የተሟላ ኑሮ

88/201

የፈቃድ ኃይል

በክርስቶስ የሚያምኑ ሰዎች ሁሉ በተወረሰ ወይም ከራሳቸው በመነጨ አጉል ልምድ ሊታሠሩ አይችሉም፡፡ ለሥጋ ፍላጎታቸው በመገዛት ፋንታ ሱስና አመላቸውን ሁሉ ይቆጣጠራሉ፡፡ በተወሰነው ኃይላችን ክፉን ለብቻችን እንድንጋፈጠው እግዚአብሔር አልተወንም፡፡ ከዘርም ሆነ ከራሳችን ያገኘነው መጥፎ አመል እርሱ በሚሰጠን ኃይል ልንቋቋመው እንችላለን፡፡ CLAmh 89.7

ተፈታኙ የፈቃድን ኃይለኛነት ማወቅ ያሻዋል፡፡ በሰው ተፈጥሮ የሚገኘው የገዥነት ሥልጣን ይህ ነው፡፡ የመወሰንና የምርጫ ኃይል ነው፡፡ ሁሉ ነገር የሚወሰነው በፈቃዳችን መሠረት ነው፡፡ ከቀጠልንበት መልካምና የቀናውን ለመሥራት መመኘት ደግ ነው፤ ግን ሌላ ነገር ካልተጨመረበት ብቻውን አይረባም፡፡ ክፉ መንገዳቸውን ለማቃናት እየተመኙ ጠፍተው የሚቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ፈቃዳቸውን ለእግዚአብሔር አይሰጡም፡፡ እርሱን ማገልገል አይመርጡም፡፡ CLAmh 90.1

እግዚአብሔር የሰጠንን የምርጫ መብት ከሥራ ላይ ማዋል የእኛ ፋንታ ነው፡፡ ልባችንን ልንለውጥ፤ አሳባችንን ልንቆጣጠር፤ አለመቻላችን ልናርም አንችልም፡፡ ራሳችንን ንጹህ አድርገን ለእግዚአብሔር አገልግሎት ልናቀርብ እንችላለን፡፤ ፈቃዳችንን ልንሰጠው እንችላለን፡፡ ከዚያ በኋላ የሚያስደስተውን እንድንሠራ በእኛ በኩል አድሮ ይረዳናል፡፡ ራሳችን በክርስቶስ ቍጥጥር ሥር ይሆናል፡፡ ፈቃዳችንን በትክክል በማሠራት ሕይወታችን በሙሉ የተለወጠ ይሆናል፡፡ ፈቃዳችንን ለክርስቶስ በመስጠት ራሳችንን ከመለኮት ኃይል ጋር እናስተባብራለን፡፡ አጽንቶ የሚይዘን ብርታት ከላይ እንቀበላለን፡፡ ከጽኑውና ከኃያሉ አምላክ ጋር የራሱን ደካማ ፈቃድ የሚያስተባብር ሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ጨዋና ንጹህ ኑሮ መኖር፤ ሱስንና አመልን ድል መንሣት ይችላል፡፡ CLAmh 90.2

መጥፎ የምግብና የመጠጥን አምሮት ለማሸነፍ የሚታገሉ ሁሉ ስለጤና ደንብ መማር ይገባቸዋል፡፡ የጤናን ሕግ ችላ ማለት ጤናን ስለሚበድል የመጠጥ ሱስ መትከሉን ማወቅ አለባቸው፡፡ ከመጥፎ ልምድ መላቀቅ የሚችሉ የጤናን ሕግ አክብረው ሲኖሩ ብቻ መሆኑን ይወቁ፡፡ CLAmh 90.3

ከምግብ ግዛት በመለኮት ኃይል መላቀቅ እንደሚችሉ ሲያምኑ ሕጉን በመታዘዝ የሞራልንና የአካልን ደንብ ማክበር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይዞታቸውን ለማሻሻል የሚሞክሩ ሁሉ ርዳታ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ CLAmh 90.4

የወደቁትን ለማንሳት የሚደክሙት ሠራተኞች ብዙዎችን ተስፋ ከሰጡ በኋላ ቅር ያሰኙአቸዋል፡፡ በምግባቸውና በኑሮ ይዞታቸው የሚያሳዩት ለውጥ ለሰው ይምሰል ነው፡፤ በስሜት ብቻ ተነሳስተው ለጊዜው የተሸሻሉ ይመስላሉ፡፡ ግን ነገሩን ከልባቸው እንዳልያዙት ይታወቅባቸዋል፡፡ራሳቸውን መውደዳቸው፤ አጉል ደስታ መፈለጋቸው፤ ያው እንደዱሮው ይሆናል፡፡ ጠባይን የማሻሻል ችሎታና ዕውቀት የላቸውም፤ የደንብና የሥርዓት ሰዎች ተብለው ዕምነት ሊጣልባቸው አይችሉም፡፡ የማሰብና የሞራል ኃይላቸውን ባልተገባ ምግብና በከንቱ ነገር ስላደከሙት ያዋርዳቸዋል፡፡ ወላዋዮችና ያልጸኑ ናቸው፡፡ ስሜታቸው ጊዜያዊና ያልተገታ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ለሌሎችም እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ CLAmh 90.5

ተሻሽለዋል ተብለው ስለሚገመቱ ኃላፊነት ሲጣልባቸው አርኣያነታቸው ሌሎችን ያሰናክላል፡፡ CLAmh 91.1