ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ
ምዕራፍ 8 - ወደክርስቶስ ሙላት ማደግ
በእግዚአብሔር ልጆች የምንሆንበትን የልብ ለውጥ መጽሐፍ ቅዱስ ከመወለድ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ እንዲሁም በገበሬ ከተዘራና ከሚያቆጠቁጥ ጥሩ ዘር ጋር ያነጻጽረዋል፡፡ ከዚህ አኳያ፣ ወደ ክርስቶስ የተለወጡ ሁሉ «አዲስ እንደተወለዱ ህፃናት» በክርስቶስ ሙሉ ሰው ወደ መሆን «ማደግ» እንደሚያስፈልጋቸው ወይም በእርሻ እንደተዘራ መልካም ዘር፣ ማደግና ፍሬ ማፍራት እንደሚኖርባቸው ተጽፎአል (1ኛ ጴጥ. 2:2፣ ኤፌ. 4:15)፡፡ ኢሳይያስም «እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የፅድቅ ዛፎች ይባላሉ» ይለናል (ኢሳ. 61፡ 3)፡፡ የመንፈሳዊውን ሕይወት ምስጢራዊ እውነቶች በተሻለ ሁኔታ ለመረዳት እንችል ዘንድ እነዚህ ምሳሌዎች ከተፈጥሮ ተወስደዋል:: ክየመ 62.1
የሰው ጥበብ እና ክህሎት ሁሉ ትንሿ የተባለችን ሕይወት ማፍራት አይችልም፡፡ እፅዋት ወይም እንስሳት በሕይወት የሚኖሩት እግዚአብሔር ራሱ በሚሰጣቸው ሕይወት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በሰዎች ልብ ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወት የሚወለደው ከእግዚአብሔር በሚገኝ ሕይወት ብቻ ነው:: መንፈሳዊ ሕይወትም እንደዚሁ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ የሚወለደው ከእግዚአብሔር በተገኘ ሕይወት አማካይነት ብቻ ነው:: አንድ ሰው «ከላይ ካልተወለደ በስተቀር ክርስቶስ ሊሰጠን የመጣው ሕይወት ተካፋይ ሊሆን አይችልም ዮሐ. 3:3)፡፡ እድገትንም በተመለከተ እንደዚያው ነው፡፡ እንቡጥን ወደ ማበብ ፣ አበባንም ወደ ፍሬነት የሚለውጠው እግዚአብሔር ነው:: ዘር የሚያድገው በእግዚአብሔር ኃይል ነው:: «ምድሪቱ አውቃ በመጀመሪያ ቡቃያ ኋላም ዛላ ኋላም በዛላው ፍፁም ሰብል ታፈራለች» (ማር. 4:28)፡፡ ነብዩ ሆሴዕ ስለ እስራኤል ሲናገር «እንደ አበባ ያብባል፤» «እንደ ወይንም አረግ ያብባሉ፤ መታሰቢያውም እንደ ሊባኖስ ወይን ጠጅ ይሆናል፡፡» ይላል (ሆሴዕ 14፡5-7)፡፡ እንደዚሁም ኢየሱስ «አበቦችን እንዴት እንዲያድጉ ተመልከቱ፤» በማለት ይናገረናል (ሉቃ.12:27)፡፡ ዕፅዋትና አበቦች በራሳቸው ክብካቤ ወይም ጭንቀት ወይም ጥረት አያድጉም:: እነርሱ የሚያድጉት ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን በሙሉ ከእግዚአብሔር በመቀበል ነው፡፡ አንድ ህፃን ልጅ የተቻለውን ያህል እንኳን ቢጥር በቁመቱ ላይ ምንም ሊጨምር እንደማይችል ሁሉ እኛም በራሳችን ጥረት መንፈሳዊ ዕድገትን ልናመጣ ከቶ አንችልም፡፡ እፅዋት እና ህፃናት ለሕይወታቸው የሚያስፈልጋቸውን አየር፣ የፀሐይ ብርሃንና ምግብ ስለሚያገኙ ነው ዕድገትን የሚያሳዩት:: ተፈጥሮ ለእንስሳት እና ለእፅዋት የምትለግሳቸውን እነዚህን ነገሮች ክርስቶስ ደግሞ በእርሱ ለሚታመኑት ይሰጣቸዋል፡፡ እርሱ ለእነርሱ «የዘለዓለም ብርሃን» «ፀሐይ እና ጋሻ» ነው (ኢሳ. 60፡19፤ መዝ. 84፡11)፡፡ እርሱ «የእስራኤል ጠል» ነው:: «በግጦሽ ሳር ላይ እንደዝናብ ይመጣል» (ሆሴ. 14፡5፤ መዝ. 72:6)፡፡ እርሱ የሕይወት ውሃ ነው:: «የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነው» ዮሐ. 6፡33)። ክየመ 62.2
ተወዳዳሪ በሌለው በልጁ ስጦታ፣ እግዚአብሔር አለምን ልክ እንደተከበበችበት አየር በጸጋው ከቧታል:: ይህንን ሕይወት ሰጪ አየር ለመተንፈስ ፈቃደኞች የሆኑ ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ያለውን ሕይወት ይኖራሉ፤ ወደ ሙሉ ሰውነት ደረጃም ያድጋሉ፡፡ ውበትና መልካም አቋም እንዲኖረው አበባ የብርሃን ጨረርን ለማግኘት ወደ ፀሐይ እንደሚያጋድል እኛም የሰማይ ብርሃን በእኛ ላይ እንዲያበራና ባሕርያችን ክርስቶስን ወደ መምሰል እንዲያድግ ወደ ጽድቅ ጸሐይ ፊታችንን ልናዞር ይገባል፡፡ ክየመ 63.1
ኢየሱስ በዮሐንስ 15:4-5 ላይ ‹በእኔ ኑሩ እኔም በእናንተ፡፡ ቅርንጫፍ በወይኑ ግንድ ባይኖር ከራሱ ፍሬ ሊያፈራ እንዳይቻለው፣ እንዲሁም ደግሞ በእኔ ባትኖሩ አትችሉም:: እኔ የወይን ግንድ ነኝ እናንተም ቅርንጫፎች ናችሁ፡፡ ያለእኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉምና በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፣እርሱ ብዙ ፍሬ ያፈራል፡፡» በማለት ተመሳሳይ ነገርን አስተምሯል፡፡ ቅርንጫፍ ለማደግ እና ፍሬ ለማፍራት በግንዱ ላይ ጥገኛ እንደሚሆን ሁሉ እናንተ የቅድስና ሕይወት እንድትኖሩ በክርስቶስ ላይ ጥገኞች ናችሁ::ከእርሱ ተለይታችሁ ሕይወት አይኖራችሁም፡፡ ያለ እርሱ ፈተናን ለመቋቋም ወይም በጸጋ እና በቅድስና ለማደግ ብቃት አይኖራችሁም፡፡ በእርሱ ከኖራችሁ ታብባላችሁ:: ሕይወታችሁ ከእርሱ ጋር የተጣበቀ ከሆነ አትደርቁም፤ ፍሬ አልባም አትሆኑም፡፡ በወንዝ ዳር እንደተተከለ ዛፍ ሁልጊዜ ለምለም ትሆናላችሁ፡፡ ክየመ 63.2
ብዙዎች በመንፈሳዊ ሕይወት ለማደግ የሚያስፈልገውን ሥራ ቢያንስ የተወሰነውን ክፍል ብቻቸውን የመሥራት ሃሳብ አላቸው:: በርግጥ ለኃጢአታቸው ይቅርታን ለማግኘት ክርስቶስን ታምነው የነበረ ቢሆንም፣ መንፈሳዊ ሕይወትን ለመኖር ግን በራሳቸው ጥረት ላይ ይደገፋሉ፡፡ ይሁን እንጂ፣ እንዲህ ያለው ጥረት የማይሳካ ነው:: ኢየሱስ «ከእኔ በቀር ምንም ልታደርጉ አትችሉም» ብሎናል፡፡ የእኛ በፀጋ ማደግ፣ ደስታና ጠቃሚነታችን ሁሉ ከክርስቶስ ጋር በሚኖረን ሕብረት ላይ የተመሰረተ ነው:: በፀጋ የምናድገው ከእርሱ ጋር ዕለት ተዕለትና በየሰዓቱ ስንኖር እንዲሁም በእርሱ ውስጥ ስንሆን ነው:: እርሱ የእምነታችን ጀማሪ ብቻ ሳይሆን ፈጻሚም ነው፡፡ ክርስቶስ ፊተኛውና ኋለኛው እንዲሁም ሁሉ በሁሉ ነው:: እርሱ በጅማሬ እና በፍፃሜያችን ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን በእያንዳንዱ ርምጃ ላይ አብሮን ሊሆን ይገባል፡፡ ዳዊት በመዝሙር 16፡8 ላይ «ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን በፊቴ አየዋለሁ በቀኜ ነውና አልታወክም፡፡» ብሏል፡፡ ክየመ 64.1
«በክርስቶስ እንዴት እኖራለሁ?» ብላችሁ ጠይቃችኋል? በእርሱ የምትኖሩት ልክ መጀመሪያ እርሱን ስትቀበሉት በነበረበት ሁኔታ ነው፡፡ «እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፡፡» «ፃድቅ ግን በእምነት ይኖራል» (ቆላ. 2፡6፤ ዕብ 10:38)፡፡ ሙሉ በሙሉ የእርሱ ለመሆን፣ እርሱን ለማገልገልና ለመታዘዝ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር ሰጥታችኋል፤ ክርስቶስንም እንደ ግል አዳኛችሁ ተቀብላችሁታል:: በራሳችሁ ኃጢያታችሁን ልታስተሰርዩና ልባችሁንም ልትለውጡ አትችሉም፡፡ በራሱ የሚታመን አዕምሮ የብርታትና የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከክርስቶስ የራቀ ነው፡፡ ነገር ግን ራሳችሁን ለእግዚአብሔር በመስጠት እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስለ ክርስቶስ ሲል እርሱ እንዳደረገላችሁ አምናችኋል፡፡ በእምነት የክርስቶስ ሆናችኋል:: እንደዚሁም በመስጠትና በመቀበል ላይ በተገነባ እምነት በእርሱ ውስጥ ታድጋላችሁ:: እርሱን በሁሉም መስፈርቱ ለመታዘዝ ልባችሁን ፣ በፊስ ፈቃዳችሁን፣ አገልግሎታችሁን፣እራሳችሁንም ባጠቃላይ ሁለንተናችሁን ለእርሱ መስጠት አለባችሁ:: ከዚያም ክርስቶስ ጥንካሬያችሁ እንዲሆን፣ጽድቃችሁና የዘላለም ረድኤታችሁ እንዲሆንላችሁ፣ ለመታዘዝ ኃይል እንዲሰጣችሁ እርሱን ከነሙሉ በረከቱ በልባችሁ እንዲኖር መውሰድ አለባችሁ:: ክየመ 64.2
በማለዳ እራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሱ፤ ይህ የመጀመሪያ ሥራችሁ እንዲሆን አድርጉ፡፡ ፀሎታችሁ «ኦ! ጌታ ሆይ ውሰደኝ፣ ሙሉ በሙሉ የራስህ አድርገኝ! እቅዶቼን ሁሉ በእግርህ ስር አስቀምጣለሁ፡፡ ዛሬ ለአገልግሎትህ ተጠቀምብኝ። ከእኔ ጋር ሁንና የማደርገውን ነገር ሁሉ በአንተ እንዳደርገው እርዳኝ» የሚል ይሁን፡፡ ይህም በየዕለቱ የምንለማመደው ፀሎት ይሁን፡፡ በየማለዳው ለዚያን ቀን እራሳችሁን ለእግዚአብሔር ቀድሳችሁ ስጡ:: የእርሱ ምሪት በሚያሳያችሁ መሰረት ወይ እንዲከናወኑ አልያም እንዲከሽፉ እቅዶቻችሁን ሁሉ ለእርሱ ስጡ፡፡ በዚህም መሰረት ዕለት በዕለት ሕይወታችሁን ለእግዚአብሔር እጆች ትሰጣላችሁ፤ሕይወታችሁም ክርስቶስን ወደ መምሰል እየተለወጠ ይሄዳል፡፡ ክየመ 65.1
በክርስቶስ የሆነ ሕይወት የዕረፍት ሕይወት ነው፡፡ ምንም አይነት የፍንደቃ ስሜት ላይኖረን ይችላል፤ ነገር ግን በሰላም የተሞላ መታመን ይኖረናል፡፡ ተስፋችን በራሳችን ሳይሆን በክርስቶስ ነው:: የእኛ ድካም ከእርሱ ብርታት፣ አላዋቂነታችን ከእርሱ ጥበብ፣ ልፍስፍስነታችን ከእርሱ ዘለዓለማዊ ኃይል ጋር ተቆራኝቶአል፡፡ ስለዚህም መመልከትና አዕምሮአችን ማተኮር ያለበት በራሳችን ነገር ላይ ሳይሆን፣ ወደ ክርስቶስ ልንመለከት ይገባል፡፡ አዕምሮአችን የእርሱን ፍቅር፣ የባሕርይውን ውበትና ፍጽምና ያስብ፡፡ ነፍስ ልታሰላስለው የሚገባ ርእስ ቢኖር፣ የክርስቶስ ራሱን መካድ፣ትህትናው፣ ንጽሕናው፣ ቅድስናው እንደዚሁም ወደር የለሽ ፍቅሩ ሊሆኑ ይገባል፡፡ እርሱን በማፍቀር፣ የእርሱ ቅጂ በመሆን ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ በመደገፍ እርሱን ወደመምሰል ማደግ አለባት፡፡ እርሱን ወደ መምሰል የምንለወጠው፣ እርሱን በመውደድ፣ ከእርሱ በመቅዳት፣ እንደዚሁም ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ በመደገፍ ነው:: ክየመ 65.2
ኢየሱስ «በእኔ ኑሩ» ብሏል፡እነዚህም ቃላት የያዙት የዕረፍት፣ የመረጋጋትና የመተማመን ሃሳብ ነው:: እንደገናም እርሱ «ወደ እኔ ኑ ...እኔም አሳርፋችኋለሁ» (ማቴ. 11:28) ሲል ጋብዟል፡፡ የመዝሙረኛውም ቃል ይህንኑ ይገልፃል፡- «በእግዚአብሔር ፊት ፀጥ በል በትዕግስትም ተጠባበቀው» (መዝ. 37፡7)፡፡ ኢሳይያስም ይህን ሲያረጋግጥ፡- «በመመለስ እና በማረፍ ትድናላችሁ፤ በፀጥታ እና በመታመን ኃይል ይሆንላችኋል» (ኢሳ. 30፡15) አዳኛችን የሰጠን የዕረፍት ተስፋ ከአገልግሎት ጥሪ ጋር የተያያዘ ስለሆነ እጅና እግርን አጣጥፎ በመቀመጥ አይገኝም፡፡ «ቀንበሬን ተሸከሙ ... ዕረፍት ታገኛላችሁ» (ማቴ 11:29)፡፡ በክርስቶስ ሙሉ በሙሉ ያረፈ ልብ ክርስቶስን በሙሉ ልቡ እና በትጋት ያገለግለዋል፡፡ ክየመ 66.1
በራሱ የሚተማመን አዕምሮ የብርታትና የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከክርስቶስ የራቀ ነው፡፡ በመሆኑም የሰይጣን የማያቋርጥ ጥረት፣ ትኩረታችንን ከአዳኛችን ላይ አንስቶ በሌላ ነገር ላይ በማድረግ፣ ነፍሳችን ከክርስቶስ ጋር ያላትን ግንኙነትና አንድነት ማደናቀፍ ነው:: ሰይጣን ወደ ዓለም ደስታ፣ የኑሮ ውጣ ውረድ፣ ጭንቀቱና ሃዘኑ እንዲሁም ወደ ሌሎች ሰዎች ስህተት ወይም ወደ እኛ ጥፋትና ፍጹም አለመሆን፣ እነዚህንና እነዚህን ወደ መሳሰሉት ነገሮች ትኩረታችንን ለመቀልበስ ይተጋል፡፡ በእርሱ ማታለያዎች መደናቀፍ የለብንም፡፡ በእርምጃቸው ጥንቁቆች የሆኑና ለእግዚአብሔር ለመኖር ከልባቸው የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይሁንና ሰይጣን ደግሞ በስህተቶቻቸውና በድክመታቸው ላይ ትኩረታቸውን ዘወትር እንዲያነጣጥሩና ከክርስቶስ እንዲለዩ በማድረግ ድል ሊነሳቸው ተስፋ ያደርጋል፡፡ ትኩረታችንን በእኛ በራሳችን ላይ ብቻ በማድረግ «እንድናለን ወይስ አንድንም?» በማለት በጭንቀትና በፍርሀት መዋጥ የለብንም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ነፍስን የብርታት ምንጭ ከሆነው ዘወር እንድትል ያደርጋል፡፡ ነፍሳችሁን የመጠበቅን አደራ ለእግዚአብሔር በመስጠት በእርሱ ታመኑ፡፡ ኢየሱስን አስቡ እርሱን ተጫወቱት፤ በራስ የመመካት ነገር እርሱን በመታመን ይተካ፡፡ ጥርጣሬን አስወግዱ፤ ፍርሀትን ሁሉ ደምስሱ፤ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር «ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል» (ገላ. 2:20) በሉ፡፡በእግዚአብሔር እረፉ፡፡ እርሱ አደራ የሰጣችሁትን ነገር ሁሉ በብቃትመጠበቅ ይችላል፡፡ እራሳችሁን በእርሱ እጅ ላይ ብታኖሩት በእርሱበወደዳችሁ ከአሸናፊዎች በላይ አድርጎ ያቆማችኋል፡፡ ክየመ 66.2
ክርስቶስ የሰውን ተፈጥሮ ለብሶ በመምጣቱ፤ በራሳችን ምርጫ ካልሆነ በስተቀር፤ የትኛውም ኃይል ሊበጥሰው በማይችል ጠንካራ የፍቅር ገመድ እራሱን ከእኛ ከሰብዓዊያን ጋር አጣምራል፡፡ ሰይጣን ደግሞ ያለማቋረጥ እኛን የሚማርክ ነገር በማቅረብ ይህንን ገመድ በራሳችን እንድንበጥስ፣ራሳችንንም ከክርስቶስ ለመለየት እንድመርጥ ለማድረግ ይጥራል፡፡ከክርስቶስ በስተቀር በላያችን ላይ ሌላ ገዢ እንዳንሾም ሁል ጊዜ ነቅተን መጠበቅ፣ መጋደል፣ እንዲሁም መጸለይ ይኖርብናል፡፡ ምክንያቱም የፈለግነውን የመምረጥ ነጻነቱ አለንና፡፡ ዓይናችንን በክርስቶስ ላይ ስንተክል፤እርሱም ከጥፋት ይጠብቀናል፡፡ ወደ ክርስቶስ እስከተመለከትን ድረስ ምንምአያሰጋንም:: ምንም ነገር ከእጁ ነጥቆ ሊወስደን አይችልም:: ያለማቋረጥእርሱን በመመልከት « መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ የእርሱን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን» (2ኛቆሮ. 3:18)፡፡ ክየመ 67.1
የቀድሞዎቹ ደቀመዛሙርት ውዱን አዳኛቸውን የመሰሉበት መንገድ ይህ ነበር፡፡ እነዚያ ደቀመዛሙርት የኢየሱስን ቃል ሲሰሙ ጉድለታቸውን አስተዋሉ፡፡ ፈለጉት፤ አገኙት ከዚያም ተከተሉት:: እነዚያ ደቀመዛሙርት ከእርሱ ጋር አንድ ቤት ውስጥ ነበሩ፤ አንድ ላይ በልተዋል፤ በእልፍኝ ውስጥም በሜዳም ላይ አብረውት ነበሩ፡፡ እነርሱም እንደ ተማሪ ሆነው ከመምህራቸው ከኢየሱስ አንደበት በየዕለቱ የቅዱሱን እውነት ትምህርት ተማሩ፡፡ ደቀመዛሙርቱ «እንደ እኛ የሆነ ሰው» ነበሩ (ያዕ. 5:17)፡፡ እነርሱ ልክ እንደእኛ ከኃጢአት ጋር ትግል ውስጥ ነበሩ:: ቅዱስ ሕይወት ለመኖር ይችሉ ዘንድ የሚያስፈልጋቸውም ጸጋ ልክ ለእኛ እንደሚያስፈልገው አይነት ነበር፡፡ ክየመ 67.2
የአዳኙን መልክ በተሻለ ሙላት ማንጸባረቅ ችሎ የነበረው ተወዳጁ ደቀመዝሙር ዮሐንስም እንኳን ቢሆን ያንን በፍቅር የተሞላ ባሕርይ በተፈጥሮ ያገኘው አልነበረም፡፡ ዮሐንስ ግትር እና ለክብር የሚጓጓ ብቻ ሳይሆን በአደጋ ጊዜ ቁጡ እና ግልፍተኛም ነበር፡፡ የመለኮት ባህርይ በተገለጠለት ጊዜ ግን የእራሱን ጉድለት ተረዳ፤ ይህን ባስተዋለ ጊዜ ራሱን ዝቅ አደረገ፡፡በእግዚአብሔር ልጅ የየዕለት ሕይወት ውስጥ ይገለፅ የነበረው ብርታት እና ትዕግስት፣ ኃይልና ርህራሄ፣ ግርማና ትህትና የዮሐንስን ነፍስ በአድናቆት እና በፍቅር ሞሉት፡፡ በራሱ ላይ የነበረው መመካት ለጌታው ባለው ፍፁም ፍቅር እስኪዋጥ ድረስ ልቡ ዕለት ዕለት ወደ ክርስቶስ ይጠጋ ነበር፡፡ የእርሱ በቁጣና በትምክህት የተሞላ ስሜት፣ መቅረፅ ለሚችለው ለክርስቶስ ኃይል ተሰጠ፡፡ ልቡ እንደገና መፍጠር በሚችለው በመንፈስ ቅዱስ ታደሰ፡፡የክርስቶስ የፍቅር ኃይል በውስጡ የባህሪ ለውጥን አመጣ፡፡ ይህ ከኢየሱስ ጋር እውነተኛ ሕብረት የማድረግ ውጤት ነው፡፡ ክርስቶስ በልብ ውስጥ ሲኖር፣ መላ ተፈጥሮ ይቀየራል፡፡ የክርስቶስ መንፈስና ፍቅሩ ልብን አለስልሶ ነፍስን ይማርክና፣ አስተሳሰብንና ፍላጎትን ወደ እግዚአብሔር እና መንግስቱ ከፍ ከፍ ያደርጋል፡፡ ክየመ 68.1
ክርስቶስ ወደ ላይ ሲያርግ የእርሱ የአብሮነት መንፈስ ግን ከተከታዮቹ ጋር ነበር፡፡ ከእነርሱ ጋር የተጓዘው እና የተነጋገረው፣አብሮአቸውየፀለየው፣ ለልባቸው ተስፋንና መጽናናትን የተናገረው አዳኙ ኢየሱስ የሰላም መልእክት በአንደበቱ ላይ እያለ ነበረ ወደ ላይ የተነጠቀው። ሊቀበሉት በመጡ የመላእክት ደመና ከመሸፈኑ በፊት እንዲህ የሚለው ድምጽ በጆሮአቸው አስተጋባ፡- «እነሆ እኔ እስከዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ» (ማቴ. 28:20)፡፡ ወደ ሰማይ ያረገው ሰብአዊውን ተፈጥሮ እንደለበሰ ነው:: በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት የሚቀርበው እርሱ፣ አሁንም ወዳጃቸውና አዳኛቸው እንደሆነ፣ ርህራኄው እንደማይለወጥ፣ ኃጢአት ከሚሰቃየው ሰብአዊ ቤተሰብ ጋር ራሱን እንዳቆራኘ ያውቃሉ፡፡ የገዛ ራሱን ክቡር ደም ብቁነት፣ የቆሰሉ እጆችና እግሮቹን፣ ለተቤዣቸው የከፈለውን ዋጋ በማስታወስ በእግዚአብሔር ፊት ያሳያል፡፡ ደቀዛሙርቱ እርሱ ወደ ሰማይ ያረገው ቦታ ሊያዘጋጅላቸው እንደሆነና ዳግመኛም እርሱ ወዳለበት ሊወስዳቸው እንደሚመጣም ያውቁ ነበር፡፡ ክየመ 68.2
ከእርገቱ በኋላ አንድ ላይ ሲሰበሰቡ፣ በኢየሱስ ስም ጥያቄያቸውን ለአብ ሊያቀርቡ ጓጉተው ነበር፡፡ አክብሮትን በተሞላ አግራሞት ውስጥ ሆነው በጸሎት እንዲህ የሚሉትን የጌታን የተስፋ ቃላት ይደጋግሙ ነበር፡-«እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ክየመ 69.1
ክርስቶስ በልብ ውስጥ ሲኖር፣ መላ ተፈጥሮ ይቀየራል፡፡
ይሰጣችኋል።እስከአሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበላላችሁ» (ዮሐ.16:23-24)፡፡ እንዲህም በማለት የእምነት እጃቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ፡-«የሞተው፣ ይልቁንም ከሙታን ይሰጣችኋል።እስከአሁን በስሜ ምንም አልለመናችሁም ደስታችሁ ፍጹም እንዲሆን ለምኑ ትቀበላላችሁ» (ዮሐ.16:23-24)፡፡ እንዲህም በማለት የእምነት እጃቸውን ከፍ ከፍ አደረጉ፡-«የሞተው፣ ይልቁንም ከሙታን የተነሳው በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፣ደግሞ ስለእኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው» (ሮሜ 8:34)፡፡ጴንጤቆስጤም፣ ክርስቶስ እራሱ «በእናንተ ይኖራል» ያለው እና «እኔ ብሄድ ይሻላችኋል፣ እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ፡፡» ያለውን አጽናኙን ይዞላቸው መጣ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ክርስቶስ ያለ ማቋረጥ በመንፈሱ አማካይነት በልጆቹ ውስጥ ይኖራል፡፡ ከእርሱም ጋር አሁን ያገኙት ሕብረት፣ እርሱ በአካል ከእነርሱ ጋር ይኖርበት ከነበረው ጊዜ ይልቅ የቀረበ ነበር፡፡ በውስጣቸው ያደረው የክርስቶስ ብርሃን፣ ፍቅርና ኃይል በእነርሱ ላይ ይንጸባረቅ ነበርና የተመለከቷቸው ሰዎች «መጽሐፍን የማያውቁና ያልተማሩ ሰዎች እንደሆኑ አስተውለው አደነቁ» (የሐዋ. 4፡13)፡፡ ክየመ 69.2
ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ሆኖላቸው የነበረውን ሁሉ፣ ዛሬም ላሉትልጆቹ እንደዚያው ሊሆንላቸው ይፈልጋል፡፡ በመጨረሻው ጸሎቱ ላይ፣ ከእርሱ ጋር ከተሰበሰቡት ጥቂት ደቀመዛሙርቱ ጋር ሆኖ እንዲህ አለ፡- «ከቃላቸው የተነሳ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለእነዚህ ብቻ አልለምንም» (ዮሐ. 17:20)፡፡ ክየመ 70.1
ኢየሱስ እርሱ ከአብ ጋር አንድ እንደሆነ እኛም ከእርሱ ጋር አንድ እንድንሆን ፀልዮልናል፡፡ ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ሕብረት ነው! አዳኙ ስለ ራሱ ሲናገር እንኳን «ወልድ በራሱ ምንም ማድረግ አይችልም»፤ «በእኔ የሚኖረው አብ ግን ይህን አድርጓል» ዮሐ. 5:19 ና 14፡10) በማለት ተናግሯል፡፡ ክርስቶስ በእኛ ልብ የሚኖር ከሆነ «ስለ በጎ ፈቃዱ መፈለግንም ማድረግንም» በእኛ ውስጥ ይሰራል ማለት ነው (ፊሊ. 2:13)። ያን ጊዜ እርሱ እንዳደረገ እንደዛው እናደርጋለን፤ ያንኑ መንፈስ እንገልጻለን፡፡ እናም እርሱን በማፍቀርና በእርሱ በመኖር «በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ» እናድጋለን (ኤፌ. 4፡15)፡፡ ክየመ 70.2