የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
ምዕራፍ 4
ከባድ ሕመም በቤተሰብ ውስጥ ሲገባ ራስን በጤንነት ለመጠበቅ እና ይህን በማድረግ ከበሽታ ለመከላከል እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለግል ንጽሕና እና ለምግብ ጥብቅ ትኩረት የመስጠት ታላቅ አስፈላጊነት አለበት፡፡ ሕመምተኛው የሚተኛበት ክፍልም ከመጀመሪያው ጀምሮ በደንብ አየር እንዲያስገባ ማድረግ ታላቅ ጠቀሜታ አለው፡፡ ይህ ለታማሚው ጠቃሚ ነው፣ረዘም ላለ ጊዜ ከሕመምተኛው ጋር አብረው ለመሆን የተገደዱትን በጤንነት ለመጠበቅም በከፍተኛ ደረጃ አስፈላጊ ነው፡፡ {2SM 455.1} Amh2SM 455.1
በክፍል ውስጥ የተስተካከለ ሙቀት መኖር ለሕመምተኛው ታላቅ ዋጋ አለው፡፡ የክፍሉን ሙቀት ሕመምተኛውን የሚከታተሉ ሰዎች እንዲወስኑ ከተተወ ሁልጊዜ በትክክል ላይመጣጠን ይችላል፡፡ ሕመምተኛውን የሚከታተሉ ሰዎች ትክክለኛው የሙቀት መጠን የትኛው እንደሆነ በተሻለ ሁኔታ መወሰን ላይችሉ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች ከሌሎች የበለጠ ሙቀት ሊፈልጉ ስለሚችሉ ለሌሎች ምቾት የሚነሳ የሙቀት መጠን ያለው ክፍል ለእነርሱ ሊመቻቸው ይችላል፡፡ በክፍሉ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሰው ለራሱ ትክክለኛ ሙቀት ሊሰጠው በሚችል ሁኔታ እሳቱን ለማሰናዳት ነጻነት ከተሰጠው ሕመምተኛው በሚተኛበት ክፍል ውስጥ የሚኖረው የሙቀት መጠን ተለዋዋጭ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለሕመምተኛው በሚያስጨንቅ ሁኔታ ይሞቃል፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ እጅግ ይቀዘቅዛል፡፡ ይህ በሕመምተኛው ላይ ጎጂ ውጤት ይኖረዋል፡፡ የህመምተኛው ጓደኞች ወይም የሚጠነቀቁለት ሰዎች፣ ከስጋትና ሕመምተኛውን ከመከታተል የተነሳ በቂ እንቅልፍ ያጡና የሕመምተኛውን ሁኔታ ለመከታተል ሲባል በሌሊት በድንገት የሚነቁ ስለሆነ ለቅዝቃዜ የተጋለጡ ናቸው፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ሰዎች ለሕመምተኛው የመኝታ ክፍል የሙቀት መጠን ትክክለኛ የሙቀት መለኪያዎች (ቴርሞሜትሮች) አይደሉም፡፡ እነዚህ ነገሮች ትንሽ ዋጋ ያላቸው ይመስላሉ፣ ነገር ግን ለሕመምተኛው ማገገም የሚያደርጉት አስተዋጽዖ ከፍተኛ ነው፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች በሕመምተኛው ክፍል ውስጥ ከሚከሰቱ ከልክ ያለፉ ለውጦች የተነሳ ሕይወት ለአደጋ ተጋልጧል፡፡ {2SM 455.2} Amh2SM 455.2
ሕመምተኛው ምቹ በሆነ የአየር ንብረት ውስጥ በምንም ምክንያት ቢሆን በቂ የሆነ ንጹህ አየር መነፈግ የለበትም፡፡ ክፍሎቹ ሁልጊዜ ከሁለት አቅጣጫ የሚመጣ ንፋስ ቀጥታ ወደ ሕመምተኞቹ ሳይመጣና ለቅዝቃዜ ሳያጋልጣቸው መስኮቶች ወይም በሮች በክፍላቸው ውስጥ እንዲከፈቱ በሚፈቅዱበት ሁኔታ ላይገነቡ ይችላሉ፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በሮችና መስኮቶች መከፈት ያለባቸው በሚቀጥለው ክፍል ሲሆን ሕመምተኛው ወዳለበት ክፍል ንጹህ አየር እንዲገባ መፍቀድ አለባቸው፡፡ ለሕመምተኛ ሰው ከመድሃኒት ይልቅ ንጹህ አየር የበለጠ ጠቃሚ ነው፣ ከምግባቸው በላይ አስፈላጊ ነው፡፡ አየር ከመከልከል ይልቅ ምግብ ቢከለከሉ ኖሮ የተሻለ መሥራት እና ቶሎ ማገገም ይችላሉ፡፡ {2SM 455.3} Amh2SM 455.3
ብዙ የማይጠቅሙ ሆነው የቀሩት ሰዎች ለሳምንታት ወይም ለወራት በተዘጋ ክፍል ውስጥ ብርሃን እንዳያገኙ የተከለከሉ እና አየር ሕመምተኛው ደህና ለመሆን የሚፈልገው መድሃኒት ሆኖ ሳለ እንደ ክፉ ጠላት በመታየቱ ብርታት ከሚሰጠው ንጹህ የሰማይ አየር ተለይተው የተዘጉ ናቸው፡፡ አየር ከማጣቱ የተነሳ መላው አካል ደክሟል፣ በሽተኛም ሆኗል፡፡ ተፈጥሮ በምታደርጋቸው ጥረቶች እስክትሸነፍና እስክትሰበር ድረስ በሐኪሞች ከሚሰጡት የተለያዩ ዓይነት መድሃኒቶች በተጨማሪ እየተጠራቀሙ ካሉ ቆሻሻዎች ጭነት የተነሳ እየሰመጠች ስለሆነ ሕመምተኛው ይሞታል፡፡ መኖር ይችሉ ነበር፡፡ እንዲሞቱ ሰማይ ፈቃዱ አልነበረም፡፡ የሞቱት ከራሳቸውና ከጓደኞቻቸው ድንቁርና፣ ዋና ለሆኑ የአካል ክፍሎች ብርታት ለመስጠት፣ ደምን ለማንጻት እና በአካል ውስጥ ያሉ መጥፎ ሁኔታዎችን እንድትቋቋም ተፈጥሮን ለመርዳት ንጹህ ውኃን እንዳይጠጡና ንጹህ አየርን እንዳይተነፍሱ በመከልከል የተለያዩ ዓይነት መድሃኒቶችን ከሰጡ ሐኪሞች ድንቁርና የተነሳ ነው፡፡ ሐኪሞች ያዘዙአቸው መርዞች በጭፍን መታመን እየተወሰዱ ሳለ ሰማይ ያለ ገንዘብ እና ያለ ዋጋ ያዘጋጃቸው እነዚህ ጠቃሚ ፈውሶች ወደ ጎን ተትተዋል፤ እንደ ዋጋ ቢስ መቆጠር ብቻ ሳይሆን እንደ አደገኛ ጠላቶች ተደርገውም ታይተዋል፡፡ {2SM 456.1} Amh2SM 456.1
በሕይወት መኖር ይችሉ የነበሩ በሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች ንጹህ አየርንና ንጹህ ውኃን ካለማግኘታቸው የተነሳ ሞተዋል፡፡ ለራሳቸውና ለሌሎችም ሸክም ሆነው የሚኖሩ በሺሆች የሚቆጠሩ ዋጋ ቢሶች ሕይወታቸው የሚደገፈው ከሐኪሞች የሚሰጡ መድሃኒቶችን በመውሰዳቸው እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ያለማቋረጥ ራሳቸውን ከአየር ይከላከላሉ፣ ውኃን ከመጠቀምም ይሸሻሉ፡፡ ደህና ለመሆን እነዚህ በረከቶች ያስፈልጓቸዋል፡፡ እውነቱ ቢበራላቸውና ምስኪን የሆነ ኑሮን በመድሃኒት ከመመረዝ ይልቅ መድሃኒትን ትተው ከቤት ውጭ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ጋር ራሳቸውን ቢያለማምዱ፣ በጋም ሆነ ክረምት በቤታቸው ውስጥ አየር እንዲገባ ቢፈቅዱ፣ ለመጠጥና ለመታጠብ ንጹህ ውኃን ቢጠቀሙ ኖሮ ደህና እና ደስተኛ ይሆኑ ነበር፡፡ {2SM 456.2} Amh2SM 456.2
አስታማሚዎችና ነርሶች በተለይ አስጊ የሆነ ትኩሳትና የሰንባ ነቀርሳ በሚሆንበት ጊዜ ለራሳቸው ጤንነት የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው፡፡ አንድ ሰው በሕመምተኛ ክፍል ውስጥ ተወስኖ መቆየት የለበትም፡፡ የሚታመኑ ሁለት ወይም ሶስት ጥንቁቅና የሚረዱ ነርሶች ለሕመምተኛው የሚደረገውን ጥንቃቄና በክፍሉ ውስጥ መቆየትን ተራ በተራ ቢያደርጉ የጉዳቱ መጠን ይቀንሳል፡፡ በተቻለ ፍጥነት እያንዳንዳቸው ከክፍል ውጭ እንቅስቃሴ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህ ለህመምተኛው አልጋ ጥንቃቄ ለሚያደርጉ፣ በተለይም የህመምተኛው ጓደኞች አየር ወደ ሕመምተኛው ክፍል ከገባ ጠላት እንደሆነ አድርገው የሚቆጥሩና መስኮትና በር እንዳይከፈት የሚያደርጉ ከሆነ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ከሕመምተኛው ጓደኞች ይቅርታ የማይገባው ድንቁርና የተነሳ ሕመምተኛውና አስታማሚዎቹ ከቀን ወደ ቀን መርዘኛ የሆነ አየርን ለመተንፈስ ይገደዳሉ፡፡ {2SM 456.3} Amh2SM 456.3
በብዙ ሁኔታዎች አስታማሚዎች አካል ምን እንደሚፈልግ፣ ንጹህ አየርን መተንፈስ ጤንነትን ከመጠበቅ ጋር ያለውን ግንኙነት፣ እና በሕመምተኛ ክፍል ውስጥ ያለውን በበሽታ የተበከለ አየር መተንፈስ ሕይወትን የሚያጠፋ ተጽዕኖ እንዳለው አያውቁም፡፡ በዚህ ሁኔታ የሕመምተኛው ሕይወት ለአደጋ ተጋልጧል፣ አስታማሚዎቹም በሽታውን ለመቀበል፣ ጤንነታቸውን ለማጣት እና ምናልባትም ሕይወትን ለማጣት የተጋለጡ ናቸው፡፡ {2SM 457.1} Amh2SM 457.1
በቤተሰብ ውስጥ ትኩሳት ሲገባ ብዙ ጊዜ ከአንድ በላይ ሰዎች በትኩሳቱ ይጠቃሉ፡፡ የቤተሰቡ ልምዶች ትክክለኛ ቢሆኑ ኖሮ ይህ መሆን አልነበረበትም ነበር፡፡ ምግባቸው መሆን እንደሚገባው ቢሆን፣ የንጽህናን ልምዶች ቢጠብቁ እና አየርን የማስገባትን አስፈላጊነት ቢገነዘቡ ኖሮ ትኩሳቱ ወደ ሌላ የቤተሰብ አባል አይዛመትም ነበር፡፡ በቤተሰቦች ውስጥ ትኩሳት የሚታይበትና አስታማሚዎች ለበሽታ የሚጋለጡበት ምክንያት የህመምተኛው ክፍል በንጽህና ስለማይያዝና በክፍሉ ውስጥ በቂ አየር እንዲዘዋወር በማድረግ መርዘኛ ከሆኑ ብክለቶች ነጻ ስለማይደረግ ነው፡፡ {2SM 457.2} Amh2SM 457.2
አስታማሚዎች የጤና ጉዳይን በተመለከተ ንቁ ከሆኑ እና ለራሳቸው፣ ለሕመምተኛውና ለዘመዶች ጥቅም ሲባል በቂ አየር እንዲዘዋወር የማድረግን አስፈላጊነት ከተገነዘቡ፣ ወደ ሕመምተኛው ክፍል አየርና ብርሃን እንዳይገባ ተቃውሞ ከገጠማቸው፣ የሕመምተኛውን ክፍል ትተው በመውጣታቸው የሕሊና ወቀሳ ሊኖራቸው አይገባም፡፡ ለሕመምተኛው ካለባቸው ግዴታ ነጻ መሆናቸው ሊሰማቸው ይገባል፡፡ በበሽታ የመያዝን ዕዳ መቀበልና መርዘኛ አየርን በመተንፈስ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ መጣል የማንም ግዴታ አይደለም፡፡ ሕመምተኞች ለራሳቸው የተሳሳቱ አመለካከቶች ተጠቂ ከሆኑና ከሰማይ በረከቶች እጅግ አስፈላጊ የሆነው አየር ወደ ክፍላቸው እንዳይገባ በራቸውን ከዘጉ ያድርጉት፣ ነገር ግን ይህ መኖር የሚገባቸውን ሌሎች ሰዎች አደጋ ላይ በመጣል መሆን የለበትም፡፡ {2SM 457.3} Amh2SM 457.3
እናት፣ ሀላፊነት ስለሚሰማት፣ ንጹህ አየር እንዳይገባ በተደረገ ክፍል ውስጥ ሕመምተኛውን ለመርዳት ቤተሰቧን ትታ በመሄድ እሷንና መላ አካሏን የጎዳውን በበሽታ የተበከለ አየር በመተንፈስ ሕመምተኛ ሆናለች፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ከተሰቃየች በኋላ ልጆቿን እናት አልባ በማድረግ ሞታለች፡፡ የዚህችን ራስ ወዳድነት የሌላትን እናት ርህራሄ የተጋራው ሕመምተኛ ከበሽታው አገገመ፣ ነገር ግን ሕመምተኛውም ሆነ የሕመምተኛው ጓደኞች ንጹህ አየር ከጤንነት አጠባበቅ ጋር ያለውን ግንኙነት ካለማወቃቸው የተነሳ ውድ ሕይወት መስዋዕት መሆኑን አልተገነዘቡም፡፡ ያለ እናት እንክብካቤ ለቀሩትና ለተበተኑት መንጎችም ሀላፊነት አልተሰማቸውም፡፡ {2SM 457.4} Amh2SM 457.4
አንዳንድ ጊዜ እናቶች ሴት ልጆቻቸው በቂ አየር በሌለበት ክፍል ውስጥ ለበሽተኞች እንዲጠነቀቁ ይፈቅዳሉ፤ ከዚህ የተነሳ በሕመም ላይ በሚቆዩበት ወቅት ሁሉ ይጠነቀቁላቸዋል፡፡ እናት ለልጇ ካላት ጭንቀትና ጥንቃቄ የተነሳ ትታመምና ብዙ ጊዜ አንዳቸው ወይም ሁለቱም ይሞታሉ፣ ወይም የተሰበረ የአካል አቋም ይኖራቸዋል፣ ወይም በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ የሚሰቃዩ ዋጋ ቢሶች ይሆናሉ፡፡ ንጹህ የሆነ የሰማይ አየር እንዳይገባ የተከለከለበት የሕመምተኛ ክፍል መነሻቸው የሆነ የሚያሳዝኑ የክፋት ዝርዝሮች አሉ፡፡ ይህን መርዘኛ አየር የሚተነፍሱ ሁሉ የአካል ሕጎችን ስለሚጥሱ ቅጣቱን መቀበል አለባቸው፡፡ {2SM 458.1} Amh2SM 458.1
በአጠቃላይ ሲታይ ሕመምተኞች ጸጥታ በሚሹበትና መረበሽ በማይፈልጉበት ጊዜ እያጫዎቱአቸውና በተለያዩ ርዕሶች ላይ ውይይት እያነሱ በሚያደክሟቸው በብዙ ጠያቂዎችና ጎብኝዎች የተጨናነቁ ናቸው፡፡ ብዙዎች ሥራ እያበዙ ጉልበታቸውን በመበዝበዝ ራሳቸውን በሽተኛ አድርገዋል፡፡ ጉልበታቸው ተንጠፍጥፎ ሲያልቅ ሥራን ለማቆም ይገደዳሉ፣ የአልጋ ቁራኛ በመሆንም ይሰቃያሉ፡፡ እንዲሻላቸው የሚያስፈልጓቸው ነገሮች እረፍት፣ ከጭንቀት ነጻ መሆን፣ ብርሃን፣ ንጹህ አየር፣ ንጹህ ውኃ እና አነስተኛ ምግብ ናቸው፡፡ ብዙዎች ሕመምተኞችን እንዲጎበኙ የሚመራቸው ይሉኝታና የተሳሳተ ደግነት ነው ፡፡ ሕመምተኞቹ በጠያቂዎች ከተጎበኙ በኋላ ብዙ ጊዜ እንቅልፍ የለሽ ሌሊቶችን ያሳልፋሉ፡፡ ይብዛም ይነስም ስሜታቸው ስለተቀሰቀሰ የዚያ ምላሹ ለተዳከመው ጉልበታቸው ከሚችለው በላይ ይሆንበታል፣ ከእነዚህ ይፈራረቁ ከነበሩት ጉብኝቶች የተነሳ እጅግ አደገኛ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሟቸውና አስተዋይነት ያለበት ጥንቃቄ ስለሚጎድላቸው ብዙ ነፍሳት ተሰውተዋል፡፡ {2SM 458.2} Amh2SM 458.2
አንዳንድ ጊዜ ሕመምተኞች ሲጎበኙ እና በመከራቸው ጊዜ ጓደኞቻቸው እንዳልረሱአቸው ሲያውቁ እርካታን ይሰጣል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ጉብኝቶች እርካታ የሚሰጡ ቢሆኑም በብዙ አጋጣሚዎች እነዚህ የሚፈራረቁ ጉብኝቶች ሕመምተኛው እየዳነ ሳለ ሚዛኑን በማዛባት ወደ ሞት መርተዋል፡፡ ለሕመምተኛው የማይጠቅሙ ሰዎች ሕመምተኛውን በመጎብኘት ረገድ ጥንቁቆች መሆን አለባቸው፡፡ የማይጠቅሙ ከሆነ ይጎዳሉ፡፡ ነገር ግን ሕመምተኞች ችላ መባል የለባቸውም፡፡ ከሁሉ የተሻለ ጥንቃቄ ሊደረግላቸውና የጓደኞችና የዘመዶች ርህራኄ ሊያገኙ ይገባል፡፡ {2SM 458.3} Amh2SM 458.3
ማታ ሕመምተኞችን የሚጠብቁ ሰዎች አጠገባቸው ከመሆን ዓለም አቀፋዊ ባሕል የተነሳ ሕመምተኞች ብዙ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አስጊ በሆነ ሁኔታ ይህ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከዚህ ልምምድ የተነሳ ሕመምተኞች ከሚጠቀሙ ይልቅ የበለጠ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ወደ ሕመምተኛው ክፍል አየር እንዳይገባ ማድረግ ልማድ ነው፡፡ አሳንሰን ብንናገር፣ እንደዚህ በተደረጉ ክፍሎች ውስጥ ያለው አየር የህመተኞችን ሁኔታ እጅግ እንዲከፋ የሚያደርግ ቆሻሻ አየር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ወደ ሕመምተኛው ክፍል በበር ወይም በመስኮት ስንጥቅ የሚገባውን ጥቂት አስፈላጊ የሆነ አየር የሚሻሙ ሁለት ወይም ከሁለት በላይ አስታማሚዎች በክፍል ውስጥ ማድረግ ከሕመምተኞቹ ሕያውነታቸውን እየወሰደባቸው ብቻቸውን ቢሆኑ ኖሮ ከሚሆኑት የበለጠ እያዳከማቸው ነው፡፡ ክፋቱ እዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ ይብዛም ይነስም አንድ አስታማሚ ብቻ እንኳን ሕመምተኛውን የሚረብሽ እንቅስቃሴ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ሁለት አስታማሚዎች ሲሆኑ አንዳንድ ጊዜ ጮክ ብለው፣ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ በሹክሹክታም ቢሆን ያወራሉ፡፡ እነዚህ ሹክሹክታዎች ጮክ ብሎ ከመናገር ይልቅ የህመምተኛውን ነርቮች የሚፈታተኑና የሚረብሹ ናቸው፡፡ {2SM 459.1} Amh2SM 459.1
ከአስታማሚዎች የተነሳ ሕመምተኞች በስቃይ የተሞሉና እንቅልፍ የሌላቸውን ብዙ ሌሊቶች ችለው አሳልፈዋል፡፡ መብረት ጠፍቶ ለብቻቸው እንዲሆኑ ቢተዉ ኖሮ ሁሉም ሰው መተኛቱን ስለሚያውቁ ራሳቸውን ለእንቅልፍ ስለሚያዘጋጁ ጧት ታድሰው ይነቁ ነበር፡፡ ምንም እንኳን አብዛኞቹ ሕመምተኞች ባያውቁትም በሕመምተኛ ክፍል ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሕይወት አዘል አየር ከሁሉ የበለጠ ዋጋ አለው፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባያውቁም እጀግ በጣም ድብርት ይሰማቸዋል፡፡ በክፍላቸው ውጥ ንጹህ አየር መንቀሳቀስ ደስታን እና ብርታትን የመስጠት ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ {2SM 459.2} Amh2SM 459.2
ነገር ግን አየርን በመፍራት ይህ በረከት እንዳይደርሳቸው ራሳቸውን ከዘጉ እነርሱ ዘንድ እንዲደርስ የተፈቀደው ትንሽ አየር በአስታማሚዎችና በፋኖስ መብራት መወሰድ የለበትም፡፡ ሕመምተኞችን የሚያስታምሙ ሰዎች ከተቻለ በአቅራቢያ ያለ ክፍል በመያዝ ሌሊቱን ጸጥ ብለው እንዲያርፉ ይተዉአቸው፡፡ {2SM 459.3} Amh2SM 459.3
አለአስፈላጊ የሆነ የሚረብሽ ድምጽና እንቅስቃሴ ሁሉ ከሕመምተኛ ክፍል ተወግዶ ቤቱ በሙሉ በተቻለ መጠን ጸጥ ያለ መሆን አለበት፡፡ ብልህና አሳቢ ከሆኑ አስታማሚዎች ተገቢ የሆነ እንክብካቤ አግኝተው ቢሆን ኖሮ መኖር ይችሉ የነበሩ ብዙ ሕመምተኞች ካለማወቅ፣ ከመርሳትና ከግድ የለሽነት የተነሳ ሞተዋል፡፡ በር መዘጋትና መከፈት ያለበት በታላቅ ጥንቃቄ ነው፤ አስታማሚዎች የማይቸኩሉ፣ ረጋ ያሉ እና ራሳቸውን የሚገዙ መሆን አለባቸው፡፡ {2SM 459.4} Amh2SM 459.4
ከተቻለ የህመምተኛ ክፍል ቀንም ሆነ ማታ የአየር እንቅስቃሴ ያለበት መሆን አለበት፡፡ ንፋሱ በቀጥታ ሕመምተኛውን ማግኘት የለበትም፡፡ ትኩሳት በሚኖርበት ጊዜ ቅዝቃዜን መቀበል አደጋ የለውም፡፡ ነገር ግን ችግሩ ሲመጣና ትኩሳቱ ሲያልፍ የተለየ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በአካል ውስጥ ሕያውነትን ለመጠበቅ ነቅቶ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ሕመምተኛ ንጹህ ብርታት የሚሰጥ አየር ማግኘት አለበት፡፡ ሌላ ዘዴ መቀየስ የማይቻል ከሆነ፣ ከተቻለ የህመምተኛው ክፍል፣ አልጋውና በአልጋው ላይ የሚነጠፉ ነገሮች አየርን በማግኘት በሚነጹበት ሰዓት ሕመምተኛው ወደ ሌላ ክፍል እና ወደ ሌላ አልጋ መዛወር አለበት፡፡ ጤነኞች የሆኑ ሰዎች የብርሃንን እና የአየርን በረከት የሚፈልጉ ከሆነና ጤናማ ሆነው ለመቀጠል የንጽህና ልማዶችን መጠበቅ ካስፈለጋቸው፣ ሕመምተኞች ከደካማ ሁኔታቸው ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መጠን እነዚህ ነገሮች በጣም ያስፈልጓቸዋል፡፡ {2SM 460.1} Amh2SM 460.1
ሁሉም የጤና ሕጎችን በጥብቅ በመታዘዝ በሽታን ለመከላከል ቢጥሩ ኖሮ ከብዙ ሥቃይ መዳን ይቻል ነበር፡፡ ጥብቅ የሆኑ የንጽህና ሕጎች መጠበቅ አለባቸው፡፡ ብዙዎች ጤነኛ ሆነው ሳሉ ራሳቸውን በጤንነት ለመጠበቅ ራሳቸውን አያጨናንቁም፡፡ የግል ንጽህናቸውን ችላ ይላሉ፣ ልብሶቻቸውን በንጽህና ለመጠበቅም ጥንቁቅ አይደሉም፡፡ ቆሻሻዎች ያለማቋረጥ እና ሳይታዩ ከሰውነት ቀዳዳዎች እየወጡ ያልፋሉ፣ የቆዳችን ውጭኛው ክፍል በጤናማ ሁኔታ ካልተጠበቀ፣ አካል በቆሻሻ ይጨናነቃል፡፡ የሚለበሱ ልብሶች ብዙ ጊዜ የማይታጠቡ እና ቶሎ ቶሎ አየር የማያገኙ ከሆነ ከሰውነት ውስጥ እየተሰማንም ሆነ ሳይሰማን በእርጥበት መልክ ከሚወጡ ቆሻሻዎች የተነሳ ይቆሽሻሉ፡፡ የሚለበሱ ልብሶች ከእነዚህ ቆሻሻዎች የማይጸዱ ከሆነ በቆዳችን ውስጥ ያሉ ቀዳዳዎች ያስወጡአቸውን ቆሻሻዎች መልሰው ይመጣሉ፡፡ ከሰውነት የሚወጡ ቆሻሻዎች ወደ ውጭ እንዲወጡ ካልተፈቀደላቸው ተመልሰው ወደ ደም ይቀላቀሉና በውስጣችን ባሉት የአካል ክፍሎች ላይ ይጫናሉ፡፡ ተፈጥሮ ራሷን ከእነዚህ መርዘኛ ቆሻሻዎች ነጻ ለማድረግ ስትል አካልን ነጻ ለማውጣት ጥረት ታደርጋለች፡፡ ይህ ጥረት ትኩሳትን ይፈጥራል፣ ይህ ትኩሳት በሽታ የሚል ስም ይሰጠዋል፡፡ እንዲህም ሆኖ ሳለ ታማሚው ንጹህ ውኃን በመጠቀም ተፈጥሮን በምታደርገው ጥረቷ ቢያግዛት ኖሮ ብዙ ስቃይ እንዳይደርስ መከልከል ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ይህን ከማድረግና ከሰውነታቸው ውስጥ መርዘኛ የሆነ ነገርን ለማስወጣት ከመፈለግ ይልቅ በውስጥ ያለውን መርዝ ለማስወጣት የበለጠውን አደገኛ የሆነ መርዝ ይወስዳሉ፡፡ {2SM 460.2} Amh2SM 460.2
አጠቃላይ ንጽሕና የሚያስገኛቸውን ጠቃሚ ውጤቶች እያንዳንዱ ቤተሰብ ቢገነዘብ ኖሮ እያንዳንዱን ቆሻሻ ከአካላቸው እና ከቤቶቻቸው ለማስወገድ የተለየ ጥረት ያደርጉ ነበር፣ ጥረታቸውን ወደ ጊቢያቸውም ያሰፉ ነበር፡፡ ብዙዎች በጊቢያቸው ውስጥ የሚበሰብሱ አትክልቶችን ዝም ብለው ይተዋሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች ምን ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው ገና አልነቁባቸውም፡፡ ከእነዚህ ከሚበሰብሱ ነገሮች አየርን የሚመርዝ ሽታ ያለማቋረጥ ይነሳል፡፡ ንጹህ ያልሆነ አየርን በመተንፈስ ደም ይመረዛል፣ ሳንባዎች ይጎዳሉ፣ መላው አካልም በሽተኛ ይሆናል፡፡ በእነዚህ በሚበሰብሱ ነገሮች የተበከለ አየርን መተንፈስ እያንዳንዱ መግለጫ የሚሰጠውን በሽታ ያስከትላል፡፡ {2SM 460.3} Amh2SM 460.3
ቤተሰቦች በትኩሳት ሕመም ተጠቅተዋል፣ አንዳንዶች ደግሞ ሞተዋል፣ ሌሎቹ በቤተሰብ ክበብ ውስጥ ያሉት ለደረሰባቸው ሕመም እና ሞት ብቸኛው ምክንያት የራሳቸው ግድ የለሽነት ሆኖ ሳለ ለደረሱባቸው አስጨናቂ ሀዘኖች በእግዚአብሔር ላይ እስከማጉረምረም ደርሰዋል፡፡ በጊቢያቸው ውስጥ ያሉ ቆሻሻዎች ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችንና እግዚአብሔርን ተጠያቂ የሚያደርጓቸውን አሳዛኝ ስቃዮችን አምጥተውባቸዋል፡፡ {2SM 461.1} Amh2SM 461.1
የእሥራኤል ልጆች በምንም ምክንያት ቢሆን አካላቸውን ወይም ልብሳቸውን እንዳያቆሽሹ እግዚአብሔር አዞአቸው ነበር፡፡ የግል ንጽህና ችግር ያለባቸው ግለሰቦች ከእሥራኤል ልጆች ሰፈር ተለይተው እስከ ምሽት ይዘጉና ወደ ሰፈር ተመልሰው ከመግባታቸው በፊት ራሳቸውንና ልብሳቸውን እንዲያጥቡ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሰፈራቸው ሲያልፍ ቆሻሻነታቸውን እንዳይመለከት ከሰፈራቸው ረዥም ርቀት እስኪደርስ ድረስ በዙሪያቸው ምንም ዓይነት ቆሻሻ እንዳይኖር እግዚአብሔር አዞአቸው ነበር፡፡ {2SM 461.2} Amh2SM 461.2
ንጽህናን በተመለከተ እግዚአብሔር ከጥንቱ እሥራኤል ከፈለገባቸው ያነሰ ነገር አሁን ካሉት ሕዝቦቹ አይፈልግባቸውም፡፡ ንጽህናን ችላ ማለት በሽታን ይቀሰቅሳል፡፡ በሽታና ያለ እድሜ መሞት ያለ ምክንያት አይመጡም፡፡ ከዚህ በፊት ጤነኛ ተደርገው ይታዩ በነበሩ ጎረቤቶችና ከተማዎች ውስጥ በቀላሉ የማይበርዱ ትኩሳቶችና ሀይለኛ በሽታዎች ታይተዋል፤ ከዚህ የተነሳ አንዳንዶች ሙተዋል፣ ሌሎች ደግሞ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሕመም ሽባ እስኪሆኑ ድረስ አቋማቸው ተሰብሮ ቀርተዋል፡፡ በብዙ አጋጣሚዎች፣ የራሳቸው ቅጥር ግቢ፣ ቤተሰባቸውና ጎረቤቶቻቸው እንዲተነፍሱ አደገኛ የሆነ መርዝን ወደ አየር የሚልክ የጥፋት ወኪል ይዟል፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚታይ ቸልተኝነት እና ግድ የለሽነት እንስሳዊነት ሲሆን እንደ እነዚህ ያሉ ነገሮች በጤና ላይ ያላቸውን ውጤቶች አለማወቅ የሚያስገርም ነው፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ቦታዎች በተለይ በበጋ ጊዜ በኖራና በአመድ ወይም በአፈር ውስጥ በየቀኑ በመቀበር መጽዳት አለባቸው፡፡ {2SM 461.3} Amh2SM 461.3
አንዳንድ ቤቶች ለቤተሰቡ ደስታና ምቾት ከማሰብ ይልቅ ለኩራትና እንግዶችን ለመቀበል ተብሎ በውድ ዕቃዎች ተሞልተዋል፡፡ ከሁሉም የተሻሉት ክፍሎች ጨለማ ሆነው እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ የሰማይ ብርሃን ውድ የሆኑ የቤት ዕቃዎችን እንዳይጎዳ፣ ምንጣፎችን ወይም የፎቶ ማቀፊያዎችን እንዳያደበዝዝ ብርሃንና አየር እንዳይገቡ ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ውድ ክፍሎች ውስጥ እንግዶች እንዲቀመጡ በሚደረጉበት ጊዜ የዚህ የዕቃ ማከማቻ ክፍል ከባቢ አየር ስለሚያውዳቸው ጉንፋን የመያዝ አደጋ ውስጥ ናቸው፡፡ ማረፊያ ክፍሎችና መኝታ ክፍሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ለተመሳሳይ ምክንያቶች ተዘግተው ይቆያሉ፡፡ እነዚህን ለጸሐይ ብርሃንና አየር ያልተጋለጡ ክፍሎችን የሚይዝ ማንኛውም ሰው ጤንነቱን እና ሕይወቱንም ጭምር ለአደጋ በማጋለጥ ላይ ነው፡፡ {2SM 462.1} Amh2SM 462.1
ብርሃን እና አየር የማያገኙ ክፍሎች እርጥበት ይፈጥራሉ፡፡ አልጋዎችና የአልጋ ልብሶች እርጥበትን ስለሚሰበስቡና በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ያለው ከባቢ አየር በብርሃንና በአየር አማካይነት ነጽቶ ስለማያውቅ መርዘኛ ነው፡፡ በእነዚህ ዘመናዊ (ፋሽንን በተከተሉ) እና ለጤና ጎጂ በሆኑ ክፍሎች ውስጥ መተኛት የተለያዩ ዓይነት በሽታዎችን አምጥቷል፡፡ ከፋሽን ተከታይ እንግዶች ባዶ ሙገሳ በላይ ለጤንነት ዋጋ የሚሰጡ ቤተሰቦች በቤቶቻቸው በእያንዳንዱ ክፍል ውስጥ በየቀኑ ለብዙ ሰዓቶች አየር እንዲዘዋወር እና በቂ ብርሃን እንዲገባ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ብዙዎች ፋሽንን በቅርበት ስለሚከተሉ እና የእሱ ባርያዎች ስለሚሆኑ ከፋሽን ውጭ ላለመሆን በሽታንና ሞትን ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናሉ፡፡ ፋሽንን የተከተለ ዘመናዊ ኑሮ ይኖራሉ፣ ከዚህ የተነሳ በሽታ ይይዛቸዋል፣ ዘመናዊ በሆኑ መርዞች ይታከማሉ፣ በመጨረሻም ዘመናዊ የሆነ ሞት ይሞታሉ፡፡ {2SM 462.2} Amh2SM 462.2
በተለየ ሁኔታ የመኝታ ክፍሎች በደንብ አየር የሚዘዋወርባቸው መሆን አለባቸው፡፡ በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ያለው ከባቢ አየር በብርሃንና በአየር ጤናማ እንዲሆን መደረግ አለበት፡፡ መስኮቶች በየቀኑ ለበርካታ ሰዓታት ክፍት መሆን አለባቸው፣ መጋረጃዎች ወደ ጎን ተደርገው ክፍሉ በደንብ አየር ማግኘት አለበት፡፡ የአየሩን ንጽህና የሚበክል ምንም ነገር ለአጭር ጊዜም ቢሆን መቅረት የለበትም፡፡ {2SM 462.3} Amh2SM 462.3
ብዙ ቤተሰቦች በራሳቸው ድርጊት ባመጡአቸው የጎሮሮ ቁስለት፣ በሳንባ በሽታዎች እና በጉበት ሕመም ይሰቃያሉ፡፡ የመኝታ ክፍሎቻቸው ለአንድ ሌሊት እንኳን ገጣሚ ያልሆኑ ጠባብ ክፍሎች ሲሆኑ እነርሱ ግን እነዚህን ትንንሽ ክፍሎች ለሳምንታት፣ ለወራት እና ለዓመታት ይይዟቸዋል፡፡ አየርን የሚያስገባ ትንሽ ክፍተት ካለ ቅዝቃዜ እንዳያገኛቸው በመፍራት መስኮቶቻቸውንና በሮቻቸውን ይዘጋሉ፡፡ ከሰውነታቸው በሳንባና በቆዳ ቀዳዳዎች አማካይነት የሚወጡ መርዘኛ ቆሻሻዎች እስኪያጥለቀልቋቸው ድረስ ያንኑ አየር መልሰው መላልሰው ይተነፍሳሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ከቤት ውጭ ቆይተው ተመልሰው በመግባት ጉዳዩን በመፈተን በተዘጋ ክፍላቸው ውስጥ ያለው አየር ጤነኛ አለመሆኑን ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በሳንባዎቻቸው አማካይነት በመተንፈስ ወደ ደማቸው ስላስተላለፉአቸው ቆሻሻዎች ግንዛቤ ይኖራቸዋል፡፡ ጤንነታቸውን በዚህ መልክ ያለ አግባብ የሚጎዱ ሰዎች በሽታ ያጠቃቸዋል፡፡ ሁሉም ብርሃንን እና አየርን ሰማይ ከሰጣቸው እጅግ ውድ ስጦታዎች መካከል እንደ አንዱ አድርገው ይቁጠሩ፡፡ እነዚህን በረከቶች ጠላቶቻቸው እንደሆኑ በመቁጠር እንዳይገቡ መከልከል የለባቸውም፡፡ {2SM 462.4} Amh2SM 462.4
ለመኝታ አገልግሎት የሚውሉ አፓርታማዎች ትላልቆችና ቀንና ማታ አየር ሊዘዋወርባቸው በሚችል መልኩ የተዘጋጁ መሆን አለባቸው፡፡ ወደ መኝታ ክፍላቸው አየር እንዳይገባ ያደረጉ ሰዎች በአስቸኳይ ድርጊታቸውን መቀየርን መጀመር አለባቸው፡፡ ደረጃ በደረጃ አየር እንዲገባ በማድረግ ምንም ብርድ ሳያገኛቸው በጋና ክረምቱን ሁሉ በክፍላቸው ውስጥ የአየር ዝውውርን መሸከም እስኪችሉ ድረስ መጠኑን መጨመር አለባቸው፡፡ ሳንባዎች ጤናማ ለመሆን ንጹህ አየር ማግኘት አለባቸው፡፡ {2SM 463.1} Amh2SM 463.1
ሌሊቱን በቂ የአየር ዝውውር በሌለባቸው ክፍሎች የተኙ ሰዎች መንስኤውን ባያውቁትም ጧት ሲነቁ በአጠቃላይ ድካምና ትኩሳት እየተሰማቸው ይነቃሉ፡፡ የዚህ ምክንያቱ መላው አካል ይፈልግ የነበረውና ማግኘት ያልቻለው የአየር እጥረት ነው፡፡ ጧት ሲነሱ ብዙ ሰዎች በአንድ ባልዲ ውኃ ገላቸውን በእስፖንጅ ወይም እንደ አመቺነቱ በእጃቸው በመታጠብ ጥቅም ያገኙበታል፡፡ ይህ ከቆዳቸው ላይ ቆሻሻን ያስወግድላቸዋል፡፡ ከዚያም የመኝታ ልብስ ሁሉ ከአልጋ ላይ አንድ በአንድ በመነሳት ለአየር መጋለጥ አለበት፡፡ መስኮቶች መከፈት አለባቸው፣ መጋረጃዎችም ወደ ጎን መያዝ አለባቸው፣ ቀኑን ሁሉ ማድረግ ባይቻል እንኳን ለበርካታ ሰዓታት በመኝታ አፓርታማዎች ውስጥ አየር እንደ ልብ መዘዋወር አለበት፡፡ በዚህ መልኩ አልጋና የአልጋ ልብሶች አየርን እንደ ልብ ስለሚያገኙ ከከፍሉ ቆሻሻዎች ይወገዳሉ፡፡ {2SM 463.2} Amh2SM 463.2
በቤት ዙሪያ የሚገኙ የጥላ ዛፎች እና ጥቅጥቅ ያሉና ወደ ቤት እጅግ የቀረቡ ቁጥቋጦዎች ነጻ የሆነ የአየር ዝውውርን ስለሚከለክሉና የፀሐይ ጮራዎች በበቂ ሁኔታ እንዳይደርሱ ስለሚከለክሉ ለጤና ተስማሚ አይደሉም፡፡ ከዚህ የተነሳ በቤት ውስጥ እርጥበት ይሰበሰባል፡፡ በተለይም ዝናባማ በሆኑ ወቅቶች በመኝታ ክፍሎች ውስጥ እርጥበት ስለሚጠራቀም በአልጋዎች ላይ የሚታኙ ሰዎች በቁርጥማት፣ በአእምሮ ነርቭ በሽታና በሳንባ ሕመም ይሰቃያሉ፡፡ ይህ በመጨረሻ የሳንባ ነቀርሳን ያስከትላል፡፡ በርካታ የጥላ ዛፎች ቅጠልን በብዛት ያረግፋሉ፡፡ እነዚህ ቅጠሎች ቶሎ ተሰብስበው የማይወገዱ ከሆነ ይበሰብሱና አየርን ይመርዛሉ፡፡ ዘርዘር ያሉ ዛፎች ያሉበትና ከቤት በተገቢ ርቀት በተተከሉ ቁጥቋጦዎች የተዋበ ቅጥር ግቢ በቤተሰብ ላይ ደስታን የማምጣት ተጽዕኖ ይኖረዋል፡፡ እነዚህ ተክሎች በአግባቡ ከተያዙ በጤንነት ላይ ምንም ጉዳት አያደርሱም፡፡ ከተቻለ መኖሪያዎች ከፍ ባለና ደረቅ ቦታዎች ላይ መገንባት አለባቸው፡፡ ቤት ውኃ በሚያቁር ቦታ ከተገነባና ውኃው ለተወሰነ ጊዜ ቆይቶ ከጊዜ በኋላ የሚደርቅ ከሆነ መርዘኛ የሆነ ቀፋፊ የአየር ፀባይ ይፈጠራል፡፡ የዚህ ውጤቶች እንደ ወባ የሚያንቀጠቅጥ ብርድና ትኩሳት፣ የጎሮሮ ቁስለት፣ የሳንባ በሽታዎች እና ትኩሳቶች ናቸው፡፡ {2SM 463.3} Amh2SM 463.3
ብዙዎች ስለጠየቁት ብቻ እግዚአብሔር ከበሽታ እንደሚጠብቃቸው ይሰማቸዋል፡፡ ነገር ግን እምነታቸው በተግባር ፍጹም ስላልሆነ እግዚአብሔር ፀሎታቸውን አልተቀበለውም፡፡ ለራሳቸው ጤንነት ሳይጠነቀቁ በቀጣይነት የጤናን ሕግ እየጣሱ ያሉትንና በሽታን ለመከላከል ምንም ጥረት የማያደርጉትን ሰዎች ከበሽታ ለመከላከል እግዚአብሔር ተአምር አይሰራም፡፡ ጤንነት እንዲኖረን በእኛ በኩል የሚቻለንን ሁሉ ስናደርግ የተባረኩ ውጤቶች እንደሚከተሉ መጠበቅ እንችላለን፣ ጤንነታችንን ለመጠበቅ የምናደርገውን ጥረት እንዲባርክልን እግዚአብሔርን በእምነት መጠየቅ እንችላለን፡፡ በዚህ ስሙ የሚከበር ከሆነ ጸሎታችንን ይሰማል፡፡ ነገር ግን ሁሉም መስራት ያለባቸው ሥራ እንዳለ ይገንዘቡ፡፡ ከግድ የለሽነታቸው የተነሳ ለጤና ሕጎች ትኩረት ባለመስጠት ራሳቸውን ሕመምተኛ የሚያደርገውን መንገድ እየተከተሉ ያሉ ሰዎችን ጤንነት ለመጠበቅ እግዚአብሔር በተአምራዊ ሁኔታ አይሰራም፡፡ -- How to Live, No. 4, pp. 54-64. {2SM 464.1} Amh2SM 464.1