የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)

101/349

ከክርስቶስ አይደለም

ክርስቶስ ተከታዮቹን ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ከሌላቸውና ሊቆጣጠራቸው በሚችለው በመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ ሥር ካልሆኑ ሰዎች ጋር አንድነት እንዲፈጥሩ የሚያደርጋቸውን ቃለ-መሃላ እንዲወስዱ በፍጹም አይመራቸውም፡፡ ብቸኛው ትክክለኛ የሆነ የባሕርይ መመዘኛ የእግዚአብሔር ቅዱስ ሕግ ነው፣ ያንን ሕግ የሕይወታቸው ገዥ ለሚያደርጉ ሰዎች የእግዚአብሔርን እውነት ወደ ውሸት ከሚቀይሩና የእግዚአብሔርን ሥልጣን እንደ ከንቱ ነገር ከሚቆጥሩ ጋር በመተማመንና ልባዊ በሆነ ወንድማማችነት አንድነት መፍጠር የማይቻል ነገር ነው፡፡ {2SM 127.2} Amh2SM 127.2

አለማዊ በሆነ ሰውና በታማኝነት እግዚአብሔርን በሚያመልክ ሰው መካከል ታላቅ ገደል አለ፡፡ እግዚአብሔርን፣ እውነትንና ዘላለምን በመሳሰሉ በአብዛኞቹ በጣም አስፈላጊ ትምህርቶች ላይ ሀሳቦቻቸው፣ ስምምነታቸውና ስሜቶቻቸው አይጣጣሙም፡፡ አንዱ ክፍል እንደ ስንዴ ለእግዚአብሔር ጎተራ እየጎመራ ሲሆን ሌላኛው ክፍል ደግሞ እንደ እንክርዳድ ለጥፋት እሳት እየተዘጋጀ ነው፡፡ በመካከላቸው የዓላማና የተግባር አንድነት እንዴት ሊኖር ይችላል? {2SM 127.3} Amh2SM 127.3

«ዓለምን መውደድ ለእግዚአብሔር ጥል እንዲሆን አታውቁምን? እንግዲህ የዓለም ወዳጅ ሊሆን የሚፈቅድ ሁሉ የእግዚአብሔር ጠላት ሆኖአል (ያዕ. 4፡4)፡፡ {2SM 127.4} Amh2SM 127.4

«ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም” (ማቴ. 6፡24)፡፡ {2SM 127.5} Amh2SM 127.5

ነገር ግን የአክራሪነትና የትዕግሥት የለሽነት መንፈስ እንዳይኖረን መጠንቀቅ አለብን፡፡ «ወደ እኔ አትቅረብ፤ እኔ ከአንተ ይልቅ ቅዱስ ነኝ» የሚል በሚመስል መንፈስ ከሌሎች ተለይተን መቆም የለብንም፡፡ እንደ እናንተ ካሉ ሰዎች ራሳችሁን መዝጋት የለባችሁም፣ ነገር ግን የራስህን ልብ የባረከውን ውድ እውነት ልታካፍላቸው ፈልግ፡፡ የአንተ ኃይማኖት የፍቅር ኃይማኖት መሆኑ ይታወቅ፡፡ {2SM 127.6} Amh2SM 127.6

«መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” (ማቴ. 5፡16)፡፡ {2SM 128.1} Amh2SM 128.1

ነገር ግን እኛ ክርስቲያኖች ከሆንን፣ ሰዎችን ከኃጢአታቸው ሊያድናቸው የሞተው የእርሱ መንፈስ ስላለን፣ እንደ እኛ ያሉ ሰዎችን በጣም ስለምንወዳቸው ኃጢአት በመፈጸም የሚያገኙትን ደስታ በመገኘታችን ወይም በተጽእኖአችን ማረጋገጥ አንችልም፡፡ ከእነርሱ ጋር ሕብረት በመፍጠር፣ እግዚአብሔር በማይገኝበት ግብዣቸውና ምክራቸው በመካፈል እነርሱ የሚከተሉትን መንገድ ማረጋገጥ አንችልም፡፡ የዚህ ዓይነት መንገድ እነርሱን ከመጥቀም ይልቅ የኃይማኖታችንን እርግጠኝነት እንዲጠራጠሩ ያደርጋቸዋል፡፡ በምሳሌያችን ነፍሳትን ወደ ጥፋት የምንመራ ከሆንን የውሸት ብርሃኖች ነን፡፡ {2SM 128.2} Amh2SM 128.2

በቅርቡ በባሕር ላይ እየቀዘፈ ሳለ በእኩለ ሌሊት ላይ ከአለት ጋር አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ ስለተጋጨ ግርማ ሞገስ ስላለው መርከብ አነበብኩ፤ ተሳፋሪዎቹ በድንጋጤ የነቁት ተስፋ ቢስ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ለማየት ብቻ ሲሆን ዳግመኛ ላይመለሱ ከመርከቡ ጋር ሰመጡ፡፡ የመርከቡን መሪ ይዞ የነበረው ሰው የወደብ መብራትን ስለተሳሳተ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነፍሳት በአንድ አፍታ ማስጠንቀቂያ ብቻ ወደ ዘላለም ጥፋት ተወረወሩ፡፡ ክርስቶስን በተሳሳተ ሁኔታ የሚያሳይ ባሕርይ ካሳየን፣ እያሳየን ያለነው የስህተት ብርሃን ስለሆነ፣ በእርግጠኝነት ነፍሳት በእኛ ምሳሌነት ወደ ስህተት ይመራሉ፡፡ {2SM 128.3} Amh2SM 128.3