የተሟላ ኑሮ

12/201

የሰማይ ኑሮ ቅምሻ

ምንም እንኳን ችግርና ተስፋ መቁረጥ ቢያጋጥማቸውም ባለዮውም ሆነ ሚስቲቱ በመጋባታችን ተሳስተናል የማለት ስሜት ሊኖርባቸው አይገባም፡፡ በዚህ ፈንታ ሊሆኑ የሚገባውን ለመሆን መሞከር ነው፡፡ በፊት የነበረውን የፍቅር ስሜት መቀጠል ይገባል፡፡ በሕይወት ጦርነት አሸናፊ ለመሆን እርስ በእርስ መደፋፈር ነው፡፡ ሚስቲቱ ባልዋ የሚደሰትበትን፤ ባልዮውም ሚስቲቱ የምትደሰትበትን ነገር ማወቅ አለባቸው፡፡ የጋራ ፍቅርና የጋራ መቻቻል ሊኖር ይገባል፡፡ ይህ የሆነ እንደሆነ ጋብቻው የፍቅር መፈጸሚያ መሆኑ ቀርቶ የፍቅር መጀመሪያ ይሆናል፡፡ የእውነተኛ ወዳጅነት ግለትና ልብን ከልብ ጋር የሚያቆራኝ ፍቅር የሰማያዊ ደስታ ቅምሻ ነው፡፡ CLAmh 15.4

እያንዳንዱ ቤተሰብ ሊቋረጥ የማይገባው የተቀደሰ ኅብረት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንንም የግል ኅብረት ሌላ ሰው ሊገባበት አይገባም፡፡ ባልዮውም ሆነ ሚስቲቱ የግል ምስጢራቸውን ለሌላ ማካፈል የለባቸውም፡፡ CLAmh 16.1

ባልና ሚስቱ እኔ ያልሁት ይሁን ከማለት ፈንታ ምክር መለዋወጥ አለባቸው፡፡ ጥሩ ጠባይህን ኮትኩተው፤ የሌሎችንም ጥሩ ጠባይ ለማወቅ ፍጠን፡፡ እንደተወደዱ ማወቅ ደስታን ያመጣል፡፡ ርኅራኄና አክብሮት ለመሻሻል እንዲጥሩ ያደፋፍራል፤ ፍቅርም የማሻሻያ መሣሪያ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ እያደገ ይሔዳል፡፡ CLAmh 16.2

ባለቤትዮውም ሆነ ባልቤቲቱ ግለሰብነታቸውን (እነሱነታቸውን) ማጥፋት የለባቸውም፡፡ እያዳንዳቸው ከእግዚአብሔር ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት አላቸው፡፡ እያዳንዳቸውም እግዚአብሔርን “ትክክለኛው ነገር ምንድን ነው?” “ስህተቱስ ነገር የቱ ነው?” “የሕይወትንስ ዓላማ በተሻለ አኳኋን ልደርስበት የምችለው እዴት አድርጌ ነው?” ብለው መጠየቅ አለባቸው፡፡ ለሞተልህ አምላክ ፍቅርህን ለግስለት፡፡ ክርስቶስን የማንኛውም ነገር መነሻና መድረሻ አድርገው፡፡ ለእርሱ ያለህ ፍቅር እንደጠነከረና ሥር እንደሰደደ መጠን እርስ በእርሳችሁ ያላችሁ ፍቅር ንጹህና ጠንካራ እየሆነ ይሔዳል፡፡ CLAmh 16.3

ክርስቶስ ለኛ ያሳየን መንፈስ ባልና ሚስት እርስ በእርሳቸው ሊኖራቸው የሚገባ መንፈስ ነው፡፡ “ክርስቶስም ደግሞ እደወደዳችሁ፤ … በፍቅር ተመላለሱ፡፡ ዳሩ ግን ቤተክርስቲያን ለክርስቶስ እደምትገዛ እንዲሁም ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ፡፡ ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ደግሞ ቤተክርስቲያን እንደወደዳት ስለርስዋም ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ እንዲሁም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፡፡” ኤፌ 5፡2፣ 24፣ 25 CLAmh 16.4

ባልየው ሚስቱን፤ ሚስቱም ባልዋን በጭቆና ለመግዛት መሞከር የለባቸውም፡፡ የኔን ሐሳብ ካልተቀበሉ ብሎ ግትር ማለት አያስፈልግም፡፡ ይህን እያደረጉ ፍቅርን እንዲቀጥል ለማድረግ የማይቻል ነገር ነው፡፡ ቸር፣ ታጋሽ፣ ይቅር ባይ፣ አሳቢና አክባሪ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በጋብቻው ሥዕለት እንደተጠቀሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ጸጋ ባል ሚስቱን፤ ሚስትም ባልዋን ሊያስደስቱ ይችላሉ፡፡ CLAmh 16.5

ባልና ሚስት መፋቀራቸው ብቻ ደስታ ሊያስገኝ እንደማይችል ማስታወስ ይገባል፡፡ በአካባቢው የሚገኙትን ሰዎችም ለማስደሰት የሚያጋጥመውን ዕድል ሁሉ መጠቀም ነው፡፡ እውነተኛ ደስታ የሚገኘው ራስን ባለመውደድ አገልግሎት መሆኑን አለመርሳት ነው፡፡ CLAmh 17.1

በክርስቶስ አዲስ ሕይወት የሚኖሩ ሰዎች አንደበትና ምግባር በይቅርባይነትና ራስን ባለመውደድ ይለያል፡፡ ሌሎችን ለማገልገልና ራስን ለማሸነፍ እንደ ክርስቶስ ለመኖር እንደሞከርህ መጠን በየቀኑ ድልን ታገኛለህ፡፡ በዚህም አኳኋን ለዓለም በረከት ትሆናለህ፡፡ CLAmh 17.2