የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)

155/349

የዓለምን መስፈርት አለመቅዳት

የዓለምን መስፈርት መቅዳት እንደሌለብን የሚገልጸውን ነጥብ በተመለከተ ብዙ ምስክርነቶች አሉኝ፡፡ አለማውያን እንደሚያደርጉት ማግኘት የምንችለውን ሁሉ ለማግኘት የመስገብገብ ዝንባሌን ማሳየት፣ ገንዘባችንን በልብስና በሕይወት ቅንጦት ላይ ማባከን የለብንም፡፡ ራሳችንን ለማስደሰት መኖር አንዲት ነጥብ ያህል እንኳን ደስተኛ አያደርገንም፡፡ አለአስፈላጊ የሆነ ገንዘብን ማባከን የእግዚአብሔርን ግምጃ ቤት መዝረፍ ነው፤ ያንን ጉድለት ሌላ የሚሞላ ሰው ያስፈልጋል፡፡ ሰዎች በአሥራትና በስጦታ እግዚአብሔርን ስለሚዘርፉ በዚህ ዓለም ላይ የክርስቶስን መንግሥት ለመገንባት የሚያስፈልጉ ነገሮች ውስን ናቸው፡፡ Amh2SM 192.3

አንድ ሰው ከፍተኛ የሆነ ደሞዝ የማግኘት ኃይል ሲኖረው ይህ ሁኔታ ግለሰቡ እንደ ሰራተኛ በእግዚአብሔር ፊት ያለው ትልቅነት መለኪያ እንደሆነ የሚገልጽ ሀሳብ ለአፍታ እንኳን መታየት የለበትም፡፡ በዓለም እይታ የሰው ትልቅነት የሚመዘነው ባለው የንብረት መጠን ነው፡፡ ነገር ግን የሰማይ መጻሕፍት መዝገብ እንደሚገልጸው የአንድ ሰው ትልቅነት የሚታየው ግለሰቡ በአደራ በተሰጠው ገንዘብ በሰራው መልካም ስራ ልክ ነው፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ያለውን እውነተኛ የሆነ ዋጋ ማሳየት የሚችለው እግዚአብሔርን በመፍራትና በመውደድ እና የእግዚአብሔር ሥራ ወደ ፊት እንዲቀጥል መክሊቶቹን ሙሉ በሙሉ በመቀደስ ነው፡፡ አንድ ሰው አስቀድሞ ወደ ሰማይ ምን ያህል እንደላከ መታወቅ የሚችለው በፍርድ ቀን የእያንዳንዱ ሰው ሥራ ተገምቶ እንደ ሥራው መጠን ሽልማት በሚሰጥበት ቀን ብቻ ነው፡፡ Amh2SM 193.1

ከአገልጋዮቻችን መካከል ለአንዳንዶች ምን ያህል አነስተኛ የሆነ ክፍያ ይከፈላቸው እንደነበር ለአመታት ምስክርነት አስተላልፌያለሁ፡፡ በመጠየቅ፣ መጻሕፍትን በመመርመር፣ ከአገልጋዮቻችን መካከል ከአንዳንዶች ጋር እጅግ የቀረበ ምክከር እንደነበረ ታገኛላችሁ፡፡ የንብረት ተቆጣጣሪ ኮሚቴ አባላት ሥራቸውን ማወቅ አለባቸው፣ እንዲሁም የክርስቶስ አእምሮ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ጠባብ አእምሮ ያላቸው፣ ከእግዚአብሔር አገልጋይ የሚፈለግ ራስን የመካድና መስዋዕት የማድረግ እውነተኛ የሆነ ሀሳብ የሌላቸው አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ ቤትን፣ ሚስትን እና ልጆችን መተውና ለእግዚአብሔር ሚስዮናውያን መሆን፣ እንዲሁም ለሰሩት ሥራ ምላሽ እንደሚሰጡ ሰዎች ለነፍሳት ድነት መስራት ምን ማለት እንደሆነ እውነተኛ የሆነ ግምት የላቸውም፡፡ እውነተኛ የሆነ የእግዚአብሔር አገልጋይ መላ ሕይወቱን ወደ መስዋዕት ይለውጣል፡፡ Amh2SM 193.2