የቤተ ፡ ክርስቲያን፡ ምክሮች፡፡

23/126

በሰንበት ዕለት ወደ ትምህርት ቤት ስለመሔድ፡፡

አራተኛውን ትዕዛዝ የሚታዘዝ ሁሉ በርሱና በዓለም መኻከል የሚያለያይ መሥመር መደረጉን ያገኛል፡፡ ሰንበት መፈተኛ ነው፤ የሰው ፍላጎት አይደለም ፤ ያምላክ መፈተኛ ነው፡፡ እግዚአብሔር በሚያገለግሉና በማያገለግሉት መኻከል ለይቶ የሚያስታውቅ ነው፤ በዚህም ግብ ላይ በእውነትና በስህተት መኻከል የመጨረሻው ታላቁ የክርክር ተጋድሎ ይመጣል፡፡ CCh 51.1

አንዳንዶች ሰዎቻችን ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በሰንበት ዕለት ልከዋል፡፡ ይህን እንዲያደርጉ አልተገደዱም ነበር ፤ ግን የትምህርት ቤቱ ባለሥልጣኖች ልጆቹ ስድስት ቀናት ትምህርት ቤት ካለገቡ ስለማይቀበሏቸው ነው፡፡ ባንዳንዱ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ፤ ተማሮቹ የተለመዱትን የትምህርት (የጥናት) ቅርንጫፎች ብቻ የሚማሩ አይደለም፤ ግን ልዩ ልዩ ዓይነት ሥራ ይሰሩ ዘንድ ይማራሉ ፤ በስም የትዕዛዝ ጠባቂዎች ልጆች የተባሉት ወደዚህ በሰንበት ዕለት ተልከዋል፡፡ አንዳንዶች ወላጆች በሰንበት ቀን መልካም ማድረግ እንደሚገባ የክርስቶስ ቃላት በመጥቀስ የወሰዱትን እርምጃቸውን ለማመፃደቅ ሞክረዋል፡፡ ግን ይኸው ሐሳብ፤ ሰዎች በሰንበት ዕለት ለልጆቻቸው እንጀራ ያተርፉ (ያገኙ) ዘንድ የሚገባቸው ስለሆነ እንዲሠሩ የሚያስረዳ ነው፤ እንግዲህ ምን ሊደረግ ምንስ ሊደረግ የማይገባ መሆኑን ለማሳየት ወሰን የለም፤ የወሰንም መስመር የለም፡፡ CCh 51.2

ወንድሞቻችን ልጆቻቸው አራተኛውን ትእዛዝ ለመታዘዝ ከማይቻላቸው ሥፍራ ላይ ሲያቀምጧቸው እግዚአብሔር የሚደስትባቸው መሆኑን ተስፋ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡ ልጆቻቸው በሰባተኛው ቀን ወደ ትምህርት ቤት አንዳይሔዱ እንዲፈቀድላቸው ከባሥልጣኖች ጋር አንዳች ስምምነት ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህ የማይቻል እንደሆነ ከዚያ በኋላ የሆነ ይሁን፤ ለእግዚአብሔር ፍላጎቶች መታዘዝ ተግባራቸው ግልጽ ነው፡፡ CCh 51.3

አንዳንዶች ጌታ በፍላጎቶቹ ይህን ያህል ጥብቅ አይደለም ፤ ይህን ያህል በብዙ በመጨነቅ ሰንበትንም አጥብቀው መጠበቅ ፤ ወይም ስለዚሁ ነገር ካገር ሕጎች ጋር በመቃወስ ራሳቸውን ማጋፈጥ ተግባራቸው እንዳልሆነይናገራሉ፤ ግን የእግዚአብሔርን ሕግ ከሰዎች ፍላጎቶች በላይ የምናከብር መሆናችን ፈተናው የሚመጣብን እዚሁ ላይ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሚያከብሩና በማያከብሩት መኻከል የሚለየው ይኸው ነው፡፡ ታዛዥነታችንን የምናስረዳው እዚሁ ላይ ነው፡፡ በዘመናቱ ሁሉ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላደረገው አድራጎቶች የተነገረው ታሪክ የሚገባውን መታዘዝ የሚጠይቅ (የሚፈልግ) መሆኑን ያሳያል፡፡ ወላጆች ለልጆቻቸው ከዓለም ጋር ዕውቀትን ያገኙ ዘንድ ሰንበትን ተራ ቀን እንዲያደርጉ የሚፈቅዱላቸው ከሆነ ፤ እንግዲያውስ የእግዚአብሔር ማኅተም ሊደረግባቸው አይቻልም፡፡ ከአለም ጋር ይጠፋሉ ደማቸው በወላጆቻቸው ላይ የሚያርፍ አይደለምን? CCh 51.4

የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ልጆቻችንን በታማኝነት ብናስተምራቸውና ለወላጅ ሥልጣን እንዲገዙ ብናደርጋቸው ከዚያ በኋላም በሃይማኖትና በጸሎት ለእግዚአብሔር አደራ ብንሰጣቸው ተስፋ ሰጥቶናልና ከጥረቶቻችን ጋር ይሠራል፡፡ በአገርም የሚያጥለቀልቅ ግርፋት (ቅሥፈት) ሲወርድ እነሱም ከኛ ጋር በምሥጢራዊው ያምላክ ድንኳን ውስጥ ይሸሸጋሉ፡፡ CCh 52.1