የተሟላ ኑሮ

28/201

የምግብ አምሮትን መቆጣጠር

ወላጆች የልጆቻቸውን የምግብ ፍላጎት መቆጣጠር አለባቸው፤ ለጤና የማይስማማ ምግብ እንዲበሉ ሊፈቅዱላቸው አይገባም፡፡ ምግባቸውን ለመመጠን በምንጥርበት ጊዜ ልጆች የማይፈልጉትን ነገር እንዲበሉ ወይም ያለ ልክ እንዲበሉ ላለማስገደድ መጠንቀቅ አለብን፡፡ የልጆች መብት ሊጠበቅ ይገባዋል፡፡ የሚፈልጉትንም ነገር ስህተት ካልሆነ ሊነፈጉ አይገባም፡፡ CLAmh 29.6

በተወሰነ ሰዓት የመብላት ሐግ ሊጠበቅ ይገባዋል፡፡ በምግብ ሰዓቶች መካከል ምንም ዓይነት ምግብ፤ ማለት ኦቾሎኒ፣ ፍራፍሬ ሊበላ አይገባል፡፡ ያለ ጊዜ መብላት የጨጓራንና የአንጀትን ሁናቴ ስለሚያቃውስ የጤንነትንና የደስታ ስሜትን ይቀንሳል፡፡ ልጆች በምግብ ሰዓት ትክክለኛውን ምግብ ካላገኙ የምግብ አምሮታቸው ወደ ሚጎዳቸው ምግብ ያዘነብላል፡፡ CLAmh 30.1

የልጆቻቸውን ያልተስተካከለ የምግብ አምሮት ለማርካት ሲሉ ጤናን የሚያጓድል ነገር ለልጆቻቸው የሚያደርጉ ወላጆች ሁሉ ቆይቶ የሚያፈራ መጥፎ ዘር መዝራታቸውን ይወቁት፡፡ በቃኝን ያለማወቅ ልምድ አብሯቸው ያድግና የአእምሮና የአካላቸውን ኃይል የሚያዳክም ጠንቅ ይሆንባቸዋል፡፡ የዚህ ዓይነት ዘር የሚዘሩ ወላጆች የጸጸትና የእንባ መከር ይሰበስባሉ፡፡ ልጆቻቸው ለቤተሰብም ሆነ ለኅብረተሰብ የማይጠቅ ሆነው ሲያድጉ ያይዋቸዋል፡፡ ጤናን የማይሰጥ ምግብ መብላት የአካልንና የመንፈስን ኃይል ይቀንሳል፡፡ ሕሊና ስለሚደነዝዝ ጥሩ ነገር ለመቀበል ያለው የስሜት ኃይል ይቀንሳል፡፡ CLAmh 30.2

ልጆች የምግብ አምሮታቸውን እንዲገቱና ለጤና የሚስማማ ምግብ ብቻ እንዲበሉ በሚማሩበት ጊዜ የሚከለከሉት ነገር ሁሉ የሚጐዳቸው መሆኑን መረዳት አለባቸው፡፡ የሚጐዳ ነገር የሚተዉት የተሻለ ነገር ለማግኘት ሲባል ነው፡፡ እግዚአብሔር በችሮታው የሰጠን ምግብ በገበታ ላይ በተደረደረ ጊዜ ልጆች ለመብላት እንዲጓጉ የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡ በእግዚአብሔር ስጦታ በምንደሰትበት ጊዜ ላገኘነው ጸጋ ምስጋና ማቅረብ አለብን፡፡ CLAmh 30.3

ብዙውን ጊዜ ልጆች የሚታመሙበት ምክንያት ከወላጆች ጥንቃቄ ማነስ የተነሣ ነው፡፡ የሕመም መነሻ ሰበብ የሚሆኑት ያለጊዜ መብላት፣ በብርድ ጊዜ በቂ ልብስ አለመልበስ፣ ደም በደንብ እንዲዘዋወር የሚያደርግ የሰውነት ማጠንከሪያ ልምምድ አለማድረግና ንጹህ አየር አለማግኘት ናቸው፡፡ ወላጆች የህመምን መነሻ ምክንያት ማወቅና በፍጥነት ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ CLAmh 30.4

ወላጆች ሕመምን የመከላከልና በመጠኑ ሕክምና የመስጠት ችሎታ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በተለይ እናቲቱ በቤት ውስጥ ሕመም በተነሳ ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባት ማወቅ አለባት፡፡ የታመመውን ልጅ እንዴት ማስታመም እንዳለባት ማወቅ ይገባታል፡፡ ለሌላ አስታማሚ ሊሰጥ የማይገባውን የፍቅርና የርኅራሔ ሕክምና ራስዋ መቻል አለባት፡፡ CLAmh 30.5