የተሟላ ኑሮ
ለምጻሙ ነፃ
በምሥራቅ አገር ካለው የበሽታ ዓይነት ሁሉ እንደ ለምጽ አሰቃቂ የበሽታ ዓይነት አልነበረም፡፡ ሊድን የማይችልና ተላላፊ ከመሆኑም በላይ የበሽተኛውን ገላ ሲያፈራርሰው ጀግና ነኝ ባዩ ሳይቀር ያን ሲመለከት ይባባል፡፡ በአይሁዶች አስተያየት ደግሞ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣ ሕመም ተብሎ ስለሚታመንበት “ቅጣት” “የእግዚአብሔር እጅ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ CLAmh 149.4
ስር የሰደደ፤ የማይድን ለሞት የሚያደርስ በመሆኑ የኃጢአት ምልክት ሆኖ ይቆጠር ነበር፡፡ CLAmh 149.5
በኦሪት ሕግ የለምፅ በሽታ የያዘው ሰው ርኩስ ተብሎ ይጠራ ነበር፡፡ በበሽተኛው ትንፋሽ አየሩ እንደተበከለ ይቈጠራል፡፡ እንደ ሞተ ተቈጥሮ ከሕዝብ መኖሪያ ይገለላል፡፡ በበሽታው የተጠረጠረ ሰው ራሱን ነገሩን ለሚወስኑት ለካህናት ማስመርመር ነበረበት፡፡ ለምፃም ነው ከተባለ ከወዳጅ ከዘመድ ተለይቶ፤ ከእሥራኤል ጉባዔ ወጥቶ በበሽታው ከተለከፉት ከሌሎች መሰሎቹ ጋር እንዲኖር ይፈረድበታል፡፡ CLAmh 149.6
አይጣል እንጂ ከጣለ ነገሥታትና ገዥዎችም ልዩነት አይደረግላቸውም፡፡ ሕመሙ ያደረበት ንጉሥ በትረ መንግስቱን አስረክቦ ከኅብረተሰብ ይወገዳል፡፡ CLAmh 150.1
ከወዳጅ ከዘመድ በመለየት ለምፃሙ ስለ ኃጢአቱ ተቀጣ ማለት ነው፡፡ የራሱን በሽተኛነት እንዲያውጅ፤ ልብሱን እንዲቀድ፤ ሌሎች ሰዎች በሽታው እንዳይጋባባቸው እንዲሸሹ ማስጠንቀቅ ነበረበት፡፡ CLAmh 150.2
“ርኩስ! ርኩስ!” የሚለው ቃል ከበሽተኛው ከተሰማ በፍርሃትና በድንጋጤ ከእርሱ ዘንድ መሸሽ ብቻ ነው፡፡ ክርስቶስ በሚያስተምርበት አካባቢም ለምፃሞች ነበሩ፡፡ ስለርሱ ወሬ በሰሙ ጊዜ ከመካከላቸው አንዱ ዕምነት ተሰማው፡፡ ግን የሱስን እንዴት ሊያገኝ ይችላል? ለዘለዓለም ብቻውን እንዲኖር ተፈርዶበት ሳለ እንዴት ወደ ፈዋሹ ሊቀርብ ይችላል? ክርስቶስ ይፈውሰው ይሆን? እንደፈሪሣውያንና እንደ ሐኪሞቹ ከሕዝብ እንዲለይና ርጉም መሆኑን ይናገርበት ይሆን? CLAmh 150.3