የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ሃምሳ አራት—የቤተሰብ ኃይማኖት
የቤተሰብ ኃይማኖት ሲገለጽ፦ የቤተሰብ ኃይማኖት ልጆችን በእግዚአብሔር ትምህርትና ተግሳጽ ሥር ማሳደግን ያቀፈ ነው። ሰይጣን አታልሎና ማርኮ ከአምላክ እንዳያርቀው እያንዳንዱ የቤተሰብ አካል በክርስቶስ ትምህርት ሊመገብና የማያወላውል ዘብ ሊቆምለት ይገባል። እያንዳንዱ ቤተሰብ ሊደርስበት የሚያስፈልገው ደረጃ ይህ ነው። እንዳይወድቁ ወይም ተስፋ እንዳይቆርጡ ግልጽ ውሳኔ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ወላጆች በሚሰጡት ትምህርትና በመመሪያቸው ትጉና ንቁ መሆን ይገባቸዋል። ዓይናቸው ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ የተሰጠ ሆኖ፣ ልጆቻቸውን ሲያሠለጥኑ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ይተባበራሉ፤ ክርስቶስ የሞተለትን የልጆችን ነፍስ ለማትረፍ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር አብሮ ይሠራል። 1 AHAmh 226.1
ኃይማኖታዊ መመሪያ ማለት ከተለመደው መመሪያ የላቀ ነው። የሱስን እንዴት እንደሚቀርቡት እያስተማራችኋቸው፣ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ [ለክርስቶስ]እየነገራችሁት፣ ከልጆቻችሁ ጋር መፀለይ ማለት ነው። ፍቅሩ ታጋሽ፣ ቸርና ይቅርባይ አድርጓችሁ ሳለ፣ ልክ እንደ አብርሃም ልጆቻችሁ ትዛዛታችሁን እንዲከተሉ ጥብቅ በመሆን የሱስ ሁሉን በሁሉ እንደሆነላችሁ በሕይወታችሁ ማሳየት ማለት ነው። 2 AHAmh 226.2
በትዳር ሕይወት እራሳችሁን ስትመሩ በሰማይ መጻሕፍት ትመዘገባላችሁ፤ በሰማይ ቅዱስ የሚሆን፣ እርሱ መጀመሪያ በቤተሰቡ ቅዱስ መሆን አለበት። አባቶችና እናቶች ለቤተሰቦቻቸው እውነተኛ ክርስቲያናዊነት የሚያሳዩ ከሆኑ፣ ጠቃሚ የቤተ-ክርስቲያን አባላት በመሆን ቤተሰባቸውን የሚያሳስቡ ቋጠሮዎችን በሚፈቱበት መንገድ፣ የቤተክርስቲያንንና የማህበረሰቡን ጉዳዮች መፍታት ይችላሉ። ወላጆች ሆይ ኃይማኖታችሁ መጠሪያ ብቻ ሆኖ አይቅር፤ እውነታው ገሃድ ሆኖ ይውጣ። 3 AHAmh 226.3
ኃይማኖት የቤት ውስጥ ትምህርት አካል ይሁን፦ የቤት አምልኮ በሚያስፈራ ሁኔታ ቸል ተብሏል። ወንዶችና ሴቶች ለውጭ ተልእኮዎች ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። በቤት ውስጥ ትክክለኛ ተምሣሌት መሆን የተገባቸውን ኃላፊነት ቸል በማለታቸው፣ የሠሩትን ጥፋት የሚያካክስ ይመስል ለእግዚአብሔር ጉዳይ መሰጠታቸውን እንደ ንስሐ መግባት በመቁጠር፣ የውጭ ተልዕኮውን በመፈፀም ከወቀሳ ነፃ በመሆን ሕሊናቸውን ለማሳመን ይሞክራሉ። ቤታቸው ግን የተለየ የሥራ መስካቸው ነው፤ ይህንንም መስክ ቸል ማለታቸውን ምንም ዓይነት ማሳበቢያ ቢያቀርቡ እግዚአብሔር አይቀበልም። 4 AHAmh 226.4
ሃይማኖታዊ አምልኮ በቤት ውስጥ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የበዛ የመልካምነት ክንውን ያገኛል። እምነት እንዲከናወን እግዚአብሔር እራሱ ያቀደውን ሥራ እንዲሠሩ ይመራቸዋል። ልጆች በጌታ ፍርሃትና ተግሳጽ ያድጋሉ። 5 AHAmh 227.1
የዚህ ዘመን ወጣቶች የበለጠ ለኃይማኖታዊ ነገሮች ያዘነበሉ ያለመሆናቸው ምክንያት [ከቤት] ያገኙት ትምህርት ጉድለት ስላለበት ነው። የተመኙትን ሁሉ እንዲያገኙ መፍቀዳችሁ ወይም ያስቀመጣችሁት ሕግ ሲጣስ በዝምታ ማለፋችሁ [ይህ] እውነተኛ ፍቅር የሚፈጽመው ተግባር አይደለም። ቅርንጫፉ ሲያጎነብስ ዛፉም ያዘነብላል። 6 AHAmh 227.2
ኃይማኖት ማህበረሰቡ ላይ ተጽዕኖ እንዲኖረው ካስፈለገ መጀመሪያ በቤት ክበብ ተጽዕኖው መታየት አለበት። ልጆች እግዚአብሔርን እንዲፈሩትና እንዲወድዱት በቤት ውስጥ ከሠለጠኑ ወደ ዓለም ሲወጡና ጎጆ ሲያቀኑ የራሳቸውን ቤተሰቦች ለእግዚአብሔር ለማሠልጠን የተዘጋጁ ይሆናሉ፤ የእውነት መመሪያም በማህበረሰቡ ውስጥ ተተክሎ የማሳመን ተጽዕኖ ይኖረዋል። አምልኮ ከቤት ውስጥ ትምህርት መፋታት የለበትም። 7 AHAmh 227.3
የቤት ውስጥ አምልኮ የቤተ-ክርስቲያንን መቅደም አለበት፦ የቤተ-ክርስቲያን የብልጽግናዋ መሠረት በቤት ውስጥ ይጣላል። የቤትን ሕይወት የሚያስተዳድሩ ተጽዕኖዎች ወደ ቤተ-ክርስቲያን ሕይወት ይተላለፋሉ፤ ስለዚህ የቤተ-ክርስቲያን ሥራዎች መጀመሪያ በቤት ውስጥ መጀመር አለባቸው። 8 AHAmh 227.4
ጥሩ የቤት ውስጥ አምልኮ ካለን ለኃይማኖታችን ፍጹም ገጣሚዎች እንሆናለን። ምሽጋችሁ በቤታችሁ ይሁን፤ ቤተሰባችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችሁ በንግግርና በሥራ እንደ ክርስቲያን በቤት ውስጥ ተመላለሱ። መምህራን እንደሆናችሁ ተገንዝባችሁ ቸር፣ ይቅር-ባይና ታጋሽ ሁኑ። እያንዳንዷ እናት መምህርት ናት፤ እንዴት ማስተማር እንዳለባት ታወቅ ዘንድ ትክክለኛውን መልክና ሸራፋ የሌለበትን የባህርይ ቅርጽ፣ ለልጆችዋ መስጠት ትችል ዘንድ በክርስቶስ ትምህርት ቤት ተማሪ ትሁን። 9 AHAmh 227.5
የቤት ውስጥ አምልኮ እጥረት ካለ የእምነት ሰው ተብሎ መጠራት ዋጋ-ቢስ ነው….ባህርያችን ክርስቶስ ሲመጣ ይለወጣል ብለው ብዙዎች ራሳቸውን ያታልላሉ። በእርሱ መገለጽ ግን የልብ መለወጥ አይኖርም። ግድፈት ካለው ባህርያችን አሁን መለወጥ ግድ ይለናል፤ በክርስቶስ ፀጋ የሙከራ ጊዜያችን ሳያበቃ የተበላሹትን ባህርያት ልናሸንፋቸው ይገባል። 10 AHAmh 227.6
የቤት ውስጥ አምልኮ እጅግ አስፈላጊ ነው፤ ንግግራችንም የመልካም ባህርይ ውጤት 228 የአድቬንቲስት ቤት ይሁን፤ ያለዚያ የቤተ-ክርስቲያን ምስክርነታችን ምንም ዋጋ አይኖረውም። በቤታችሁ ደግነት፣ ቸርነትና ርኅራኄ ካላንፀባረቃችሁ በስተቀር ኃይማኖታችሁ (አምልኮአችሁ) ከንቱ ነው። እውነተኛ የቤት ውስጥ አምልኮ ቢኖር ኖሮ የቤተ-ክርስቲያን ኃይል በጨመረ ነበር። 11 AHAmh 228.1
ኃይማኖታዊ ትምህርትን ማዘግየት እጅግ ከባድ ስህተት ነው፦ ልጆች የእግዚአብሔር ዕውቀት ሳይኖራቸው እንዲያድጉ ማድረግ በክብደቱ ተወዳዳሪ የሌለው ስህተት ነው። 12 AHAmh 228.2
ወደ ፊት ይስተካከላሉ፤ እያደጉ ሲሄዱ ለኃይማኖታዊ ልምምድ ድንጉጥ እየሆኑ ይሄዳሉ በሚል አስተሳሰብ፣ ለልጆቻቸው መስጠት የሚገባቸውን ኃይማኖታዊ ሥልጠና ቸል ሲሉ ወላጆች እጅግ አስከፊውን ስህተት ይፈጽማሉ። ወላጆች ሆይ የከበረውን የእውነት ዘር ካልዘራችሁ፣ የፍቅርንና ሰማያዊ ባህርያትን ያዘለ ተክል በልብ ውስጥ ካልተከላችሁ፣ ሰይጣን በልብ ማሳ ላይ እንክርዳድ እንደሚዘራ አይታያችሁምን? 13 AHAmh 228.3
ብዙውን ጊዜ ልጆች ያለ ኃይማኖት እንዲያድጉ ይፈቀድላቸዋል፤ ምክንያቱ ደግሞ ክርስትና የሚጠይቀውን የኃላፊነት ቀንበር ለመሸከም ልጆች ገና ሕፃናት በመሆናቸው ለዚህ ትምህርት ያልደረሱ ናቸው ብለው ወላጆቻቸው ስለሚያስቡ ነው…. AHAmh 228.4
በኃይማኖት ዙሪያ ያሉ የልጆች የኃላፊነት ጥያቄዎች፣ ያለ ምንም ጥርጥር የቤተሰቡ አባል የሆኑበት ዘመን ሳያልቅ [ከቤት ወጥተው የራሳቸውን ቤተሰብ መመሥረት ሳይጀምሩ] እልባት ማግኘት አለበት። 14 AHAmh 228.5
ወላጆች እራሳቸውን በፍጹም ተቆጣጥረው በሚያረጋግጥ ሁኔታ፣ ልጆቻቸው ማድረግ ያለባቸውንና የሌለባቸውን ይነግሯቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ቦታ የተተኩ ናቸው። እያንዳንዱ በቸርነትና ራስን በመግዛት የተደረገላቸው ጥረት ጠንካራና የውሳኔ ሰዎች ይሆኑ ዘንድ ባህርያቸውን ያጎለብተዋል…. አባቶችና እናቶች ይህንን ጥያቄ በጥዋቱ መስመር ሊያስይዙት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል፤ በኋላም ልጁ ሰንበትን ባያከብር ኃይማኖታዊ አምልኮንና የቤተሰብ ፀሎት ቸል ማለትን ሲያስብ፣ ከስርቆት አሳንሶ አያየውም። ወላጆች በራሳቸው እጆች የመከለያውን ቅጥር መገንባት አለባቸው። 15 AHAmh 228.6
ገና በጨቅላ ዕድሜ የክርስቶስን መሥመር የተከተለ ብልሃተኛና በጥበብ የተሞላ አካሄድ ሊጀመርና ወደ ፊትም ሊቀጠል ይገባል። ልጆች ልባቸው ገና በብዙ ነገሮች በቀላሉ መማረክ በሚችልበት ጊዜ ስለ ዘለዓለማዊ እውነታዎች መማር ይገባቸዋል። ወላጆች የሚኖሩት፣ የሚናገሩትና የሚንቀሳቀሱት በእግዚአብሔር ፊት እንደሆነ አይርሱ። 16 AHAmh 228.7
ወላጆች ሆይ ምን ዓይነት መንገድ ነው የምትከተሉት? በኃይማኖት ጉዳይ ልጆቻችሁ ያለምንም ገደብ ነፃ መሆን አለባቸው የሚለውን ሐሳብ ትደግፋላችሁ? በልጅነትና በወጣትነት ጊዜያቸው ያለምክርና ተግሳጽ ትተዉአቸዋላችሁ? እንደፈለጉ እንዲያደርጉ ትለቋቸዋላችሁ? እንደዚያ የምታደርጉ ከሆነ በእግዚአብሔር ለተሰጣችሁ ኃላፊነቶች ደንታ-ቢስ ሆናችኋል። 17 AHAmh 229.1
ትምህርቱ ለልጅ ዕድሜ የሚመጥን ይሁን፦ ልጆች ነገሮችን መረዳት እንደጀመሩ ስለ ቤተልሔሙ ሕፃን ወርቃማውን እውነት ይጠጡ ዘንድ ወላጆች የየሱስን ታሪክ ይንገሯቸው። ለችሎታቸውና ለዕድሜአቸው በሚመጥን መልኩ እግዚአብሔርን የማክበር ሐሳብ በዕእምሮአቸው እንዲቀረጽ አድርጉ። ቋንቋን ለመናገር ቃላቱን በሚማሩበት ጊዜ ኃይማኖትንም መማር እንዲችሉ እርሱ ክህሎት ሰጥቷቸዋልና ልጆቻችሁን በፀሎት ወደ የሱስ አምጧቸው። 18 AHAmh 229.2
ልጆች ገና ሕፃን እያሉ ለመለኮታዊ ተጽዕኖ የሚመቹ ናቸው። ጌታ እነዚህን ልጆች በተለየ እንክብካቤ ሥር ያደርጋቸዋል፤ በጌታ ትምህርትና ተግሳጽ ሲያድጉ ለወላጆች ረዳት እንጂ የሚጎትቷቸውና የሚያደናቅፏቸው አይሆኑም። 19 AHAmh 229.3
ወላጆች የቤትን አምልኮ በጥምረት ያስፋፉ፦ አምልኮ በቤት ውስጥ ተጠብቆ እንዲቀጥል ኃላፊነቱ በእናትና በአባት ላይ ተጥሏል። 20 AHAmh 229.4
እናት ብዙ ኃላፊነቶችን በራስዋ ላይ በመቆለል ለቤተሰቧ መንፈሳዊ ፍላጎት ጊዜ ማጣት የለባትም። ወላጆች በሥራቸው ሁሉ እግዚአብሔር እንዲመራቸው ይጠይቁ። በፊቱ በመንበርከካቸው ስለተጣለባቸው ኃላፊነት ትክክኛ መረዳት ያገኛሉ። በዚሁም ሥፍራ በምክሩና በትዕዛዛቱ ለማይሳሳተው ፍጹም ጌታ ልጆቻቸውን ማስረከብ ይችላሉ…. AHAmh 229.5
አባት የመንፈሳዊ ትምህርት የማካፈሉን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ በእናት ላይ መጣል የለበትም። በእናቶችና በአባቶች የሚከናወን ሰፊ ሥራ አለ። ሁለቱም የየግል ድርሻቸውን በመወጣት ልጆቻቸውን ለታላቁ የፍርድ ምርመራ ቀን ሊያዘጋጇቸው ይገባል። 21 AHAmh 229.6
ወላጆች ወደ አምልኮ ስትሄዱ ልጆቻችሁን ይዛችኋቸው ሂዱ። በእምነት ክንዳችሁ አቅፋችሁ ለክርስቶስ ቀድሷቸው። ልጆቻችሁን በትክክለኛው መንገድ ከማሠልጠን የሚያደናቅፋችሁን ምንም ነገር አትፍቀዱ፤ ምንም ዓይነት ዓለማዊ ፍላጎት ልጆቻችሁን ወደኋላ እንድትተዋቸው አያባብላችሁ፤ ክርስቲያናዊ ኑሮአችሁ እንኳ ከእነርሱ እንዲነጥላችሁ ፈጽሞ አትፍቀዱ። ወደ ጌታ ይዛችኋቸው መጥታችሁ አዕምሮአቸው ከመለኮታዊ እውነት ጋር እንዲለማመድ አድርጉ። እግዚአብሔርን ከሚወዱ ጋር ጓደኝነት ይመሥርቱ። ለዘለዓለማዊነት ገጣሚ በሚሆን ባህርይ 230 የአድቬንቲስት ቤት እንዲታነፁ የምትጥሩላቸው ልጆቻችሁ እንደሆኑ አድርጋችሁ ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ አምጧቸው። 22 AHAmh 229.7
የቤት ውስጥ አምልኮ ምን የማያሳካው ነገር አለ? እግዚአብሔር በእያንዳንዱ ቤተሰብ ማከናወን ያቀደውን ያንኑ ሥራ መፈጸም ይችላል። ልጆች በጌታ ትምህርትና ተግሳጽ ሥር ያድጋሉ። የዓለማዊው ህብረተሰብ አገልጋዮችና አድናቂዎች መሆናቸው ቀርቶ የጌታ ቤተሰብ አባላት እንዲሆኑ ይማራሉ፤ ይሠለጥናሉም። 23 AHAmh 230.1
ለተደላደለ ሕይወት ልጆች ወደ ወላጆቻቸው ይመልከቱ፦ ሁሉም ነገር በወጣት አዕምሮ ላይ አሻራውን ጥሎ ያልፋል። የፊት ገጽታ ይጠናል፤ ድምፅ የራሱ ተጽዕኖ አለው፤ የሚያዩትንም ጠባይ በቅርበት ለማመሳሰል ይሞክራሉ። ነጭናጫና ነዝናዛ የሆኑ አባቶችና እናቶች አሁን ለልጆቻቸው የሚያስተምሩት ትምህርት፣ እየቆየ ሲሄድና በሕይወታቸው ሲንፀባረቅ ሲያዩ ዓለም የእነርሱ ብቻ ብትሆንና በውስጧ ያለውን ሁሉ ከፍለው ልጆቻቸው የያዙትን ብልሹ ጠባይ ማስተው የሚችሉ ቢሆን ኖሮ ያደርጉት ነበር። ልጆች ጽኑና ተከታታይነት ያለውን እምነታቸውን መሠረት ያደረገ ባህርይ በወላጆች ማየት አለባቸው። እራስን በመግዛትና በማይዋዥቅ ሕይወት ወላጆች የልጆቻቸውን ባህርያት መቅረጽ ይችላሉ። 24 AHAmh 230.2
ሥነ-ሥርዓት ያለውን ቤተሰብ እግዚአብሔር ያከብረዋል፦ በቤተሰባቸው ጌታን የሚያስቀድሙ፣ የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ ለልጆቻቸው የሚያስተምሩ ወላጆች ሥነ-ሥርዓት ያለውና የተቀጣ፤ በአምላክ ላይ በማመጽ ፈንታ እርሱን የሚወድና የሚታዘዝ ቤተሰብ ለዓለም በማበርከት በመላእክትና በሰው ፊት እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያደርጉታል። ክርስቶስ በቤታቸው እንግዳ አይደለም [ክርስቶስ ቤተኛቸው ነው]፤ ስሙ የተወደሰና የተከበረ የቤተሰብ ስም ነው። እግዚአብሔር በበላይነት በሚያስተዳድረው ቤት መላእክት ሐሴት ያደርጋሉ። ልጆችም ሃይማኖታቸውን መጽሐፍ ቅዱስንና ፈጣሪያቸውን ማወደስ ይማራሉ። እንደዚህ ዓይነት ቤተሰቦች ቃል-ኪዳኑን ይወርሳሉ፤ “የሚያከብሩኝን አከብራለሁ” ይላልና። 25 AHAmh 230.3
ክርስቶስን ወደ ቤት እንዴት እንደምናመጣው፦ ክርስቶስ በ[ግለሰቡ] ልብ ውስጥ ሲኖር ወደ ቤተሰቡም ይመጣል። የድነት ወራሾችን ሁሉ የሚያገለግሉት ሰማያዊ መላእክት፣ በቤታቸው ተገኝተው ልጆቻቸውን ማስተማር ያለባቸውን ትምህርት እንደ መምህር ሆነው እንዲያስተምሯቸውና እንዲያሠለጥኗቸው በማገዝ፣ አባትና እናት ጭምር በመንፈስ ቅዱስ እዝ ሥር የመኖር ጥቅምን መረዳት እንዲችሉ ያደርጋሉ። አዳኙን የሚያከብርና ከፍ ከፍ የሚያደርግ ትንሽ ቤተ-ክርስቲያን በቤት ውስጥ መመሥረት ይቻላል። 26 AHAmh 230.4
ኃይማኖታችሁን ማራኪ አድርጉት፦ የክርስትናን ሕይወት ማራኪ አድርጉት፤ የክርስቶስን ተከታዮች ስለሚጠብቃቸው [ሰማያዊ] አገር ተናገሩ። እንዲህ በምታደርጉበት ጊዜ እግዚአብሔር ልጆቻችሁን ወደ ሙሉ እምነት ይመራቸዋል። ክርስቶስ ሄዶ ለሚወዱት እያዘጋጀው ላለው እልፍኝ ገጣሚዎች የመሆን ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። 27 AHAmh 231.1
የኃይማኖት ቅርጽ ይይዙ ዘንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ማስገደድ የለባቸውም፤ ሆኖም ዘለዓለማዊ መመሪያዎችን በሚማርክ ብርሃን ሊያቀርቡላቸው ይገባል። 28 AHAmh 231.2
በደስተኛነታቸው በክርስቲያናዊ ደግነታቸውና ለስላሳና አዛኝ በሆነው ርኅራኄአቸው፣ ወላጆች የክርስቶስን ኃይማኖት ማራኪ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን ከልጆቻቸው ለሚገባቸው ክብርና ፍፁም መታዘዝ ጥብቅ መሆን አለባቸው። ትክክለኞቹ መርሆዎች በልጆቹ ጭንቅላት ውስጥ ሥር መስደድ አለባቸው። 29 AHAmh 231.3
መልካም እንዲያደርጉ የሚገፋፉ ነገሮችን ለወጣቱ ማቅረብ አለብን፤ ብርና ወርቅ በዚህ ተግባር ብቁ አይደሉም። የክርስቶስን ፍቅር፣ ምህረቱን፣ ፀጋውን፣ የቃሉን ተመን-የለሽለትና በመጨረሻም አሸናፊውን የሚጠብቀውን ደስታ ግለጹላቸው። ይህ ዓይነቱ ጥረታችሁ ለዘለዓለም የሚዘልቅ ሥራን የሚያከናውን ነው። 30 AHAmh 231.4
አንዳንድ ወላጆች ለምን እንደሚወድቁ፦ አንዳንድ ወላጆች ኃይማኖተኛ መሆናቸውን ቢያውጁም እግዚአብሔርን የማገልገልና የመታዘዝ እውነታ በልጆቻቸው ፊት አይጠብቁም። የራስ ምቾት ደስታ ወይም ዝንባሌ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ካለው መጠይቅ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው አያሳዩም። “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው”፤ ይህ እውነታ ከሕይወትና ከባህርይ ጋር መሸመን አለበት። እኛ እንድን ዘንድ ሕይወቱን በሰጠው በክርስቶስ እውቀት በኩል ስለ እግዚአብሔር ያላቸው ትክክለኛ ንድፈ-ሐሳብ በአዕምሮአቸው ላይ አሻራ መጣል አለበት። 31 AHAmh 231.5
ወላጆች ይህንን ሁሉ ለማድረግ ጊዜ የለንም ብላችሁ ታስቡ ይሆናል፤ ነገር ግን የቤተሰባችሁን ሥራ የመፈጸም ግዴታ አለባችሁ። ያለበለዚያ ሰይጣን በጎደለው ይሞላላችኋል። ይህን ሥራ ከመሥራት የሚያግደውን የሕይወታችሁ አካል ቆርጣችሁ አውጡ፤ በጌታ ትዕዛዝ መሠረት ልጆቻችሁን አሠልጥኑ። ጊዜያዊና ምድራዊ የሆነውን ነገር ቸል በሉ፤ ባላችሁ የሀብት መጠን ረክታችሁ ለመኖር ጣሩ፤ ፍላጎቶቻችሁን ወድሯቸው፤ ነገር ግን እባካችሁ ስለ ክርስቶስ ብላችሁ ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ ኃይማኖታዊ ሥልጠና ደንታ-ቢስ አትሁኑ። 32 AHAmh 231.6
እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለእግዚአብሔር ተቀድሶ መሰጠት አለበት፦ ሙሴ የፋሲካን በዓል በተመለከተ የሰጣቸው ትዕዛዛት፣ በጠቃሚ ነገሮች የተሞሉና ተግባራዊነታቸው ለአሁኑ ዘመን ወላጆችና ልጆች አስፈላጊዎች ናቸው…. AHAmh 232.1
አባት የቤተሰቡ ካህን እንዲሆን፣ እርሱ ከሞተ ደግሞ በሕይወት ያለው ታላቅ ወንድ ልጁ ቦታውን ተክቶ በበሩ ጉበን ላይ ደም እንዲረጭ ነበር። ይህ በእያንዳንዱ ቤተሰብ ሊሠራ ላለው ሥራ ምሳሌ ነው። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ቤታቸው ሊሰበስቡና ክርስቶስ ፋሲካቸው እንደሆነ ሊያቀርቡላቸው ይገባል። አባት እያንዳንዱ የቤቱን ነዋሪ ለእግዚአብሔር ሊሰጥና በፋሲካው በዓል የተወከለውን ሥራ ሊያከናውን ይገባዋል። ይህንን ከባድና ክቡር ኃላፊነት ለሌሎች መተው አደገኛ ነው። 33 AHAmh 232.2
ክርስቲያን ወላጆች ለእግዚአብሔር ታማኝ ለመሆን ይወስኑ፤ ልጆቻቸውንም ወደ ቤታቸው አስገብተው አዳኝና ምሽግ ለመሆን የሚችል፣ እርሱ ብቻ እንደሆነ ክርስቶስን በመወከል አጥፊው መልአክ ይህንን የተወደደ ቤተሰብ ያልፈው ዘንድ መቃኑን በደም ይርጩ። ከፍጡር ተጽዕኖ በላይ የሆነ ኃይል በቤት ውስጥ በሥራ ላይ እንዳለ ዓለም ሁሉ ይይ። ወላጆች ከእግዚአብሔር ጋር ሕያው ግንኙነታቸውን በማስጠበቅ ራሳቸውን በክርስቶስ ጎን አሰልፈው በፀጋው እርዳታና በእነርሱ ውክልና ምን ያህል መልካም ነገር መከናወን እንደሚችል ያሳዩ። 34 AHAmh 232.3