የተሟላ ኑሮ

129/201

ቀላል ምግብ ማቅረብ

ክርስቶስ ሕዝቡን በተአምር መገበ፡፡ ግን የቀረበው ምግብ ቀላል ነበር፡፡ የገሊላ ዓሣ አጥማጆች የዕለት ምግብ የሆነው የገብስ እንጀራና ዓሣ ነበር፡፡ ክርስቶስ ለሕዝቡ ግሩም ድግስ ማዘጋጀት በቻለ ነበር፤ ግን ፍላጎትን ለማርካት የተዘጋጀ ውድ ምግብ ትምህርት ሰጭነቱ አጭር ነው፡፡ CLAmh 139.1

ክርስቶስ በዚህ ተዓምር አማካይነት በልክ መኖር ጠቃሚ መሆኑን ሊያስተምራቸው ፈለገ፡፡ CLAmh 139.2

ዛሬ ሰዎች እንደ አዳምና እንደ ሔዋን በልክ ቢኖሩ ኖሮ ለሰው ዘር የፈለገው ነገር ሁሉ በተትረፈረፈለት ነበር፡፡ ግን ሁሉን ለእኔ የማለት ስሜትና መስገብገብ ኃጢአትና ችግርን አስከተለ፡፡ አንዱ ክፍል በቁንጣን ሲጨነቅ ሌላው ክፍል በችጋር ይሰቃያል፡፡ CLAmh 139.3

ክርስቶስ ሰዎችን በድሎትና በምቾት በማቀማጠል ተከታዮቹ ሊያደርጋቸው አልፈለገም፡፡ ለዚህ ለደከመውና ለተራበው ጉባዔ ቀላል ምግብ ማቅረቡ ደግነቱንና ኃይሉን መግለጡ ነበር፡፡ ክርስቶስ ተከታዮቹን የአለም ከበርቴዎች ለማድረግ ቃል አልገባላቸውም፡፡ እንዲያውም ከድሆች ጋር ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ ግን የሚስፈልጋቸውን እንደሚያዘጋጅላቸው ቃል ገብቶላቸዋል፡፡ ከዚህ ዓለም ሀብት ሁሉ የበለጠውን የእርሱን መገኘት አረጋግጦላቸዋል፡፡ CLAmh 139.4

ጉባዔው ተመግቦ ካበቃ በኋላ ብዙ ምግብ ተረፈ፡፡ የሱስ “ምንም እንዳይባክን ትራፊውን ሰብስቡት” አላቸው፡፡ (ዮሐንስ 6፡12) ፡፡ ይህ ትዕዛዝ በቅርጫት ከመሰብሰብ የበለጠ ትርጉም አለው፡፡ ሁለት ትርጉም አዝሏል፡፡ ምንም ነገር ቢሆን መባከን የለበትም፡፡ የሰብአዊ ዘርን ሊያገለግልና ሊጠቅም የሚችል ከሆነ ማንኛውንም ነገር መናቅ ተገቢ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ ያሉትን ረሃብተኞች የሚያጠግብ ነገር ከሆነ በሚገባ መጠበቅ አለበት፡፡ በዚሁ አንፃር ከሰማይ የሚወርደውን የሕይወት እንጀራ ነፍሳትን እንዲጠግን በሥራ ላይ ማዋል አለብን፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል በሙሉ ማክበር ያሻናል፡፡ እግዚአብሔር ከተናገረው ሁሉ ምንም መጣል የለበትም፡፡ ሊያድነን የሚችለውን የእግዚአብሔርን ቃል ችላ ማለት የለብንም፡፡ አንድም ቃል ጥቅም እንደሌለው ተቆጥሮ በመሬት ላይ መውደቅ የለበትም፡፡ CLAmh 139.5