የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ሰማንያ አራት—መታደስን በተመለከተ የወጣትን አስተሳሰብ አቅጣጫ ማስያዝ
ደረጃዎች ዝቅ እየተደረጉ ነው፡- ልጆቻቸው ለሚያንፀባርቁት የአፍቅሮተዓለም ዝንባሌዎች ክርስቲያን ወላጆች እጅ እየሰጡ ነው። መርሆዎቻቸውን በጥብቅ ሲከተሉ በነበሩበት ጊዜ ይከለክሏቸው የነበሩትን ፈንጠዝያዎች አሁን በራቸውን ከፍተው ይቀበሏቸው ጀምረዋል።1 AHAmh 386.1
በክርስቲያን ወላጆች መካከል እንኳ የፈንጠዝያ ፍቅር ከሚገባው በላይ ቦታ ተሰጥቶታል። ወላጆች የዓለምን መመሪያ ተቀብለውታል፤ በመሆኑም የልጆችና የወጣቶች የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ምንም ባለመሥራት፣ በራስ-ወዳድ ፈንጠዝያዎችና የሞኝነት እርካታዎች የተሞሉ መሆናቸው አስፈላጊ እንደሆነ ዓለም በተለምዶ የሚያስበውን ሐሳብ ይስማሙበታል። በዚህም ምክንያት ከሚያቅበጠብጥ የእርካታ ፍቅር የሚገኘው ጣዕም በውስጣቸው ይፈጠራል። የልጆችና የወጣቶች አዕምሮም በሚያስደስቱ ትዕይንቶች ሐሴት አንዲያደርግ ይሠለጥናል። በዚህም ምክንያት የተለመዱ ሆኖም ጠቃሚ ለሆኑ የሕይወት ኃላፊነቶች ፍላጎት ይጠፋባቸዋል። የጨካኙን ፍጡር ሥርዓት በመከተል ሕይወታቸውን ይመራሉ። የእግዚአብሔር ወይም የዘለዓለማዊ እውነታዎች ትዝ አይሏቸውም። ወቅታቸውን ጠብቀው ከቦታ ቦታ እንደሚዘዋወሩት ቢራቢሮዎች ወዲያ ወዲህ ይውረበረባሉ። ሕይወታቸው ከእግዚአብሔር ሕይወት ጋር ሊመሳሰል የሚችል አቅም እንዳለው አስበው እንደ አስተዋይ ፍጡር አይንቀሳቀሱም፤ ለተሰጣቸው ለእያንዳንዷ ሰዓትም ተጠያቂ እንደሆኑ አያስተውሉም።2 AHAmh 386.2
እናቶች መደሰቻዎችን መፍጠርና መቆጣጠር ይገባቸዋል፡- እናት ጫጫታቸው እንዳያውካት እንዲሁም አሁንም ቅድምም በሚፈልጓቸው የተለያዩ ትኩረቶች እንዳትረበሽ ስትል ከአጠገብዋ ፈቀቅ እንዲሉ በማድረግ ፈንታ በመደባበስ ንቁና ቅብጥብጥ የሆነውን አዕምሮአቸውን በጨዋታና በቀላል ግን በሚያስደስት ሥራ ከመጥመድ የበለጠ ሥራ ልትሠራ እንደማትችል ሊሰማት ይገባል። ለልፋትዋና የተለያዩ መጫዎቻዎችን በመዘየድ ለ ምታጠፋው ጊዜ ተትረፍርፎ ይከፈላታል ። ታዳጊዎች ማህበራዊነትን ይወድዳሉ። እንደ እውነታ ሆኖ ብቻቸውን የሚደሰቱ አይደሉም። ልጆች በቤት ውስጥ በሚሆኑበት ጊዜ ባብዛኛው እርስዋ ባለችበት ክፍል መገኘት እንዳለባቸው ሊሰማት ይገባል። አብራቸው በመሆንዋም ጥቃቅን ልዩነታቸውን ታስተካክልላቸዋለች፤ ሲፈልጓት ትገኛለች፤ መጥፎ ልማድን የራስወዳድነት ነፀብራቅንና ፍላጎትን ታርማለች፤ ለአዕምሮአቸውም ትክክለኛውን አቅጣጫ ትቀይሳለች። ልጆች እነርሱን የሚያስደስታቸው ነገር ሁሉ እናታቸውን የሚያስደስታት ይመስላቸዋል፤ በጥቃቅን ግራ መጋባታቸው እናታቸውን ማማከራቸውም ፍጹም ተፈጥሮአዊ ነው። በትንንሽ ጉዳዮቻቸው ላለመበጥበጥ እምቢ በማለትና ለነገሮቻቸው ቁብ ባለመስጠት እናት በቀላሉ የሚጎዳውን የልጆችዋን ልብ ልታቆስል አይገባትም። ለእርስዋ መናኛ የሆነው ለእነርሱ ግን እጅግ አስፈላጊ ነው። በመሆኑም በትክክለኛው ጊዜ የሚሰጥ ትዕዛዝ ወይም ማስጠንቀቂያ ጠቃሚነቱ ከፍተኛ ነው።3 AHAmh 386.3
ግድፈት የሌለባቸውን መደሰቻዎች አትንፈጓቸው፡- ጊዜና እሳቤ በማጣት ብዙ እናቶች ከመልካም ጨዋታዎች ልጆቻቸውን ይከለክላሉ፤ በሥራ የተጠመዱት ጣቶችና የዛሉት ዓይኖች በትጋት የሚሠሩት ጌጣጌጥ ለመስፋት ብቻ የሚውል ከሆነ የሚያስከትለው ነገር ቢኖር በወጣቶች ልብ የሚፈጥረው ከንቱነትንና ብኩንነቱን ማበረታታት ነው። ልጆች ወደ ጎልማሳነት እየቀረቡ ሲሄዱ እነዚህ ትምህርቶች የኩራትና የግብረ-ገብነት እርባና-ቢስነት ፍሬ ያፈራሉ። እናት በልጆችዋ ጥፋቶች ታዝናለች፤ ሆኖም እየሰበሰበች ያለው መከር ራስዋ የዘራችው ዘር እንደሆነ አታስተውልም። AHAmh 387.1
አንዳንድ እናቶች በልጆቻቸው አያያዝ መዋዠቅ ይታይባቸዋል፤ አንዳንድ ጊዜ የሚጎዷቸውን ነገሮች እንዲያደርጉ ሲፈቅዱ በሌላ ጊዜ ደግሞ የልጅነት ልባቸውን በደስታ ሊሞላው የሚችለውን ንጹህ መዝናኛ ይከለክሏቸዋል። በዚህም ክርስቶስን አይመስሉም፤ እርሱ ልጆችን ያፈቅራቸው ነበር፤ ስሜታቸውን ይረዳ፣ ደስታቸውንና ሐዘናቸውንም ይካፈል ነበር።4 AHAmh 387.2
ሚስስ ዋይት እንዴት ልጆችዋን ትቆጣጠር እንደነበር፡- ልጆችዋ ከነዚህ ጓደኞች ወይም ከነዚያ የፓርቲ ጨዋታዎች ይቀላቀሉ ዘንድ እንዲፈቀድላቸው ሲለምኑ እንዲህ ይባሉ ነበር፡- “ወደ እዚያ እንድትሄዱ አልፈቅድላችሁም፤ ኑ እዚህ ቁጭ በሉና ለምን እንደማልሰዳችሁ ልንገራችሁ። የዘለዓለምና የእግዚአብሔር የሆነ ሥራ እየሠራሁ ነው። እግዚአብሔር እናንተን ሰጠኝ፤ እንድንከባከባችሁም አደራ አለኝ። ልጆቼ ሆይ እኔ ለእናንተ የእግዚአብሔርን ቦታ ወስጄ በውክልና ቆሜአለሁ። ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀን እንደምጠየቅ አስቤ ልጠብቃችሁ ይገባኛል። የእናታችሁ ስም በሰማይ መጻሕፍት ውስጥ ግዴታዋን መወጣት ያልቻለች እናት ተብሎ እንዲፃፍ ትፈልጋላችሁ? እኔ መያዝ የነበረብኝን ቦታ ጠላት መጥቶ እንዲወርረው የፈቀደች እናት ተብሎ እንዲመዘገብ ትፈልጋላችሁ? ልጆች ትክክል የሆነውን እነግራችኋለሁ፤ እርስዋን እምቢ ብላችሁ የጥፋትን መንገድ ብትመርጡ እናታችሁ ከደሙ ንፁህ ናት፤ ነገር ግን በራሳችሁ ኃጢአት መቀጣታችሁ አይቀርም።” AHAmh 387.3
እንዲህ ነበር ከልጆቼ ጋር የማደርገው፤ ተናግሬ ሳልጨርስ ማልቀስ ይጀምራሉ፤ በመቀጠልም እንዲህ ይላሉ፡- “አትፀልይልንም?” ለመፀለይ ፈጽሞ እምቢ ብያቸው አላውቅም። ከጎናቸው ተንበርክኬ አብሬአቸው እፀልይ ነበር። ከዚያም ሄጄ ፀሐይ በሰማይ እስኪታይ ድረስ የጠላት መተት እስኪሰበር ድረስ፤ ሌሊቱን ሙሉ ጌታዬን እማፀነው ነበር፤ ድሉም የእኔ ነበር። የአንድ ሌሊት ሙሉ ድካም ዋጋ ቢያስከፍለኝም ልጆቼ አንገቴን ጠምጥመው “ኦ! እማማ እንድንሄድ በፈለግንበት ጊዜ ስላልፈቀድሽልን በጣም ደስተኞች ነን፤ ስህተት እንደነበር አሁን ገባን” ሲሉኝ ግን ያኔ በገፍ እንደተካስሁ ይሰማኛል። ወላጆች ሆይ እንደዚህ ነው ማድረግ ያለባችሁ፤ የምትሉት ከልባችሁ እንደሆነ አሳዩአቸው። ልጆቻችሁ በእግዚአብሔር መንግሥት ቦታ ይኖራቸው ዘንድ የምትፈልጉ ከሆነ ይህን የዕለት ተዕለት ተግባራችሁ አድርጉት።5 AHAmh 388.1
ግራ የሚያጋቡት የወጣትነት ዓመታት (Teen Ages) ችግሮች፡- አሁን ባለው የህብረተሰብ ሁኔታ ልጆቻቸውን ሊገድቡና በመጽሐፍ ቅዱስ የብርሃን መመሪያ ያስተምሯቸው ዘንድ ለወላጆች ቀላል ሥራ አይደለም። ልጆች ሁልጊዜ ትዕግሥት ያጣሉ፤ የፈለጉትን እንዲያደርጉ እንደፈለጉ እንዲወጡና እንዲገቡ መለቀቅ ይፈልጋሉ። በተለይም ከአሥር እስከ አሥራ ስምንት የዕድሜ ክልል ያሉ ልጆች ከዓለማዊ ስብስቦችና ወጣት ጓደኞች ጋር ጊዜ ቢያጠፉ ምንም ጉዳት እንደሌለው የሚሰማቸው ናቸው። ነገር ግን ልምድ ያካበቱት ክርስቲያኖች አደጋ ሲያንዣብብ ይታያቸዋል። ከልጆቻቸው ለየት ያሉ ባህርያት ጋር ስለተለማመዱ እነዚህ ተጽዕኖዎች በአዕምሮአቸው ላይ የሚያመጡትን ጉዳት ያውቃሉ። ይድኑ ዘንድ ካላቸው ፍላጎት የተነሣ በደስታ ከሚያቀልጡ ከነዚህ ፈንጠዝያዎች ሊጠብቋቸው ይገባል።6 AHAmh 388.2
ከመለወጥ በኋላ በንቃት መጠበቅ አስፈላጊ ነው፡- የዓለምን ደስታ ለመተውና የክርስቶስ ደቀ-መዝሙር ለመሆን ልጆች በራሳቸው ሲወስኑ ጥንቁቅና ታማኝ ከሆኑ ወላጆች ጫንቃ እንዴት ዓይነት ሸክም ነው የሚወርደው! ሆኖም ከዚያም ጊዜ በኋላ የወላጆች ጥረት መቆም የለበትም። እነዚህ ልጆች ኃጢአትን ለመዋጋትና የተፈጥሮአዊ ልብን ክፋት ለማሸነፍ በቅንነት ሥራ ጀምረዋል፤ ቀጣይ የሆነ የወላጆች ምክርና እንክብካቤ በተለየ ሁኔታ ያስፈልጋቸዋል።7 AHAmh 388.3
ከዓለማዊ ማራኪ ነገሮች ልጆችን የመጠበቅ ምሥጢር፡- ለቤታቸው ፍቅር ስለሌላቸው ልጆቻቸውን በቤት ውስጥ ማስቀረት ተስኗቸው የሚያለቅሱ ስንቶች ናቸው! ገና በልጅነታቸው ከወዘ-ልውጦች ጋር የመጎዳኘት ፍላጎት አላቸው፤ ዕድሜአቸው እንደደረሰም ማነቆና አግባብነት የሌለው ቁጥጥር እንደሆነ ከሚመስላቸው የወላጅ መመሪያ ሰብረው ይወጣሉ፤ የእናታቸውን ልመናም ሆነ የአባታቸውን ምክር አይሰሙም። ጉዳዩ ቢመረመር ኃጢአቱ ያለው በወላጆች ደጃፍ መሆኑ ይታያል። ወላጆች ቤት መሆን ያለበትን አላደረጉትም - በማራኪና ደግ ቃላት፣ በአስደሳች ፊትና በእውነተኛ የፍቅር ነፀብራቅ መሞላት የነበረበትን ቤት እንደሚፈለገው አላደረጉትም። ልጆቻችሁን ለማዳን የሚያስችል ምሥጢር ያለው ቤታችሁን ማራኪና ውብ በማድረግ ውስጥ ነው። ማሞላቀቅ ልጆችን ከእግዚአብሔር ጋርም ሆነ ከቤተሰቦቻቸው ጋር አያስተሳስራቸውም። ሆኖም አዕምሮን የሚያሠለጥንና የሚያስተምር ጥብቅ እግዚአብሔርን መሰል ተጽዕኖ ብዙ ልጆችን ከጥፋት ይታደጋቸዋል።8 AHAmh 388.4
የልጆቻቸውን መውጣትና መግባት ይቆጣጠሩ ዘንድ የወላጆች ኃላፊነት ነው። ወላጆቻቸው ለእነርሱ ጉዳዮች ግድ እንደሚላቸው የሚያሳዩአቸውን፣ የሚያበረታቷቸውንና ወደ ቤት የሚስቧቸውን ነገሮች ማቅረብ ይገባቸዋል። ቤትንም አስደሳችና ማራኪ ያድርጉት።9 AHAmh 389.1