የተሟላ ኑሮ
የሁለት ሰዎች ሕይወት መዋሀድ
ምንም እንኳ ጋብቻ በጥንቃቄና በጥበብ ቢጀመርም የሠርጉ ዕለት በሙሉው የሚዋሃዱት ባልና ሚስት ጥቂት ናቸው፡፡ የሁለቱ እውነተኛ መዋሃድ የሚመጣው ከሠርጉ በኋላ በሚቀጥሉት ዓመታት ነው፡፡ ሙሽሮቹን የሕይወት ችግርና ጣጣ ሲጋፈጣቸው የሠርጉ ዕለት የነበረው የፍቅር ስሜት ይቀንስ ይሆናል፡፡ ባልና ሚስቱም በፊት ሊያደርጉት ከሚችሉት በበለጠ አኳኋን የእያንዳንዳቸውን ጠባይ ለማጥናት ይችላሉ፡፡ ከሕይወታቸው በጣም አስቸጋሪው ጊዜ ይህ ነው፡፡ የወደፊቱ ሕይወታቸው ደስታና ጠቃሚነት የሚወሰነው በዚህ ጊዜ ትክክለኛውን መስመር በመያዛቸውና ባለመያዛቸው ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በፊት ያላዩትን ጉድለት ከእያንዳንዳቸው ያገኛሉ፡፡ ሁሉም ስሕተት ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ ጥሩውን ጠባይ ለማየት ይጣሩ፡፡ ብዙውን ጊዜ የሌላው ሰው ጠባይ እንዲገለጽልን ወይም እንዳይገለጽልን የሚያደርገው የራሳችን ስሜት፤ ወይም የከበበን ሁናቴ ነው፡፡ CLAmh 15.2
ብዙ ሰዎች የፍቅርን ስሜት መግለጽ ነውር ስለሚመስላቸው ሰውን የሚያርቅ አስታየት ይታይባቸዋል፡፡ ይህ ዓይነት መንፈስ ርኅራኄን ይቀንሳል፡፡ የጋራ ኑሮ ፍላጎትና የተፈጥሮ ጥሩ ስሜቶች በደንብ እንዳልተገለጹ መጠን እየተቀነሱ ስለሚሔዱ ልብ እየቀዘቀዘና ባዶ እየሆነ ይሔዳል፡፡ ከዚህ ዓይነት ስህተት መጠንቀቅ አለብን፡፡ ፍቅር እንዲቀጥል ከተፈለገ መገለጽ አለበት፡፡ ፍቅርና ርኅራኄ በማጣት ምክንያት የሕይወት ጓደኛ (የባል ወይም የሚስት) ልብ መራብ የለበትም፡፤ CLAmh 15.3