የተሟላ ኑሮ
“ሊመጣ የሚገባው አንተ ነህ”
ዮሐንስ መጥምቁ ሄሮድስ አስሮት በእሥር ቤት ሲማቅቅ ከቈየ በኋላ “የሚመጣው አንተ ነህን ወይስ ሌላ እንጠብቅ” የሚል መልዕክት ወደ የሱስ ላከ፡፡ (ማቴ 11፡3) CLAmh 132.7
የሱስ ለዮሐንስ ደቀመዛሙርት ወዲያው መልስ አልሰጠም፡፡ በዝምታው ተደንቀው ቆመው ሲመለከቱ በሽተኞች ወደ እርሱ መጡ፡፡ የኃያሉ ፈዋሽ ድምፅ የደናቁርትን ጆሮ ከፈተ፡፡ በቃሉና በእጁ በመዳሰስ ብርሃንን እንዲያዩ፤ ተፈጥሮን እንዲመለከቱ፤ የወዳጆቻቸውንና የአዳኛቸውን ፊት እንዲያዩ የዕውራንን ዓይኖች ከፈተ፡፡ በድምፁ ሊሞቱ የሚያጣጥሩትን ተናግሮ ብርታት ሰጣቸው፡፡ በሰይጣን የተያዙትን ወፈፌዎች ቃሉን አክብረው ሙሉ ባለጤና ሆኑ፡፡ አመለኩት፤ ሰገዱለት፡፡ ሊቃውንቱ እንደ ርኩስ ይቆጥሯቸው የነበሩት ተራ ሰዎች በየሱስ ዙሪያ ተሰበሰቡ፡፡ ስለ ዘለዓለም ሕይወት በሚያበስሩ ቃላት አነጋገራቸው፡፡ CLAmh 132.8
የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይህ ካዩና ከሰሙ በኋላ መሸ፡፡ የሱስ ጠራና ያዩትን ሁሉ ለዮሐንስ እዲነግሩ አዝዞ አሰናበታቸው፡፡ በተጨማሪም “በእኔ የማይሰናከለው ሁሉ ብጹዕ ነው” አላቸው፡፡ (ቁ.6) ደቀመዛሙርቱ መልእክቱን ይዘው መሄዳቸው በቂ ነበር፡፡ ዮሐንስ “የጌታ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ለድሆች የምሥራችን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛልና ልባቸው የተሰበረውን እጠግን ዘንድ፤ ለተማረኩት ነፃነት፤ ለታሠሩት መፈታትን እናገር ዘንድ ልኮኛል፤ የተወደደችው የእግዚአብሔርን ዓመት አምላካችንም የሚበቀልባትን ቀን እናገር ዘንድ ልጆኛል፤” ተብሎ ስለክርስቶስ የተነገረውን ትንቢት አስታወሰ፡፡ (ኢሣይያስ 61፡1-2) ፡፡ CLAmh 133.1
የሱስ የናዝሬቱ ተስፋ የተጣለበት መሢህ ነበር፡፡ የመለኮታዊነቱ ምልክት በሥቃይ ለተያዙት ሰብዓዊ ፍጥረት በአበረከተው አገልግሎቱ አማካይነት ተገልጧል፤ ክብሩ በእኛ መጠን ዝቅ ብሎ በመዋረዱ ተገለጠ፡፡ CLAmh 133.2
የክርስቶስ ሥራ የገለጠው መሢህነቱን ብቻ ሣይሆን መንግስቱ እንዴት እንደሚቋቋም ጭምር ነው፡፡ ለኤልያስ በምድረ በዳ በለስላሳው ድምጽ አማካይነት እንደተገለጠለት ሁሉ ለዮሐንስ ዕውነቱ ተገለጠለት፡፡ “በእግዚአብሔር ፊት ትልቅና ብርቱ ነፋስ ተራሮችን ሰነጠቀ ዓለቶቹንም ሰባበረ፡፡ እግዚአብሔር ግን በነፋስ ውስጥ አልነበረም፡፡ ከነፋሱም በኋላ የምድር መናወጥ ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በምድር መናወጥ አልነበረም፡፡ ከምድር መናወጥ በኋላ እሳት ሆነ፤ እግዚአብሔር ግን በእሳቱ ውስጥ አልነበረም፡፡ ከእሳቱ በኋላ ትንሽ የዝምታ ድምፅ ሆነ፡፡ እግዚአብሔርም በዚያ በዝምታ ድምፅ ውስጥ ነበር አነጋገረም፡፡” CLAmh 133.3
ክርስቶስ ሥራውን ያከናወነ የነገሥታትን ዙፋን በመገልበጥና መንግሥታትን በመጨበጥ አልነበረም፡፡ በጉራና በውጫዊ ታይታ አልነበረም፡፡ ግን ሰዎችን በምሕረት ቃል በማነጋገርና ራሱን መሥዋዕት በማድረግ ሥራውን ያካሂድ ነበር፡፡ CLAmh 133.4