የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)

342/349

ተጨማሪ መግለጫ 2—የትዳር አጋርን ስለ መምረጥ የተሰጡ ተጨማሪ ነገሮች

(በኤለን ኋይት ጽሁፎች ባለአደራዎች የተሰጠ መግለጫ)

የተመረጡ መልእክቶች በሚሉ ሁለቱ መጻሕፍት ውስጥ እንደተቀመጠው አንባቢው «ዘ ወርድ ቱ ዘ ሪደር” የሚለውን ክፍል በጥንቃቄ ሲያነብ ሳለ ሁለቱም መጻሕፍት ውስጥ ምክር ያዘሉ፣ በዘመናት ውስጥ የተሰጡ፣ ወደ ሥራ መስክ በበራሪ ጽሁፎች፣ በመጽሔቶች፣ በእጅ ጽሁፎች እና በታይፕ በተጻፉ መልእክቶች የደረሱ መሆናቸውን፣ ነገር ግን ኤለን ኋይት ከመሞቷ በፊት ከታተሙት ዘጠኙ የቴስቲሞኒ መጻሕፍት ምክሮች ውስጥ የተወሰዱ አለመሆናቸውን ይመለከታል፡፡ በዚህ መልክ በ1958 ዓ.ም ለኤለን ኋይት ጽሁፎች በተሰጠው ሶስት ቅጽ ባለው አጠቃላይ ተጨማሪ መግለጫ ውስጥ ማካተት በሚቻልበት ሁኔታና ጊዜ የታተመው ሕትመት ለቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ምክሮችን ይሰጣል፡፡ Amh2SM 481.1

በእነዚህ ሁለቱ መጻሕፍትና በሌሎች የኤለን ኋይት መጻሕፍት ውስጥ ያሉ በርካታ ገጾች፣ እንዲሁም ጥቂት የማይባሉ ለግለሰቦች የተሰጡ የግል ምስክርነቶች፣ የትዳር ወይም የሕይወት ጓደኛን መምረጥን የሚመለከቱ ጥያቄዎችን የሚዳስሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ምክሮች ደስተኛና ስኬታማ ለሆነ ጋብቻ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እና ከዚያ ጋብቻ ለሚወለዱ ሕጻናት ደህንነት የሚያስፈልጉ ነገሮችን የሚገልጹ ናቸው፡፡ ስኬታማ የሆነ የጋብቻ አንድነት እንዳይፈጠር የሚከለክሉ ነገሮችንም ያቀርባሉ፡፡ ኤለን ኋይት «ኢየሱስ ደስታ ያለባቸውን ጋብቻዎች፣ በእሳት ምድጃ ዙሪያ ያሉ የቤተሰብ አባላት ደስተኛ የሆኑባቸውን ቤቶች ለማየት እንደሚፈልግ” ታረጋግጣለች (The Adventist Home, p. 99)፡፡ «የሕይወት ጓደኛ ምርጫ ለወላጆችና ለልጆቻቸው አካላዊ፣ አእምሮአዊና፣ እና መንፈሳዊ ጥንካሬን ለማምጣት የተሻለ መሆን አለበት፡፡» --The Ministry Of Healing, P. 357. Amh2SM 481.2

በእነዚህ ጽሁፎች ውስጥ የቤት ተጽዕኖ በቤተ ክርስቲያን ፊት ተቀምጧል፡፡ ጋብቻን ለመፈጸም እያሰቡ ያሉትን ሰዎች ያ እያሰላሰሉ ያሉት ጋብቻ የሚኖረውን ተጽዕኖ በደንብ እንዲያስቡበት ትጋብዛላች፡፡ ይህን በተመለከተ ራስ ወዳድነት ወይም ክፉ ምኞት ወይም አርቆ ሳያስቡ የሚፈጸሙ ውሳኔዎች እንዳይኖሩ አደፋፍራለች፡፡ ለመጋባት እያሰቡ ላሉት ወንዶችና ሴቶች «ዝም ብሎ ደስታን በሚሰጥ እና ትርፋማ በሆነ ነገር መካከል ያለውን ልዩነት እወቁ” በማለት ጥሪ አቅርባለች (Letter 4, 1901)፡፡ ብዙ ወንዶችና ሴቶች በዚህ ሕይወት ስኬታማነታቸውን ወይም ውድቀታቸውን እና የወደፊት ሕይወታቸውን ተስፋ የሚጀምሩት ከጋብቻ ሰዓት ጀምሮ ነው» በማለት ተናግራለች፡፡ --The Adventist Home, P. 43. Amh2SM 482.1

ጋብቻ ደስታ ያለበት እንዲሆን መጣጣም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ኤለን ኋይት ትናገራለች፡፡ «እርስ በርሳቸው የማይጣጣሙ ሰዎች ከሚፈጥሩት ጥምረት» የተነሳ የሚመጣውን ችግር «የእድሜ ልክ እርግማን” ብላ ጽፋለች (Patriarchs and Prophets, P. 189). መልእክት ለወጣቶች በሚል መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ብላለች፡- Amh2SM 482.2

“ዛሬ ዓለም በመከራና በኃጢአት የተሞላው ጥሩ ቅንጅት ከሌላቸው ጋብቻዎች የተነሳ ነው፡፡ በብዙ ሁኔታዎች ሲታይ ባልና ሚስት የእርስ በርስ ባሕርያቸው በፍጹም መዋሃድ የማይችል መሆኑን ለማወቅ የሚወስድባቸው ጥቂት ወራትን ብቻ ነው፡፡ የዚህ ውጤቱ የሰማይ ፍቅርና መጣጣም ብቻ መኖር ባለበት ቤት ውስጥ ጥላቻ መግነን ነው፡፡»--Youth’s Instructor, Aug. 10, 1899; Messages to Young People, P. 453; And The Adventist Home, P. 83. Amh2SM 482.3

ጋብቻን እያሰቡ ባሉ ሰዎች መካከል ያለው «ትልቅ የዕድሜ ልዩነት በዕድሜ ወጣት የሆነውን ግለሰብ ጤና እንደሚያጓድል» እና የልጆችን «አካላዊና አእምሮአዊ ብርታት» እንደሚቀማ በማስጠንቀቅ የተቃውሞ ድምጽዋን አሰምታለች (The Ministry of Healing, P. 358). Amh2SM 482.4

ጋብቻን እያሰላሰሉ ላሉ ሰዎች የትዳር አጋራቸው የጤና ሁኔታ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ኤለን ኋይት በአጽንዖት ተናግራለች፡፡ «ብዙ ጊዜ ታማሚ የሆኑ ወንዶች ጤናማ የሆኑ ሴቶችን በፍቅር አሸንፈዋል፣ እርስ በርሳቸው ስለተዋደዱ ብቻ ለመጋባት ፍጹም ነጻነት እንዳላቸው ስለሚሰማቸው ይብዛም ይነስም በሽተኛ ከሆነ ባል የተነሳ ሚስት ስቃይ እንደሚደርስባት ሳያገናዝቡ ጋብቻን ይፈጽማሉ፡፡” --Selected Messages, Book 2, P. 423፡፡ ከዚያ በኋላ ጉዳዩን ተገቢ ወደሆነ አስተሳሰብ ድምዳሜ ትወስዳለች፡፡ «ወደ ጋብቻ ሕብረት የሚገቡት ብቻ ችግሩ የሚመለከታቸው ቢሆን ኖሮ ኃጢአታቸው ያን ያህል ትልቅ ባልሆነም ነበር፡፡ ከወላጆቻቸው በሚተላለፍ በሽታ ልጆቻቸው ለመሰቃየት ይገደዳሉ፡፡” --Ibid. Amh2SM 482.5

የትዳር አጋሮች በገቢያቸው ራሳቸውን ለማስተዳደር መቻልም ለተሳከ ጋብቻ እንደ ቅድመ ሁኔታ መታየት እንዳለበት ሚስስ ኋይት አስቀምጣለች፡፡ «ሃብት ሳይኖራቸው፣ ወይም ሃብት ለማፍራት የአካል ብርታት ወይም የአእምሮ አቅም ሳይኖራቸው ጋብቻን ለመፈጸም የሚቸኩሉ እና በትክክል ግንዛቤ የሌላቸውን ሀላፊነቶች የሚወስዱ” ሰዎች እንዳሉ ጠቁማለች፡፡ ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ ዋነኞቹ የችግሩ ገፈት ቀማሾች ልጆች ናቸው፡፡ «አብዛኛውን ጊዜ ቤትን በልጆች የሚሞሉት የሥራ ጥበብ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎድላቸው እና በዓለም ውስጥ ለመኖር ብቃት የሌላቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ልጆች «በቂ ምግብና ልብስ እንደማያገኙ፣ እና የአካልና የአእምሮ ስልጠናም እንደማያገኙ” ጠቁማለች፡፡ (Ibid., PP. 420, 421). Amh2SM 482.6

ምክር የተሰጠበት ሌላ አከባቢም አለ፡፡ ያውም የተለያየ የዘር እና የባህል ዳራ ያላቸውን ወንዶችና ሴቶች በጋብቻ ማጣመር ነው፡፡ ይህን የሚመስሉ አራት ትምህርቶች ባልታተሙ የእጅ ጽሁፎችና በታተሙ መዛግብት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ ከቀረቡት ከአራቱ መግለጫዎች መካከል ሁለቱ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 343 እና 344 ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ መግለጫዎች የተጻፉት በተከታታይ በ1896 እና በ1912 ዓ.ም ሲሆን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ለመታተም የተመረጡበት ምክንያት መሠረታዊ የሆኑ መርሆዎችን ስለሚያካትቱና እነዚህን የመሰሉ ጋብቻዎች ለምን መደፋፈር እንደሌለባቸው ስለሚገልጡ ነው፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ጋብቻዎች በቀላሉ «ግጭትንና ውዝግብን” ይፈጥራሉ ተብሎ ተገልጾአል፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ጋብቻዎችን ላለማበረታታት የወሰነችበት ሌላኛው ምክንያት ወላጆች በልጆቻቸው ላይ ያለ ምርጫቸው ስለሚጭኑባቸው «ጉዳቶች” ሲሆን ይህ ሁኔታ ልጆቹ «ይህን የእድሜ ልክ ውርስ በሰጡአቸው ወላጆቻቸው ላይ የምሬት ስሜት” እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ ነው፡፡ (ልብ በሉ፡- ከሌሎቹ ሁለት መግለጫዎች መካከል የመጀመሪያው የምክር መግለጫ የሚገኘው ኤለን ኋይት መጋቢት 21 ቀን 1891 ዓ.ም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች በአሜሪካ ወዳሉ ጥቁሮች ለመስራት ወደ ሥራ እንዲገቡ ተማጽኖ ባቀረበችበት ወቅት ነበር፡፡ ሙሉ መግለጫውን በ1966 ዓ.ም በታተመው በደቡባዊ ሥራ እትም ገጽ 9-18 ላይ ይመልከቱ፡፡ በዚህ እትም ውስጥ ስለ ሰብአዊ ዘር ወንድማማችነት ጉልህና በማያሻማ ሁኔታ ያስቀመጠች ሲሆን በአምልኮም ሁሉም በእግዚአብሔር ፊት እኩል እንደሚቆሙ ግልጽ አድርጋለች፡፡ በዚያኑ ጊዜ ስለማስጠንቀቂያ ቃላት ድምጽ ሰጥታለች፡፡ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች በተነበበው በዚህ መግለጫ ውስጥ የሚከተሉትን መስመሮች እናገኛለን፡- Amh2SM 483.1

«እንደ ቤተ ክርስቲያን ኃጢአት የሚሆንብን ነገር ቢኖር በጥቁር ሕዝብ መካከል ላሉት ነፍሳት ድነት ከፍተኛ ጥረት አለማድረጋችን ነው፡፡… እናንተ ከምታመልኩባቸው የአምልኮ ቦታዎች ጥቁሮችን ለማግለል ከእግዚአብሔር ፈቃድ አልተሰጣችሁም፡፡ ልክ እንደ እናንተው የክርስቶስ ንብረት ስለሆኑ እንደ ክርስቶስ ንብረት አድርጋችሁ ያዙአቸው፡፡ ከነጭ ወንድሞች ጋር የቤተ ክርስቲያን አባልነት ሊይዙ ይገባል፡፡ በእነርሱ ላይ የተደረገውን እያንዳንዱን አሰቃቂ ስህተት ለማጥፋት እያንዳንዱ ጥረት መደረግ አለበት፡፡ እንዲሁም ነገሮችን ወደ ጽንፍ በመውሰድ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ አክራሪነት መሄድ የለብንም፡፡ አንዳንዶች እያንዳንዱን የመለያ ግርግዳ በማፍረስ ከጥቁሮች ጋር መጋባት ትክክል ነው ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፣ ነገር ግን ይህን ማስተማርም ሆነ መተግበር ትክክል አይደለም፡፡” --The Southern Work, P. 15. Amh2SM 483.2

በዚህ ነጥብ ላይ የተሰጠው ሌላ መግለጫ ከነጮች ዘር የሆነ አንድ ግለሰብ ከጥቁር ዘር ጋር እንዲጋባ እቅድ ላዘጋጀ ለአንድ ወጣት ጥር 8 ቀን 1901 ዓ.ም የተጻፈ የምክር ደብዳቤ ነው፡፡ ምክሩ በ1912 ዓ.ም በተሰጠው ተመሳሳይ በሆነ የሀሳብ ልውውጥ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በገጽ 344 ላይ ተመዝግቦ ያለ ነው፡፡ ነገር ግን ኤለን ኋይት በደንብ ማሰላሰልን የሚጠይቁ ቃላትን እንዲህ በማለት ትጨምራለች፡- Amh2SM 483.3

«ለወሰደችው እርምጃ ለዘላለም እየተጸጸተች እንድትኖር የሚያደርግ ጋብቻን ከአንዲት ልጃገረድ ጋር አትፈጽም፡፡….» Amh2SM 483.4

«ሰብዓዊ ፍጡራን እንዴት ያሉ በምኞት የተሞሉ፣ ራስ ወዳዶች፣ እና አርቆ ማሰብ የማይችሉ ፍጡራን ናቸው፡፡ በራሳችሁ የአእምሮ ውሳኔ ከመደገፍ ይልቅ በእግዚአብሔር ውሳኔ ተደገፉ፡፡ አስደሳችና ትርፋማ በሆነ ነገር መካከል ያለውን ልዩነት ለይታችሁ እወቁ፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በመገዛት ፈጽሙ፡፡…የራሳችሁን መንገድና ፈቃድ ከተከተላችሁ እሾክና አሜካላ ያገኛችኋል፡፡» --Ellen G. White Letter 4, 1901.) Amh2SM 483.5

እነዚህ አራት ምክሮች በተወሰነ መልክዓ ምድራዊ ቦታ ለነበሩ ሁኔታዎች መልስ እንዲሆኑ በተወሰነ ጊዜ የተጻፉ ቢሆኑም ጋብቻውን አደጋ ውስጥ ለመጣል እና አንዳንድ ልጆች በተሰጣቸው ውርስ ቅር የሚሰኙበትን ሁኔታ የሚፈጥር ጋብቻ ለመፈጸም እያሰላሰሉ ላሉት እንደ ማስጠንቀቂያ ሊያገለግሉ አይችሉምን? Amh2SM 484.1

እነዚህ ምክሮች በሕይወት ውስጥ ወሳኝና ዘለቄታ ያለውን ልምምድ እየተጋፈጠ ለነበረ እና የልብ ጭንቀትን ለሚያስከትሉና የጋብቻ አንድነትን ለሚያጠፉ ነገሮች ንቀት ለነበረው ለአንድ አማኝ ከተሰጡት ምክሮች መካከል የተወሰዱ ናቸው፡፡ ኤለን ኋይት እንዳለችው «ኢየሱስ ደስታ ያለባቸውን ጋብቻዎችና በደስታ የተሞላ ቤት ይሻል፡፡” Amh2SM 484.2

ኤለን ጂ ኋይት በቃልም ሆነ በጽሁፎቿ ውስጥ በተደጋጋሚ የሰጠቻቸው መግለጫዎች ግልጽ እንደሚያደርጉት ጉዳዩ የዝርያዎች እኩል ያለመሆን ጉዳይ አይደለም፡፡ በሰብአዊ ዘር መካከል የቀረበ ወንድማማችነት መኖሩን እና በሰማይ መዛግብት የአንዱ የሰው ዘር ስም በሌላኛው የሰው ዘር ስም አጠገብ እንደሚቆም ሁልጊዜ ስትገልጽ ነበር፡፡ ከዚህ ቀጥሎ «የሰብዓዊ ዘር ወንድማማችነት» የሚል ርዕስ የተሰጠውን ተጨማሪ መግለጫ በጥንቃቄ ያንብቡ፡፡ Amh2SM 484.3

የኤለን ኋይት ጽሁፎች ባለአደራዎች፣

ዋሽንግተን ዲ ሲ፣

ነሐሴ 1967 ዓ.ም.