የአድቬንቲስት ቤት

81/88

ምዕራፍ ሰማንያ—ምን እንጫወት?

ክፉውን በመልካሙ ተኩ፡- ወጣቶች እንደ ሽማግሌዎች የተረጋጉና ኮስታራዎች፤ ልጆች እንደ አባቶች ደርባባ ሆነው እንዲቆዩ ሊደረጉ አይችሉም። በኃጢአት የተሞሉ ፈንጠዝያዎች መወገዝ የሚገባቸውን ያህል ሲኮነኑ ሳለ፣ በምትካቸው ግብረ-ገብነታቸውን የማይበርዙና የማያበላሹ ከኃጢአት ነፃ የሆኑ መጫዎቻዎችን ወላጆች መምህራንና አሳዳጊዎች ማቅረብ ይገባቸዋል። ወጣቶችን በግትር ሕጎችና ስነሥርዓቶች አጉብጣችሁ እንደተጨቆኑ እንዲሰማቸው በማድረግ፣ ቀንበራችሁን ሰብረው በመውጣት በችኮላ ወደ ስህተትና ጥፋት ጎዳና እንዲገቡ አታድርጓቸው። ዓላማቸውንና አስተሳሰባቸውን እየተቆጣጠራችሁና እየመራችሁ በልስላሴ፣ በጥበብና በፍቅር ሆኖ ለእነርሱ መልካም እንደምታስቡ ሊያውቁ በሚችሉበት መንገድ እየተገበራችሁ በጥብቅ ሆኖም በአሳቢና በበጎ እጅ የማስተዳደርን መስመር ያዙ።1 AHAmh 366.1

እንደ ዳንስ፣ ካርታ፣ ቼዝና ዳማ የመሳሰሉት ጨዋታዎች ቢኖሩም አዎንታችን የምንሰጣቸው አይደሉም፤ ምክንያቱም ሰማይ የሚያወግዛቸው ናቸው። እነዚህ መዝናኛዎች (amusements) ለታላቅ ርኩሰት በር የሚከፍቱ ናቸው። የሚፈጥሩት ዝንባሌ የሚጠቅም አይደለም። በአንዳንዶች ጭንቅላት የቁማርና የብኩንነትን ፍላጎት የሚፈጥሩ ናቸው። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ጨዋታዎች በክርስቲያኖች ሊወገዙ ይገባል። በምትካቸውም ፍጹም ጉዳት-አልባ የሆኑ መደሰቻዎች ሊዘጋጁ ይገባቸዋል።2 AHAmh 366.2

የማበላሸትና በስህተት መንገድ የመምራት ዝንባሌ ያላቸውን ዓለማዊ ደስታዎች ልጆቻችንን የምንከለክል ሆኖ ሳለ፣ የሚዝናኑባቸውን ነገሮች በማቅረብ አደጋ በሌለበት የደስታ ጎዳና እንዲጓዙ ማድረግ ግን ይኖርብናል። ማንም የእግዚአብሐር ልጅ የሆነ የሐዘንና የዋይታ ልምድ ሊኖረው አይገባም። መለኮታዊ ትዕዛዛትና ተስፋዎቹ የሚያሳዩን እንደዚህ እንደሆነ ነው፤ የጥበብ መንገድ “የደስታ መንገድ ነው መውጫና መግቢያዋም ሁሉ ሠላም ነው።” 3 AHAmh 366.3

ውሸትና ሰው ሠራሽ የሆነውን ሸሽተን ሳለ፤ ፈረስ ግልቢያውን(ጉግስ)፣ ካርታውን፣ ሎተሪውን፣ ገንዘብ አስይዞ መደባደቡን፣ አልኮል መጠጣቱን፣ ትንባሆ መጠቀሙን ገሸሽ አድርገን ሳለ፤ የደስታ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ንጹህ የከበሩና ከፍ ከፍ የሚያደርጉ መጫዎቻዎችን ግን ማቅረብ ይኖርብናል።4 AHAmh 366.4

የጅምናዚየም ትክክለኛ ቦታ፡- የአካል አንቅስቃሴ ጅምናዚየሞች በብዙ ትምህርት ቤቶች ጠቃሚ ሥፍራ ተሰጥቷቸዋል፤ ያለ ጥንቁቅ ቁጥጥር ግን ሁልጊዜ ከመጠን በላይ ይተገበራሉ። በጅምናዚየም ውስጥ ብዙ ወጣቶች የአካል ብቃት ጀብዱ ለመሥራት ሲሞክሩ የዕድሜ ልክ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በጅምናዚየም የሚደረግ እንቅስቃሴ ምኑንም ያህል በጥንቃቄ ቢተገበር፣ በተፈጥሮ ነፃ አየር የሚገኘውን መታደስ ግን ሊተካ አይችልም፤ በመሆኑም ትምህርት ቤቶቻችን ለዚህ የተሻለ ዕድል ማመቻቸት ይኖርባቸዋል።5 AHAmh 366.5

የኳስ ጨዋታ - መሠረታዊ አቅጣጫ ጠቋሚ መመሪያዎች፡- ከኳስ ጋር የሚደረገውን ቀላል እንቅስቃሴ አላወግዘውም ሆኖም ከመጠን በላይ መሆን የለበትም። AHAmh 367.1

እንደነዚህ ዓይነቶቹ ጨዋታዎች (amusements) በእርግጥ ሊያመጡት የሚችሉትን መዘዝ ሳይ እሸማቀቃለሁ። ክርስቶስን ሳያገኙ የሚጠፉትን ነፍሳት ወደ ብርሃን ለማምጣት መውጣት ያለበት ገንዘብ በነዚህ ጨዋታዎች ምክንያት ይባክናል። ራስን ለማስደሰት ሲባል የሚወጣው ገንዘብና መዝናኛ ቀስ በቀስ ራስን ከፍ ከፍ ወደማድረግ ይመራና ለእንደዚህ ያሉት ነገሮች ያለው ፍላጎትና ፍቅር እየጠነከረ ሄዶ ባህርይን ለመሞረድና ወደ ክርስቲያናዊ ፍጽምና ለማምጣት የማይስማማ ይሆናል። AHAmh 367.2

በኮሌጅም የሚተገበሩበት አኳኋን የሰማይን ማህተም ማግኘት የማይችል ነው። አዕምሮን አያዳብርም፤ ባህርይን አያነጥርም፤ አያጠራምም። ወደ ዓለማዊ አድራጎቶች፣ ባህሎችና ወጎች የሚመሩ ቅደም ተከተል የያዙ ሐሳቦች አሉ፤ ተዋናዮቹም በነዚህ ነገሮች ተውጠውና ደንዝዘው ከእግዚአብሔር አፍቃሪነታቸው የበለጠ ተድላን የሚወዱ ተብለው በሰማይ የሚወሱ ይሆናሉ። ጭንቅላትን በማጎልመስ እንደ ተማሪ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲፈጽሙ በማድረግ ፈንታ፤ እንደ ክርስቲያን መሥራት ያለባቸውን ሥራ መከወን እንዲችሉ ብቁ ክርስቲያኖች በማድረግ ፈንታ፤ እነዚህ ጨዋታዎች (games) አዕምሮአቸውን በመሙላት ከኃላፊነታቸው የሚያዘናጓቸውን ሐሳቦች ያበዙባቸዋል…. AHAmh 367.3

በእነዚህ ግጥሚያዎች ዐይን ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የተሰጠ ነውን? እንዳልሆነ አውቃለሁ። የጌታን መንገድና የዓላማውን ዕይታ ስተዋል። በዚህ የአመክሮ ጊዜ ልዩ የማስተዋል ችሎታ የተሰጠው ፍጡር የእግዚአብሔርን የተገለጸ ፈቃድ ገሸሽ በማድረግ በምትኩም በራሱ ግምታዊና ፈጠራዊ ጥበብ እየተካቸው ነው፤ በሥራ አስፈጻሚነቱም ሰይጣን ከጎኑ ቆሞ በመንፈሱ ሊሞላው ተዘጋጅቷል… እጅግ በሚመስጡት ግጥሚያዎች አሸናፊ ለመሆን ያለውን የሚነድ ስሜት ሰማያዊ ጌታ እግዚአብሔር የሚቃወመው ነው።6 AHAmh 367.4

የብዙ የሰውነት እንቅስቃሴዎች (athletic-sports) ችግር፡- ተማሪዎች ጠንከር ያሉ እንቅስቃሴዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ከስንፍናና ከዓላማ-የለሽነት የባሰ የሚፈሩ ብዙም ጥፋቶች የሉም። ሆኖም ይህ የሰውነት ቅልጥፍናና እንቅስቃሴ ለወጣቱ ደህንነት ለሚያስቡ ሁሉ የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ ሆኗል። በትምህርት ቤት ባላቸው መሻሻልና ከዚያም ቀጥሎ ባላቸው ሕይወት የእነዚህ የአካል እንቅስቃሴዎች ተጽዕኖ መምህራንንም የሚያሳስባቸው ሆኗል። ሰፊውን ጊዜ የሚውስዱት ግጥሚያዎች አዕምሮን ከጥናት ያዘናጉታል። እነዚህ ጨዋታዎች በሕይወት ለሚያጋጥማቸው ተግባራዊና ከባድ ኃላፊነቶች ወጣቶችን የሚያዘጋጁ አይደሉም። ተጽዕኗቸው ወደ ንጥረትና ለጋሥነት ወይም ወደ እውነተኛ የወንድ ባህርያት የሚመሩ አይደሉም። AHAmh 367.5

እጅግ በጣም ከሚወደዱት ጨዋታዎች መካከል እግር ኳስና የቦክስ ግጥሚያ የጭካኔ ትምህርት ቤቶች ሆነዋል። ጥንታዊ ሮም ስታካሂድ የነበረውን ግጥሚያ የሚመስሉ ባህርያትን እያስፋፉ ነው። የበላይነት ፍቅር፤ የጭካኔ ኃይል በማሳየት ብቻ የሚታየው መኮፈስ እንዲሁም ለሕይወት የሚንፀባረቀው ግድ-የለሽነትና ቸልተኝነት በወጣቱ ላይ የሚያሳድረው ግብረ-ገብነትን የመግደል ተጽዕኖ አስደንጋጭ ነው። AHAmh 368.1

ሌሎችም የአትሌቲክስ ጨዋታዎች የጭካኔ ተግባር በብዛት ባይተገበርባቸውም ከመጠን ያለፉ ስለሆኑ ተቃውሞ የሚቀርብባቸው ናቸው። ለሐሴትና ደስታ ያለውን ስሜት በማነሣሳት ለጠቃሚ ሥራ ያለውን ጥላቻ በማበረታታትና ተግባራዊ ግዴታዎችንና ኃላፊነቶችን የመሸሽ ጠባይን በማጎልበት የሚጎዱ ናቸው። ከዚያም አሰቃቂ ውጤት ተጎናጽፈው ለሚመጡት ብኩንነትና ሕግ-አልበኝነት በሩ ወለል ተደርጎ ይከፈታል።7 AHAmh 368.2

ሕይወት እምብዛም ውስብስብ ባልነበረበት ጊዜ፡- በጥንት ዘመን ሰዎች በእግዚአብሔር ምሪት ሥር በነበሩበት ጊዜ ሕይወት ውስብስብ አልነበረም። ከተፈጥሮ እንብርት አጠገብ ነበር የሚኖሩት። ልጆች የወላጆቻቸውን ሥራ በመጋራት የተፈጥሮ ግምጃ ቤት የነበራትን ውበትና ምሥጢር ያጠኑ ነበር። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን እንደ ከበረ ቅርስ የሚቆጠረውን ታላቅ እውነት እያሰላሰሉ በዚያ ፀጥ ባለው መስክና ጫካ ይመላለሱ ነበር። ይህ ዓይነቱ ሥልጠና ጠንካራ ሰዎችን ያፈራ ነበር። AHAmh 368.3

በዚህ ዘመን ኑሮ ሰው ሠራሽ ሆኗል፤ ሰዎቸም ቆርቁዘዋል። ድሮ ወደ ነበረው ቀላል የሆነ ሕይወትና ልማድ ሙሉ በሙሉ መመለስ ባንችልም ስሙ የሚወክለውን ትክክለኛ የመዝናናት ትርጉም ግን ከእነርሱ ልንማር እንችላለን፤ እርሱም የመዝናኛ ጊዜውን እውነተኛ የአካል፣ የአዕምሮና የነፍስ ግንባታ ወቅት ማድረግ ነው።8 AHAmh 368.4

የቤተሰብ ሽርሽር፡- በመንደር ወይም በከተማ የሚኖሩ ብዙ ቤተሰቦች አንድ ላይ ተሰባስበው ወደ ገጠር ወጣ በማለት ባማረ ሐይቅ ዳር ወይም ውብ የተፈጥሮ ገጽታ በሚታይበት ጫካ አጠገብ በማረፍ አካላቸውንና አዕምሮአቸውን ከበዘበዘው ሥራቸው እፎይ ይበሉ። ቀላልና ንጹህ ምግብ ለራሳቸው በማዘጋጀት ጠረጴዛቸውን በዛፍ ጥላ ሥር ወይም በሰማይ ጣራ ሥር በመዘርጋት ከሁሉም የሚበልጡትን ፍራፍሬዎችና ጥራጥሬዎች ይመገቡ። ሩጫው እንቅስቃሴውና የአካባቢው ትዕይንት የምግብ ፍላጎት ይቀሰቅሳል፤ ነገሥታት የሚቀኑበትን ምግብ እነርሱ መብላት ይችላሉ። AHAmh 368.5

በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት ወላጆችና ልጆቻቸው ጭንቀታቸውን፣ ሥራቸውንና ግራ መጋባታቸውን መርሳት ይኖርባቸዋል። በሚችሉት ሁሉንም ነገር አስደሳች በማድረግ ከልጆቻቸው ጋር ሲሆኑ ወላጆች እንደልጆች ይሁኑ። ቀኑ በሙሉ የመዝናኛ ጊዜ ይሁን። የሥራቸው ሁኔታ ከበር ለማያስወጣቸውና ታቁረው ለከረሙ በሰፊውና በክፍቱ አየር ቢመላለሱ ጤናቸው ይመለስላቸዋል። ማድረግ የሚችሉ ሁሉ ይህ ኃላፊነታቸው እንደሆነ ይሰማቸው። ምንም የሚጠፋ ነገር የለም፤ እንዲያውም ብዙ ይተረፋል። ሥራቸውን በጉጉት ለማከናወን ወደ ኃላፊነታቸው በአዲስ ሕይወትና በአዲስ ብርታት ይመለሳሉ። በሽታንም ለመቋቋም የተሻለ ዝግጅት ያደረጉ ይሆናሉ።9 AHAmh 369.1

በተፈጥሮ ድማማት ሐሴት አድርጉ፡- ለኛ ደስታ ሲባል የተፈጠረልንን ጥለነው እንሄድ ዘንድ በማስቀመጥ እንዳንጠቀምበት እግዚአብሔር የሚፈልግብን እንዳይመስላችሁ። እንድንተወው የሚፈልግብን ብናስቀምጠው ለመልካም የማይሆንልንን ብቻ ነው። ግርማ ሞገስ ያላቸውን ዛፎች በቅጠል ያለበሰ፤ ውብና ማራኪ አበቦችን የለገሰን፤ የምናያቸውን ተፈጥሮአዊና ያማሩ የእጁን ሥራዎች የሰጠን እግዚአብሔር የተከፋን እንሆን ዘንድ እቅዱ አይደለም። በነዚህ ነገሮች ጣዕምና ደስታ እንዳይኖረን አላጨንም። ደስ እንሰኝባቸው ዘንድ ዓላማው ነው። በተፈጥሮ ውበት ደስ ይለን ዘንድ የእርሱ ንድፍ ነው- እነርሱም ድንቅ የእጁ ሥራዎች ናቸውና።10 AHAmh 369.2

ትርፋማ ማህበራዊ ስብሰባዎች፡- የሚሰበሰቡት ሰዎች የእግዚአብሔር ፍቅር በልባቸው ደምቆ የሚያበራ ሲሆን፤ ሲገናኙ ስለ እግዚአብሔር ቃል የሚነጋገሩ ወይም ሥራውን ወደ ፊት ለመግፋት መንገድ የሚቀይሱና ለሰዎች መልካም የሚያደርጉ ሲሆኑ፤ ግንኙነታቸው ወደር የሌለው ትርፍና ትምህርት ይሆንላቸዋል። መንፈስ ቅዱስ በእውነት በሚጋበዝበት ስብሰባ ላይ እርሱ አዝኖ እንዲለያቸው የሚያደርገው ምንም ነገር ካልተባለና ካልተሠራ እግዚአብሔር ይከብራል፤ የሚገናኙትም ይታደሳሉ፤ ይጠነክራሉ።11 AHAmh 369.3

ስብሰባችን መካሄድ ያለበት ራሳችንንም መቆጣጠር ያለብን ከሰውም ሆነ ከእግዚአብሔር ቅያሜ ነፃ የሆነ ሕሊና እንዲኖረን ሆኖ፣ አብረውን ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል የጎዳነው ወይም ያቆሰልነው ወይም ተጽዕኖአችን ጎጂ የሆነበት አንድም ሰው እንዲኖር በማናደርግበት ሁኔታ መሆን አለበት።12 AHAmh 369.4

በንጹህ የደስታ ትዕይንቶች የሱስ እርካታ አግኝቷል፡- ራስን ማዕከል ያደረገን ማንኛውንም እርካታ የሱስ ተቃውሞታል፤ ሆኖም እርሱ በተፈጥሮው ማህበራዊ ነበር። የሁሉንም መደቦች መስተንግዶ አሺ ብሎ ተቀበለ፤ የድኃውንም፣ የሀብታሙንም፣ የምሁሩንም፣ ያልተማረውንም ቤት ጎበኘ፤ ጎሰኛ አስተሳሰባቸውንም ከተራ ዓለማዊ የሕይወት ጥያቄዎች ወደ መንፈሳዊና ዘለዓለማዊ ዕይታ አሳደገው። ለብኩንነት ፈቃድ አልሰጠም፤ የዓለማዊ የቅብጠት ጥላም ጠባዩን አልበከለውም። ሆኖም ንጽህናቸውን በጠበቁ መደሰቻዎች ደስ ይለው ነበር፤ መገኘቱም ማህበራዊ ስብሰባዎችን ቀድሷል። የአይሁድ የጋብቻ በዓል ግሩም ጊዜ ነበር። የሠርጉም ደስታ የሰውን ልጅ [የሱስን] የሚያስከፋው አልነበረም… የሠርጉ ደስታ የሱስ ሙሽራዋን ወደ አባቱ ቤት ሲያመጣት የሚኖረውን ተድላ አመላካች ነበር። የተዋጁትና አዳኛቸው አንድ ላይ ቁጭ ብለው የበጉን የሠርግ እራት የሚበሉበትን ቀን ያስታውሰው ነበር።13 AHAmh 369.5

የንግግርና የጠባይ አርዓያነቱ፡- ሥራውን ሲቀጥል በቀራጮችም ሆነ በፈሪሳዊያን ድግስ ለእራት ሲጋበዝ ግብዣውን ይቀበል ነበር… በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት በጠረጴዛ ዙሪያ የሚደረጉ ንግግሮችን የሱስ በቀዳሚነት በመቆጣጠር ብዙ ወርቃማ ትምህርቶችን ሰጥቷል። በቦታው የነበሩት ያዳምጡት ነበር፤ ምክንያቱም የታመሙትን አልፈወሰምን? ሐዘናቸውን አላጽናናምን? ልጆቻቸውን በእቅፉ ይዞ አልባረካቸውምን? ቀራጮችና ኃጥአን ወደርሱ ይሳቡ ነበር፤ ለመናገር አፉን ሲከፍት ትኩረታቸው በሞላ ከእርሱ ጋር ይጣበቅ ነበር። AHAmh 370.1

በሚያምኑም ሆነ በማያምኑ መካከል ሲሆኑ ባህርያቸው ምን መምሰል እንዳለበት ክርስቶስ ደቀ-መዛሙርቱን አስተምሮአቸዋል። በማንኛውም ሕዝባዊ ስብሰባ በሚሳተፉበት ጊዜ አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ምንም ማለት እንደሌለባቸው በምሣሌ ነገራቸው። ነገር ግን የእርሱ ንግግር በድግሶች ላይ ሲደመጡ ከነበሩት ፈጽሞ የተለየ ነበር። የሚናገረው እያንዳንዱ ቃል ለሚያደምጡት የሕይወት ሽታ ያለው ነበር። ዓላማዬ ብለው በፍላጎት እንደሚሰሙት ሆነው በተሰበረ ል ብ ያዳምጡት ነበር።14 AHAmh 370.2

ኤለን ጂ.ዋይትና የሚያስደስት ማህበራዊ ስብሰባዋ፡- ወደ ምሥራቅ ባደረግሁት ረዥም ጉዞ መጨረሻ የአዲስ ዓመት ዋዜማን በቤቴ ለማክበር ሄልድስበርግ በጊዜ ደረስኩኝ። የኮሌጁ አዳራሽ ለሰንበት ትምህርት የአንድነት ጊዜ ተዘጋጅቶ ነበር። የቆጵሮስ ጉንጉን የመከር ቅጠሎች፣ አረንጓዴ ዕፀዋትና አበቦች በሚማርክ ሁኔታ ተቀምጠው ነበር። በመግቢያው በር ጉበን አረንጓዴ ዕፀዋት ተንጠልጥለዋል። ዛፉ ለድኆች ዕርዳታ በሚሆንና ደወል ለመግዛት በሚያስችሉ ሥጦታዎች ተንዠርግጎ ነበር…. በዚህ ጊዜ የሌሎችን ሕሊና በሸክም የሚያጎብጥ ምንም ነገር አልተባለም፤ አልተሠራምም። AHAmh 370.3

አንዳንዶች እንዲህ አሉኝ:- “እህት ዋይት እንዴት አየሺው? እምነታችንን መሠረት ያደረገ ነው?” መለስኩላቸው “አዎ እምነቴ ነው” [አልኳቸው]።15 AHAmh 370.4

በሚያሸንፍ ኃይል ወጣቱን ሳቡ፡- እያንዳንዱ ቤተሰብና እያንዳንዱ ቤተክርስቲያን ከሚወሰውሰው የዓለም ደስታና የማበላሸት ዝንባሌ ካለው የጉድኝት ተጽዕኖ ወጣቱን ለማራቅ አሸናፊ ኃይል መጠቀም እንዳለበት እግዚአብሔር ያሳስበዋል። ወጣቱ ለየሱስ እንዲሸነፍ ጥናት አድርጉ።16 AHAmh 370.5