የአድቬንቲስት ቤት
ምዕራፍ ሃምሳ ሦስት—የአንድነት ግንባር
የማስተዳደር ሃላፊነት የጋራ ነው፦ በአንድነትና በፀሎት አባትና እናት ልጆችን ወደ ትክክለኛው መንገድ የመምራት ከባድ ኃላፊነትን በጋራ መሸከም አለባቸው። 1 AHAmh 222.1
ወላጆች አንድ ሆነው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ በመካከላቸውም ምንም ዓይነት ልዩነት አይኑር። ነገር ግን ብዙ ወላጆች በተጣረሰ ዓላማ ስለሚሠሩ በአመራር ብልሹነት ልጆች ሞልቃቃ ይሆናሉ…. አንዳንድ ጊዜ በእናትና በአባት መካከል የሚፈጠር ክስተት አለ፤ አንደኛው ልጆቹን እንዳላችሁ የሚል ሆኖ ሌላኛው ወገን ደግሞ ከልክ ያለፈ ጥብቅ ይሆናል። ይህ ልዩነት ልጆቻቸው መልካም ሥነ-ምግባር እንዳያጎለብቱ የሚያደርግ ነው። ለውጥ ለማምጣት ኃይል መጠቀም ተገቢ ባይሆንም እንዳላችሁ የሚል ደካማ አመራር ማሳየትም ጥሩ አይደለም። እናት በልጆችዋ ጥፋት ዙሪያ የባልዋን ዓይን ልታሳውር አይገባትም፤ አባታቸው የከለከላቸውን ሁሉ እንዲሠሩ ተጽዕኖ ማድረግ የለባትም። የአባትን የአስተዳደር ችሎታና ጥበብ በሚመለከት እናት አንድም የጥርጣሬ ዘር እንኳ በልጆችዋ አዕምሮ ውስጥ መዝራት የለባትም። በእንቅስቃሴዋም ሁሉ የአባትን ሥራ የሚቃረን ተግባር መፈፀም የለባትም። 2 AHAmh 222.2
በአባቶችና በእናቶች መካከል ልዩነት ካለ፤ አንዳቸው የሌላኛውን ተጽዕኖ ለማክሸፍ የሚጥሩ ከሆነ፤ ቤተሰቡ ወኔ-አልባ ከመሆኑም በላይ ለመልካም የቤተሰብ አስተዳደር አስፈላጊ የሆነውን ክብርና አመኔታ ሁለቱም ያጡታል…. በቤተሰብ ላይ እንዲንፀባረቁ የሚፈለጉትን ሕጎችና ደንቦች በተለይም እንቅስቃሴአቸውን የሚገድቡ ሥርዓቶችን ለማወቅ ልጆች ጊዜ አይወስድባቸውም። 3 AHAmh 222.3
ልጆቻቸውን ሥነ-ሥርዓት በማስያዝ እናትና አባት መተባበር አለባቸው። በተቻለ መጠን ለጥሩ አካላዊ ጤንነትና ለዳጎስ ላለ መልካም ባህርይ ያበቃቸው ዘንድ ልጆቻቸውን በማሠልጠን በእግዚአብሔር ለተጣለባቸው ከባድ ኃላፊነት እውቅና በመስጠት እያንዳንዳቸው የፈንታቸውን ቀንበር መሸከም አለባቸው። 4 AHAmh 222.4
አሳሳች ትምህርት እንዴት ሊሰጥ እንደሚችል፦ አንዳንድ ሞኝ እናቶች ለደቂቃ እንኳን መፍቀድ የሌለባቸውን፣ ልጆቻቸው እንዲያደርጉ በመፍቀድ በልጆቻቸው ላይ ስህተት ይሠራሉ። አንዳንድ ጊዜም የልጆቹን ጥፋት ከአባትየው ይደብቃሉ። አባት እንደሚቃወም ስለሚገባት ስለጉዳዩ ምንም ነገር እንዳያውቅ ከልጆችዋ ጋር በመመሣጠር እርሱ የማይስማማበትን የአለባበስ ዓይነት ወይም ሌላ ነገር እንዲያደርጉ ትፈቅድላቸዋለች። AHAmh 222.5
እዚህ ላይ ልጆቹ ሥር የሰደደ የአታላይነት ትምህርት ይማራሉ። እነዚህን ስህተቶች አባት ሲደርስባቸው ከእውነታው ግማሹ ብቻ ተነግሮት የሆነው ሁሉ ተለባብሶ እንዲቀር ይደረጋል። እናትየዋ ግልጽ አይደለችም። እራስዋ ያላትን ያህል እርሱም ለልጆቹ ፍላጎት አንዳለው በውል አልተገነዘበችም። ከሚሠሩት ጥፋት፣ ከወረሯቸው ነገሮችና ገና በልጅነታቸው መስተካከል ካለባቸው ልማዶቻቸው አባታቸውን ማግለል ትክክል እንዳልሆነ አልተረዳችም። ነገሮች ተሸፋፍነዋል፤ ልጆች ወላጆቻቸው ሕብረት እንደሌላቸው አውቀዋል፤ ይህ ደግሞ ጎጂ ነው። ልጆችም ያዩትን በመድገም ገና ሕፃን እያሉ ማታለል፤ መሸፋፈንና የነገሮችን ትክክለኛነት ከእናታቸውና ከአባታቸው መደበቅ ይጀምራሉ። ማጋነን ልማዳቸው ይሆናል፤ ያለምንም የሕሊና ወቀሳ ወይም ፀፀት ዓይን ያወጡ ውሸ ቶችን በድርቅና መናገር ይጀም ራሉ። AHAmh 223.1
እነዚህ ስህተቶች ልጆቻቸው እየመሠረቱት ስላለው ባህርይ ከእናትየዋ እኩል ከሚያገባው አባት መደበቁ ቀጥሏል። አባት ያለምንም ገደብ መማከር ሁሉም ነገር ለእርሱ መከፈት ነበረበት። ነገር ግን የልጆችን ስህተቶች ከእርሱ ለመደበቅ የተወሰደው ተቃራኒ መንገድዋ፣ የማታለል ባህርይን በማበረታታት ሐቀኝነታቸውንና ታማኝነታቸውን ያሳጣቸዋል። 5 AHAmh 223.2
ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያስተዳድሩ ሁልጊዜም ቋሚ (የማይለዋወጡ) መመሪያዎች ሊኖሯቸው ይገባል። በዚህ ጉዳይ ላይ በአንዳንድ ወላጆች ጉድለት አለ - አንድነት ማጣት። ጥፋቱ አንዳንድ ጊዜ በአባት ብዙውን ጊዜ ግን በእናት የሚፈጸም ነው። ሞኝዋ እናት ልጆችዋን ታቀብጣለች፤ ታሞላቅቃለች። አባት በሥራ ምክንያት ከቤት ይርቃል፤ ከልጆቹ አብሮነትም ይለያል። በኋላም የእናታቸው ተጽዕኖ በግልጽ ይናገራል። በልጆቻቸው ባህርይ አቀራረጽ ሰፊውን ድርሻ የሚይዘው የእናትየዋ ተጽዕኖ ነው። 6 AHAmh 223.3
በወላጆች ልዩነት ልጆች ግራ ይጋባሉ፦ የቤተሰቡ ድርጅት የተቀናጀ መሆን አለበት፤ ባልና ሚስት በአንድ ላይ ኃላፊነታቸውን በማጤን በግልጽ መረዳዳት ሥራቸውን ሊያከናውኑ ይገባቸዋል። ልዩነት መኖር የለበትም። አባትና እናት [ልጆች ባሉበት] በሚያደርጉት ውይይት ወይም ክርክር አንዱ የሌላውን ሐሳብ ፈጽሞ ማውገዝ የለበትም። እናት በእግዚአብሔር ዕውቀት ልምድ የሌላት ከሆነች፤ በመንስኤና ውጤት ነገሮችን ለማገናዘብ ትሞክር። እርስዋ የምትከተለው ሥነ-ሥርዓት አባት ለልጆቹ ደህንነት የሚያደርገውን ተጋድሎ የሚያባብስበት መሆን አለመሆኑን ትመርምር። የጌታን መንገድ እየተከተልኩ ነውን? ብላ ትጠይቅ። ከሁሉም በላይ አስፈላጊ የሆነው ጥያቄ ይህ ነው። 7 AHAmh 223.4
ወላጆች መግባባት ተስኗቸው ከሆነ መስማማት ላይ እስኪደርሱ ድረስ ራሳቸውን ከልጆቻቸው ፊት ዘወር ያድርጉ። 8 AHAmh 224.1
አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች በቤተሰባቸው አስተዳደር አይተባበሩም። የባህርያቸውንና የዝንባሌአቸውን የተለያየ ገጽታ የማያውቀው፣ እጅግ ውስን ጊዜ ከልጆቹ ጋር የሚያሳልፈው አባት ብዙ ጊዜ ሸካራና ጨካኝ ነው። ብስጭቱን መቆጣጠር እያቃተው በግለት ይገስፃል። ልጁ ይህን ያውቃል፤ ዝቅ ብሎ ለአባቱ ተግሳጽ በመገዛት ፈንታ ቅጣቱ በንዴት ይሞላዋል። እናት በሌላ ጊዜ በአይቀጡ ቅጣት የምታስተካክለውን ጥፋት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ዝም ብላ ታልፈዋለች። ልጆቹ ምን ማድረግና መጠበቅ እንዳለባቸው የወላጆቻቸው አፀፋ ምን እንደሚሆን ባለማወቅ ግራ ይገባቸውና ሥርዓት መጣሳቸው ሳይቀጣ ምን ያህል መሄድ እንደሚችል መሞከር ይፈልጋሉ። ከዚያም ተመንድጎ የሚያድግና ፍሬ የሚያፈራ የጥፋት ዘር ይዘራባቸዋል። 9 AHAmh 224.2
ሥነ-ሥርዓት በማስያዝ ተግባር ወላጆች አንድ የሚሆኑ ከሆነ ልጁ ከእርሱ የሚጠበቀው ምን እንደሆነ ይረዳል። ነገር ግን አባት በቃል ወይም በፊቱ ገጽታ፣ እናት የምትሰጠውን መመሪያ የማይቀበለው እንደሆነ ካሳየ፤ ቁጥጥሯ ከመጠን ያለፈ እንደሆነ ከተሰማውና የርስዋን ሸካራነት ለማካካስ እሽሩሩ የሚለውና የሚያሞላቅቀው ከሆነ ልጁ ጠፋ ማለት ነው። ሳይቆይም ልጁ እንደፈለገው ማድረግ እንደሚችል ይማራል። ይህን አይነቱን ጥፋት በልጆቻቸው ላይ የሚፈጸሙ ወላጆች ለነፍሳቸው ጥፋት ተጠያቂዎች ናቸው። 10 AHAmh 224.3
መላእክት በጥልቅ ፍላጎት እያንዳንዱን ቤተሰብ ይመለከታሉ፤ ወላጆች አሳዳጊዎች ወይም ጓደኞች ልጆቻቸውን እንዴት እንደሚንከባከቧቸው ያያሉ። የእናትና የአባት ልዩነት ያለበት ቤት ውስጥ ምን ዓይነት እንግዳ የሆነ የአስተዳደር ግድፈት ይመለከቱ ይሆን! የድምፃቸው ቅላጼ አስተያየታቸውና ንግግራቸው ሁሉ በልጆቻቸው አስተዳደር አንድነት እንደሌላቸው የሚያሳዩ ናቸው። አባት የሚስቱን ገጽታ በመቀየር ለትናንሽ ፍጥረቶችዋ ያላትን ርኅራኄና ፍቅር በአክብሮት እንዳያዩት ይመራቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የአባትየውን ሸካራነትና ትዕግሥተ-ቢስነት በማጤን የጭካኔውን ተጽዕኖ ለማካካስ በማሰብ እናት ፍቅርዋን ልታበዛላቸው ትገደዳለች፤ የሚፈልጉትን ሁሉ በማሟላት ታሞላቅቃቸዋለች። 11 AHAmh 224.4
ብዙ ፀሎትና አስተዋይ አስተሳሰብ አስፈላጊ ነው፦ በቤት ክበብ ውስጥ እንኳ ቢሆን ፈቃድና ፍላጎት ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የሚጣጣም ካልሆነ በቀር ፍቅር እስከመጨረሻው አይዘልቅም። ሁሉም ክፍሎችና ፍላጎቶች ከየሱስ ክርስቶስ መስፈርቶች ጋር መስማማት አለባቸው። ባልና ሚስት በእግዚአብሔር ፍርሃትና ፍቅር ኃይላቸውን አንድ አድርገው በቤት ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ የበዛ ፀሎትና የአስተዋይ አስተሳሰብ አስፈላጊነት ይታያቸዋል። እግዚአብሔርን ሲፈልጉት አይናቸው ተከፍቶ በእምነት ለፀለዩት ፀሎት መልስ ይዘው ሊጠብቋቸው የሚመጡትን ሰማያዊ መልእክተኞች ማየት ይችላሉ። ደካማነታቸውን አሸንፈው ወደ ፍጽምና ይመጣሉ። 12 AHAmh 224.5
ልቦች በሐር የፍቅር ገመድ ይተሳሰሩ፦ እናቶችና አባቶች ሆይ ልባችሁን በተቀራረበና ፈጽሞ ደስተኛ በሆነ ቁርኝት አስተሳስሩት። የበለጠ በመቀራረብ ተጣመሩ እንጅ በመለያየት አትደጉ። ከዚያም የልጆቻችሁን ልቦች በፍቅር የሐር ገመድ ልታስተሳስሩ የተዘጋጃችሁ ትሆናላችሁ። 13 AHAmh 225.1
ለዘመንና ለዘለዓለም የሚሆነውን ዘር መዝራታችሁን ቀጥሉ። የክርስቲያን ወላጅን ጥረት ሰማይ ሁሉ በአንክሮ እየተከታተለው ነው። 14 AHAmh 225.2