የተሟላ ኑሮ

114/201

እግዚአብሔር ጸሎትን ይሰማል

አምላክ ጸሎትን ሰሚ ነው፡፡ ክርስቶስ “በስሜ የለመናችሁትን ሁሉ አደርግላችኋለሁ” ይላል፡፡ (ዮሐንስ 14፡14) በተጨማሪም “የሚያገለግለኝ ቢኖር አብ ያከብረዋል” አለ፡፡ (ዮሐንስ 12፡26)፡፡ እንዳዘዘን ብንኖር ተስፋ የሰጠንን ነገር በሙሉ ይፈጽምልናል፡፡ ምህረቱ የማይገባን ሳለን በእርሱ ካመንን የሚያስፈልገንን ሁሉ ያደርግልናል፡፡ CLAmh 120.1

ግን ተስፋውን መውረስ የምንችል ያዘዘንን ስንፈጽም ብቻ ነው፡፡ ባለመዝሙሩ “በልቤ በደልን አይቼ ቢሆን ጌታ አይሰማኝም ነበር” ይላል፡፡ መዝሙር 66፡18፡፡ ከልብ ያልሆነ ታዛዥነት ብናሳየው ተስፋው አይፈጸምልንም፡፡ CLAmh 120.2

በሽተኞች እንዲድኑ የተለየ ጸሎት እንዴት እንደምንጸልይ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ ግን የዚህ ዓይነት ጸሎት ከፍተኛ ስለሆነ ልዩ ዝግጅት ሳይደረግ ሊሞክር አይገባም አንዳንድ ጊዜ ለበሽተኞች ሲጸልይ የሚታየው እምነት ከግምት ያልተሻለ ነው፡፡ CLAmh 120.3

ብዙ ሰዎች በበሽታ የሚለከፉ በራሳቸው ጥፋት ነው፤ በሕግና በንጽሕና ተወስነው አይኖሩም፡፡ ሌሎችም በአለባበሳቸው፤ በአበላላቸው ወይም በአጠጣጣቸው የጤናን ሕግ ይተላለፋሉ፡፡ ለአካልና ለአእምሮ መዳከም ምክንያት የሚሆነው አብዛኛውን ጊዜ ሕገ-ወጥነት ነው፡፡ ከበሽታው ነፃ ሆነው ጤናቸው ቢመለስላቸው እንደ ጥንቱ የእግዘአብሔርን መንፈሳዊና ተፈጥሮአዊ ሕግ መተላለፋቸውን ይቀጥላሉ፡፡ የሚያቀርቡትም ምክንያት እግዚአብሔር ጸሎት ሰሚ ሆኖ ከፈወሳቸው የፈለጉትን መብላትና መጠጣት መቻላቸውን ነው፡፡ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸውን ሰዎች በማዳን እግዚአብሔር ታምር ቢሠራ የኃጢአትን ሥራ እንደደገፈ ይቈጠር ነበር፡፡ CLAmh 120.4

ሰዎች ጤናቸውን ከሚጎዳ ነገር ሁሉ እንዲርቁ ካልተማሩ እግዚአብሔር ከማንኛውም ነገር እንደሚጠብቃቸው መናገር አጉል ድካም ነው፡፡ ለጸሎታቸው መልስ ለማግኘት ክፉ መሥራትን ትተው መልካም መሥራትን መማር አለባቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ተፈጥሮአዊና መንፈሳዊ ሕግ ማክበር ያስፈልጋቸዋል፡፡ CLAmh 120.5

በጸሎት ጤናቸውን ለማስመለስ የሚፈልጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕግ መሻር ኃጢአት መሆኑን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ከእግዚአብሔር በረከት ለማግኘት ደግሞ ከኃጢአት መናዘዝና ኃጢአትን መተው ማስፈለጉን ይገንዘቡ፡፡ CLAmh 121.1

መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ፡፡ ትፈወሱም ዘንድ አንዱ ለሌላው ይጸልይ፡፡ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች” ይላል፡፡ ያዕቆብ 5፡16፡፡ ጸልዩልኝ ብሎ የሚጠይቅ ሰው የሚከተለው መልስ ሊሰጠው ይችላል፡፡ “የልብህን እኛ አናውቅም፤ የሕይወትህን ምሥጢር ማንበብ ያዳግታል፡፡ ከኃጢአትህ መመለስና መናዘዝ የራስህ ፋንታ ነው፡፡” የግል ኃጢአት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል እርሱ ብቻ አማላጅ ለሆነው ለክርስቶስ ብቻ መነገር አለበት፡፡ “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡” 1ኛ ዮሐንስ 1፡9 “ማንም ኃጢአት ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ የሱስ ክርስቶስ ነው፡፡” (1ኛ ዮሐንስ 2፡1) ኃጢአት ሁሉ እግዚአብሔርን ስለሚያሳዝን በክርስቶስ አማካይነት ኃጢአትን መናዘዝ ያስፈልጋል፡፡ በግልጽ የተሠራውን ኃጢአት በግልጽ መናዘዝ ነው፡፡ የተበደለ ሰው ካለ ከሰውየው ጋር መታረቅ ያስፈልጋል፡፡ ጤናቸው እንዲመለስላቸው የሚፈልጉ ሰዎች ክፉ ነገር በመናገር በቤታቸው ውስጥ ጥል አፍርተው እንደሆን ወይም ጎረቤትን ካስቃየሙ፤ አለዚያም ቤተክርስቲያንን ቢበድሉ ነገሩን በተበደሉት ሰዎችና በእግዚአብሔር ዘንድ ማቃናት ያስፈልጋቸዋል፡፡ CLAmh 121.2

የጎደለው ከተቃና በኋላ ነገሩን በሃይማኖት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለእግዚአብሔር ልናቀርብ እንችላለን፡፡ እያንዳንዱ ሰው በስሙ ያውቀዋል፤ በምድር ላይ ሌላ አንዱን ልጁን የለወጠለት ሰው የሌለ በማስመሰል ለሁሉም ያስብለታል፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ታላቅና የማይወሰን ነው በሽተኛው ሊያምንበትና ሊጽናና ይገባል፡፡ ስለራስ ብቻ ማሰብና መባከን ደካማነትንና በሽታን ያስከትላል፡፡ CLAmh 121.3

ተስፋ ባይቆርጡና ባይተክዙ ቶሎ በዳኑ ነበር፡፡ “የእግዚአብሔር ዓይኖች ለምሕረቱ ወደሚታመኑት ናቸው፡፡” መዝሙር 33፡18 CLAmh 121.4