አእምሮ፣ባሕርይና ማንነት፣ክፍል 1

3/45

ክፍል አንድ--የአእምሮ ጥናት

ምዕራፍ 1—አስፈላጊነቱ

ከሁሉ የበለጠ ጥሩ ሥራ-- ከሰው አእምሮዎች ጋር የሚሰራው ሥራ ሰዎች እስካሁን ተሰማርተውበት ከሚያውቁት ሥራ ሁሉ የበለጠ ጥሩ ሥራ ነው።—Testimonies for the Church 3:269 (1873). 1MCPAmh 5.1

አእምሮንና አካልን የሚገዙ ሕጎችን ማወቅ።--ለራሱና ለሰብአዊ ዘር ሲል ከሕይወት ሕጎች ጋር ራሱን ማስተዋወቅና አስተውሎ መታዘዝ የእያንዳንዱ ግለሰብ ተግባር ነው። ሕይወት ካላቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ አስደናቂ ከሆነው የሰው አካል ጋር ሁሉም መተዋወቅ ያስፈልጋቸዋል። የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ሥራዎች እና ሁሉም ጤናማ በሆነ ሁኔታ ሥራቸውን መስራት እንዲችሉ አንዱ በሌላው ላይ እንደሚደገፍ መረዳት አለባቸው። አእምሮ በአካል ላይና አካልም በአእምሮ ላይ ያለውን ተጽእኖ እና እነርሱ የሚገዙባቸውን ሕጎች ማጥናት አለባቸው።—The Ministry of Healing, 128 (1905). 1MCPAmh 5.2

አእምሮን ማሰልጠንና ሥርዓት ማስተማር።--አንተ ማንም ብትሆን...እግዚአብሔር ሰፊ የመሻሸል ዕድል ባላቸው የአእምሮ ኃይሎች ባርኮሃል። መክሊቶቻችሁን ትጋት ባለበት ጽናት አሳድጉአቸው። አእምሮአችሁን በጥናት፣ በመመልከትና በማሰላሰል አሰልጥኑ፣ ሥርዓትንም አስተምሩ። እያንዳንዱን ኃይል ሥራ ላይ ካላዋላችሁ በቀር የእግዚአብሔርን አእምሮ መገናኘት አትችሉም። የአእምሮ ኃይሎች የሚበረቱትና የሚያድጉት ወደ ሥራችሁ በፈሪሀ-እግዚአብሔር፣ ራስን ዝቅ በማድረግ፣ እና ልባዊ ጸሎት በማድረግ የምትሄዱ ከሆነ ነው። ቆራጥ ዓላማ ድንቆችን ይሰራል።—Life Sketches of Ellen G. White, 275 (1915). 1MCPAmh 5.3

የተገራ አእምሮ ያለው አቅም።--ራስን መግራትን መለማመድ አለብን።...በደንብ የተገራ ተራ አእምሮ ራሱን ከማይቆጣጠር እጅግ ከፍተኛ ትምህርትና እጅግ ከፍተኛ መክሊቶች ካሉት አእምሮ የበለጠ ከፍተኛ ሥራ ይሰራል።—Christ’s Object Lessons, 335 (1900). 1MCPAmh 5.4

ከአእምሮዎች ጋር መሥራት ከፍተኛ ሥራ ነው።--የዛሬ ወጣቶች የወደፊቱን ህብረተሰብ አመላካች ናቸው። በእነርሱ ውስጥ የአገርን ባህርይና መዳረሻ የሚወስኑትን የወደ ፊቱን መምህራን፣ ሕግ አውጪዎችና ዳኞች፣ መሪዎችና ሕዝብ እናያለን። ስለዚህ ባሕርይን የሚመሰርቱና ወደ ፊት በሚነሳው ትውልድ ሕይወት ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ሰዎች ተልእኮ ምንኛ ጠቃሚ ነው። ከሰዎች አእምሮ ጋር መሥራት ለሰዎች ከተሰጠ ሥራ ሁሉ ትልቁ ሥራ ነው። የወላጆች ጊዜ የምግብ ፍላጎትን በማርካትና ሀብትን ወይም ፋሽንን በመከተል መባከን የለበትም። እግዚአብሔር በእጃቸው ክቡር ወጣቶችን ያስቀመጠው በዚህ ሕይወት ጠቃሚ የሆነ ቦታ እንዲይዙ ብቻ ሳይሆን ለሰማያዊው መኖሪያ እንዲዘጋጁም ጭምር ነው።—Historical Sketches of the Foreign Missions of the Seventh-day Adventists, 209, 1886. (Temperance, 270.) 1MCPAmh 5.5

የመምህር ጠቃሚነት በሰለጠነ አእምሮ ይደገፋል።—የአንድ መምህር ጠቃሚነት በሚያልመው መስፈርት ላይ የሚደገፈውን ያህል የራሱ ባደረጋቸው ነገሮች መጠን አይደገፍም። እውነተኛ መምህር አሰልቺ በሆኑ አሳቦችና ሰነፍ አእምሮ ወይም በደንብ ባልተደራጀ የማስታወስ ችሎታ አይረካም። ሁል ጊዜ ከፍ ያሉ ስኬቶችንና የተሻሉ ዘዴዎችን ይሻል። ሕይወቱ የማያቋርጥ እድገት ያሳያል። በእንደዚህ ዓይነቱ መምህር ሥራ ውስጥ ተማሪዎቹን የሚያነቃና የሚያነሳሳ አዲስነት፣ የሚቀሰቅስ ኃይል አለ።—Education, 278 (1903). 1MCPAmh 6.1

እጅግ ከፍ ያለ የአእምሮና የሞራል ብቃት ለማግኘት ይጥራል። ራስን ማወቅ ትልቅ እውቀት ነው። ራሱን በትክክል የሚገምት መምህር እግዚአብሔር አእምሮውን እንዲቀርጽና እንዲገራ ይፈቅዳል። የኃይሉን ምንጭ እንዳለ ይቀበላል።..ራስን ማወቅ ራስን ዝቅ ወደ ማድረግና በእግዚአብሔር ወደ መታመን ይመራል፣ ነገር ግን ራስን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ቦታ አይወስድም። የራሱን ጉድለቶች የሚገነዘብ ሰው ሊደርስበት የሚችለውን የአካል፣ የአእምሮና የሞራል ብቃትን ከፍተኛ ደረጃ ለመድረስ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። በዝቅተኛ መስፈርት የሚረካን ወጣት በማሰልጠን ሥራ ውስጥ ማንም ቢሆን ድርሻ ሊኖረው አይገባም።—Special Testimonies On Education, 50, (Counsels to Parents, Teachers, and Students, 67. 1MCPAmh 6.2

ለዘላለም ያዘጋጃል።-- በሥራችሁ ሁሉ አትክልተኛው ለምድር ፍሬዎች እንደሚሰራ መስራት አለባችሁ። እርሱ ዝም ብሎ ዘሩን ይዘራል፣ ነገር ግን በአፈር ውስጥ ከተቀበራ በኋላ ዘሩ ይበቅላል። የህያው እግዚአብሔር ኃይል ሕይወትንና ከፍተኛ ወኔንና ጥንካሬን ስለሚሰጠው ‹‹በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍጹም ሰብል ታፈራለች›› (ማርቆስ 4፡ 28)። ይህን አስደናቂ ሂደት አጥኑ። መመርና ማስተዋል ያለብን ነገር ምንኛ ብዙ ነው! ችሎታችን የሚፈቅደውን ያህል አእምሮአችንን ብናሻሽል ኖሮ ለዘላለም የእግዚአብሔርን መንገድና ሥራዎች ማጥናታችንን እንቀጥል ነበር፤ ስለ እርሱም የበለጠ እናውቅ ነበር።—Counsels to Parents, Teachers, and Students, 252 (1913). 1MCPAmh 6.3

የክርስትና ሳይንስና አእምሮ።--በደንብ መታወቅ ያለበት የክርስትና ሳይንስ አለ--ሰማይ ከምድር የሚርቀውን ያህል ከሰብአዊ ሳይንስ እጅግ የራቀ፣ ጥልቅና ሰፊ የሆነ ሳይንስ ነው። አእምሮ መገራት፣ መማርና መሰልጠን አለበት፤ ይህ መሆን ያለበት ሰዎች ለእግዚአብሔር የሚሰጡት አገልግሎት በውርስ ከተገኘው ዝንባሌ ጋር የሚጣጣም መሆን ስለሌለበት ነው። ብዙ ጊዜ አንድ ግለሰብ በክርስቶስ ትምህርት ቤት ተማሪ መሆን ካለበት በሕይወት ዘመኑ ያገኘው ስልጠናና ትምህርት መወገድ አለበት። ልብ በእግዚአብሔር ጽኑ ለመሆን መማር አለበት። አዛውንትና ወጣቶች ፈተናን እንዲቋቋሙ የሚያስችሉአቸውን ልምዶችና ሀሳቦች መመስረት አለባቸው። ወደ ላይ መመልከትን መማር አለባቸው። የእግዚአብሔር ቃል መርሆዎች--የሰማይን ያህል ከፍ ያሉና ዘላለምን የሚያካትቱ መርሆዎች--በዕለታዊ ተግባሮቻቸው ውስጥ ግንዛቤ ማግኘት አለባቸው። እያንዳንዱ ድርጊት፣ እያንዳንዱ ቃል፣ እያንዳንዱ ሀሳብ ከእነዚህ መርሆዎች ጋር የሚስማማ መሆን አለበት።—Counsels to Parents, Teachers, and Students, 20 (1913). 1MCPAmh 7.1

በተቃርኖ ውስጥ ብቻ ወደ ፊት መቀጠል።-- በተማሪ ሕይወት ውስጥ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ከሚያሳድግ ሳይንስ ጋር የሚስተካከል ሌላ ሳይንስ የለም። የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑ ሰዎች አንድን ነገር ለማድረግ አዲስ ማነሳሻዎች ተሰጥተው፣ አዲስ ሀሳቦች ተነስተው ያገኛሉ፣ አዳዲስ ድርጊቶችም መፈጸም አለባቸው። ነገር ግን ነፍስ እንድትጠራጠርና ኃጢአት እንድትሰራ ሁል ጊዜ የሚገዳደር ጠላት ስላለ ወደ ፊት መቀጠል የሚችሉት በተቃርኖ ውስጥ ነው። በውርስ ያገኘናቸውና ከአከባቢ የተገኙ ልናሸንፋቸው የሚገቡ የክፉ ዝንባሌዎች አሉ። የምግብ ፍላጎትና ጠንካራ ስሜት በመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥር ሥር መሆን አለባቸው። ከዘላለም ወዲህ ላለው ጦርነት ማብቂያ የለውም። ነገር ግን መዋጋት ያለብን የማያቋርጡ ጦርነቶች ቢኖሩም መገኘት ያለባቸው የከበሩ ድሎችም አሉ፤ በራስና በኃጢአት ላይ የሚገኝ ድል አእምሮ ከሚገምተው በላይ ዋጋ ያለው ነው።—Counsels to Parents, Teachers, and Students, 20 (1913). 1MCPAmh 7.2

አእምሮን ለማሳደግ የእያንዳንዱ ክርስቲያን ተግባር።--የሥርዓትን፣ የምሉእነትን እና የመመልከትን ልምዶች ማግኘት የእያንዳንዱ ክርስቲያን ሀላፊነት ነው። ማንኛውንም ሥራ ቀስ ብሎ አድበስብሶ ለመሥራት ምንም ሰበብ የለም። አንድ ሰው ሁል ጊዜ ሥራ ላይ ሆኖ ምንም ስራ ካልተሰራ አእምሮና ልብ በሥራ ላይ አልተጠመዱም ማለት ነው። ቀርፋፋ የሆነና በሥራው ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሰው እነዚህ ነገሮች መታረም እንዳለባቸው መገንዘብ አለበት። የተሻሉ ውጤቶችን ለማግኘት ጊዜውን እንዴት መጠቀም እንዳለበት በማቀድ ሂደት አእምሮውን ማሰራት አለበት። በብልሃትና በዘዴ፣ አንዳንዶች በአሥር ሰዓት የሚሰሩትን ሥራ ሌሎች በአምስት ሰዓት ይሰራሉ። አንዳንድ በቤት ውስጥ ሥራ ላይ ተሰማርተው ያሉ ሰዎች ሁል ጊዜ ሥራ ላይ ናቸው፤ ይህ የሚሆንበት ምክንያት ብዙ ሥራ ስላላቸው ሳይሆን ጊዜን ለማትረፍ ስለማያቅዱ ነው። ቅርፍፍ ካሉና መዘግየት ከሚታይባቸው ዘዴዎቻቸው የተነሣ ትንሹን ሥራ ትልቅ ያደርጉታል። ነገር ግን ፈቃደኛ የሆኑት ሁሉ ይህን አናዳጅ የሆነ የመዘግየት ልምዶችን ማሸነፍ ይችላሉ። በሥራቸው የተወሰነ ዓላማ ይኑራቸው። አንድን ሥራ ለመስራት ምን ያህል ሰዓት እንደሚያስፈልግ ወስኑና በዚያ ሰዓት ውስጥ ሥራውን ለመጨረስ ጥረት አድርጉ። የፈቃድ ኃይልን ሥራ ላይ ማዋል እጆች በቅልጥፍና እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋል።—Christ’s Object Lessons, 344 (1903). 1MCPAmh 7.3

እያንዳንዱን የአእምሮና የአካል ኃይል ለማሰልጠን።-- እግዚአብሔር ለእያንዳዱ ሰብአዊ ፍጡር አእምሮ ሰጥቶታል። ይህ አእምሮ ለእርሱ ክብር ጥቅም ላይ እንዲውል ይፈልጋል።...ከእኛ መካከል ከመጠን በላይ የሆነ የአእምሮ ኃይል ወይም የማገናዘብ ችሎታ ያለው ማንም የለም። እያንዳንዱን የአእምሮና የአካል ኃይል--ክርስቶስ የገዛውን ሰብአዊ አካል-- በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ ማዋል እንድንችል ማስተማርና ማሳልጠን አለብን። እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር አብረን ውጤታማ ሰራተኞች ስንሆን ደስ ስለሚለው እነዚህን ኃይሎች ለማጠናከር ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ አለብን።—Sermon at St. Helena Sanitarium, Jan 23, 1904. (Selected Messages 1:100.) 1MCPAmh 8.1

የሰው መለኪያው በደንብ ተኮትኩቶ ያደገ አእምሮ ነው።--የሚበቃህን ያህል ስለተማርክ አሁን ጥረትህን ላላ ማድረግ እንደምትችል በፍጹም አታስብ። በደንብ ተኮትኩቶ ያደገ አእምሮ የሰው መለኪያው ነው። በዕድሜህ ዘመን ሁሉ ትምህርት መቀጠል አለበት፤ በየቀኑ መማርና ያገኘኸውን ትምህርት በሥራ ላይ ማዋል አለብህ።—The Ministry of Healing, 499 (1905). 1MCPAmh 8.2

ባልታረመ መስክና ባልሰለጠነ አእምሮ መካከል ያለው መመሳሰል አስደናቂ ነው። ልጆችና ወጣቶች በአእምሮአቸውና በልባቸው ውስጥ ለመብቀልና ጤነኛ ያልሆነ መከርን ሊሰጥ የተዘጋጀ መጥፎ ዘር አለ፤ አእምሮን ኮትኩቶ የከበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በውስጡ ለማከማቸት እጅግ ከፍተኛ ጥንቃቄና ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል።—The Review and Herald, November 9, 1886. (Our High Calling, 202.) 1MCPAmh 8.3

እውቀትንና የአእምሮ ስልጡንነትን ማግኘት።--እውቀትንና የአእምሮ ስልጡንነትን የማግኘት ስኬታችን ጊዜያችንን በትክክል በመጠቀማችን ላይ ይደገፋል። የአእምሮ እውቀትን ማሳደግ በድህነት፣ ከደሃ ቤተሰብ በመወለድ፣ ወይም ከአካባቢ አለመመቸት የተነሳ መከልከል የለበትም።...ቆራጥ ዓላማ፣ ሳይታክቱ መስራት እና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ሰዎችን ለማንኛውም ተጽእኖ ማሳደር ለሚቻልበትና ጠቃሚ ሊያደርግ ለሚችል ቦታ ብቁ ሊያደርግ የሚችል እውቀትና የአእምሮ ሥነ-ሥርዓት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።—Christ’s Object Lessons, 343, 344 (1900). 1MCPAmh 8.4

ከሕመምተኞች ጋር ሲሰራ ትልቅ ዋጋ ያላቸውን አእምሮዎች መረዳት።--በአእምሮ ምክንያት ከመጡ በሽታዎች ጋር ሲሰራ ትልቅ እውቀት ያስፈልጋል። የቆሰለ፣ የታመመ ልብና ተስፋ የቆረጠ አእምሮ ቀላል ሕክምና ያስፈልጋቸዋል። ...ብዙ ጊዜ ቀዝቀዝ ባለና ግድ የለሽነት በሚታይበት ሁኔታ ከሚሰጥ እጅግ ጥበብ ከተሞላበት ሕክምና ይልቅ ርኅራኄና ብልሃት ያለበት አያያዝ ለበሽተኛው ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል።—The Ministry of Healing, 244 (1905). 1MCPAmh 9.1

አእምሮዎችንና ሰብአዊ ተፈጥሮን መረዳት በድነት ስራ ውስጥ ይረዳል።--እግዚአብሔር እንድትሆኑለት ፈልጎ እንደጠራችሁ ጠቃሚዎችና ብቁ ሆናችሁ ለመገኘት ቁርጠኞች ሁኑ። በምታደርጉት ነገር ሁሉ ጥብቅና ታማኝ ሁኑ። የአእምሮ ችሎታችሁን ለማጠናከር ልትደርሱበት የምትችሉትን እያንዳንዱን መልካም አጋጣሚ ተጠቀሙ። የመጻሕፍት ጥናት ጠቃሚ ከሆነ የጉልበት ሥራ ጋር ይቀላቀልና ታማኝነት ባለበት ጥረት፣ ነቅቶ በመጠበቅና በጸሎት ከላይ የሆነውን ጥበብ የራሳችሁ አድርጉት። ይህ የተሟላ ትምህርት ይሰጣችኋል። በዚህ ሁኔታ በባሕርይ ከፍ ትሉና በሌሎች አእምሮዎች ላይ ተጽእኖ ይኖራችኋል፤ ይህ እነርሱን በታማኝነትና በቅድስና መንገድ እንድትመሩአቸው ያስችላችኋል።—Christ’s Object Lessons, 334 (1900). 1MCPAmh 9.2

መካኒኮች፣ ጠበቆች፣ ነጋዴዎች፣ ሁሉንም ዓይነት ሥራ የሚሰሩ ባለሙያዎች፣ የሥራቸው ጌቶች መሆን እንዲችሉ ራሳቸውን ማስተማር አለባቸው። የክርስቶስ ተከታዮች በእውቀታቸው ከሌሎች ያነሱና በእርሱ አገልግሎት ውስጥ እንዳሉ የሚናገሩ ሰዎች መጠቀም ላለባቸው መንገዶችና ዘዴዎች መሃይም መሆን አለባቸውን? የዘላለምን ሕይወት የማግኘት ዝግጅት ከማንኛውም ምድራዊ ክፍያ በላይ ነው። ነፍሳትን ወደ ኢየሱስ ለመምራት የሰብአዊ ተፈጥሮ እውቀትና የሰብአዊ አአምሮ ጥናት መኖር አለበት። በታላቁ የእውነት ትምህርት ላይ ወንዶችንና ሴቶችን እንዴት መቅረብ እንደሚቻል ለማወቅ በጣም ጥንቃቄ የተሞላበት ማሰብና ግለት ያለው ጸሎት ያስፈልጋሉ።—Testimonies for the Church 4:67 (1876). 1MCPAmh 9.3

በደንብ ተኮትኩተው ያደጉ ኃይሎች አገልግሎታችንን ለማግኘት የሚደረገውን ፍላጎት ይጨምራሉ።--ግለሰቦች ራሳቸውን በእጃቸው ይዘው ለማደስ ቁርጠኝነት ስለሌላቸው በተሳሳተ የተግባር መንገድ ላይ በመሆን የራሳቸውን ሀሳብ ማፍለቅ የማይችሉ ሊሆኑ ወይም ኃይሎቻቸውን በማሳደግ ከሁሉ የተሻለ አገልግሎት የመስጠት ችሎታ ሊያገኙ ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ራሳቸውን በማንኛውም ቦታና በሁሉም ቦታ ተፈላጊ ሆነው ያገኙታል። የተገቡ ሆነው ለተገኙበት ነገር ሁሉ አድናቆት ይሰጣቸዋል።—Christ’s Object Lessons, 344 (1900). 1MCPAmh 10.1

ከመላእክት ብቃት ጋር የሚስተካከል የብቃት ደረጃ ላይ ልንደርስ እንችላለን።-እግዚአብሔር ለሰው የማያቋርጥ መሻሻል የሚያሳይ ችሎታና በሥራ ውስጥ ሊገኝ የሚችለውን እርዳታ ሁሉ ሰጥቶታል። መለኮታዊ ጸጋን በመቀበል ከመላእክት ብቃት ጋር የሚስተካከል የብቃት ደረጃ ላይ ልንደርስ እንችላል።—The Review and Herald, June 20, 1882. (Our High Calling, 218.) 1MCPAmh 10.2