የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
ጽንፈኛ አቋሞችን በተመለከተ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
ቤተ ክርስቲያንን የመርዳት አቅም ያላቸው ግን በመጀመሪያ የራሳቸውን ልብ በሥርዓት መጠበቅ ያለባቸው አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ አንዳንዶች በክርስቲያን ሕብረት ውስጥ አነስተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን ነገሮች በማጉላት እና ከባድ ሸክሞችን በሌሎች ላይ በመጫን ሀሰተኛ መስፈርቶችን እያመጡ የራሳቸውን ሀሳቦችና ምኞቶች መስፈርት አድርገው ነበር፡፡ በመሆኑም ለቤተ ክርስቲያን ከባድ ጉዳትን ያስከተለ የነቀፌታ፣ ስህተት የመፈለግ እና የመከፋፈል መንፈስ ገባ፡፡ ይህ በማያምኑት ሰዎች ዘንድ ያሳደረው ተጽእኖ ሰንበት ጠባቂ አድቬንቲስቶች የአክራሪዎችና የጽንፈኞች ስብስብ እንደሆኑ እና ልዩ የሆነ እምነታቸው ክፉዎች፣ ትህትና የሌላቸውና በባሕርያቸው ክርስቲያን ያልሆኑ እንደሆኑ አድርጎ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ ጥቂት ጽንፈኞች የተከተሉት መንገድ የእውነት ተጽዕኖ ወደ ሕዝብ እንዳይደርስ ከለከለ፡፡ Amh2SM 318.3
አንዳንዶች ሌሎች የለበሷቸውን ልብሶች በመንቀፍና ከእነርሱ ሀሳብ ጋር በትክክል የማይገጥመውን እያንዳንዱን ነገር ለመኮነን በመዘጋጀት የአለባበስ ጉዳይን የመጀመሪያ ቦታ ሲሰጡ ነበር፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ስዕሎችን በተመለከተ ሁለተኛው ትዕዛዝ የሚከለክለው ነገር ስለሆነ ይህን የሚመስል ነገር ሁሉ መጥፋት አለበት በማለት ስዕሎችን አውግዘዋል፡፡ Amh2SM 319.1
እነዚህ አንድ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ወደ አእምሮአቸው የሚመጣውን አንድ ነገር እንዲተገበር ግፊት ከማድረግ በስተቀር ሌላ ምንም ነገር አያዩም፡፡ ከዓመታት በፊት ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነን መንፈስና ሥራ መጋፈጥ ነበረብን፡፡ ስዕሎችን የሚኮንን መልእክት ተሰጥቷቸው እንደተላኩ በመናገር እና የማንኛውም ነገር ምሳሌ እንዲጠፋ አጥብቀው በማስገንዘብ ተነስተው ነበር፡፡ በላያቸው ቅርጽ ወይም «ስዕል» ያለባቸውን ሰዓቶች እስከማውገዝ ድረስ ርቀው ሄደው ነበር፡፡ Amh2SM 319.2
አሁን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መልካም ህሊና እናነባለን፤ መልካም ብቻ ሳይሆን መጥፎ ህሊናዎችም አሉ፡፡ ሁሉንም ነገር ወደ ጽንፍ የሚወስድና አይሁዶች የሰንበት አጠባበቅን ሸክም እንዳደረጉት ሁሉ የክርስቲያን ተግባራትን ሸክም የሚያደርግ ህሊና አለ፡፡ ኢየሱስ ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን የሰጠው ተግሳጽ ለእነዚህ ሰዎችም ይሆናል፡፡ «ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፣ ፍርድንና እግዚአብሔርን መታዘዝን ስለምትተላለፉ ወዮላችሁ” (ሉቃስ 11፡ 42)፡፡ አንድ ወግ አጥባቂ ካለው ጠንካራ መንፈስና ለውጥ ፈላጊ ሀሳቦቹ ጋር ትክክል መሆን የሚፈልጉ ግለሰቦች የሰዎችን ህሊና የሚጫን ታላቅ ጉዳት ያስከትላሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ከመሰሉ ተጽእኖዎች ሁሉ መጽዳት አለባት፡፡ Amh2SM 319.3