መልዕክት ለወጣቶች
የጓደኝነት ተፅዕኖ
ወጣቶች ጓደኛ መያዛቸው የማይቀር ስለሆነ በርግጠኝነት የጓደኞቻቸው ተፅእኖ ይሰማቸዋል። የአንዱ ልብ ለሌላኛው ልብ ምላሽ እንዲሰጥ የሚያደርግ ምስጢራዊ የሆነ ነፍሶችን የሚያስተሰስር ግንኙነት አለ። አንዱ የሌላኛውን ሐሳቦች፣ ግምቶችና መንፈስ በቀላሉ ይረዳል። ይህ ግንኙነት በረከት ወይም እርግማን ሊሆን ይችላል። ወጣቶች አንዱ የሌላውን ባሕርይ፣ አመለካከትና እውቀት በማሻሻል እርስ በርስ ሊረዳዱና ሊበረታቱ ወይም ራሳቸውን ለግድየለሽነትና አለመታመን አሳልፈው በመስጠት የሚያዋርድ ተፅእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። MYPAmh 262.1
ተማሪዎች እጅግ ሊገነዘቡት የሚገባው ጉዳይ የጓደኛ ምርጫ ጉዳይ ነው። በእኛ ትምህርት ቤቶች በሚማሩ ተማሪዎች መካከል ሁልጊዜ ሁለት ክፍሎች አሉን! አንደኛው ክፍል እግዚአብሔርን ለማስደሰትና መምህሮቻቸውን ለመታዘዝ የሚፈልጉ ሲሆኑ ሌላኛው ክፍል ደግሞ በህገ ወጥነት መንፈስ የተሞሉ ናቸው። ወጣቶች ክፉ ለማድረግ ከአብዛኛው ሕዝብ ጋር የሚሄዱ ከሆኑ የእነርሱ ተፅዕኖ የነፍሳት ጠላት በሆነው ወገን ይሆናል! በሁኔታዎች መወሰን የሌለበትን የታማኝነት መርህ ያልተለማመዱትን ወደ ስህተት ይመራሉ። MYPAmh 262.2
“ጓደኛህን አሳየኝና ባሕርይህን አሳይሃለሁ” የሚለው አባባል ትክክል ነው። ወጣቶች በጓደኛ አመራረጣቸው ባሕርያቸውና ያላቸው መልካም ስም እንዴት እንደሚነካ መገንዘብ ያቅታቸዋል። አንድ ሰው ጓደኛ ለማድረግ የሚፈልገው ሰው በፍላጎቱ፣ በባሕርዩና በተግባሩ መጣጣም የሚችለውን ሰው ነው። ከአለአዋቂዎች ጋር ጓደኝነት መፍጠር የሚፈልግና ጠቢብና መልካም የሆኑትን የሚጠላ ሰው የራሱን ባሕርይ ጉድለት እያሳየ ነው። ጓደኛ ሊያደርጋቸው የሚፈልጋቸው ሰዎች ባሕርይና ፍላጎት በመጀመሪያ በፍፁም ከእርሱ ባሕርይና ፍላጎት ጋር የማይመሳሰሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ከነዚህ ግለሰቦች ጋር መቀላቀል ሲጀምር አስተሳሰቡና ስሜቱ ይለወጣል። ትክክለኛ መርሆዎችን መስዋዕት በማድረግ ለውጡ ሳይሰማው ግን ሊቋቋም በማይችልበት ሁኔታ ጓደኞቹ እስካሉበት ደረጃ ይወርዳል:: የሚፈስ ውኃ ሁልጊዜ የአከባቢውን አፈር ባሕርይ እንዲሚቀበል ሁሉ ወጣቶች የሚከተሉአቸው መርሆዎችና ባሕርያቸው አብረው ከሚሆኑት ጓደኞቻቸው ባሕርይ ጋር ይመሳሰላል። MYPAmh 262.3