ታላቁ ተስፋ
የክፋት አጀማመር
የኃጢአት አጀማመርና ኃጢአት የሚባል ነገር እንዴት ሊኖር እንደቻለ ማሰቡ የብዙዎችን አእምሮ በታላቅ ድንግርግር ውስጥ የሚጨምር ነው፡፡ በዋይታና በጥፋት ከሚሞላው ውጤቱ ጋር የክፋትን ሥራ ሲመለከቱ «እንዴት ጥልቅ በሆነ ጥበብ፣ ኃይልና ፍቅር በተሞላ ሉዓላዊ አምላክ አስተዳደር ስር ይኼ ሁሉ ሊከሰት ቻለ?» ብለው ይጠይቃሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ ውስጥም ምንም አይነት ማብራሪያ ሊሰጡ የማይችሉበትን ምስጢር ያገኛሉ፡፡ ከዚህ እርግጠኛ ካልሆኑበትና በጥርጣሬ ከተሞሉበት ሁኔታ የተነሳም በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በግልጽ የተቀመጡትንና ለድነታቸውም አስፈላጊ የሆኑትን እውነቶች ከማየት ይታወራሉ፡፡ የኃጢአትን ህልውና አስመልክቶ በሚያደርጉት ምርምር እግዚአብሔር ያልገለጠውን ለመፈልፈል የሚፈልጉ አሉ፡፡ በመሆኑም ለገጠማቸው አስቸጋሪ ሁኔታ ምንም አይነት መፍትሔን አያገኙም፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎችም በጥርጣሬ የተሞሉና የሚያጠራጥሯቸውንም ምክንያቶች ቅዱሱን ቃል ለመቃወም እንደ ምክንያት አድርገው መውሰድ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ሌሎች ደግሞ፣ ስለ ታላቁ የክፋት ችግር በቂ መረዳት የሌላቸው ሲሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ፣ ስለ መንግስቱ ጠባይና ከኃጢአት ጋር የተያያዙ ነገሮችን ለማስተናገድ ስለሚከተላቸው መርሆዎች የተሸፈነባቸው ናቸው፡፡ ታተ 4.1
የኃጢአትን አጀማመር አስመልክቶ ስለ ህልውናው መንስኤ ለመጠቆም ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ክፋትን ለማስወገድ በሚወስደው እርምጃ ሁሉ ምን ያህል ፍትሐዊና ቸር መሆኑን ለማስተዋል በሚያስችለን መልኩ ስለ ኃጢአት መነሻም ሆነ መጨረሻ ማስተዋል እንችላለን፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የኃጢአትን መከሰት አስመልክቶ እግዚአብሔር ተጠያቂ እንዳልሆነ፣ የመለኮት ጸጋ በማንአለብኝነት እንዳልተወሰደ፣ የእግዚአብሔር መንግሥትም ፍፁም ባለመሆኑ እንዳልሆነ ከየትኛውም ርዕስ በላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በእግዚአብሔር አገዛዝ ላይ የተፈጠረ ችግር ለዓመጹ መንስኤ አልነበረም፡፡ ኃጢአት ከየት እንደመጣ ሳይታወቅ ነው የገባው፡፡ ምስጢራዊ ነው፤ ሰበብ ሊሰጥበት አይችልም፡፡ ሰበብ ከተሰጠበት ወይም መንስኤው ከተገኘለት ያ ጉዳይ ኃጢአት መሆኑ ያቆማል፡፡ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ስለ ኃጢአት የተሰጠን ብቸኛው ትርጓሜ «ሕግን መተላፍ» የሚል ነው፡፡ ይህም የመለኮት መንግስት መሠረት ከሆነው ከታላቁ የፍቅር ሕግ በተቃራኒ የሚሰራ ነው፡፡ ታተ 4.2
ኃጢአት ከመግባቱ በፊት ሰላምና ደስታ በዩኒቨርስ ሁሉ ሰፍኖ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ከፈጣሪ ፈቃድ ጋር ፍጹም ስምሙ ነበር፡፡ ፍጡር ለፈጣሪው የነበረው ፍቅር ላቅ ያለ ሲሆን፣ የእርስ በርስ ፍቅርም ያለ አድሎ ይፈስ ነበር፡፡ ቃል የሆነው የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ክርስቶስ ከዘላለማዊ አባቱ ጋር በባሕርይውና በዓላማው አንድ ነበር፡፡ በዩኒቨርስ በጠቅላላ ካሉት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ዕቅድና ምክር ውስጥ ሊገባ የሚችል ብቸኛው አካል እርሱ ነበር፡፡ በክርስቶስ አማካኝነት አብ የሰማይ ሠራዊትን ሁሉ ፈጠረ፡፡ «የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና፡፡» (ቆሎ. 1፡16) እናም ሰማይ ሁሉ ከአብ እኩል ለክርስቶስ ታማኝነትን ይሰጠው ነበር፡፡ ታተ 4.3
የፍቅር ሕግ የእግዚአብሔር መንግስት መሠረት እንደመሆኑ፣ የፍጡራን ሁሉ ደስታ ከዚህ ሕግ ታላላቅ የጽድቅ መርሆዎች ጋር የተስማማን ሕይወት በመኖር ላይ የተደገፈ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ከፍጥረታቱ ሁሉ የፍቅር አገልግሎትን መቀበል ይፈልግ ነበር፤ ይህንንም የእርሱን ባሕርይ በማድነቅ ከተሞላ ልብ አፍልቀው እንዲሰጡት ነበር የሚፈልገው፡፡ እርሱ በግዴታ በሚቀርብ መታዘዝ አይደሰትም፤ እናም በፈቃዳቸው መርጠው ለእርሱ አገልግሎትን ይሰጡ ዘንድ ለሁሉም የመምረጥ ነጻነትን ሰጣቸው፡፡ ታተ 4.4
ነገር ግን ይህንን ነጻነት ሊያበላሸው የፈለገ አንድ ፍጥረት ነበር፡፡ ኃጢአት የተጠነሰሰው በዚህ ፍጡር ልብ ውስጥ ሲሆን እርሱም በኃይልና በግርማ ከሌሎች የሰማይ ነዋሪዎች ሁሉ በላይ እና ከክርስቶስ ቀጥሎ የተቀመጠ ነበር፡፡ ከውድቀቱ በፊት፣ ሉሲፈር ቅዱስና በአንዳች ያልረከሰ የእግዚአብሔርን ክብር የሚጋርድ ኪሩብ ነበር፡- «የሰው ልጅ ሆይ፥ በጢሮስ ንጉሥ ላይ ሙሾ አሞሽተህ እንዲህ በለው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጥበብን የተሞላህ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ። በእግዚአብሔር ገነት በዔድን ነበርህ የከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያስጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅ፥ ልብስህ ነበረ፣ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበር፣ በተፈጠርህበት ቀን ተዘጋጅተው ነበር። አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ፣ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፣ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ፣ ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስኪገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ።» (ሕዝ. 28፡12-15)፡፡ ታተ 4.5
ሉሲፈር የተሰጠውን ስልጣን ሌሎችን ለመባረክና ፈጣሪውን ለማክበር በመጠቀም በእግዚአብሔር ፊት ያገኘውን ሞገስ እንደጠበቀ፣ በመላእክት ሠራዊት ሁሉ እንደተወደደና እንደተከበረ መቆየት ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ነብዩ እንደዚህ አለ፣ «በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል» (ቁጥር 17)፡፡ ቀስ በቀስ፣ ሉሲፈር ራሱን ከፍ ከፍ የማድረግ ፍላጎት አደረበት፡፡ «ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና» (ቁጥር 6)፡፡ «አንተም በልብህ፡- ወደ ሰማይ አርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ፥ በሰሜንም ዳርቻ በመሰብሰቢያ ተራራ ላይ እቀመጣለሁ፣ ከደመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።» (ኢሳ. 14፡13-14)፡፡ እግዚአብሔርን በፍጥረታቱ ፊት ታላቅና የተከበረ አድርጎ ከማቅረብ ይልቅ፣ የእነርሱን አክብሮትና ፍቅር ለራሱ ለማድረግ ፈለገ፡፡ ዘላለማዊው አባት ለልጁ የሰጠውን ክብር ለራሱ እንዲሆን በመመኘት፣ የመላእክት አለቃ ለክርስቶስ ብቻ የተሰጠውን ስልጣን በእጁ ለማስገባት ፈለገ፡፡ ታተ 5.1
ሰማይ በሙሉ የፈጣሪን ክብር ለማንጸባረቅና የእርሱንም ምስጋና ለማወጅ በደስታ ይመኙ ነበር፡፡ በዚህም እግዚአብሔር ይከብር የነበረ ሲሆን ፍጥረት ሁሉ ደግሞ በደስታና በሰላም ተሞልቶ ነበር፡፡ አሁን ግን የሰማይን ስምምነት (Harmony) የሚያፈርስ ነገር ተከሰተ፡፡ ከፈጣሪ እቅድ ተቃራኒ የሆነው ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ የእግዚአብሔርን ክብር ያስቀድሙ በነበሩ አእምሮዎች ውስጥ ብቅ ብቅ አለ፡፡ የሰማይ መማክርት ሉሲፈርን ተማጸኑት፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የፈጣሪን ታላቅነት፣ መልካምነትና ፍትህ እንደዚሁም የሕጉን የማይለወጥ ተፈጥሮ አቀረበለት፡፡ የሰማይን ስርዓት የዘረጋው ራሱ እግዚአብሔር ነበር፡፡ እናም ከዚህ ስርዓት ፈቀቅ በማለት፣ ሉሲፈር ፈጣሪውን እንደሚያዋርደውና በራሱም ላይ ጥፋትን እንደሚያመጣ ነገረው፡፡ ነገር ግን ጥልቅ በሆነ ፍቅርና ምህረት የተሰጠው ይህ ማስጠንቀቂያ፣ በልቡ ውስጥ ይበልጥ አመጸኝነትን አነሳሳ፡፡ ሉሲፈር በክርስቶስ ላይ የነበረው ቅንዓት ሁለንተናውን እንዲቆጣጠረው ፈቀደ፣ እናም ይበልጥ ልቡን አደነደነ፡፡ ታተ 5.2
ስለ ራሱ ክብር የነበረው ትምክህት የበላይ ለመሆን የነበረውን ፍላጎት አፋፋው፡፡ የተሰጡት ትልልቅ ማዕረጎች ከእግዚአብሔር እንደተሰጡ ስጦታዎች አላያቸውም ነበርና ስለ እነርሱ ፈጣሪን አያመሰግንም ነበር፡፡ በአንጸባራቂ ውበቱና ክብሩ ተመካ፤ ከእግዚአብሔርም ጋር እኩል ለመሆን ተመኘ፡፡ በሰማይ ሠራዊት ዘንድ ተወዳጅና የሚከበር ነበረ፡፡ መላእክት የእርሱን ትእዛዝ በመፈጸማቸው ይደሰቱ ነበር፤ እርሱም ከሁሉም የበለጠን ጥበብና ግርማ ተላብሶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ በሰማይ ሁሉን ማድረግ የሚችልና ከአብ ጋር በስልጣን እኩል የነበረው የእግዚአብሔር ልጅ ነበር፡፡ በሁሉም የእግዚአብሔር ምክር ውስጥ፣ ክርስቶስ ተሳታፊ የነበረ ሲሆን፣ ሉሲፈር ደግሞ በመለኮታዊ ምክክር ውስጥ አይሳተፍም ነበር፡፡ «ለምን?» የሚል ነበር የዚህ ኃያል መልአክ ጥያቄ፤ «ለምን ክርስቶስ የበላይነት ሊኖረው ቻለ? ለምንድን ነው እርሱ ከሉሲፈር ይልቅ የተከበረ የሆነው?» ታተ 5.3
ከእግዚአብሔር አጠገብ የነበረውን ሥፍራ በመተው ሉሲፈር ያለ መርካትን መንፈስ በመላእክቱ ልብ ውስጥ ለመርጨት ወጣ፡፡ ለጊዜው ለእግዚአብሔር ክብር የሚሰራ በመምሰል ስውር አጀንዳውን ደብቆ ምስጢራዊ በሆነ መንገድ እየሰራ፣ አላስፈላጊ የሆነ ማዕቀብ እንደሚያስቀምጥባቸው ለማሳየት በመሞከር የሰማይ ሠራዊትን በሚመራው ሕግ ላይ እርካታ እንዳይኖራቸው ለማድረግ ጣረ፡፡ ተፈጥሮአቸው ቅዱስ ስለሆነ መላእክት የራሳቸውን ፈቃድ ብቻ መከተል እንዳለባቸው አሳሳበ፡፡ እግዚአብሔር ለክርስቶስ ብዙ ክብርን በመስጠት እርሱን እንደበደለው አድርጎ በማቅረብ በመላእክት ዘንድ የሚያዝኑለትን ለማግኘት ጣረ፡፡ ተጨማሪ ኃይልና ክብር ሲፈልግ ራሱን ይበልጥ ከፍ ከፍ ለማድረግ ሳይሆን ይልቁንም በሰማይ ለሚኖሩ ነዋሪዎች በሙሉ ነጻነትን ለማስጠበቅና በዚያም ደግሞ የሁሉም ኑሮ አሁን ካሉበት ደረጃ ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲደርስ እንደሆነ አድርጎ አቀረበላቸው፡፡ ታተ 5.4
እግዚአብሔርም በብዙ ምህረቱ ሉሲፈርን ታገሰው፡፡ ያለ መርካትን መንፈስ ባስተናገደ ጊዜ፣ ወዲያውኑ ከክብር ማእረጉ አልወረደም፡፡ በታማኝ መላእክቶች ፊት የተሳሳቱ መረጃዎቹን በሚያቀርብበት ጊዜ እንኳን ምንም አላደረገውም፡፡ በሰማይም ለረዥም ጊዜ ቆየ፡፡ ንስሐ እንደሚገባና ራሱንም መልሶ እንደሚያስረክብ በማሰብ በተደጋጋሚ ይቅርታ ይደረግለት ነበር፡፡ ወሰን የለሹ ፍቅርና ጥበብ ሊያደርጉለት የሚችሉት ነገር ሁሉ ይደረግ የነበረው እርሱን ከስህተቱ ለመመለስ ነበር፡፡ የአለመርካት መንፈስ ከዚህ ቀደም በሰማይ አይታወቅም ነበር፡፡ ሉሲፈር ራሱ በመጀመሪያ መስመር ለቆ እየወጣ መሆኑን አልተረዳም ነበር፡፡ ይሰማው የነበረውን ስሜት ትክክለኛ ምንነት ገና በቅጡ አላስተዋለውም ነበር፡፡ ነገር ግን የእርሱ አለመርካት መንስኤ የለሽ መሆኑ ሲረጋገጥ፣ ሉሲፈር በስህተት ጎዳና ላይ እንደሆነ አስተዋለ፡፡ መለኮት የሚለው ነገር ሁሉ ትክክል እንደሆነና ይህንንም አስመልክቶ በሰማይ ሁሉ ፊት ለዚህ እውነታ እውቅና መስጠት ነበረበት፡፡ ይህንን አድርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ራሱንና ብዙ መላእክትን ባተረፈ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ለእግዚአብሔር የነበረውን ታማኝነት ሙሉ በሙሉ አልጣለም ነበር፡፡ ምንም እንኳን እንደ ጠባቂ ኪሩብ የነበረውን ስልጣን ቢተውም፣ ነገር ግን የፈጣሪን ጥበብ በማድነቅና በእግዚአብሔር ታላቅ እቅድ የተሰጠውን ቦታ ደስ ብሎት ለመያዝ በመፈለግ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ቢፈልግ ኖሮ፣ እግዚአብሔር ወደ ቀድሞ ስልጣኑ በመለሰው ነበር፡፡ ነገር ግን እንዲህ ያለውን አካሄድ እንዳይመርጥ ትእቢት ከለከለው፡፡ አልበገር ባይ በመሆን የእርሱ አሳብ ትክክል እንደሆነ ለማሳመን ታገለ፡፡ ምንም ንስሐ እንደማያስፈልገው አወጀ፤ ከፈጣሪው በተቃራኒ ለመሰለፍም በታላቁ ተጋድሎ ውስጥ ራሱን አስገባ፡፡ ታተ 5.5
ታላቅ ጥበቡን የማታለል ስራን ለመስራትና በእርሱ ሥር ከነበሩት መላእክት ዘንድ አዘኔታን ለማግኘት ሊጠቀምበት ፈለገ፡፡ ክርስቶስ የሰጠው ምክርና ማስጠንቀቂያ እንኳን ሳይቀር ይበልጥ የክፋት ዓላማውን ለማራመድ እልህ ውስጥ እንዲገባ አደረገው፡፡ እርሱን ለሚወዱትና ለሚያምኑትም፣ ሰይጣን በስህተት እንደተፈረደበት፣ ስልጣኑም እንዳልተከበረ፣ ነጻነቱም እንደተነፈገ አድርጎ አቀረበላቸው፡፡ ኢየሱስን በተሳሳተ መንገድ ከማስተዋወቅ አንስቶ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ የሃሰት ክሶች በመፈልሰፍ በሰማይ ሠራዊት ፊት ሊያዋርደው ፈለገ፡፡ በእርሱና ታማኝ ሆነው በቆዩት መላእክት መካከልም ጠብ እንዲኖር ለማድረግ ፈለገ፡፡ ከእርሱ ጋር በሙላት የማይስማሙትን ሁሉ ለሰማይ ፍጥረታት ደህንነት ፍላጎት እንደሌላቸው አድርጎ አቀረባቸው፡፡ እርሱ ራሱ እየሰራ ያለውን የክፋት ስራ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሆነው ለመቆየት የመረጡት መላእክት እየሰሩት እንደሆነ አድርጎ አቀረበ፡፡ የእግዚአብሔርን ኢፍትሐዊነት አስመልክቶ ያቀረበውን ክስ ለመደገፍ፣ የፈጣሪን ቃላትና ድርጊቶች በተሳሳተ መንገድ ወደ ማቅረብ አመራ፡፡ የእግዚአብሔርን ዓላማ አስመልክቶ ብልጠት የተሞላባቸውን ሙግቶች በማቅረብ የመላእክቱን አእምሮ ማወናበድ የእርሱ ፖሊሲው ነበር፡፡ ቀላል የሆነውን ነገር ሁሉ ምስጢር አድርጎ ያቀርበው ነበር፡፡ ጥበብ በተሞላበት የማጣመም ስራውም ግልጽ በሆኑት የይሖዋ ንግግሮች ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር አደረገ፡፡ የነበረው ከፍተኛ ስልጣንና ከመለኮት አስተዳደር ጋር የነበረው የጠበቀ ቅርርብ፣ ለሚናገራቸው ነገሮች ተአማኒነት እንዲያገኝ ጉልበት ሰጠው፤ ብዙዎችም በሰማይ አገዛዝ ላይ ለማመጽ ከእርሱ ጋር ለመተባበር ፈለጉ፡፡ ታተ 6.1
ይህ ያለ መርካት መንፈስ አመጽ ሆኖ እስኪፈነዳ ድረስ እግዚአብሔር በጥበቡ ሰይጣን ስራውን ወደፊት እንዲገፋበት ፈቀደለት፡፡ እውነተኛ ተፈጥሮአቸው ምን እንደሆነ በሁሉ ዘንድ እንዲታይ፣ የሰይጣን እቅዶች ሙሉ በሙሉ ይዳብሩና ይገለጡ ዘንድ አስፈላጊ ነበር፡፡ ሉሲፈር፣ ጠባቂ ኪሩብ እንደመሆኑ ከፍ ያለ ክብር ተሰጥቶት ነበር፡፡ በሰማይ ፍጥረታት ዘንድም በእጅጉ ይወደድ ነበር፡፡ በእነርሱም ላይ የነበረው ተጽእኖ ጠንካራ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ደግሞ የሰማይ ነዋሪዎችን ብቻ ሳይሆን ፣ እርሱ የፈጠረውን ዓለም ሁሉ የሚያካትት ነው፡፡ እናም ሰይጣን የሰማይ መላእክትን በአመጽ መንገድ ይዞአቸው መሄድ ከቻለ፣ ሌሎቹንም ዓለማት መያዝ እንደሚችል አሰበ፡፡ ጥያቄዎቹን ለእርሱ በሚመቹት መንገድ ያቀርብ የነበረ ሲሆን፣ በውሸት የተገመዱ የብልጠት አካሄዶቹን በመጠቀም ሊያጠምድ ወደሚፈልጋቸው ቀረበ፡፡ ለማታለል የነበረው ኃይል በጣም ታላቅ ነበር፡፡ ታማኝ የተባሉት መላእክት እንኳን ሳይቀሩ የእርሱን ባሕርይ በሙላት ሊያስተውሉና አካሄዱም ወዴት እደሚያመራው ለመመልከት አልቻሉም፡፡ ታተ 6.2
ሰይጣን በጣም ከፍተኛ ክብር የነበረውና ድርጊቶቹም ምስጢራዊ ስለሆኑ፣ እውነተኛውን የእርሱን ባሕርይ ለመላእክት ገላልጦ ማሳየት አስቻጋሪ ነበር፡፡ ኃጢአት በደንብ ዳብሮ ካልታየ በስተቀር በውስጡ ያለውን ክፋት በሙላት ለመመልከት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በዩኒቨርስ ውስጥ ያልነበረ ጉዳይ ነውና ቅዱሳን ስለ ምንነቱም ሆነ አጥፊነቱ መረዳቱ አልነበራቸውም፡፡ መለኮታዊውን ህግ ወደ ጎን በማድረግ የሚመጣውን ጥፋት አጥርተው ለማየት አልቻሉም፡፡ ሰይጣን በመጀመሪያ ላይ ለእግዚአብሔር ታማኝ እንደሆነ በማስመሰል ነበር የሚሰራው፡፡ የእግዚአብሔርን ክብር በማስፋፋት፣ መንግስቱንም በማጽናት፣ ለሰማይ ነዋሪዎችም መልካም ነገር እንዲመጣ በመስራት ላይ እንዳለ ነበር የሚገልጸው፡፡ በእርሱ ስር ባሉት መላእክቶች አእምሮ ውስጥ አለመርካትን በሚረጭበት ጊዜም እንኳን፣ ያንን ያደርግ የነበረው አለመርካትን ለማስወገድ እንደሆነ ጥበብ በሞላበት አቀራረቡ ለማሳመን ሞክሮአል፡፡ በእግዚአብሔር መንግስት ሕግ ላይ ለውጦች መደረግ እንዳለባቸው በሚያሳስብበት ጊዜም፣ በሰማይ ያለውን ቅንጅት ጠብቆ ለማቆየት በማሰብ እንደሆነ አድርጎ ነበር የሚያቀርበው፡፡ ታተ 6.3
ከኃጢአት ጋር በሚያደርገው ፍጥጫ እግዚአብሔር መጠቀም የሚችለው ጽድቅንና እውነትን ብቻ ነበር፡፡ እንደ ማታለልና መዋሸት የመሳሳሉትን እግዚአብሔር መጠቀም የማይችላቸውን ነገሮች ሰይጣን ይጠቀም ነበር፡፡ የእግዚአብሔን ቃል ውሸት ለማድረግና እግዚአብሔር ሕጉን በሰማይ ነዋሪዎች ላይ ሲጭን ትክክል እንዳልሆነ፣ ከፍጡራኑም መታዘዝንና መሰጠትን በሚጠይቅበት ጊዜ ራሱን ከፍ ከፍ እያደረገ እንደሆነ በማሳየት በመላእክቱም ፊት የመንግስቱን እቅድ በስህተት ለማቅረብ ፈለገ፡፡ በመሆኑም በሰማይ ነዋሪዎችም ሆነ በመላው ዓለም ፊት፣ የእግዚአብሔር አገዛዝ ፍትሃዊ፣ ሕጉም ፍጹም እንደሆነ መገለጥ ነበረበት፡፡ ሰይጣንም ቢሆን የዩኒቨርስን መልካም ነገር ለማስጠበቅ እየጣረ እንዳለ አድርጎ ራሱን አቅርቦ ነበርና፡፡ የዚህ ለእርሱ የማይገባውን ስልጣን በእጁ ሊያስገባ የፈለገ ፍጥረት እውነተኛ ባሕርይ በሁሉ ዘንድ መስተዋል ነበረበት፡፡ በክፉ ድርጊቶቹ ማንነቱን በይበልጥ ይገልጽ ዘንድ ጊዜ ሊሰጠው ይገባ ነበር፡፡ ታተ 6.4
ሰይጣን በራሱ መንገድ በመሄድ ያመጣውን ክፍፍል፣ «በእግዚአብሔር ሕግና አስተዳደር የተነሳ የመጣ ነው» በማለት ክሱን አቀረበ፡፡ ክፋት ሁሉ የመለኮታዊ አመራር ውጤት መሆኑን አወጀ፡፡ የይሖዋን ሕግጋት ማስተካከል የእርሱ ተቀዳሚ ዓላማ መሆኑንም ገለጸ፡፡ ስለዚህም የሚላቸው ነገሮች ሁሉ በትክክል ምን እንደሆኑና በመለኮት ሕግ ላይ መደረግ እንዳለበት የሚናገረው ለውጥ በትክክል ምን ውጤት እንደሚያመጣ ማሳየት ነበረበት፡፡ የራሱ ሥራ በራሱ ላይ ሊፈርድበት ይገባ ነበር፡፡ ሰይጣን ከመጀመሪያ አንስቶ በአመጻ ውስጥ እንዳልነበረ አድርጎ ራሱን ያቀርብ ነበርና መላው ዩኒቨርስ ይህ አታላይ ጭምብሉ ተገፎበት እንዲያየው ማድረግ አስፈላጊ ነበር፡፡ ታተ 7.1
በሰማይ ከእንግዲህ ወዲህ መቆየት እንደማይችል በተወሰነበት ጊዜ እንኳን፣ ወሰን የለሽ በሆነ ጥበብ የተሞላው አምላክ ሰይጣንን አላጠፋውም፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይት ያለው አገልግሎት ከፍቅር የመነጨ ብቻ እንደመሆኑ፣ ፍጥረታቱ ከእርሱ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት የእርሱን ፍትህና ለጋስነት በማስተዋል ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት፡፡ የሰማይ ነዋሪዎችና ሌሎችም ፍጥረታት የኃጢአትን ምንነትና መዘዙን ለማስተዋል ስለማይችሉ እግዚአብሔር ሰይጣንን ቢያጠፋው በዚያ ድርጊቱ ውስጥ ምህረቱንና ፍትሃዊነቱን መመልከት ባልቻሉ ነበር፡፡ ታተ 7.2
ሰይጣን ወዲያውኑ ከሕያዋን ዓለም ቢወገድ ኖሮ፣ ሌሎች ፍጥረታት እግዚአብሔርን በፍቅር ሳይሆን በፍርሃት ተሞልተው ባገለገሉት ነበር፡፡ የአታላዩም ተጽዕኖ እንደዚሁም የአመጻ መንፈስ ሙሉ በሙሉ አይወገዱም ነበር፡፡ ክፋት ማንነቱ እስኪገለጥ ድረስ መብሰል ነበረበት፡፡ ለመላው ዩኒቨርስ ዘላለማዊ ደህንነት ሲባል ሰይጣን መርሆዎቹን በደንብ አብስሎ ማሳየት ነበረበት፡፡ በዚህም በመለኮት አስተዳደር ላይ የሚሰነዝራቸው ክሶች በፍጥረት ሁሉ ዘንድ በእውነተኛ ብርሃን በትክክል መታየት ይችላሉ፤ ዘላለማዊ የሆነው የእግዚአብሔር ሕግ የእርሱ ምህረትና ጽድቅም ከምንም አይነት የጥርጣሬ ጥያቄ ነጻ ይሆናሉ፡፡ ታተ 7.3
የሰይጣን አመጽ በቀጣይ ዘመናት ለዩኒቨርስ ትምህርት ሰጪና የኃጢአትን ተፈጥሮና አስከፊ ውጤቱን በተመለከተ ያለማቋረጥ የሚመሰክር ነው፡፡ የሰይጣን ህግ በተግባር ላይ እንዲውል ማድረግና በሰውም ሆነ በመላእክት ላይ ያለውን ውጤት ማሳየት የመለኮትን ስልጣን ወደጎን የማድረግ ውጤት ምን እንደሚመስል የሚያመለክት ነው፡፡ በእግዚአብሔር የተፈጠሩ ፍጥረታትን ሁሉ በደህንነት አስተሳስሮ የሚጠብቃቸው የእግዚአብሔር አስተዳደርና ህጉ መሆናቸውን ይመሰክራል፡፡ በመሆኑም የዚህ አሰቃቂ የሆነ አመጽ ምን እንደሚመስል ራሱን እንዲያሳይ የመፍቀድ ሙከራ ኃጢአት ያልነካቸውን ፍጥረታት የአመጻን ትክክለኛ ምንነት በተመለከተ እንዳይታለሉ ለመጠበቅ፣ ኃጢአትን ከመስራትና በቅጣቱም ከመሰቃየት እነርሱን ለዘለቄታው ለማትረፍ ነበር፡፡ ታተ 7.4
በሰማይ ላይ እየተካሄደ የነበረው ታላቁ ተጋድሎ ወደ መገባደዱ ሲደርስ፣ ታላቁ አታላይ የእርሱ ድርጊቶች ትክክል መሆናቸውን ለማሳመን ጥረቱን ቀጠለ፡፡ ከነተከታዮቹ ከዚያ የደስታ ስፍራ እንደሚባረር በተነገረ ጊዜ፣ ይህ የአመጽ መሪ በግልጽ በፈጣሪ ሕግ ላይ ያለውን ጥላቻ ማወጅ ጀመረ፡፡ መላእክት ምንም አይነት ቁጥጥር እንደማያስፈልጋቸው፣ ይልቁንም የራሳቸውን ፈቃድ ለማድረግ ሊተው እንደሚገባ፣ በዚህም መንገድ በመሄድ ሁልጊዜ ወደ ትክክለኛው መንገድ እንደሚደርሱ ደግሞ ተናገረ፡፡ የመለኮት ሕጎች ነጻነታቸውን የሚገድቡባቸው ማዕቀቦች ናቸው በማለት አወገዛቸው፡፡ እናም ህጉን ማስወገድ ዓላማው መሆኑን ገለጸ፡፡ ከዚህ ማዕቀብ ነጻ በመሆንም የሰማይ ሠራዊት ወደ ታላቅ ክብርና ባለ ግርማ ወደ ሆነ ኑሮ እንደሚገቡም ተናገረ፡፡ ታተ 7.5
ሰይጣንና ተከታዮቹ በአንድ ልብ በመሆን ለአመጻቸው ምክንያት የሆናቸው ክርስቶስ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ ባይገሰፁ ኖሮ፣ አመጻቸው ይቀር እንደነበረ ተናገሩ፡፡ ስለዚህ፣ በአመጻቸው ልባቸውን በማደንደናቸውና የእግዚአብሔርን መንግስት መገልበጥን ብቻ በመፈለጋቸው እንዲሁም ደግሞ እነርሱ የጭቆና ኃይል ሰለባዎች እንደሆኑ በመግለጽ በመሳደባቸው ምክንያት ቀንደኛው አማጺና ከእርሱ ጎን የተሰለፉት ሁሉ በመጨረሻ ከሰማይ ተባረሩ፡፡ ታተ 7.6
በሰማይ አመጽን ያነሳሳው ያው መንፈስ ዛሬም በምድር ላይ የአመጽ ጥንስስ ሆኖ ይታያል፡፡ ሰይጣን ከመላእክቱ ጋር የሰራበትን ተመሳሳዩን ፖሊሲ ከሰብአዊ ፍጥረት ጋርም ይጠቀምበታል፡፡ ይህ መንፈሱ በአመጻ ልጆች ሁሉ ላይ ሰፍኖ ይታያል፡፡ ልክ እንደ እርሱ የእግዚአብሔርን ሕግ የሚጥሱና በዚያም የጥሰት ጎዳና ሰዎች አርነትን እንደሚለማመዱ የሚናገሩ ናቸው፡፡ ኃጢአታቸው በሚገሰጽበት ጊዜ ጥላቻና ተቃውሞ ውስጣቸውን ይሞሉታል፡፡ የእግዚአብሔር የማስጠንቀቂያ መልእክቶች ወደ አእምሮቸው ሲመጡ፣ ሰይጣን ደግሞ ሰዎች ለኃጢአታዊ ድርጊቶቻቸው ምክንያት እንዲያቀርቡና ሌሎች ሰዎች እንዲደግፏቸው ያደርጋል፡፡ እነርሱም ስህተታቸውን ከማረም ይልቅ፣ የችግራቸው ሁሉ ብቸኛ መንስኤ እርሱ እንደሆነ በማሰብ በገሰጻቸው ጌታ ላይ ይቆጣሉ፡፡ ከጻድቁ አቤል ዘመን አንስቶ ኃጢአትን በሚኮንኑ ሰዎች ላይ የሚንጸባረቀው መንፈስ ይኼው ነው፡፡ ታተ 7.7
በሰማይ እንደተለማመደው የእግዚአብሔርን ባሕርይ በተሳሳተ መንገድ በመግለጽ፣ እግዚአብሔር ጨካኝና ጨቋኝ ተደርጎ እንዲታይ በማድረግ ሰይጣን ሰውን ወደ ኃጢአት ጎዳና ውስጥ አስገባው፡፡ ይህ ከተሳካለት በኋላ ደግሞ፣ የሰውን ውድቀት ያስከተሉት የእግዚአብሔር ፍትሃዊ ያልሆኑ ማእቀቦች እንደሆኑ ተናገረ፡፡ ታተ 7.8
ነገር ግን ዘላለማዊው አምላክ ራሱ የራሱን ባሕርይ እንዲህ በማለት አውጆታል፡- «እግዚአብሔር፥ እግዚአብሔር መሐሪ፥ ሞገስ ያለው፥ ታጋሽም፥ ባለ ብዙ ቸርነትና እውነት፥ እስከ ሺህ ትውልድም ቸርነትን የሚጠብቅ፥ አበሳንና መተላለፍን ኃጢአትንም ይቅር የሚል፥ በደለኛውንም ከቶ የማያነጻ፥ የአባቶችንም ኃጢአት በልጆች እስከ ሦስትና እስከ አራት ትውልድም በልጅ ልጆች የሚያመጣ አምላክ ነው» (ዘጸ. 34፡6-7)፡፡ ታተ 8.1
ሰይጣንን ከሰማይ ሲያባርረው እግዚአብሔር ፍትሐዊነቱን አወጀ፤ የዙፋኑንም ክብር አስጠበቀ፡፡ ነገር ግን ሰው ለክህደት መንፈስ እጅ በመስጠት ኃጢአትን በሰራ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ለወደቀው ሰብአዊ ዘር ሕይወቱን ይሰጥ ዘንድ አንድ ልጁን አሳልፎ በመስጠት ለፍቅሩ ማስረጃን አቀረበ፡፡ ታተ 8.2
በመስቀሉ የእግዚአብሔር ባሕርይ ተገለጠ፡፡ የመስቀሉ ዋንኛ ሙግት ሰይጣን የመረጠው የኃጢአት ጎዳና በእግዚአብሔር አስተዳደር ሊሳበብ የማይችል መሆኑን ለመላው ዩኒቨርስ የሚያሳይ ነበር፡፡ ታተ 8.3
በክርስቶስና በሰይጣን መካከል በተደረገው ጦርነት፣ በአዳኛችን ምድራዊ አገልግሎት ወቅት የዚህ ታላቅ አታላይ ጭምብል ተገፈፈ፡፡ ሰይጣን ከሰማያዊ መላእክትም ሆነ ከሌሎች ያልወደቁ ፍጥረታት ልብ ውስጥ ሰይጣንን ነቅሎ በማውጣት ረገድ በዓለም አዳኝ ላይ የሰነዘረውን ጥቃት የሚያክል ሌላ ነገር አልነበረም፡፡ ክርስቶስን ለእርሱ እንዲሰግድለት በድፍረት መጠየቁ፣ ወደ ቤተመቅደሱ ጫፍ ላይ እርሱን ተሸክሞ ማውጣቱና ከዚያም እንዲዘል መጠየቁ፣ ከቦታ ቦታ እየተከታተለ በተንኮል እርሱን ለማጥመድ መሞከሩ፣ በካህናቱና በሕዝቡ ልብ ውስጥ የእርሱን ፍቅር የመቃወም መንፈስን መክተቱና በመጨረሻም «ስቀለው! ስቀለው!» እያሉ እንዲጮኹ ማድረጉ፤ ይህ ሁሉ መላውን ዩኒቨርስ በመገረምና በብስጭት ሞላው፡፡ ታተ 8.4
ዓለም ክርስቶስን እንዳይቀበል ያደረገው ሰይጣን ነበር። የክፋት ልዑል የሆነው ጠላት፣ አዳኛችን በምህረቱ፣ በፍቅሩ፣ በርህራሄውና በአዛኝነቱ የእግዚአብሔርን ባህሪይ ለዓለም እያሳወቀ መሆኑን በተረዳ ጊዜ ብልሃቱንና ያለውን ኃይል ሁሉ ተጠቅሞ ኢየሱስን ለማስወገድ ተነሳ። የእግዚአብሔር ልጅ የተናገረውን እያንዳንዱን ቃል ተቃወመ። የአዳኛችንንም ሕይወት በስቃይና በመከራ ለመሙላት ሰዎችን ወኪሎቹ አድርጎ ተጠቀመባቸው። በማደናገርና በሐሰት ተግባሩ የክርስቶስን ሥራ ለማስተጓጎል ሞከረ። «የአለመታዘዝ ልጆች» በተባሉት አማካኝነትም ጥላቻው ተገለጸ። አቻ የሌለው መልካምነትን በተላበሰው በኢየሱስ ላይ የጭካኔ ክስ ሰነዘረ። ይህ ሁሉ ግን በልቡ ስር ሰዶ ከተቀመጠው የበቀል ስሜት የመነጨ ነበር። እንደ እሳት ተዳፍነው የቆዩት የቅንአት፣ የክፋት፣ የጥላቻና የበቀል ኃይላት በቀራንዮ በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ነደዱ። ሰማይም ይህንን ትዕይንት በታላቅ ሰቀቀን ውስጥ ሆኖ በዝምታና በአትኩሮት ተመለከተ። ታተ 8.5
ታላቁ መስዋዕትነት ሲጠናቀቅ ክርስቶስ ወደ ላይ አረገ። «አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ» ሲል ልመናውን ከማቅረቡ በፊት የመላእክትን ስግደት ለመቀበል አልወደደም (ዮሐንስ 17፡24)። ልመናውንም በአብ ፊት እንዳቀረበ ሊገለፅ በማይችል ፍቅርና ኃይል ከአባቱ ዙፋን ምላሽ ወጣ። «የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ» ተባለለት (ዕብራውያን 1፡6)። ኢየሱስ፣ ሕይወቱ እንከን የለሽ ነበር። መዋረዱ ሲያበቃ፣ መስዋዕትነቱም ሲያከትም፣ ከስሞች ሁሉ በላይ የሆነ ስም ተሰጠው። ታተ 8.6
አሁን የሰይጣን ኃጢአት ያለ አንዳች ማመካኛ ቁልጭ ብሎ ታየ። እውነተኛ ባህሪይው ሐሰተኛነትና ነፍሰ ገዳይነት መሆኑ ግልጽ ሆነ። በእርሱ ኃይል ስር ያሉትን የሰው ልጆች የሚመራበት መንፈስ ታወቀ። ያኔ የሰማይ ነዋሪዎችን እንዲቆጣጠር ተፍቅዶለት ቢሆን ኖሮ ይህንኑ መንፈስና አሰራር ይጠቀም ነበር። የእግዚአብሔርን ህግ መጣስ ነፃነትንና ከፍ ከፍ ማለትን ያመጣል ሲልም ተናግሮ ነበር። ነገር ግን አለመታዘዝ ባርነትንና ውርደትን እንደሚያስከትል ተረጋገጠ። ታተ 8.7
በመለኮት ባህርይና በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ የሚያነሳቸው የሐሰት ክሶች ትክክለኛ መልካቸው ታየ። «እግዚአብሔር፣ ፍጥረታት በሙሉ እንዲገዙለትና እንዲታዘዙለት የሚፈልገው ራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ ብቻ ሲል ነው» በማለት ክሱን አቀረበ። «ሌሎች ራሳቸውን እንዲያዋርዱ የሚጠይቀው ፈጣሪ፣ እርሱ ራስን ማዋረድና መስዋዕትነትን መክፈል አይታይበትም» በማለትም ቅሬታውን ገልጾ ነበር። አሁን ግን የዓለማት ሁሉ ገዥ በኃጢአት ለወደቀው የሰው ዘር ድነት ሲል ከፍቅር የመነጨ ታላቅ መስዋዕትነትን እንደከፈለ አየ። «እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና» (2ኛ ቆሮንቶስ 5፡19)። ሉሲፈር ለራሱ ክብርንና ታላቅነትን በመመኘት ኃጢአት ወደ ዓለም እንዲገባ በሩን ሲከፍት ክርስቶስ ደግሞ ኃጢአትን ለማስወገድ እራሱን አዋርዶ እስከሞት ድረስ የታዘዘ ሆነ። ታተ 8.8
እግዚአብሔር አመጽን እንደሚጠላ ይገልጻል። በሰይጣን ኩነኔና በሰው ድነት የእግዚአብሔር ፍትህ መታየቱን ሰማያት ሁሉ ተመለከቱ። «የእግዚአብሔር ሕግ የማይሻር ከሆነና ከቅጣቱም ነፃ መሆን የማይቻል ከሆነ፣ እያንዳንዱ በደለኛ ለዘለዓለም ከፈጣሪ ፀጋ ሊታገድ ይገባል» ሲል ሉሲፈር ተናግሮ ነበር። በኃጢአት የወደቀው የሰው ዘር ከድነት ክልል ውጭ ስለሆነ ሰዎችን የእርሱ ሰለባ የማድረግ መብት እንዳለውም አሳወቀ። ነገር ግን ክርስቶስ በሰው ፈንታ መሞቱ ሊረታው የማይችለው ነጥብ ሆነበት። የህግ መቀጮ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ በሆነው በኢየሱስ ላይ አረፈ። ሰው የክርስቶስን ጽድቅ ለመቀበልና በንስሀ ራስን በማዋረድ የእግዚአብሔር ልጅ እንዳደረገው ሁሉ በሰይጣን ኃይል ላይ ድል ለመቀዳጀት ነጻነትን አገኘ። እግዚአብሔር ጻድቅ፣ በኢየሱስ የሚያምኑትንም የሚያጸድቅ ነው። ታተ 9.1
ክርስቶስ መከራንና ሞትን ለመቀበል ወደዚህች ምድር የመጣው የሰው ልጆችን ድነት ለመፈጸም ብቻም አልነበረም። «ሕጉን ታላቅ ያደርግና ያከብር ዘንድ» መጣ (ኢሳይያስ 42፡21)። ክርስቶስ የመጣው የዚህ ዓለም ነዋሪዎች ለሕጉ ተገቢውን ክብር እንዲሰጡ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔር ሕግ የማይለወጥ መሆኑን ለዓለማት ሁሉ ለማሳየት ነበር። ሕጉ የሚናገረውን ወደ ጎን መጣል ቢቻል ኖሮ የእግዚአብሔር ልጅ ለኃጢአት ስርየት ራሱን አሳልፎ መስጠት ባላስፈለገው ነበር። የክርስቶስ ሞት የሕጉን ዘላለማዊነት ያረጋግጣል። በመለኮታዊ ፍቅር ተገደው አብና ወልድ ኃጥአን እንዲድኑ ያደረጉት መስዋዕትነት፣ ለኃጢአት ስርየት ከዚህ ያነሰ አንዳች ነገር ሊቀርብ እንደማይችል ለዓለማት ሁሉ ያሳያል። የእግዚአብሔርም ሕግና መንግሥት በፍትህና በምህረት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ታተ 9.2
የመጨረሻው ፍርድ በሚሰጥበት ወቅት ለኃጢአት ምክንያት ተብሎ የሚቀርብ ማመካኛ አይኖርም። የምድር ሁሉ ዳኛ ሰይጣንን «ለምንድን ነው ያመጽክብኝ? ለምንስ በግዛቴ ስር የነበሩትን ነፍሳት ቀማኸኝ?» ብሎ ሲጠይቀው፣ የክፋት ሁሉ ጠንሳሽ ምላሽ ያጣል። አንደበት ሁሉ ዝም ይላል። የአመጽ ሠራዊትም በሙሉ በፀጥታ ይዋጣሉ። ታተ 9.3
የቀራኒዮ መስቀል የእግዚአብሔር ሕግ ዘላለማዊ መሆኑን በመግለጽ የኃጢአት ዋጋ ሞት እንደሆነ ለዓለማት ሁሉ ያውጃል። አዳኛችን «ተፈፀመ» ብሎ በታላቅ ድምፅ ሲጮህ የሰይጣን የሞት ደወል ተሰማ። ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ የቆየው የታላቁ ተጋድሎ ውጤት ተወሰነ፤ ክፋትም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንደሚወገድ ተረጋገጠ። የእግዚአብሔር ልጅ «በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን [ዲያብሎስን] በሞት እንዲሽር» በመቃብር ውስጥ ማለፍ ግድ ሆነበት (ዕብ. 2፡14)። ሉሲፈር ራሱን ከፍ ከፍ በማድረግ ምኞት ተነሳስቶ «ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፥ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ ከፍ አደርጋለሁ ... በልዑልም እመሰላለሁ» ሲል፤ እግዚአብሔር ደግሞ «በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ ... እስከ ዘላለምም አትገኝም» አለው። (ኢሳይያስ 14፡13-14፤ ሕዝቅኤል 28፡18-19)። ታተ 9.4
በመላው ፍጥረተ-ዓለም የሚኖሩ ሁሉ ስለ ኃጢአት ባህርይና ኃጢአት ስላስከተለው ውጤት ምስክር ይሆናሉ። ኃጢአት ያኔውኑ ብቅ እንዳለ በኃይል ቢደመሰስ ኖሮ መላእክት በፍርሃት ይዋጡና ለእግዚአብሔርም የነበራቸው ክብር ይቀንስ ነበር። አሁን ግን የኃጢአት መደምሰስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግ በሚወዱና በልባቸው ሕጉን በሚያኖሩ ፍጥረታት ሁሉ ፊት አምላካዊ ፍቅር እንከን የለሽ መሆኑን በመግለጽ የእግዚአብሔርን ክብር ያረጋግጣል። ክፋት ዳግም አይታይም። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው፣ «መከራም ሁለተኛ አይነሣም» (ናሆም 1፡9)። ሰይጣን «የባርነት ቀንበር ነው» ብሎ የተቸው የእግዚአብሔር ሕግ የነፃነት ሕግ ሆኖ ይከበራል። ጥልቅ ፍቅርና መለኪያ የሌለው ጥበብ የሆነው የእግዚአብሔር ባህሪይ በሙላት ስለተገለፀለት፣ በኃጢአት ተፈትኖ የጠራው ፍጥረት ዳግም ለፈጣሪው ታማኝነቱን አያጎድልም። ታተ 9.5