የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
ምዕራፍ 32—ስለ ጸሎት ተገቢ የሆነ አመለካከት
የዓለማት ገዥ ወደ ሆነው አምላክ ጸሎቱን የሚያቀርብ ሰው ሊኖረው የሚገባ አመለካከት ምን መሆን እንዳለበት የሚጠይቁ ደብዳቤዎችን ተቀብያለሁ፡፡ ወንድሞቻችን ወደ እግዚአብሔር ሲጸልዩ መቆም እንዳለባቸው የሚገልጸውን ሀሳብ ያገኙት ከየት ነው? በባትል ክሪክ ለአምስት አመታት ያህል የተማረ አንድ ሰው እህት ኋይት ለሰው ከመናገሯ በፊት ጉባኤውን በጸሎት እንዲመራ ተጠይቆ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀጥ ብሎ ቆሞ ወደ እግዚአብሔር ለመጸለይ ከንፈሮቹን ሊከፍት ሲል በሕዝብ ፊት በግልጽ እንድገስጸው ነፍሴ በውስጤ ተነሳስታ ነበር፡፡ በስሙ ጠርቼ «በጉልበትህ ተንበርከክ» አልኩት፡፡ ይህ ሁልጊዜ ተገቢ የሆነ አኳኋን ነበር፡፡ Amh2SM 311.1
«ከእነርሱ የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፣ ተንበርክኮም ጸለየ” (ሉቃስ 22፡ 41)፡፡ Amh2SM 311.2
«ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፣ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ ጣቢታ ሆይ፣ ተነሺ አላት” (የሐዋ. 9፡ 40)፡፡ Amh2SM 311.3
«እስጢፋኖስም ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጣራ ይወግሩት ነበር፡፡ ተንበርክኮም ጌታ ሆይ፣ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምጽ ጮኸ፣ ይህንም ብሎ አንቀላፋ” (የሐዋ. 7፡ 59፣ 60)፡፡ Amh2SM 311.4
«ይህንም ብሎ ተንበርክኮ ከሁላቸው ጋር ጸለየ” (የሐዋ. 20፡ 36)፡፡ Amh2SM 312.1
«ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፣ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፣ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን» (የሐዋ. 21፡ 5)፡፡ Amh2SM 312.2
«በሠርክም መስዋዕት ጊዜ ልብሴና መጎናጸፊያዬ እንደ ተቀደደ ሆኖ ከመዋረዴ ተነሳሁ፣ በጉልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጄን ዘረጋሁ፡፡ እንዲህም አልሁ፡- አምላኬ ሆይ፣ ኃጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቷልና፣ በደላችንም ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ ብሏልና አምላኬ ሆይ፣ ፊቴን ወደ አንተ አነሳ ዘንድ አፍራለሁ እፈራማለሁ» (ዕዝራ 9፡ 5፣ 6)፡፡ Amh2SM 312.3
«ኑ እንስገድ ለእርሱም እንገዛ፤ በእርሱ በሰራን በእግዚአብሔር ፊት እንንበርከክ” (መዝ. 95፡ 6)፡፡ Amh2SM 312.4
«ስለዚህ ምክንያት በሰማይና በምድር ያለ አባትነት ሁሉ ከሚሰየምበት ከአብ ፊት እንበረከካለሁ» (ኤፌ. 3፡ 14)፡፡ ልብ ለመቀበል ዝግጁ ከሆነ ይህ ምዕራፍ በሙሉ መማር በምንችለው መጠን የከበረ ትምህርት ይሆናል፡፡ Amh2SM 312.5
ወደ እግዚአብሔር ስንጸልይ ማጎንበስ ትክክለኛ አመለካከት ነው፡፡ በባቢሎን አገር ይህን የአምልኮ ተግባር እንዲፈጽሙ ሶስቱ የዕብራውያን ምርኮኞች ተጠይቀው ነበር፡፡… ነገር ግን አምልኮ መቅረብ ያለበት የዓለም ንጉሥ፣ የዓላማት ገዥ ለሆነው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፤ በመሆኑም ሶስቱ ዕብራውያን ምንም እንኳን ጣዖቱ ከንጹህ ወርቅ የተሰራ ቢሆንም ይህን የመሰለ አክብሮት ለመስጠት አሻፈረኝ አሉ፡፡ ይህን ቢያደርጉ ኖሮ፣ ለምንም ዓላማ ይሁን ተግባር፣ ለባቢሎን ንጉስ መስገዳቸው ነበር፡፡ ንጉሱ ያዘዛቸውን ለማድረግ እምቢ በማለታቸው በሚነደው የእቶን እሳት የመጣል ቅጣት ደርሶባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ በአካል በመምጣት ከእነርሱ ጋር በእሳቱ ውስጥ በመመላለሱ ምንም ጉዳት አልደረሰባቸውም ነበር፡፡ Amh2SM 312.6
ተማጽኖአችንን በእግዚአብሔር ፊት ስናቀርብ በጉባኤም ሆነ በግል የአምልኮ ሰዓት በእግዚአብሔር ፊት በጉልበታችን መንበርከክ ግዴታችን ነው፡፡ ይህ ድርጊት በእግዚአብሔር መደገፋችንን ያሳያል፡፡ Amh2SM 312.7
በቤተ መቅደስ ምረቃ ጊዜ ሰለሞን ፊቱን ወደ መሰዊያው አዙሮ ቆሞ ነበር፡፡ በቤተ መቅደስ አደባባይ ውስጥ ከነሃስ የተሰራ መድረክ ወይም መወጣጫ ነበር፤ በዚህ መድረክ ላይ ወጥቶ በመቆም እጆቹን ወደ ሰማይ አንስቶ ግዙፍ የሆነውን የእስራኤልን ጉባኤ ባረከ፣ መላው የእሥራኤል ጉባኤም ቆመ፡፡ Amh2SM 312.8
«ሰለሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፣ ወርዱም አምስት ክንድ፣ ቁመቱም ሶስት ክንድ የሆነ የናስ መደገፊያ ሰርቶ በአደባባዩ መካከል ተክሎት ነበር፣ በላዩም ቆሞ፣ በእሥራኤልም ጉባኤ ሁሉ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ እጁን ወደ ሰማይ ዘረጋ” (2 ዜና 6፡ 13)፡፡ Amh2SM 313.1
የጸለየው ረዥም ጸሎት ለበዓሉ ተገቢ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አነሳስቶት ስለነበር ከፍ ያሉ የአክብሮት ሀሳቦች ጥልቅ ከሆነ ራስን ዝቅ ከማድረግ ጋር ተደባልቀው ከአፉ ይወጡ ነበር፡፡ Amh2SM 313.2