የተሟላ ኑሮ

39/201

የተሟላ ትምህርት

ከወላጆችና ከመምህራን ሳይንስን ለማስተማር ከሚጠየቀው የበለጠ የሚጠይቅ የተሟላ ትምህርት ይፈለጋል፡፡ በአእምሮ ውስጥ እውቀትን ከማጨቅ የበለጠ ነገር ይፈለጋል፡፡ ትምህርት የተሟላ የሚሆነው አካል፣ አእምሮና ልብ እኩል ትምህርት ሲያገኙ ነው፡፡ ጠባይ በደንብ እንዲመሠረት ትክክለኛ ቁጥጥር ያስፈልገዋል፡፡ የአካልና የአእምሮ ችሎታዎች ሁሉ መዳበርና በትክክል መመራት አለባቸው፡፡ CLAmh 39.1

እውነተኛ ትምህርት መላውን አካል ያጠቃልላል፡፡ ሰው እሱነቱን በትክክል እንዲጠቀምበት ያስተምራል፡፡ አእምሮን፣ አጥንትን፣ ሥጋን፣ አካልን፣ አንጎልንና ልብን በሚገባ እንድንጠቀምባቸው ያስችለናል፡፡ አእምሮ ከፍተኛ ኃይል እንደመሆኑ መጠን አካልን ማስተዳደር አለበት፡፡ የተፈጥሮ ፍላጎቶችና ስሜቶች በሕሊናና በመንፈሳዊ ስሜቶች መገታት አለባቸው፡፡ ክርስቶስ የሰብአዊ ፍጡር ሁሉ መሪ እንደመሆኑ በአገልግሎቱ በንጽህናና በቅድስና መንገድ ሊመራን ፈቃዱ ነው፡፡ በአስገራሚ የጸጋ ሥራው በእርሱ ፍጹም መሆን አለብን፡፡ CLAmh 39.2

የሱስ ትምህርቱን ከቤቱ አገኘ፡፡ ከሰው የመጀመሪያ አስተማሪው እናቱ ነበረች፡፡ ከነቢያት ብራናዎች ስለ ሰማያዊ ነገር ተማረ፡፡ በድኃ ቤት ኖረ፤ ከቤተሰቡም ቀንበር ድርሻውን በታማኝነትና በደስታ ተሸከመ፡፡ የሰማይ አዛዥ የነበረው ፈቃደኛ አገልጋይ፤ አፍቃሪና ታዛዥ ልጅ ሆነ፡፡ ሙያ ተማረ፤ በአናጺም ሱቅ ከዮሴፍ ጋር በእጁ ሠራ፡፡ የተራ ሰው የሥራ ልብስ ለብሶ ከሥራው ወደ ቤቱ፣ ከቤቱም ወደ ስራው በትንሽዋ ከተማ ይመላለስ ነበር፡፡ CLAmh 39.3

በዚያን ዘመን የነበሩ ሰዎች የማንኛውንም ነገር ዋጋ የውጩን በማየት ይገምቱ ነበር፡፡ ሃይማኖት በኃይል እየቀነሰ ሲሔድ የታይታ ነገር እየገነነ ሔደ፡፡ ያን ጊዜ የነበሩትም መምህራን በእዩልኝ ነገር ይከበሩ ነበር፡፡ የየሱስ ሕይወት ከነዚህ ሁሉ በጣም የተለየ ነበር፡፡ ሕይወቱ ሰዎች ለሕይወት አስፈላጊ ናቸው ብለው የያዝዋቸውን ነገሮች ከንቱነት ገለጸ፡፡ ትልቁን ትንሽ፤ ትንሹንም ትልቅ የሚያደርጉትን የጊዜውን ትምህርት ቤቶች አልፈለጋቸውም፡፡ ትምህርቱን ያገኘው እግዚአብሔር ካዘጋጃቸው ምንጮች፣ ከጠቃሚ ሥራ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት፣ ከሥነ ፍጥረትና ከሕይወት ልምድ ነበር፤ እነዚህም የእግዚአብሔር የማስተማሪያ መጻሐፍት ፈቃደኛ እጅ፣ የሚያይ ዓይንና አስተዋይ ልብ ላላቸው ሁሉ ብዙ ትምህርት ይገኝባቸዋል፡፡ CLAmh 39.4

“ሕጻኑም አደገ፤ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ” ሉቃስ 2፡40 CLAmh 39.5

በዚህ አኳኋን ተዘጋጀና የመጣበትን ሥራ ጀመረ፤ ከሰውም ጋር በተገናኘ ቁጥር ዓለም ዓይቶት በማያውቀው አኳኋን የበረከት ስሜትና የሚለውጥ ኃይል ይሰጣቸው ነበር፡፡ CLAmh 40.1