የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ሰማንያ አንድ—የማይጠፉ እርካታዎችን የሚሰጡ መደሰቻዎች
እጅን አዕምሮንና ባህርይን የሚያሳድግ እንቅስቃሴ፡- የሚበልጠው ጥቅም የሚገኘው እንደ አካል ማፍታቻ ወይም ጨዋታ ብቻ ከሚወሰድ እንቅስቃሴ አይደለም። በንጹህ ከባቢ አየር ውስጥ በመሆን ወይም የጡንቻ እንቅስቃሴ ማድረግ የተወሰነ ጥቅም አለው። ነገር ግን ለጡንቻ እንቅስቃሴ የሚወጣውን ጉልበት ያህል አጋዥ ለሆኑ ሥራዎች ክንውንም ማዋል አለብን፤ ጥቅሙም የበለጠ ይሆናል፤ የመርካት ስሜትም ዕውን ይሆናል። ምክንያቱም እነዚህ እንቅስቃሴዎች የአጋዥነትንና የጠቃሚነትን ስሜት በመፍጠርና ኃላፊነትን በብቃት ማከናወን የመቻልን ማስረጃ ስለሚሰጡ የሕሊና እርካታ የሚያመጡ ናቸው።1 AHAmh 372.1
በሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ሁሉ እራሳቸውን የሚጠቅምና ለሌሎች አጋዥ የሆነ ተግባር ይፈፀምበት ዘንድ የወጣቶችና የልጆች ፍላጎት በዚህ አቅጣጫ ሊቀሰቀስ ይገባዋል። አዕምሮንና ባህርይን የሚያጎለብት እንቅስቃሴ፤ ልጆች ጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ በማስተማር ወጣቱ የድርሻውን የሕይወት ሸክም እንዲሸከም የማሰልጠን እንቅስቃሴ የሚባለው አካላዊ ጥንካሬ የሚሰጥና እያንዳንዱን ችሎታ የሚያሻሽል ዓይነቱን ነው። መልካም ለማድረግ፣ የመኖርን ልማድ ለሚያሳድግና ደግነትን ለተላበሰ ታታሪነት ደግሞ ሽልማት አለ።2 AHAmh 372.2
ለልጆችም ሆነ ለወጣቶች እራሳቸውን ብቻ የሚጠቅም መዝናኛ፣ ሌሎችን መርዳት የሚያስችላቸውን እንቅስቃሴ የማድረግን ያህል በረከት አያመጣላቸውም። ጉጉና በቀላሉ የመደመም ተፈጥሮ ያላቸው ወጣቶች አስተያየት ለመቀበልና ለመተግበር ፈጣን ናቸው።3 AHAmh 372.3
የየሱስ የወጣትነት ጊዜ ምሣሌነት፡- የየሱስ ሕይወት በታታሪነት የተሞላ ነበረ፤ የተለያዩ ሥራዎችን በማከናወን ከአካላዊ ጥንካሬው እድገት ጋር የሚስማማ እንቅስቃሴ ያደርግ ነበረ። እንዲሠራ የተወሠነለትን ሥራ በአግባቡ ይፈጽም ስለነበር እራሱን ብቻ የሚያስደስቱና ከንቱ ፈንጠዝያዎች ላይ ለመሳተፍ ጊዜ አልነበረውም። ግብረ-ገብነቱን የሚመርዝ ወይም አካላዊ ይዘቱን የሚያቆረቁዝ አንድም ነገር ላይ አልተሳተፈም፤ ነገር ግን ለጠቃሚ ተግባርና መከራን መቋቋም የሚያስችለው ሥልጠና ይወስድ ነበር።4 AHAmh 372.4
በምድራዊ ሕይወቱ ክርስቶስ ለሁሉም የሰው ዘር ምሣሌ ነበር፤ በቤት ውስጥም ታዛዥና ረዳት ነበር። የእንጨት ሥራ ንግድን በመማር በናዝሬት ትንሽ ሱቅ ውስጥ በገዛ እጆቹ ይሠራ ነበር… መጽሐፍ ቅዱስ ስለ የሱስ እንዲህ ይላል “ሕፃኑ ግን አደገ በመንፈስም ፀና ጥበብም ሞልቶበት። የእግዚአብሔርም ፀጋ በእርሱ ነበረችበት።” በልጅነቱና በወጣትነቱ ሲሠራ ሳለ አዕምሮውና አካሉ ይጎለብቱ ነበር። አካላዊ ጉልበቱን በማን-አልበኝነት አልተጠቀመበትም፤ ነገር ግን በሁሉም መስክ ሥራውን በብቃት ያከናውን ዘንድ ጤናማ የሚሆንበትን እንቅስቃሴ ያደርግ ነበር። በመሣሪያዎቹ አያያዝ እንኳ ግድፈት ያለበት ይሆን ዘንድ አልፈቀደም። በባህርይው ፍጹም እንደነበር በሠራተኛነቱም ፍጹም ነበረ። ለጠቃሚ ተግባር የሚገባውን ክብር በመመሪያነትና በምሣሌነት ክርስቶስ አሳይቷል።5 AHAmh 372.5
ሥራን በማለዋወጥ መነቃቃት፡- ለእያነዳንዳቸው ለተቸራቸው ዕድል፣ ለጊዜያቸው አጠቃቀምና ለተሰጣቸውም ችሎታ ሁሉ በትክክል ጥቅም ላይ ስለማዋላቸው እንደሚጠየቁ ወጣቶች ማስታወስ ይገባቸዋል። #የመፈንጠዣም ሆነ የመታደሻ ጊዜ ሊኖረን አይገባም?; ብለው ይጠይቁ ይሆናል፤ ያለምንም ፋታና የሥራ ለውጥ መሥራት፣ መሥራት አሁንም መሥራት ብቻ ነው?6 AHAmh 373.1
ኃይላቸውን አሰባስበው እንደገና መሥራት ይጀምሩ ዘንድ አቅማቸውን እጅግ ከሚያሟጥጠው የጉልበት ሥራ ዐረፍ ማለታቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ሆኖም ብዙ ዕረፍት የሚበጅ አይደለም፤ በተለይ ለአካል ጥንካሬአቸው ይህ የሚመከር አይደለም። በአንድ ዓይነት ሥራ ደክመው ባሉበት እንኳ ቢሆን በመናኛ ነገሮች ወርቃማ ጊዜያቸውን ማጥፋት ተገቢ አይደለም፤ ብዙም አድካሚ ወዳልሆነ ሥራ በመቀየር ለእናታቸውና ለእህቶቻቸው በረከት የሆነ ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል። መሸከም ያለባቸውን ከባድ ቀንበር በመሸከም፣ ችግራቸውን በማቃለል ከመርህ የሚመነጨውን እውነተኛ ደስታ የሚያፈልቀውን መዝናኛ ማግኘት ይችላሉ፤ ጊዜያቸውም በማይረባ ወይም የራስ-ወዳድ እርካታ ላይ አይጠፋም። ሁሉም ጊዜያቸው ለጥቅም ሊውል ይችላል፤ በሥራ ልውውጥም ሳያሰልሱ ሊታደሱ ይችላሉ፤ የሚፈጽሙት ተግባርም አንድ ሰው በመልካም የሚያወሳው ይሆንላቸዋል።7 AHAmh 373.2
ብዙዎች ራስ-ወዳድ በሆኑ መዝናኛዎች እራስን ማስደሰት አካላዊ ጤናን ለመጠበቅ አስፈላጊ ነው ይላሉ። አዕምሮና አካል ስለሚታደሱና ስለሚነቃቁ ለሰውነት እድገት ለውጥ አስፈላጊ ነው የሚባለው እውነት ነው። ነገር ግን ይህ ዓላማ የሚሳካው በቂል ፈንጠዝያዎች እራስን በማርካት ወጣቶች እንዲያከናውኗቸው የተገባቸውን ኃላፊነቶች በመተው አይደለም።8 AHAmh 373.3
እግዚአብሔር የባረከው መርሐ-ግብር ለተማሪዎች፡- የአዕምሮና የአካል ኃይላትን በተመጣጠነ ሁኔታ የሚያዳብር እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ወጣቶችን ማስተማር ይገባናል። ሁሉንም ብልቶች ያካተተ እንቅስቃሴ ሰፊና ሁለንተናዊ ትምህርት የሚሰጥ ነው። AHAmh 373.4
በዚህ ረገድ ወላጆችንና ወጣቶችን እናስተምር ዘንድ በአውስትራሊያ ከባድ ሥራ ነበረብን። ነገር ግን ሙሉና ፍጹም የሆነ ትምህርት ይኖር ዘንድ የጥናት ጊዜው፣ የመጽሐፍ ዕውቀት ለመቅሰምና ተግባራዊ ትምህርት ለማግኘት የመከፋፈሉን አስፈላጊነት እስኪማሩ ድረስ ጥረታችንን በጽናት መቀጠል ነበረብን። AHAmh 373.5
የእያንዳንዱ ቀን የተወሰነው ጊዜ በጠቃሚ ሥራ ይጠፋ ነበር፤ ተማሪዎች መሬቱን እንዴት እንደሚያስተካክሉ፣ እንዴት እንደሚያርሱና በተሰጣቸው የጊዜ ገደብ ቤቶችን እንዴት እንደሚገነቡ ይማሩ ነበር። ያ ባይሆን ኖሮ ጊዜያቸው በጨዋታና በፈንጠዝያ ፍለጋ ይጠፋ ነበር። የጠቃሚነት ትምህርትን ለመማር ጊዜያቸውን የሰውቱን ተማሪዎች እግዚአብሔር ባረካቸው።9 AHAmh 374.1
ለጤና ግንባታ እግዚአብሔር ጠቃሚ ሥራዎችን ሰጥቷል፤ እነዚህ ጠቃሚ ተግባራት ተማሪዎች ለራሳቸውና ለሌሎች ረዳት እንዲሆኑ ብቁ ያደርጓቸዋል።10 AHAmh 374.2
የመዝናናት ጥቅም ብቻ የሚሰጡ መጫዎቻዎችን ከማዘጋጀት ይልቅ በእግረመንገዳቸው መልካም ነገሮችን የሚያመርቱ እንቅስቃሴዎች እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል።11 AHAmh 374.3
ሚሲዮናዊ ሥራ በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ ነው፡- በጨዋታና በፈንጠዝያ የምናገኘው ደስታ ሙሉ በሙሉ አስፈላጊ አይደለም ወደማለት የሚያቀርቡን፣ ጠቃሚና አስፈላጊ የሆኑ በዓለማችን ሊሠሩ የሚገባቸው ብዙ ሥራዎች አሉ። አዕምሮ፣ አጥንትና ጡንቻ ጥብቅና ጠንካራ የሚያደርጋቸው ዓላማ ያዘለ መልካም ሥራእንዲተገብሩ፣ ጥልቅ አስተሳሰብ እንዲሁም የጭንቅላትን ኃይልና የአካል ብልቶችን ብርታት ለማጎልበት የሚያስችሉ እቅዶችን በመቅረጽ፣ በእግዚአብሔር የተሰጣቸውን ክህሎቶች በተግባራዊ ሥራ በመጥመድ ጌታን ሊያስከብር በሚችል ተግባር ላይ እንዲውል ማድረግ ይቻላል።12 AHAmh 374.4
እግዚአብሔር ለወጣቶች የሰጠውን አካልና አዕምሮ ለመልካምና ሌሎችን በሚጠቅም ሥራ ላይ ይውል ዘንድ እንድንጥር ኃላፊነት ወድቆብናል። እነዚህ ስጦታዎቻቸው የሌሎችን ድካም በማቅለል፤ ከሐዘናቸው በማጽናናት፤ ተስፋ የቆረጡትን በማንሣት፣ ተስፋ የሌላቸውን በማበረታታት፣ ከወንድነትና ከሴትነት ክብር ውጪ የሆኑትን የሚያሳፍሩትንና የሚያዋርዱትን ጨዋታዎችና ቡረቃዎች ተማሪዎች እንዲተው በማድረግ ተግባራዊ ሥራ እንዲያከናውኑ ወጣቶችን የማሠልጠን ግዴታ አለብን። አዕምሮአችን ከፍ ከፍ ያሉትንና የከበሩትን የጠቃሚነት መንገዶች ይይዝ ዘንድ እግዚአብሔር ይፈልጋል።13 AHAmh 374.5
ይህ የአዕምሮና የጡንቻ እንቅስቃሴ ኃይል ከእግዚአብሔር ጋር የሥራ ባልደረቦች የሚያደርጓቸው ሚሲዮናዊ ሥራዎችን እንዲሰሩ በማገዝ፣ መልካም መንገዶችንና ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ ከፍ ወዳለ እንቅስቃሴ ሊመራቸው ይችላል። የትምህርት ዋና ግብ ወደ ሆነው ተወዳዳሪ ወደሌለው ጠቃሚ ተግባር በመምራት በዚህ ምድር ሕይወት ከፍተኛ ሚና መጫወትን ሊያስተምራቸው ይችላል…. AHAmh 374.6
በክርስቶስ መንገድ መሥራት እያንዳንዱ ወጣት ሊያከናውነው የሚፈልገው ተግባር አይደለምን? የክርስቶስ ዕርዳታ አለላችሁ። የተማሪዎች ሐሳቦች ይሰፋሉ፤ ሰፊ ወሰንን የሚያካልሉ ይሆናሉ። የጠቃሚነት ኃይላችሁ በተማሪ ሕይወታችሁ እንኳ ያለማቋረጥ ያድጋል። በመጨረሻ “አዎን አንተ መልካም ባርያ የታመንህም” የሚለውን ድምጽ ትሰሙ ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ክንዶቻችሁንና እጆቻችሁን የሰማይን አሻራ የሚያዝል መልካም ሥራ ሥሩባቸው።14 AHAmh 375.1
ለአልጋ ቁራኛዎች የታዘዘ መድኃኒት፡- ሕሙማን ክፍሎቻቸውን ለቅቀው ወደ ውጭ በመሄድ ንጹህ አየር ቢቀበሉ፤ አበቦችን ቢንከባከቡ፤ ወይም ቀላልና አስደሳች ሥራ ቢሠሩ አዕምሮአቸው ሕመማቸውን ከማዳመጥ ወደ ጤና ሰጪ ነገሮች ዘወር ሊል እንደሚችል ተምሬአለሁ። በክፍት አየር ውስጥ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደ ጠቃሚና ሕይወት ሰጪ መድኃኒት ተደርጎ ሊታዘዝ ይገባል።15 AHAmh 375.2
የደስተኛ ወፎችን ዝማሬ ስንሰማና ዓይናችን በለመለመው መስክና የአትክልት ሥፍራ ስንመግበው፣ ከመደሰት ውጪ ሌላ የምንሆነው ነገር የለም። እግዚአብሔር በለጋስ እጁ በሰጠን ግርማ ሞገስ በተላበሱ ነገሮች ሁሉ ፍላጎት ያድርበት ዘንድ አዕምሮአችንን ልንጋብዘው ይገባናል። እነዚህን የበለጸጉ የፍቅሩንና የእንክብካቤውን መግለጫዎች ስናይ ጎዶሎአችንን ረስተን በሐሴት እንዋጥና በልባችን ጥዑመ-ዜማ ለጌታ እናቀርባለን።16 AHAmh 375.3
ሕሙማን ጤናቸውን እንደገና ለማግኘት ሲሉ የጉልበት ሥራቸውን ማቋረጣቸው ስህተት እንደሆነ እንዲማሩ በተደጋጋሚ ለብዙ ዓመታት እንዳይ ተደርጌአለሁ። እንዲህ በማድረጋቸው ስሜታቸው እየደነዘ የደማቸው ዝውውር እየደከመና የበለጠ ቆሻሻ እየሆነ ይሄዳል። በሽተኛው ካለበት ሁኔታ የባሰ እንደታመመ በሚያስብበት ጊዜ ሥራ መፍታቱ ወደ ጥልቅ ሐዘን እንደሚመራው ጥርጥር የለውም። በአግባቡ የተመዘነ ሥራ በሽተኛውን (አካል-ጉዳተኛውን) ሰው በዚህ ዓለም ሙሉ በሙሉ ዋጋቢስ እንዳልሆነና አሁንም ጠቀሜታ እንዳለው እንዲያስብ ያደርገዋል። ይህ እርካታን ይሰጠዋል፤ መጽናናትም ይሆነዋል፤ ለጭንቅላት መዝናኛነት የሚቀርቡ ከንቱ ጨዋታዎች ፈጽሞ ሊያደርጉት የማይችሉትን ጥንካሬ ያካፍለዋል።17 AHAmh 375.4
የእግዚአብሔር አቅርቦት ለእውነተኛ ደስታ፡- ሀብታምም ሆነ ድኃ በእኩል ሐሴት ያደርጉበት ዘንድ እግዚአብሔር ፍስሐ ለሁሉም አቅርቧል፡- ራስ-ወዳድነትን በሚጥስ ሥራና የሐሳብ ንጽህናን በሚያጎለብት ተግባር የሚገኘው ደስታ፤ የቸርነት ሥራዎችን በመሥራትና የርኅራኄ ቃላትን በመናገር የሚገኘው ደስታ ለሁሉም እንዲሁ በነፃ የተሰጠ ነው። ይህንን ተግባር ከሚፈጽሙ ሰዎች የሚወጣው የክርስቶስ ብርሃን በብዙ ትካዜ ሕይወታቸው ለጨለመባቸው የሚያፈካ ጮራ ይፈነጥቅላቸዋል።18 AHAmh 375.5