የአድቬንቲስት ቤት

76/88

ምዕራፍ ሰባ አምስት—የወላጆች ምሪት በማህበራዊ ጉዳዮች

የክፋት ተጽዕኖን መቋቋም እጅግ ከባድ ነው፡- በልጆቻችን ዙሪያ ያለው የክፋት ተጽዕኖ በቀላሉ ሊያሸንፋቸው የሚችል ነው። አስተሳሰባቸውን እያበላሸ ወደ ጥፋት እየመራቸው ነው። የወጣቶች አዕምሮ በተለምዶ ለከንቱነት የተሰጠ ሆኗል። ገና በልጅነታቸው፣ ባህርያቸው መሠረት ሳይጥልና አመዛዛኝነታቸው ሳይጎለምስ የሚጎዳ ተጽዕኖ ካላቸው ጋር ወዳጅ የመሆን ዝንባሌ ይታይባቸዋል።1 AHAmh 341.1

በምድር ሁሉ ላይ ወዳሉ ወላጆች ድምጼ የሚደርስ ቢሆን አጋሮቻቸውንና ጓደኞቻቸውን በመምረጥ ረገድ ለልጆቻቸው ፍላጎት እጅ እንዳይሰጡ አስጠነቅቃቸው ነበር። ከመለኮታዊ አሻራ ይልቅ የሚጎዱ ተጽዕኖዎች በወጣቱ ዘንድ በቀላሉ ተቀባይነት እንደሚያገኙ ወላጆች እምብዛም አያስቡም። ስለዚህ የሚመሠርቱት ጓደኝነት በቃሉ የተገለጸው እውነት በልባቸው ይታነፅ ዘንድ ለፀጋ እድገት እጅግ ተስማሚ ሁኔታን የሚፈጥር መሆን አለበት።2 AHAmh 341.2

በሚቻለው ሁሉ ወጣቶች እጅግ ተስማሚ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ይለፉ። የሚሆኗቸው ጓደኞች የሚቀበሏው መርሆችና የሚመሠርቱት ልማድ በአስተማማኝ ሁኔታ እርግጥ የሆነውን የዘለዓለም ፍላጎታቸውን እንዲሁም በዚህ ምድር የሚኖራቸውን የጠቃሚነት ጥያቄ የሚመልስ ነው።3 AHAmh 341.3

ያልተገደበ ነፃነት ጉዳቶች፡- ወላጆች! ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሥነሥርዓት ከአደጋ የተጠበቁ አይደሉም። ያለ እናንተ ፈቃድና ዕውቀት እንዳሻቸው ሊሔዱና ሊመጡ ፈጽሞ ሊፈቀድላቸው አይገባም። በዚህ ዕድሜያቸው ልቅ የሆነ ነፃነት ለሺዎች መጥፋት ምክንያት እንደሆነ ተረጋግጧል። ስንቶች ናቸው በውድቅት ጎዳና ላይ የሚሆኑት፤ ወላጆችም አብረዋቸው ስላሉት ጓደኞቻቸው ግድ አይላቸውም። ብዙውን ጊዜ ደግሞ የሚመርጧቸው ጓደኞች የግብረ-ገብነት ደረጃቸውን ዝቅ የሚያደርጉባቸው ናቸው። AHAmh 341.4

ጨለማን ሽፋን አድርገው ወንዶች ልጆች በቡድን ይሰበሰቡና የካርታና ቁማር አጨዋወት፣ የማጨስና የወይን ወይም የቢራ አጠጣጥ የመጀመሪያውን ትምህርት ይማራሉ። የአማኞች ወንድ ልጆች ወደ ምግብ ቤቶች ጎራ ብለው የዛጎል ለበስ አሳ (oyster) እራት ወይም ሌላ የሚያረካቸውን ነገር ያዛሉ፤ በዚህም አካሄዳቸው እራሳቸውን በፈተና ውስጥ ይጨምራሉ። የእነዚህ መዝናኛዎች ከባቢ አየር ልዑሉን የሚያሰድብና የብክለት ሽታ ያለው ነው። ማንም በዚህ ቦታ ለረጅም ጊዜ ቆይቶ ሳይበላሽ አይወጣም። በእንደዚህ ዓይነቱ ቅርርቦሽ ምክንያት ተስፋ ያላቸው ወጣቶች ሰካራሞችና ወንጀለኞች ሆነው ይቀራሉ። መከልከል ያለበት የመጀመሪያው የክፋት ሥራ ነው። ወላጆች ሆይ አካባቢያችሁ ነቀፌታ ሊቀርብበት የማይችል ካልሆነ በስተቀር ከሌሎች ወንዶች ልጆች ጋር ለመዝናናት ወይም ለመጫወት ከመሸ በኋላ ወደ ውጭ እንዲወጡ ለልጆቻችሁ አትፍቀዱ። ይህ ህግ በጥብቅ እንዲከበር ከተደረገ ታዛዥነት የተለመደ ይሆናል፤ ለመጣስም ያለው ፍላጎት ሳይቆይ ይጠፋል።4 AHAmh 341.5

የልጆቻቸውን ጓደኞች ወላጆች መምረጥ አለባቸው፡- የዘቀጠ ግብረገብነትና ሸካራ ባሕርይ ካላቸው ጋር ጓደኝነት መመሥረት በወጣቶች ላይ አደገኛ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ወላጆች መዘንጋት የለባቸውም። ለልጆቻቸው መልካም ጓደኞችን መምረጥ ካልቻሉ ባሕርያቸው ጥያቄ ውስጥ ከሚገባው ጋር እንዲቀራረቡ ከፈቀዱላቸው የነውረኛነትን ትምህርት የሚያስተምርና የሚተገብር ትምህርት ቤት አስገቧቸው ወይም እንዲገቡ ፈቀዱላቸው ማለት ነው። ልጆቻቸው ፈተናን ለመቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ እንዳላቸው ሊሰማቸው ይችላል፤ ግን እንዴት እርግጠኛ መሆን ይችላሉ? ለክፋት ተጽዕኖዎች እጅ መስጠት ከመቋቋም እጅግ የቀለለ ነው። ወደ ማስተዋል ከመምጣታቸው በፊት ልጆቻቸው በሚያሽቆለቁል ወይም በሚያጠፋ የጓኞቻቸው መንፈስ ተሞልተው ያገኟቸው ይሆናል።5 AHAmh 342.1

በተመሳሳይ ዕድሜ ክልል ውስጥ ወዳሉ የተለያየ የሕይወት ባሕርይና ልማድ ወዳላቸው ወጣቶች መሐል ሲገቡ ልጆችን የሚገጥሟቸው አደጋዎች በእጅጉ ይጨምራሉ። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ጥረታቸውን እጥፍ አድርገው ልጆቻቸውን በመጠበቅና በመቆጣጠር ፈንታ ወላጆች ልል መሆ ን ይጀምራሉ።6 AHAmh 342.2

በአንድነትና በፀሎት አባትና እናት ልጆቻቸውን ወደ እውነት የመምራት ከባድ ሸክማቸውን በብቃት ሊወጡት ይገባቸዋል። ሌላ ምንም ነገር ቸል ሊሉ ቢችሉ እንኳ ወደ ጥፋት መንገድ ይሔዱ ዘንድ ልጆቻቸውን ፈጽሞ ሊለቋቸው አይገባም። ብዙ ወላጆች ልጆቻቸው የፈለጉትን እንዲያደርጉ እራሳቸውን እንዲያዝናኑና መጥፎ ጓደኞች እንዲኖሯቸው ይፈቅዳሉ። በቤታቸው ቁጥጥር ተደርጎባቸው ባለማደጋቸው የተነሣ ልጆቻቸው ሰማይ እንደቀረባቸው እንዲህ ዓይነቶቹ ወላጆች በፍርድ ቀን የሚገነዘቡት ይሆናል።7 AHAmh 342.3

ምሽቱ የሚጠፋው የት ነው?፡- በማታ ቤት ውስጥ የሌሉ ከሆነ ለምን እንደሌሉ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች መጠየቅ አለባቸው። ከማን ጋር እንደሆኑና ምሽቱን በማን ቤት ውስጥ እንዳሳለፉት ወላጆች ማወቅ ይኖርባቸዋል። የተሳሳተ አካሔዳቸውን ለመደበቅ አንዳንድ ልጆች ወላጆቻቸውን ያታልላሉ።8 AHAmh 342.4

ያልታረሰን መሬት አረም ይወርሰዋል፡- በአብዛኛው ልጆች የራሳቸውን መዝናኛዎች፣ ጓደኞችና ሙያ እንዲመርጡ አባቶችና እናቶች ይተዉአቸዋል። ውጤቱን ዐይቶ መፍረድ አያቅትም። እርሻን ሳይታረስ ብትተውት እሾህና ቁጥቋጦ ያበቅላል። የሚያምር አበባ ወይም የሚወደድ ተክልን ለማየት ብትሹም ደስ ከማይሉና ከመርዛማ አረሞች በላይ ብቅ ብለው ልታዩዋቸው አትችሉም። ጥቅም የሌለው ቁጥቋጦ ጥንቃቄ ሳያስፈልገው ያለ ሐሳብና ችግር በምቾት ተንዠርግጎ ሲያድግ፣ ለጥቅም ወይም ለውበት የሚፈለጉት እፀዋት ግን የተሟላ እንክብካቤ ይፈልጋሉ። ወጣቶችም ልክ እንደዚህ ናቸው፤ መልካም ልማድ እንዲቀረጽባቸውና ትክክለኛ መመሪያዎች እንዲመሠርቱ ከተፈለገ ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ ማለት ነው። መጥፎ ልማዶች እንዲስተካከሉ ከተፈለገ ሥራውን በአግባቡ ለመፈፀም ትጋትና ጽናት አስፈላጊዎች ናቸው።9 AHAmh 343.1

በወላጆች አስተያየት ልጅ አመኔታ እንዲኖረው አለማምዱት፡- ወላጆች ሆይ የልጆቻችሁን ልማዶችና መርሆች እንደ ዓይናችሁ ብሌን ተጠንቅቃችሁ ያዟቸው። ባሕርይው በደንብ ከማይታወቅ ሰው ጋር ወዳጅ እንዲሆኑ አትፍቀዱ። ምንም ጉዳት እንደማያመጣባቸው እርግጠኛ እስክትሆኑ ድረስ ጓደኝነት እንዲመሠርቱ አትፍቀዱላቸው። ልምድ ከማጣታቸው የተነሣ በቀላሉ ሊስቱ ስለሚችሉ እናንተ በተሞክሯችሁ ባሕርይን መገምገምና በተሻለ ጥራት ማየት እንደምትችሉ ውሳኔአችሁም ቸል ሊባል እንደማይገባ ንገሯቸው።10 AHAmh 343.2

መከልከላችሁ ፍንክች የማይል ሆኖም ቸርነትን የተላበሰ ይሁን፡- ወላጆች ለልጆቻቸው ዝንባሌ ሁሉ እሺ ማለት የለባቸውም። እግዚአብሔር የቀደደውን ፈር የኃላፊነት ጎዳና እንዲከተሉ በማገዝ የተሳሳተ ፍላጎታቸውን በቸርነት ነገር ግን በቆራጥነትና በጥብቅ ውሳኔ በመገደብ ብሎም በመንፈግ ፀሎት በተሞላበት ልባዊና የፀና ጥረት ከዓለም እንዲሸሹ በመርዳት ወደ ሰማይ ጉዞ እንዲጀምሩ መምራት ይጠበቅባቸዋል። ልጆች በዝንባሌአቸው እንዲሰጥሙ መለቀቅ የለባቸውም፤ በሁሉም አቅጣጫ ክፍት በሆኑ መንገዶች በመራመድ ከእውነት ፈቀቅ እንዲሉ አንተዋቸው። አደጋን እንደማያስተውሉ ለምክርና ለማስጠንቀቂያ ትዕግሥት እንደሌላቸው ልጆች ፈተና የተጋረጠበት የለም።11 AHAmh 343.3

ልትቃወሙት ከሚገባችሁ ተጽዕኖ በተቻላችሁ መጠን ልጆቻችሁን ጠብቁ። ምክንያቱም ሕጻናት እያሉ የግብረ-ገብነት ክብር፣ ንጽህናና የባሕርይ መልካምነት ወይም ራስ-ወዳድነት፣ ቆሻሻነትና እምቢተኛነት ለመቀበል የተዘጋጁ ናቸው። አንድ ጊዜ በማጉረምረም በትዕቢት በከንቱነትና በቆሻሻነት መንፈስ ተጽዕኖ ሥር ከሆኑ በኋላ ብክለቱን ለማስለቀቅ ሕይወትን 344 የአድቬንቲስት ቤት የማጥፋት ያህል ይከብዳል።12 AHAmh 343.4

ወጣቶች ሥርዓት ላለው ነገር አሻፈረኝ ማለታቸው ምክንያቱ የወሰዱት የቤት ውስጥ ሥልጠና ግድፈት ስላለበት ነው። እኔ እናት ነኝ፤ የምናገረውን ስለማውቀው ነው ይህንን የምለው። ወጣቶች ከአደጋ የተጠበቁ ብቻ ሳይሆኑ ደስተኛም የሚሆኑ ጤናማ ቁጥጥር ሲደረግባቸው እንጂ የራሳቸውን ዝንባሌ እንዲከተሉ ሲለቀቁ አይደለም።13 AHAmh 344.1

የብቻ ጉብኝት የሚመከር አይደለም፡- አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው ከልክ ያለፈ ነፃነት በመስጠት ስህተት ይሰራሉ። በልጆቻቸው ላይ አመኔታ ከማኖራቸው የተነሣ አንዳንድ ጊዜ ጥፋታቸውን እንኳን አያስተውሉም። ልጆች ወላጅ ወይም አሳዳጊ አብሯቸው ሳይሆን ብቻቸውን ሩቅ ቦታ ሔደው እንዲጎበኙ ማድረግ ስህተት ነው። ይህ በልጆች ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ነው። ትልቅ ዋጋ ያለው ሆኖ እንዲሰማቸውና የተወሰኑ መብቶችም የተገቧቸው እንደሆኑ እንዲያስቡ ያደርጋል። ይህ ፍላጎታቸው ካልተሟላም በወላጆቻቸው የተጎሳቆሉ ይመስላቸዋል። በነፃ ተለቅቀው ስለሚሔዱና ስለሚመጡ ሌሎች ልጆችን በመጥቀስ ጓደኞቻቸው ብዙ መብቶች ተሰጥቶአቸው ሳለ እነርሱ የተገደቡት ለምን እንደሆነ ይጠይቃሉ። AHAmh 344.2

እናትም ልጆችዋ #ሚዛናዊ አይደለችም; ብለው እንዳይፈርጇት በመፍራት ለጥያቄአቸው እሺ ትላለች፤ ሆኖም በመጨረሻ ይህ አካሄድ ጎጂ እንደሆነ ይረጋገጣል። የወላጆቻቸው ጥበቃ የሌላቸው ወጣት ጎብኚዎች ይዘውት የሚመለሱትን ጎጂ ልምድ ለማስወገድ ስህተታቸውን ለማየትና ለማስተካከል ይችሉ ዘንድ ለመርዳት ወራት ይፈጃል።14 AHAmh 344.3

ጥበብ የጎደለው ምክርና የማምከኛው ዘዴ፡- ልጆቻችሁ በቤታችሁ አርፈው እንዲቀመጡ አድርጓቸው። ሰዎች “የእናንተ ልጆች በዚህ ዓለም እራሳቸውን እንዴት እንደሚያስተዳድሩ አያውቁም” ቢሏችሁ ያ ጉዳይ እንደማያስጨንቃችሁ ለወዳጆቻችሁ ንገሯቸው። ነገር ግን የጥንት እናቶች ልጆቻቸውን ወደ የሱስ እንደወሰዷቸው ሁሉ ይባርካቸው ዘንድ ወደ ልዑል አምላክ ልትወስዷቸው እንደምትፈልጉ ንገሯቸው። ለመካሪዎቻችሁ እንዲህ በሏቸው “ልጆች የጌታ ርስት ናቸው፤ በመሆኑም ለተሰጠኝ አደራ ታማኝ መሆኔን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ.… ልጆች በዓለም ተጽዕኖ ተጠርገው በማይወሰዱበት ሁኔታ ማደግ አለባቸው፤ በሚፈተኑበት ቦታና ጊዜ እቅጩን፣ #አይሆንም!; መባል አለባቸው.… ቤተሰባችሁን ባማረችው ከተማ በሮች ውስጥ ልታዩዋቸው እንደምትፈልጉ ለጎረቤቶቻችሁና ለጓደኞቻችሁ ንገሯቸው።15 AHAmh 344.4

ወጣቶቻችን ከባድ ፈተና ተጋርጦባቸዋል፡- ፈተናዎችና አደጋዎች እንደሚገጥሟቸው እንዲያውቁ ችግር ሲያጋጥማቸውም የመውጫ ስሌት እንዲያዘጋጁ ልጆች መማርና መሠልጠን ይገባቸዋል። እራሳቸውን መቆጣጠር እንዲችሉና ችግሮቻቸውን በክብር ማሸነፍ ይችሉ ዘንድ መማር አለባቸው። በፈቃደኝነት እራሳቸውን ወደ አደጋ ካልከተቱና ለአላስፈላጊ ፈተናዎች እራሳቸውን ካልዳረጉ፤ ክፉ ተጽዕኖዎችንና ርጉም ጓደኝንትን ከሸሹ ሊያስወግዱት በማይችሉት ሁኔታ ተገድደው ከአደገኞች ጋር ቢጎዳኙ መመሪያቸውን ለመጠበቅና ለእውነት ለመቆም የባህርይ ጥንካሬ ይኖራቸዋል። ጠባያቸው ሳይበከል በእግዚአብሔር ብርታት በድል ይወጣሉ፤ በሥነ-ሥርዓት የተማሩ ከሆኑ የወጣቶች የግብረ-ገብነት ኃይል እጅግ ከባድ የተባለውን ፈተና የመቋቋም ኃይል አለው።16 AHAmh 345.1