ይጠብቃቸዋል፡- ወላጆች ለልጆቻቸው ተገቢውን ትምህርት ከሰጡ፣ ልጆቻቸው በሚያንፀባርቁት ክርስቶስን መሰል ባህርይ የሥልጠናቸውን ፍሬ በማየት ይደሰታሉ። እግዚአብሔርን የሚፈሩ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቤተሰቦች ላይ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ የሚያከብሩትና ከፍ ከፍ የሚያደርጉት ሥርዓት ያላቸውና ምግባረ-ሰናይ የሆኑ ቤተሰቦችን ለዓለም በማበርከት ተወዳዳሪ የሌለው አገልግሎት ለአምላክ ያቀርባሉ፤ ሽልማታቸውንም ይቀበላሉ።1 AHAmh 391.1

አማኝ የሆናችሁ ወላጆች ሆይ! የልጆቻችሁን ዱካ፣ የኃይማኖት ልምምዳቸውንም ጭምር በትክክለኛው መንገድ ትመሩ ዘንድ ታማኝነት የሚያስፈልገው ሥራ በፊታችሁ ነው። እግዚአብሔርን በእውነት ወደ መውደድ ሲመጡ ላደረጋችሁላቸው እንክብካቤ እንዲሁም ፍላጎታቸውን በመገደብና መሻታቸውን በማስገዛት ላሳያችሁት ታማኝነት ይባርኳችኋል፤ ያወድሷችኋልም።2 AHAmh 391.2

የእውነት ዘር ቀደም ብሎ ሲዘራና ተገቢው እንክብካቤ ሲደረግለት ሽልማት አለው።3 AHAmh 391.3

የወደፊቱን ምርት ግምት ውስጥ በማስገባት ወላጆች መሥራት አለባቸው። በብዙ ግድድሮሽ ውስጥ ሆነው በእንባ ሲዘሩ ሳለ በልባዊ ፀሎት ይሁን። ምርቱ የሚዘገይና ትንሽ ሆኖ ቢታያቸውም እንኳ ከመዝራት ሊቆጠቡ አይገባም። እራሳቸውን ሊያሻሽሉበትና ለልጆቻቸው ጥቅም የሚሆኑበትን እያንዳንዱን ዕድል በመጠቀም በውኃዎች መካከል ዘሩን ይዝሩ። ይህ ዓይነቱ አዘራር በከንቱ የሚቀር አይደለም። በመከር ወቅት ብዙ ታማኝ ወላጆች ነዶአቸውን ይዘው በደስታ የሚመለሱ ይሆናሉ።4 AHAmh 391.4

የአዕምሮ መዳበርና የግብረ-ገብነት ሥልጠና ለልጆቻችሁ ለግሡ። ለጋ አዕምሮአቸውን በጥብቅና ንጹህ መርሆዎች አንጹት። ዕድል በእጃችሁ ሳለ ለከበረው ጎልማሳነት የሚያበቃቸውን መሠረት ጣሉ። ልፋታችሁ አንድ ሺህ ዕጥፍ ሆኖ ይመለስላችኋል።5 AHAmh 391.5

ወላጆች ለሰማይ ገጣሚ በሆኑ ልጆች ይወደሳሉ፡- በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ስለ ደስተኛ ቤተሰብና ስለምትኖርበት ሴት ደስ የሚል ገለጻ እናገኛለን። “ልጆችዋ ይነሣሉ የተመሠገነችም እንደ ሆነች ይናገራሉ። ባልዋም ያመሠግናታል።” እዚህ ከተጠቀሰው ምሥጋና የበለጠ የቤ ት ልዕልትዋ የምትፈልገው ም ን ነገር አለ? 6 AHAmh 391.6

እውነተኛዋ ሚስትና እናት ለጥንካሬዋና መጽናናትዋ ወደ እግዚአብሔር ብትመለከት፣ በጥበቡና በፍርኃቱም የዕለት ተዕለት ሥራዋን ለማከናወን ብትጥር፣ ባልዋን ከልብዋ ጋር ማጣመር ትችላለች። የእናታቸውን ዱካ ለመከተል የግብረገብነት ብርታት ይዘው ወንዶችና ሴቶች ልጆችዋም የከበሩ ጎልማሶች ወደ መሆን ሲያድጉ ታያለች።7 AHAmh 391.7

ለምትለፋና በሸክም ለዛለች እናት ታላቁ መበረታቻ እያንዳንዱ በትክክል የሠለጠነና የውስጥ ውበት ያለው በየዋህነትና በተረጋጋ መንፈስ የተጌጠ ልጅ ለሰማይ ብቁ የሚሆንና በጌታ ቤተ-መንግሥት በብርሃን የሚያንፀባርቅ መሆኑ ነው።8 AHAmh 392.1

የሰማይ ደስታዎች በቤት ውስጥ መጀመር አለባቸው፡- ዛሬ ሰማይና ምድር ያላቸው መራራቅ፣ በግ ጠባቆች የመላእክትን ዜማ ከሰሙበት ጊዜ የባሰ አይደለም። ተራ ሥራ የሚሠሩ ተራ ሰዎች በእኩለ-ቀን በመስኩና በወይን ሥፍራው ሰማያዊ መልእክተኞችን ያነጋግሩ እንደነበር ዛሬም ሰባዊ ዘር የሰማይ ዋነኛ ትኩረት ነው። በተለመደው ኑሮ ለምንመላለስ ለእኛ ሰማይ በጣም ቅርብ ሊሆን ይችላል። መላእክት ከላይኛው ቤተ-መንግሥት ሆነው በእግዚአብሔር ዕዝ ሥር የሚመላለሱትን እርምጃ ይቆጣጠራሉ።9 AHAmh 392.2

የምድር ሕይወት በሰማይ ያለው ኑሮ ጅማሮ ነው። በምድር ያለው ትምህርትም የሰማይ መርሆች መተዋወቂያ ነው። እዚህ ያለው የሕይወት ሙያ እዚያ ላለው ሙያ መሠልጠኛ ነው። አሁን ያለን ባህርይና ቅዱስ አገልግሎታችን በእርግጥ በኋላ ለምንሆነው ጥላ ነው።10 AHAmh 392.3

በቅን ልብ የሚበረከት አገልግሎት ታላቅ ካሣ አለው። “አባትህም በስውር የሚያይ እርሱ በግልጽ ይሰጥሃል።” በክርስቶስ ፀጋ ውስጥ በምንኖረው ኑሮ ባህርይ ይመሠረታል፤ ነፍስ ወደ መጀመሪያው ውበት ትታደሳለች፤ የክርስቶስ ባህርይ መገለጫዎች ይወረሳሉ፤ የመለኮት ምሣሌም መንፀባረቅ ይጀምራል። ከእግዚአብሔር ጋር የሚሠሩ ሴቶችና ወንዶች ፊት፣ የሰማይን ሠላም ያንፀባረቃል። በሰማይ ከባቢ አየር የተጀቦኑ ናቸው። ለእነዚህ ነፍሳት የእግዚአብሔር መንግሥት ጀምራለች። የክርስቶስ ደስታ አላቸው - ለሰው ዘር በረከት የመሆን ደስታ። ለጌታ አገልጋይ ይሆኑ ዘንድ ዕድሉን የማግኘት ክብር ተሰጥቷቸዋል፤ በስሙ ሥራውን ይሠሩ ዘንድ እምነት ተጥሎባቸዋል።11 AHAmh 392.4

ለሰማይ ቤተሰብነት ብቁ ይሆኑ ዘንድ ሁሉም ተጠርተዋል፡- የሰማይ ዕቅድ እንዲተገበር እግዚአብሔር ይፈልጋል፤ ይመኛልም። በእያንዳንዱ ቤተሰብ በእያንዳንዱ ቤተ-ክርስቲያንና በእያንዳንዱ ተቋም የሰማይ መለኮታዊ ሥርዓትና መስማማት እንዲያሸንፍ ምኞቱ ነው። ይህ ፍቅር ማህበረሰቡን ቢሞላው ኖሮ የከበሩት መርሆዎች ሥራ በክርስቲያናዊ ንጥረትና ደግነት እንዲሁም በክርስቶስ ደም ለተገዙት ሁሉ ክርስቲያናዊ በጎ አድራጎት ሲገለጽ ማየት እንችል ነበር። መንፈሳዊ መለወጥ በቤተሰቦቻችን፣ በተቋሞቻችንና በቤተ-ክርስቲያኖቻችን እናይ ነበር። ይህ መለወጥ ተግባራዊ ሲሆን እነዚህ ተቋማት የሰማይን ብርሃን ለዓለም ያካፍሉ ዘንድ እግዚአብሔር በመሣርያነት ይጠቀምባቸዋል። ብሎም በመለኮታዊ ሥነ-ሥርዓትና ሥልጠና ሴቶችና ወንዶች ለሰማይ ማህበረሰብነት ብቁ እንዲሆኑ ያደርጋሉ።12 AHAmh 392.5

ሽልማት በመጨረሻው ታላቅ ቀን፡- ለልጆቻችሁ በምትሠሩት ሥራ ታላቁን የእግዚአብሔር ኃይል ተጠማጠሙ። በፀሎት ልጆቻችሁን ለጌታ አስረክቡ። በሐቀኝነት ያለ ድካም ለእነርሱ ሥሩ። እግዚአብሔር ፀሎታችሁን ሰምቶ ወደርሱ ያስጠጋቸዋል፤ በመጨረሻው ታላቅ ቀን ወደ እግዚአብሔር ፊት አቅርባችኋቸው “እነሆኝ እኔ እግዚአብሔርም የሰጠኝ ልጆች” ማለት ትችላላችሁ።13 AHAmh 393.1

ሳሙኤል የክብር ዘውዱን በሚቀበልበት ጊዜ በዙፋኑ ፊት በክብር እያወዛወዘ ከክርስቶስ መልካም ሥራዎች ጋር የእናቱ ታማኝ ትምህርቶች የዘለዓለማዊ ዘውድ ይደፋ ዘንድ እንዳስቻሉት በደስታ እውቅና ይሰጣል።14 AHAmh 393.2

የብልህ ወላጆች ሥራ በዓለም በበቂ ሁኔታ ፈጽሞ ሊመሠገን አይችልም፤ ሆኖም ፍርድ ሲቀርብና መጻሕፍት ሲከፈቱ፣ ሥራቸው እግዚአብሔር በሚያይበት ዕይታ ሲገለጽ፣ በሰውና በመላእከት ፊት ሽልማታቸውን ይቀበላሉ። በታማኝነት ያደገ አንድ ልጅ የዓለም ብርሃን እንደነበረ ይታያል። የዚህን ልጅ ባህርይ ለመገንባት ዕንባ፣ ጭንቀትና እንቅልፍ አልባ ሌሊቶች ማሳለፍ ግድ ይል ይሆናል፤ ሥራው ግን በጥበብ ተሠርቷል። ወላጆቹም “መልካም ሠራህ” የሚለውን ቃል ከጌታ ይሰማሉ።15 AHAmh 393.3

ወደ ንጉሥ ቤት የመግባት መብት፡- “ቢስም ትለብስ ዘንድ ተሰጣት የጸራ የሚያበራም” የምድር ቅዱሳት ሁሉ የሚለብሱትን በሰማይ የሸማ-ዕቃ የተሠራውን ንጉሳዊ ካባ ለራሳቸው ይመርጡ ዘንድ ወጣቶችና ሕፃናት መማር አለባቸው። ይህ ነቁጥ የሌለው የክርስቶስ ባህርይ የሆነው ልብስ ለሁሉም የሰው ዘር በነፃ ተችሮአል። የሚቀበሉት ሁሉ ግን ተቀብለ ው እዚህ [በምድር] ይለብሱታል። ለመልካምና ንጹህ አስተሳሰብ አዕምሮአቸውን ከፍተው ውብና ረዳት የሚሆን ሥራ ሲያከናውኑ በክርስቶስ ያማረ የባህርይ ልብስ እራሳቸውን እየሸፈኑ እንደሆነ ልጆች ሊማሩ ይገባቸዋል። ይህ ልብስ እዚህ ባሉበት ዘመን የሚያምሩ ያደርጋቸዋል፤ ሊመጣ ላለውም ወደ ንጉሡ ቤተ-መንግስት ይገቡ ዘንድ መብት ይሆናቸዋል። ቃል-ኪዳኑ ይህ ነው፡- “ከእኔ ጋራም ነጭ ለብሰው ይሄዳሉ ይገባቸዋልና።” 16 AHAmh 393.4

መለኮታዊ እንኳን ደህና መጣችሁ ለዳኑት፡- ቁጥራቸው እጅግ የበዛ መላእክት የእያንዳንዱ ቅዱስ ስም በላያቸው የተጻፈባቸው የክብር ዘውዶች ከከተማዋ ሲያመጡ አየሁ። የሱስም ዘውዶቹን አምጡ አለ። አቀረቡለትም፤ ውብ የሆነው የሱስም በራሱ ቀኝ እጅ ዘውዶቹን በእያንዳንዱ ቅዱስ ራስ ላይ አስቀመጠ። በተመሳሳይ ሁኔታ መላእክት በገናቸውን አመጡ፤ የሱስም ለቅዱሳን አበረከታቸው። መሪ መላእክትም ኖታ መጫወት ጀመሩ፤ ከዚያም ሁሉም የደስታና የምሥጋና ድምጽ አወጡ፤ በፍጹም ፍሰት ያማረ ዜማ እየለቀቁ የእያንዳንዱ ቅዱስ ጣቶች በቅልጥፍና በበገናዎቹ ክሮች መካከል ይመላለሱ ነበር። AHAmh 393.5

ከዚያም የሱስ የዳኑትን ወደ ከተማዋ በር ሲመራቸው አየሁ። በሩንም ይዞ ወደ ኋላ ገፋው እውነትንም የጠበቁ ሕዝቦች እንዲገቡ ጋበዛቸው። በከተማዋም ውስጥ ዓይን ሊረካበት የሚችል ነገር ሁሉ ነበር። ሁሉም ነገር ክብር የተጎናጸፈ ነበር። ከዚያም የሱስ የተዋጁትን ቅዱሳት ተመለከተ፤ ፊታቸው በክብር ድምቀት ያበራ ነበር፤ የፍቅር ዓይኖቹ አርፈውባቸው ሳለ በጥልቅ ዜማዊ ድምጹ እንዲህ አለ፡- “የነፍሴን ድካም ፍሬ አየሁ ጸገብኩም ለዘለዓለም ደስ ይላችሁ ዘንድ ይህ በረከት ለእናንተ ነው። ዋይታችሁ አብቅቷል ሞትም ከእንግዲህ አይሆንም፤ ለቅሶም ጩኸትም መጣጣርም ከእንግዲህ አይሆንም።” የዳኑትም ተጎንብሰው የሚያንፀባርቀውን ዘውዳቸውን በየሱስ እግር ሥር ሲያኖሩ አየሁ፤ ከዚያም መልካም እጁ ከተጎነበሱበት ሲያነሷቸው ወርቃማውን በገናቸውን ነኩ የሚጫወቱት ሙዚቃና ለበጉ የሚዘምሩት መዝሙር ሰማይን ሁሉ ሞላው…. AHAmh 394.1

ሰማይን ለመግለጽ ሙከራ ያደርግ ዘንድ ቋንቋ ሁሉ እጅግ የደከመ ነው። በፊቴ በማያቸው ነገሮች በመደነቅ ተዋጥኩ። ከአዕምሮ በላይ በሆነው ውበትና እጅግ ግሩም ግርማ ተወስጄ በመደነቅ ብዕሬን አንስቼ እንዲህ ፃፍኩ፡- “ኦ ምን ዓይነት ፍቅር ምን ዓይነት ግሩምና አስደናቂ ፍቅር! እጅግ የተሞገሰው [ምድራዊ] ቋንቋ እንኳ የሰማይን ክብር ወይም እኩያ የሌለውን የአዳኙን ፍቅር ጥልቀት ይገልጽ ዘንድ አይችልም።” 17 AHAmh 394.2