የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)

93/349

ለእኛ ጊዜ የተሰጡ መልእክቶች

ትንቢት መስመር በመስመር እየተፈጸመ ነበር፡፡ በሶስቱ መላእክት መልእክት ባንዲራ ሥር ጸንተን በቆምን ቁጥር የዳንኤልን ትንቢት የበለጠውን በግልጽ እናስተውላለን፤ ራዕይ በዳንኤል ላይ ተጨማሪ እንዲሆን የተሰጠ ነው፡፡ በተቀደሱ የእግዚአብሔር አገልጋዮች አማካይነት በመንፈስ ቅዱስ የተሰጠውን ብርሃን በተሟላ ሁኔታ ስንቀበል የጥንት ትንቢት እውነቶች እንደ ዘላለማዊው ዙፋን የጠለቁና እርግጠኛ መስለው ይገለጣሉ፤ የእግዚአብሔር ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው እንደተናገሩ እርግጠኛ እንሆናለን፡፡ መንፈስ ቅዱስ በነቢያቶች አማካይነት የተናገራቸውን ነገሮች ለማስተዋል ራሳቸው በመንፈስ ቅዱስ ተጽእኖ ሥር መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ መልእክቶች የተሰጡት ትንቢቶቹን ለተናገሩት ሰዎች ሳይሆን ትንቢቶቹ እየተፈጸሙ ባሉበት ወቅት ለምንኖር ለእኛ ነው፡፡ {2SM 114.2} Amh2SM 114.2

ይህን ሥራ እንድሰራ ጌታ ባይሰጠኝ ኖሮ እነዚህን ነገሮች ማቅረብ እንደምችል አይሰማኝም ነበር፡፡ ከአንተ ሌላ እንዳንተው አዲስ ብርሃን እንዳላቸው የሚያስቡ ከአንድ ወይም ከሁለት የሚበልጡ ሌሎች ሰዎች አሉ፣ ሁሉም መልእክታቸውን ለሰዎች ለማቅረብ ዝግጁ ናቸው፡፡ ነገር ግን አስቀድሞ የተሰጠውን ብርሃን ተቀብለው በእሱ ቢሄዱ እና ለብዙ አመታት በእግዚአብሔር ሕዝቦች ተይዞ የቆየውን አቋም በሚያጸኑት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ እምነታቸውን ቢመሰርቱ ኖሮ እግዚአብብሔርን ያስደስተው ነበር፡፡ ዘላለማዊው ወንጌል የሚታወጀው በሰብዓዊ ወኪሎች ነው፡፡ ለወደቀው ዓለም የመጨረሻውን ማስጠንቀቂያ ይዘው በሰማይ መካከል እንደሚበሩ የተገለጹ መላእክትን መልእክቶች ልናሰማ ነው፡፡ ትንቢት እንድንናገር ካልተጠራን፣ ትንቢቶቹን እንድናምንና ብርሃንን ለሌሎች አእምሮዎች በመስጠት ከእግዚአብሔር ጋር እንድንተባበር ተጠርተናል፡፡ ይህን ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነን፡፡ {2SM 114.3} Amh2SM 114.3

ወንድሜ ሆይ፣ በብዙ መንገዶች ልትረዳን ትችላለህ፡፡ ነገር ግን በራስህ ላይ የምታተኩር እንዳትሆን እንድነግርህ በጌታ ታልኬያለሁ፡፡ የእግዚአብሔርን ቃል እንዴት እንደምትሰማ፣ እንደምታስተውል እና እንደምትቀበል ልብ በል፡፡ ከወንድሞችህ ጋር መስመር በማስመርህ እንኳን ጌታ ይባርከሃል፡፡ የሶስተኛውን መልአክ መልእከት እንዲያውጁ እሱ የላካቸው ከሰማያዊ ኃይሎች ጋር በአንድነት በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ጌታ በአማኞች መካከል አለመስማማትን የሚያመጣን መልእክት የመስጠት ሸክም አይሰጥህም፡፡ ደግሜ እናገራለሁ፣ እሱ ለዓለማችን እንዲያስተላልፉ ለሕዝቡ በሰጣቸው ክብር ባላቸው መልአክቶች ላይ ያላቸውን እምነት የሚያናጋ ንድፈ ሀሳብ እንዲያቀናብር ማንንም ቢሆን በቅዱስ መንፈሱ አይመራም፡፡ {2SM 115.1} Amh2SM 115.1

ጽሁፎችህን እንደ ከበሩ እውነቶች እንዳትቆጥራቸው እመክርሃለሁ፡፡ እጅግ ብዙ ጭንቀትን ያመጣብህን ነገር ወደ ሕትመት በመቀየር ዘላለማዊነትን መስጠት የሚመከር ነገር አይደለም፡፡ ይህ ጉዳይ ሕዝቡ በእነዚህ የመጨረሻ አደገኛ ቀናት ማመንና መለማመድ ያለባቸውን የእውነት መልእክት ለማደናቀፍ ስለሚሰራ በሕዝብ ፊት እንዲቀርብ የእግዚአብሔር ፈቃድ አይደለም፡፡. . . {2SM 115.2} Amh2SM 115.2

የሰዎችን አእምሮ አቅጣጫ ለማሳትና እምነታቸውን ለማናጋት ንድፈ ሀሳቦች ያለማቋረጥ ይቀርባሉ፡፡ ትንቢቶችን በመግለጥ ረገድ ትክክለኛ የሆነ ልምድ ያላቸው ሰዎች ዛሬ የሆኑትን የሆኑት፣ ማለትም ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች የሆኑት፣ በእነዚህ ትንቢቶች ነው፡፡ ወገባቸውን በእውነት ታጥቀው እና ሁሉንም የጦር መሣሪያ ለብሰው መቆም አለባቸው፡፡ ይህ ልምምድ ያልነበራቸውም የእውነት መልእክትን በተመሳሳይ መታመን የመያዝ እድል አላቸው፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ለመስጠት የወደደው ብርሃን እሱ ከዚህ በፊት በመራቸው መንገድ ላይ ያላቸውን መታመን አያዳክምም፣ ነገር ግን እምነትን አጽንተው እንዲይዙ ያበረታቸዋል፡፡ የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻ አጽንተን መያዝ አለብን፡፡ {2SM 115.3} Amh2SM 115.3

«የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው» (ራዕይ 14፡12)፡፡ እዚህ በሶስተኛው መልአክ መልእክት ሥር ቆመናል፡፡ «ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፣ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች፡ በብርቱም ድምፅ፡- ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች፣ ወደቀች፣ የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፣ የእርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የእርኩሳንና የተጠሉ ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ አህዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ ወይን ጠጅ የተነሣ ወድቀዋልና፣ የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልናዋ ኃይል የተነሣ ባለጠጋዎች ሆኑ ብሎ ጮኸ፡፡ ከሰማይም ሌላ ድምጽ ሰማሁ እንዲህ ሲል፡- ሕዝቤ ሆይ፣ በኃጢአቷ እንዳትተባበሩ ከመቅሰፍቷም እንዳትቀበሉ ከእርስዋ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሷልና፣ እግዚአብሔርም አመጻዋን አሰበ” (ራዕይ 18፡1-5)፡፡ {2SM 116.1} Amh2SM 116.1