አእምሮ፣ባሕርይና ማንነት፣ክፍል 1

2/45

መግቢያ

በኤለን ጂ ኋይት የህይወት ዘመን (1827-1915) የስነ-ልቦና ትምህርት፣ ስለ አእምሮና ስለ አእምሮ ኃይሎች እንዲሁም ስለ ሥራዎቹ የሚያጠናው ሳይንስ፣ ገና በእንጭጭነት እድሜ ላይ ነበር። ሆኖም በመላው ጽሁፎቿ ውስጥ ስለዚህ ሳይንስና ስለ አእምሮ ጤና መመሪያዎች በግልጽ የተቀመጡበት ልዩ ፍልስፍና ቀርቦአል። 1MCPAmh 1.1

የዚህ ከተለያዩ ጽሁፎች ተውጣጥቶ የተደራጀው መጽሐፍ ዓላማው በዚህ ሰፊ፣ አስፈላጊና አንዳንድ ጊዜም አወዛጋቢ በሆነ የትምህርት ዘርፍ ላይ ኤለን ጂ ኋይት የጻፈቻቸውን መግለጫዎች ለጥናት ምቹ እንዲሆኑ አንድ ላይ ማምጣት ነው። ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶችም ሆኑ ሌሎች ኤለን ጂ ኋይት በእግዚአብሔር መንፈስ ተጽእኖ ስር ሆና እንደጻፈች ስለሚያምኑ የሥነ ልቦና ትምህርትን የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች የተለያዩና ተለዋዋጭ ከመሆናቸው የተነሣ ለሰብአዊ ዘር በሙሉ እጅግ አስፈላጊ በሆነ በዚህ የትምህርት ዘርፍ ላይ የሰጠቻቸውን መመሪያዎች ትልቅ ዋጋ ይሰጣሉ። 1MCPAmh 1.2

በሥነ- ልቦና ትምህርት፣ በምግብ ዝግጅት፣ በትምህርትና በሌሎች መስኮችም ላይ ኤለን ኋይት ያላት አመለካከት ትክክለኝነት በግልጽ ታይቷል። በስነ-ልቦና ትምህርትና በአእምሮ ጤና ላይ ምርምር እየተደረገ ሲሄድ ትክክለኛ የሆኑ የስነ- ልቦና ትምህርት መርሆዎችን ከማስቀመጧ የተነሣ ያላት ዝና/መልካም ስም የበለጠውን እየጨመረ እንደሚሄድ ምንም ጥርጥር የለውም። አእምሮ፣ ባህርይና ማንነት የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ሥራ ለእምነቱ ራሱን ለሰጠ አድቬንቲስት ብዙ መልሶችን ይሰጠዋል። እውነት እየተገለጠ ሲሄድ በጥልቀት ለሚያስቡ አንባቢዎች በዚህ ቦታ የተያዙ አቋሞች የበለጠውን የሚስቡ እንደሚሆኑ እርግጠኞች ነን። በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አልፍ አልፎ የምናያቸው ‹‹ተመለከትሁ፣›› ‹‹እንዳይ ተደረግሁ፣›› ‹‹መመሪያ ተሰጠኝ፣›› የሚሉ አባባሎች የሚስተዋሉ ብቻ ሳይሆኑ የተገለጹት ጽንሰ-ሀሳቦች የመነጩት ሰብአዊ አእምሮን ከሰራው ስለመሆኑ ማረጋገጫ ስለሚሰጡ ተቀባይነት ያገኛሉ። 1MCPAmh 1.3

የኋይት ጽሁፎችን በአደራ በሚጠብቁ ቢሮዎች ውስጥ ይህ ነገር ሲሰባሰብ በትምህርትና በሥነ- ልቦና መስክ ያሉ የተለያዩ ባለ ሥልጣናትን አመለካከቶች የሚደግፉ ጽሁፎችን ለመምረጥ ምንም ዓይነት ጥረት አልተደረገም። በዚህ ቦታ ጽሁፎቹን ያሰባሰቡ ሰዎች አስቀድመው በአእምሮአቸው የያዙአቸው አመለካከቶች አልተካተቱም። ይህ ሥራ የተሰራው በስድስት አስርተ አመታት ውስጥ ከታተሙ ጽሁፎቿ ሰፊ ክምችት ተወስዶ ሲሆን እነዚህ ጽሁፎች አሁን በሕትመት ላይ ያሉ ወይም ከሕትመት ውጭ የሆኑ መጽሐፍትን፣ በራሪ ጽሁፎችን፣ በሺሆች የሚቆጠሩ በተወሰነ ጊዜ የሚወጡ መጣጥፎችን እና በኋይት ርስት ባለው ግምጃ ቤት ውስጥ የተቀመጡ በርካታ ያልታተሙ የእጅ ጽሁፎቿንና መረጃዎችን ያካትታሉ። 1MCPAmh 1.4

አእምሮ፣ ባሕርይና ማንነት የሚለው መጽሐፍ አብዛኛው ክፍል የሚያቀርበው አጠቃላይ መሪ መርሆዎችን ነው። በዚህ ሥራ ላይ የቀረቡ ነገሮች የመምህርንና የተማሪን፣ የአገልጋይንና የምዕመንን፣ የሀኪምንና የሕመምተኛን፣ ወይም የወላጅንና የልጅን ግንኙነት የሚመለከቱ ተግባራዊ ተግሳጾችንና ምክሮችን የያዙ ነገሮችን በመኻል በመኻሉ ጣልቃ በማስገባትና ተጨማሪ ድጋፍ በመስጠት ነው። 1MCPAmh 2.1

በበርካታ አጋጣሚዎች ለውሳኔ ሰጭ አካል፣ ለአገልጋይ፣ ለሀኪም፣ ለመምህር፣ ለደራሲ፣ ለባል፣ ለቤት እመቤት ወይም ለወጣት የተሰጡ ምክሮች ሁኔታዎችን በሚገልጡበት አግባብና ከተሰጡ ምክሮች አንጻር ሲታዩ አንድን ሰው የሚመለከቱ ታሪኮች ይመስላሉ። ትኩረት መሰጠት ያለበት በውስጡ ወዳሉት መርሆዎች ነው። 1MCPAmh 2.2

ኤለን ኋይት እንደ የስነ-ልቦና ባለሙያ (ሳይኮሎጅስት) ሆና አለመጻፏ ግልጽ ነው። ዛሬ በስነ-ልቦና ትምህርት ዘርፍ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋሉ የተለመዱ ቃላቶችን አልተጠቀመችም። አንባቢው ‹‹ሳይኮሎጂ››፣ ‹‹የጭንቅላት ውጫዊ ቅርጽ ጥናት››፣ወዘተ... ብላ የተጠቀመቻቸውን ቃሎች በማስተዋል መቅረብ አለበት። ነገር ግን አዋቂ የሆነ አንባቢ እነዚህ ጽሁፎች በግልጽ እንደሚያሳዩት በስነ-ልቦና ትምህርት መሰረታዊ መርሆዎች ላይ ባላት ከተለመደው ውጭ በሆነ መረዳት ይደመማል። በተለያዩ የአእምሮ ገጽታዎች ላይ ኤለን ኋይት የሰጠቻቸው መግለጫዎች፣ በሰብአዊ ልምምድ ውስጥ ያለው ወሳኝ ቦታ፣ የማደግ ችሎታዎቹ፣ እና በተሳካ ሁኔታ ሥራውን ወደ መስራት የሚመሩ ነገሮች ተገቢ የሆነ ቅደም ተከተል ይዘው አንድ ላይ መቀመጣቸው ኤለን ጂ ኋይት ከሞተች በኋላ ለወጡ መጻሕፍቷ ተጨማሪ ተመራጭነትን ያስገኝላታል። እነዚህ ነገሮች ሰው ምን እንደሆነ እንድንገነዘብና ከምድራዊ አካባቢው፣ ከእግዚአብሔርና ከዩኒቨርስ ጋር ያለውን ግንኙነት እንድንረዳ ያደርጋሉ። 1MCPAmh 2.3

ከአስር አመት በፊት፣ ይህን ጽሁፍ የማሰባሰብ ሥራ በተጀመረ ጊዜ፣ በተለየ ሁኔታ በአእምሮ ጤና መስክ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉትን ተማሪዎች ከሁሉም የበለጠ ስሜታቸውን ያነሳሳል ተብሎ ታስቦ ነበር። ስለዚህ የተለያዩ ዘርፎችን ለማጥነት እያሰቡ ላሉ ሰዎች መግለጫዎቹ በቀላሉ ሊገኙ እንዲችሉ የሚረዳ ሁኔታ ተመቻችቶ ነበር። ምርምር አድራጊው በተቻለ መጠን ድግግሞሽ እንዳይኖር ለማድረግ ጥረት ቢያደርፐፕግም ተማሪው ተገቢ በሆኑ በተለያዩ ርዕሶች ሥር ማግኘት እንዲችል ጥቂት ቁልፍ የሆኑ መግለጫዎች በተለያዩ ምዕራፎች ውስጥ ተደግመዋል። አእምሮን ለመቆጣጠር በሚደረገው ጦርነት ላይ ሁላችንም ተሳታፊዎች ስለሆንን ይህ ስብስብ ለሁሉም አድቬንቲስቶችና ለጓደኞቻቸውም አብይ ጠቃሜታ እንዳለው አሁን ግልጽ ነው። 1MCPAmh 2.4

የአሰባሳቢዎቹ ሥራ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በማሰባሰብ፣ እነዚህን ነገሮች ተገቢ በሆነ ቅደም ተከተል በማስቀመጥና የተመረጡ ነገሮችን ለማስተዋወቅ የተሰጡ የጎን ርዕሶችን ጨምሮ ርዕሶችን በመስጠት ላይ የተወሰነ ነበር። አንድን ነገር ከሁሉም አቅጣጫ የመቅረብንና በተቻለ መጠን ሰፊ ሽፋን የመስጠትን ዘዴ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በቀረቡት ትምህርቶች ላይ ኤለን ኋይት በሥራ ላይ በነበረችባቸው አመታት የጻፈቻቸውን አስፈላጊ መግለጫዎች ሁሉ ለማካተት ጥረት ተደርጓል። ይህ ሲደረግ በአጠቃላይ መሰረታዊ መስመሮች ላይ ያለ እቅድ የሚያነብን ሰው ሊረብሽ (ሊያናድድ) የሚችል የሀሳብ ድግግሞሽ እዚህም እዚያም አለ። ነገር ግን ጥንቁቅ ተማሪ በውይይት ላለው ርዕስ አስተዋጽዖ የሚያደርገውን እያንዳንዱን ሀረግ በደስታ ይቀበላል። ስለዚህ አእምሮ፣ ባሕርይና ማንነት የሚለው መጽሐፍ ስለ ማንኛውም ነገር መረጃ የሚሰጥ መጽሐፍ (አውደ ጥበብ) ባሕርይ አለው። 1MCPAmh 3.1

አስፈላጊ ሲሆን አንባቢው ወደ መጀመሪያው ሙሉ አውድ መመለስ እንዲችል ለማድረግ እያንዳንዱ ጥቅስ በኤለን ጂ ኋይት ጽሁፎች ውስጥ ላለው ምንጭ የተለየ ዋጋ ይሰጣል። ቦታን ለመቆጠብ ሲባል በኤለን ጂ ኋይት ጽሁፎች ውስጥ በተለምዶ ተቀባይነት ያገኙ ምህጸረ-ቃላት ምንጩን በሚያሳዩ ማጣቀሻዎች ውስጥ ጥቅም ላይ ውለዋል። ለእነዚህ ምህጸረ-ቃላት መፍቻው የመግቢያ ገጾችን ተከትሎ ተቀምጦአል። በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የተጻፈበት አመተ ምህረት ወይም የመጀመሪያው ሕትመት ተቀምጦአል። የመጀመሪያዎቹ ምንጮች እንደ ቀዳሚ ማጣቀሻዎች የተሰጡ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በመጽሐፍ መልክ ካሉ ተገቢ የሆኑ አሁን ታተመው ያሉ ማጣቀሻዎች ይጻፋሉ። ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ (Commentary) የተሰጡ ምስጋናዎች በእያንዳንዱ የትርጓሜ ቅጾች (Volume) መዝጊያ ላይ ለሚገኙ የኤለን ጂ ኋይት ተጨማሪ ነገሮች ወይም የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጓሜ ቅጽ 7a የተሰጡ ናቸው። 1MCPAmh 3.2

የቦታ ውስንነት በእነዚህ ቅጾች ላይ እንደ ‹‹አእምሮ መታወክ››፣ ወዘተ... ያሉ ከአእምሮ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ርዕሶች ማካተት እንዳይቻል አድርጓል፣ አንባቢው ለእነዚህ ነገሮች መረጃ ሲፈልግ ለኤለን ጂ ኋይት ጽሁፎች ወደ ተሰጠው ወደ አጠቃላይ ማውጫ ተመርቷል። 1MCPAmh 3.3

ይህ ስብስብ የተዘጋጀው ኤለን ኋይት በኑዛዜዋ ላይ በሰጠችው ስልጣን መሰረት የጽሁፎቿ ባለ አደራ በሆነው ቦርድ ትዕዛዝ በኤለን ጂ ኋይት ርስት ቢሮዎች ነው።ይህ ጽሁፍ ከአብዛኞቹ ሌሎች የኤለን ጂ ኋይት ጽሁፎች ስብስብ በተለየ ሁኔታ በመጀመሪያ የተለቀቀው በመማሪያ ክፍል ውስጥ ለመፈተንና የአድቬንቲስት ምሁራን፣ የሥነ -ልቦና ጠበብቶችና የአእምሮ ሐኪሞች ጠለቅ ባለ ሁኔታ እንዲያነቡት የአእምሮ ጤና መመሪያዎች በሚል ርዕስ በጊዜያዊ መልክ ነበር። የኤለን ኋይት ርስት ፍላጎት በዚህ ቦታ ከተወከሉ ርዕሶች ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የታወቁ መግለጫዎች ሁሉ ከግንዛቤ ውስጥ መግባታቸውንና የጽሁፎቹ አደረጃጀት ተቀባይነት ያለው መሆኑን እርግጠኛ ማድረግ ነው። 1MCPAmh 3.4

በመማሪያ ክፍል ውስጥ ከሚጠቀሙት ሰዎችና ከሌሎችም የሚሰጥ ምቹ መልስ ለዚህ ሥራና ኤለን ጂ ኋይት ከሞተች በኋላ ለታተሙ ለሌሎች ብዙ መጻሕፍት ያላቸውን ቦታ ያረጋግጣል። አሁን በሁለት ክፍል በመውጣት ዝነኛ የሆነው የክርስቲያን ቤት ቤተ መጻሕፍት አካል ይሆናል። 1MCPAmh 4.1

አሁን ባለበት መልኩ በነገሮች አመራረጡ የክለሳ መልክ የያዘ ሲሆን በነገሮች አቀማመጥ ቅደም ተከተል ደግሞ መሻሻል መኖሩን ያሳያል።‹‹ሰብአዊ ልምምድ ውስጥ ፍቅርና ወሲባዊነት›› የሚል ርዕስ የተሰጠው ምዕራፍ ተጨምሮበታል። እነዚህን ርዕሶች የጨመሩ ሰዎች አንዳንድ ምዕራፎችን ያጠጋጉ ሲሆን አንዳንድ ስራዎች ደግሞ አስፈላጊ ያልሆኑ ድግግሞሾችን አስወግደዋል። በሁለቱም ክፍል ላይ የገጾች አጻጻፍ አንዱ ከሌላው የቀጠለ ሲሆን ለመላው ሥራ የመጽሐፍ ቅዱስና በመጽሐፉ ውስጥ ያለው ትምህርት ማውጫዎች በመጨረሻ ላይ ናቸው። 1MCPAmh 4.2

ሰብአዊ አእምሮን ለመቆጣጠር በክፉና በመልካም ኃይሎች መካከል ያለው ታላቁ ተጋድሎ በግልጽ መገለጹ አንባቢዎችን ሁሉ ሊያስጠነቅቅና አእምሮአቸውን ሊያበራ የሚችል ሲሆን ዛሬ ከአደጋ የጸዳ ምሪትን እንደሚሰጥና ወደፊት በሚመጣው ሕይወት የዘላለም ውርስ የሚያረጋግጡ አስተያየቶችንና አቅጣጫዎችን እንደሚሰጥ የኤለን ጂ ኋይት ጽሁፎች ባለ አደራ ቦርድ ከልቡ ተስፋ ያደርጋል። 1MCPAmh 4.3

የኤለን ጂ ኋይት ጽሁፎች ባለ አደራዎች ቦርድ

ዋሽንግተን ዲ ሲ

መጋቢት 22፣ 1977 ዓ.ም.