ታላቁ ተስፋ

1/15

ታላቁ ተስፋ

መግቢያ

ድንገተኛ ችግር እና ጥቃት ሲያጋጥመን፣ ያለምነው ስኬት እውን ሳይሆን ሲቀር፣ በሽታና ሞት የምንወዳቸውን ሲጠልፍብን፤ አንድ ነገር ብቻ ነው ቀና ብለን ወደፊት እንድናይ የሚያደርገን፡- ተስፋ ። የተሻለ ነገን የማየት ተስፋ፣ ብሩህና ደስተኛ ቀንን የማየት ተስፋ፣ አሁን ከሚታየውና ከሚጨበጠው ሕይወት ባሻገር የተሻለ ነገር እንዳለ የሚያስረግጥ ተስፋ። ታተ 3.1

ይህ መጽሐፍ ስለ ተስፋ የሚተርክ ነው። በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጻጻፍና የጊዜ ሁኔታ ቢጻፍም እንኳን፤ መጽሐፉ (The Great Hope) ለ 21ኛው ክፍለ ዘመን የሚበጅ የተሟላ ማስተዋልን ይሰጣል። ፍቅር ስለሆነውና ሰዎች ከመፈጠራቸው በፊት ጀምሮ እነርሱን ለማዳንና ለመጠበቅ ስለሚተጋው አምላክ የሚናገር መጽሐፍ ነው። ስቃይና ሞት ወደ ዓለም በገባ ጊዜ እግዚአብሔር ሁኔታውን እንዲሁ ዝም ብሎ አልተመለከተውም። ሰዎችን የማዳን እቅዱን ገለፀ። ይህ የማዳን እቅድ አሁንም በሥራ ላይ ነው። ታተ 3.2

የሰው ልጆች ታሪክን ስንመለከት ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማርና ለማስፋፋት ተንቀሳቅሰዋል። በእግዚአብሔር ስምና ሥልጣን እንሠራለን በሚሉ ሰዎች እንኳን ሳይቀር ሰላምና ተስፋ በተለያየ ጊዜ በተደጋጋሚ ሲጨናገፉ ታይቶአል። የእግዚአብሔርን ማንነት በትክክል ባለማወቅና ህልውናውን በመጠራጠር ምክንያት ዓለም በጨለማ ተውጣለች። ታተ 3.3

ነገር ግን እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር ዛሬም አልቀዘቀዘም። ምንም እንኳ ስለ እግዚአብሔር ብዙ የተተረከ ቢሆንም፣ በእርሱ ስም እንናገራለን በሚሉ ሰዎች ብዙ ቢሰበክም፣ ስለ እርሱ ትክክለኛውን እውነት የምናገኘው በተከፈተ ልብ ቅዱስ ቃሉን ስናጠና ብቻ ነው። ታተ 3.4

እውነትን እየፈለግህ/ሽ ነው? ሰላምንስ እየፈለግህ/ሽ ነው? ተስፋንስ እየፈለግህ/ሽ ነውን? ታዲያ የት ታገኛቸዋለህ/ሽ? የዓለም መንግሥታት ሁሉ በፖለቲካ ጦርነት ተይዘዋል። የዓለም ኢኮኖሚ በቀውስ ላይ ነው የሚገኘው። የተፈጥሮ መዛባት፣ የአካባቢ ስነ ምህዳር መቃወስና የአየር ንብረት ለውጥ እየተከሰተ ነው። የሰው ጥበብ ስለወደፊቱ ምንም አስተማማኝ መልስ ወይንም የሚያስደስት ተስፋ እየሰጠ አይደለም። ታተ 3.5

ይህ ሁሉ ቢሆንም፣ እኛ ያለ ተስፋ አይደለንም። እስቲ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ያደረገውን ሁሉ ተመልክተን እኛን ለማዳን የሰጠውን ስጦታ እናስተውል። ከዲያብሎስ ውሸት ሊያድነን የሚችለውን እውነት እንያዝ። ሕይወታችንን ሊቀይርና ወሰን ወደሌለው ሕይወት ሊመራን የሚችለውን እውነት እናግኝ። ታተ 3.6

በመጨረሻም ወደፊት ሊሆን ስላለው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉትን ትንቢቶች እንመልከት። ይህቺ ዓለም እየወደቀች ስትሄድ ሳለ የእግዚአብሔር ጥበቃ በእኛ ላይ ምን ያህል እንደሚበዛ እንመልከት። የእግዚአብሔርን እጅ እስከ መጨረሻው አጥብቀን ስንይዝ ብቻ ነው ወደፊት የሚገጥመን አስተማማኝ የሚሆነው። ታተ 3.7

ምንም ዓይነት ነገር በግል ሕይወታችንም ሆነ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ቢፈጠር፤ ነገን በተመለከተ ትልቅ ተስፋ ሊኖረን ይችላል። እግዚአብሔር ለሚሰጠን ለዚህ ትልቅ ተስፋ ልባችንን ዛሬ እንክፈት። ታተ 3.8

አሳታሚዎቹ