የተሟላ ኑሮ

83/201

የአልኮሆል መጠጥ ነጋዴዎች ወዮላቸው

የሰዎችን ኑሮ በመበደል ሀብት የሚያካብቱትን ሰዎች ዓለምና ቤተክርስቲያን ይደግፏቸው ይሆናል፡፡ ሰዎች ወደ ውርደትና ወደ ሃፍረት ዝቅ እንዲሉ ምክንያት የሆነውን ሰው በፈገግታ ፊት ይቀበሉት ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ግን ይመዘግበዋል፤ ትክክለኛውን ፍርድም ይበይናል፡፡ የአልኮሆል መጠጥ ነጋዴው በዓለም ዘንድ “መልካም ነጋዴ” የሚል ስያሜ ያገኝ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ግን “ወዮልህ” ይለዋል፡፡ በመጠጥ ጠንቅ ለደረሰው ተስፋ መቍረጥ፣ ሥቃይ፣ መከራ ሁሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ CLAmh 84.2

ተስፋ ለቆረጡት፤ ደስታ ፊቷን ላዞረችባቸው፤ ልብስና መጠለያ ላጡት፤ የሚቀመስ የሚላስ አጥተው በረኃብ አለንጋ ለሚገረፉት እናቶችና ልጆች የመጠጥ ነጋዴው ኃላፊነት አለበት፡፡ ለዘለዓለም ሳይዘጋጁ ለተሰናበቱት ነፍሳት ተጠያቂው ራሱ ነው፡፡ የመጠጥ ነጋዴውን የሚደግፉ ሁሉ የወንጀሉ ተካፋዮና አባሪ ተባባሪዎች ናቸው፡፡ “እጃችሁ በደም የረከሰ ነው፡፡” CLAmh 84.3

ለአልኮሆል ንግድ ፈቃድ መስጠት እንዳይስፋፋ ይረዳል የሚሉ አሉ፡፡ ግን ፈቃድ መስጠቱ በሕግ የተደገፈ ያደርገዋል፡፡ መንግሥት ንግዱን በመፍቀዱ እከላከላለሁ የሚለውን ወንጀል እንዲበረክት ያደርጋል፡፡ የሕግ ፈቃድ ስለሚሰጥ የመጠጥ ፋብሪካዎች የትም እንደ እንጉዳይ ይፈነዳሉ፡፡ ስለዚህ የመጠጥ ንግድ በየደጃችን ደርቷል፡፡ CLAmh 84.4

የመጠጥ ነጋዴው ለሰከረ ወይም ሰካራምነቱ ለታወቀ ሰው አልኮሆል መጠጥ አትሽጥ የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፡፡ ግን ወጣቶችን ከሰካራም መዝገብ የመመደቡና የሰካራሙን ቁጥር የማበርከቱ ሥራ እንደቀጠለ ነው፡፡ የንግዱ መዳበር የተመረኮዘው በወጣት ሰካራሞች መብዛት ላይ ነው፡፤ ወጣቶች ቀስ በቀስ የመጠጥ ሱሰኞ ይሆኑና እንደምንም ብለው የመጠጥ ሱሳቸውን ማርካት ከሚያስፈልጋቸው ደረጃ ይደርሳሉ፡፡ ለታወቁ ሰካራሞች አልኮሆል ከመፍቀድ ይልቅ የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች የሆኑትን ወጣቶች የአልኮሆል ሱሰኞች አድርጎ አበባቸውን ፍሬ ሳይሰጥ ማርገፉ የበለጠ ጉዳት አለው፤ የአልኮሆል መጠጥ ንግድ በሕግ በመፈቀዱ የጤናን ደንብ ለማክበር በሚሞክሩት ሰዎች ፊት ከባድ ፈተና ተደቅኖባቸዋል፡፡ CLAmh 84.5

መሻታቸውን መግዛት ያቃታቸው ሰዎች ጠባያቸውን የሚያርሙባቸው ድርጅቶች ተቋቁመው ነበር፡፡ ይህ አድራጎት ትልቅ ሥራ ቢሆንም የአልኮሆል መጠጥ ንግድ በሕግ ከተፈቀደ የመጠጥ ሱሰናው ሊረዳ መቻሉ ዘበት ነው፡፡ CLAmh 85.1

የመጠጥን ሱስ ለጊዜው መቆጣጠር ቢቻልም ፈጽሞ ማጥፋት አይቻልም፡፡ ስለዚህ እንደሌላው ኃጢአት ሁሉ ፈተና ሲበዛ መውደቁ አይቀርም፡፡ CLAmh 85.2

አደገኛ እንስሳ ያለው ሰው አደገኛነቱን እያወቀ በቸልተኛነት ቢለቀው እንስሳው ለሚያደርሰው ጉዳት ሁሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ እግዚአብሔር ለእሥራኤሎች በሰጠው ሕግ ላይ የአንድ ሰው እንስሳ ለሌላው ሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት ከሆነ የእስሳው ጌታ በቸልተኝነት ላደረሰው ጉዳይ በሞት ይቀጣ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት የመጠጥን ንግድ የፈቀደ መንግስት ለሚመጣው ጉዳት ሁሉ ኃላፊነት አለበት፡፡ አደገኛ እንስሳን መልቀቅ በሞት የሚያስቀጣ ከሆነ የመጠጥን ንግድ በነፃ ለቆ ሕዝብን ማስረስ ቅጣቱ ምን ይሆን! CLAmh 85.3