የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
በ1890 ዓ.ም የነበረው አስፈሪ የሆነ እይታ
በባትል ክሪክ ስለነበሩት የጤና ማሰልጠኛ ተቋምና ስለ ማተሚያ ቤታችን፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ስለ ተቋሞቻችን ባለው አመለካከት ተደናግጫለሁ፡፡ ሐኪሞቻችን፣ ከጤና ተቋሞቻችንና ከሕትመት ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ሊኖራቸው ስለሚገባው ባሕርይ ጌታ በቃሉ ውስጥ ከገለጠው ሙሉ በሙሉ የተለየ ባሕርይ ያለው መንፈስ ራሱን እየገለጠ እና በተቋማት ውስጥ ከዓመት ወደ ዓመት እየበረታ በመሄድ ላይ ይገኛል፡፡ በጤና ማሰልጠኛ ውስጥ ያሉ ሀኪሞችና በማተሚያ ቤት ውስጥ በሀላፊነት ቦታ የተቀመጡ ሰዎች ክርስትና በሚጠይቀው ራስን የመካድና መስዋዕት የማድረግ መርሆዎች የመገዛት ግዴታ የለባቸውም የሚል ሀሳብ ተንሸራሽሯል፡፡ ነገር ግን የዚህ ሀሳብ ጥንስሱ የሰይጣን ምክር ነው፡፡ ሀኪሞች ስለ ተቋሙ ሥራ ከሚያስቡት የበለጠ ስለሚከፈላቸው ደሞዝ ማሰባቸውን ሲገልጹ የጌታን ሥራ በመስራት ታማኝ እንደሆኑ፣ ከራስ ወዳድነት እንደ ጸዱ እና እግዚአብሔርን እንደሚፈሩ የክርስቶስ አገልጋዮች ተደርገው እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች አለመሆናቸውን ያሳያሉ፡፡ በራስ ወዳድነት ፍላጎቶች ቁጥጥር ሥር የሆኑ ሰዎች ከተቋሞቻችን ጋር ያላቸው ግንኙነት መቀጠል የለበትም፡፡. . . . Amh2SM 194.2
ሰዎች እራሳቸው ከመሰረቱት መስፈርት ባላነሰ ሁኔታ እንደ ሥራቸው መጠን ስለሚፈረድ በራሳቸውና በአገልግሎታቸው ላይ ባስቀመጡት ዋጋ መጠን መልሰው እንዲሰጡ እግዚአብሔር ይፈልጋል፡፡ ለመክሊቶቻቸው እጅግ ትልቅ ዋጋ ከሰጡና ለችሎታዎቻቸው ከፍተኛ ግምት ከሰጡ በራሳቸው ግምትና ጥያቄ መጠን ተመጣጣኝ አገልግሎት እንዲሰጡ ይፈለግባቸዋል፡፡ ከአብና ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸው ትክከለኛ የሆነ ትውውቅ ምንኛ ትንሽ ነው፡፡ በክርስቶስ መንፈስ ተሞልተው ቢሆን ኖሮ ክርስቶስ የሰራውን ሥራ ይሰሩ ነበር፡፡ «ለእናንተም በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ልብ ይሁንላችሁ» (ፊል. 2፡ 5)፡፡ Amh2SM 194.3