የተሟላ ኑሮ
ፈቃድህ ይሁን
ስለ በሽተኞች ሲጸለይ “እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅም” የሚለው ሐረግ መረሳት የለበትም፡፡ ሮሜ 8፡26፡፡ የምንጠይቀው ልመና ቢፈጸም ይበጅ አይበጅ አናውቅም፡፡ ስለዚህ ስንጸልይ የሚከተለውን አባባል መጥቀስ ይገባናል፡፡ “ጌታ ሆይ፤ የሰውን ምሥጢር አበጥረህ ታውቃለህ፡፡ እነዚህን ሰዎች በሚገባ ታውቃቸዋለህ፡፡ ስለዚህ አንተን የሚያስከብርና እነርሱንም የሚጠቅም ከሆነ ምሕረትህን ላክላቸው፡፡ ይህንም በየሱስ ስም እንለምናለን፡፡ እንዲድኑ ፈቃድህ ካልሆነ ግን ጸጋህ እንዲያጽናናቸውና በአጠገባቸው ሆነህ እንድታበረታቸው፤ ሥቃያቸውንም የሚችሉበት ኃይል ስጣቸው፡፡” CLAmh 122.1
እግዚአብሔር ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ያውቃል፡፤ የልብን አሳብ በሙሉ ያውቃል፡፡ የሚጸለይላቸው ሰዎች ቢድኑ የሚገጥማቸውን ፈተና ሊቋቋሙት መቻል አለመቻላቸውንም አስቀድሞ ያውቃል፡፡ መኖራቸው ለሌሎችና ለራሳቸው በረከት ወይም መርገም መሆኑን ለይቶ ያውቀዋል፡፡ ጸሎታችን ከልብ ካቀረብን በኋላ “ያንተ ፈቃድ እንጅ የእኔ ፈቃድ ይሁን አልልም” ማለት የሚያስፈልገን ስለዚህ ነው፡፡ ሉቃስ 22፡42፡፡ የሱስ በጌቴሰማኒ ሲጸልይ የአብን ፈቃድ ሲለምን እንዲህ አለ፡፡ “አባት ሆይ የሚቻል ከሆነ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ” ማቴዎስ 26፡39 CLAmh 122.2
የእግዚአብሔር ልጅ እንደዚህ ማለት ካስፈለገው እኛ ሥጋ ለባሽ የሆንነውና ስህተተኞቹማ ምን ያህል ያስፈልገናል! CLAmh 122.3
ተገቢው መንገድ ምኞታችንን ሁሉ በሰማይ ላለው ጠቢብ አባታችን ማስረከብና ሙሉ በሙሉ በእርሱ ማመን ነው፡፡ CLAmh 122.4
እንደ ፈቃዱ ከለመነው እግዚአብሔር እደሚሰማን እናውቃለን፡፡ ልመናችንን ስናቀርብ መንፈሳችን ካላስገዛን ጸሎታችን ከንቱ ነው፡፡ ጸሎታችን ተማኅጽኖ እንጂ ትእዛዝ መሆን የለበትም፡፡ CLAmh 122.5
ጌታ አንዳንድ ጊዜ በመለኮታዊ ኃይሉ ታምር በመሥራት፤ በሽተኞችን ይፈውሳል፡፡ ግን በሽተኞች በሙሉ አይፈወሱም፡፡ ብዙዎች በየሱስ እንዲያንቀላፉ ይሆናሉ፡፡ ዮሐንስ በጳጥሞስ ደሴት ሳለ “በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብፁዓን ናቸው፤ መንፈስ አዎን፤ ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ ሥራቸው ይከተላቸዋል ይላል” ብሎ ጻፈ፡፡ ራዕይ 14፡13 CLAmh 122.6
ይህ አባባል የሚያመለክተን የታመሙ ሰዎች ከበሽታቸው ባለመዳናቸው ሃይማኖት የጐደለው ናቸው እንዳይባሉ ነው፡፡ ሁላችንም ጸሎታችን በቶሎ መልስ እንዲያገኝ እንፈልጋለን፤ መልሱ ሲዘገይና ባሰብነው መንገድ ሲመለስልን ተስፋ እንቆርጣለን፡፡ እግዚአብሔር ግን በምሕረቱ ጸሎታችን በፈለገው ጊዜና መንገድ አይመልስልንም፡፡ ምኞታችንን በሟሟላት ፋንታ ካሰብነው የተሻለና የበለጠ ነገር ያደርግልናል፡፡ ፍቅሩንና ጥበቡን ስለምናምን ምኞታችንን እንዲያደርግልን በመወትወት ፋንታ ፈቃዱን እንዲያደርግ መለመን አለብን፡፡ የእኛ ፍላጎትና ምኞት በእሱ ፈቃድ መዋጥ ይገባዋል፡፡ የዚህ ዓይነት እምነትን የሚጠይቅ አጋጣሚ ይጠቅመናል፡፡ እምነታችን ጥብቅና የማይናጋ ወይም ከጊዜ ጋር የሚነፍስ ሥር የሌለው መሆኑ ያን ጊዜ ይለያል፡፡ ሃይማኖት የሚጸናው በምግባር ነው፡፡ CLAmh 123.1
በጌታ ለሚያምኑ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የከበሩ ተስፋዎች መኖራቸውን በመገንዘብ መታገስ አለብን፤ ግን ይህን ደንብ ሁሉም አያስተውለውም፡፡ CLAmh 123.2
እግዚአብሔር ምሕረቱን እንዲልክላቸው የሚጸልዩ ብዙ ሰዎች ለጸሎታቸው መልስ ካላገኙ ሃይማኖታቸው የጐደለ ይመስላቸዋል፡፡ በበሽታ የተለከፉ ሰዎች ሁሉ እዲያመዛዝኑ ሊመከሩ ይገባል፡፡ ለቋሚ ዘመዶቻቸው ማሰብ አለባቸው፡፡ ጤናን ለማሻሻል የሚችሉትን የተፈጥሮ ጸጋዎችንም ችላ ማለት የለባቸውም፡፡ CLAmh 123.3
ብዙ ጊዜ በዚህ በኩል ከባድ ስሕተት ይፈጸማል፡፡ በጸሎት ኃይል ብቻ እንፈወሳለን በሚል እምነት ሌላ ነገር ማድረግ የእምነት ጉድለት የሚመስላቸው አሉ፡፡ ግን እሞት ይሆናል በሚል ጥርጣሬ ነገሩን ሁሉ መልክ ማስያዝ አለባቸው፡፡ ከዘመዶቻቸው ሊለዩ ሲሉ የመጽናኛና የምክር ቃላት መናገር ሊያስፈራቸው አይገባም፡፡ CLAmh 123.4