የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)
ሌሎች የተጠቀሱ ፈውሶች
ለሕዝቅያስ የታዘዘው የሾላ ጥፍጥፍ፡፡ ሕዝቅያስ በታመመ ጊዜ የእግዚአብሔር ነቢይ ትሞታለህ የሚል መልእክት አመጣለት፡፡ ንጉሱ ወደ እግዚአብሔር ሲያለቅስ ጌታም ሰማውና በሕይወቱ ላይ አሥራ አምስት ዓመት እንደሚጨምርለት ተስፋ ሰጠው፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነ አንድ ቃል፣ የመለኮት ጣት አንዲት ንካት ሕዝቅያስን ወዲያውኑ ለመፈወስ በቂ ነበር፡፡ ነገር ግን የበለስ ጥፍጥፍ አዘጋጅቶ በቁስሉ ላይ እንዲያደርግ መመሪያ ተሰጠው፡፡ ይህ ከተደረገ በኋላ ሕዝቅያስ ተፈወሰ፡፡ እኛ ከምናደርገው ሕክምና ይልቅ እግዚአብሔር ላዘዘው ለዚህ ትዕዛዝ ዋጋ መስጠት መልካም ነው፡፡ Manuscript 29, 1911 (General manuscript). Amh2SM 299.1
የባሕር ዛፍ ዘይት ጥቅም፡፡ እህት ሲ ደህና አለመሆኗን በመስማቴ በጣም አዝናለሁ፡፡ ለሚያስላት ሕመም ፈውስ እንዲሆናት ከባሕር ዛፍ እና ከማር የተሻለ መድሃኒት ይኖራል ብዬ መምከር አልችልም፡፡ በማር ብርጭቆ ውስጥ የባሕር ዛፍን ዘይት ጥቂት ጠብታዎች አድርጉና በደንብ ካማሰላችሁ በኋላ ማሳል በሚጀምርበት በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ትውሰድ፡፡ ቀላል የማይባል የጎሮሮ ችግር ነበረብኝ፣ ነገር ግን ይህን በተጠቀምኩ ጊዜ ሁሉ ችግሩን በጣም በፍጥነት እቋቋመዋለሁ፡፡ ለጥቂት ጊዜ ከተጠቀምኩ በኋላ ሳሉ ይጠፋል፡፡ ይህንን ትዕዛዝ ከተጠቀማችሁ የራሳችሁ ሐኪም መሆን ትችላላችሁ፡፡ የመጀመሪያው ሙከራ ፈውስ ካላመጣ እንደገና ሞክሩ፡፡ ለመውሰድ የተሻለው ጊዜ ከመኝታ በፊት ነው፡፡ Letter 348, 1908 (To a worker). Amh2SM 299.2
የጎሮሮ ችግር በሚገጥመኝ ጊዜ የምጠቀመውን ፈውስ ነግሬያለሁ፡፡ አንድ ብርጭቆ የተፈላ ማር እወስድና ጥቂት የባሕር ዛፍ ዘይት ጠብታዎችን ጨምሬ በደንብ አማስላለሁ፡፡ ሳል ሲጀምረኝ የዚህን ድብልቅ አንድ ማንኪያ ስወስድ ወዲያውኑ እፎይታ ይመጣል፡፡ ይህንን በተጠቀምኩ ሰዓት ሁሉ የተሻለ ውጤት አግኝቼበታለሁ፡፡ ሳል ሲያስቸግርሽ ያንኑ መድኃኒት እንድትወስጂ እመክርሻለሁ፡፡ ይህ ትዕዛዝ እጅግ ቀላል ከመሆኑ የተነሳ ለማመን ይክብድሽ ይሆናል፣ ነገር ግን ለበርካታ አመታት ስለሞከርኩት እንድትጠቀሚበት በከፍተኛ ሁኔታ ሀሳብ እሰጣለሁ፡፡ Amh2SM 300.1
ደግሞም የባሕር ዛፍ ቅጠሎች በተጨመረበት ሙቅ ውኃ እግርሽን ታጠቢ፡፡ በእነዚህ ቅጠሎች ውስጥ ትልቅ ጠቀሜታ ስላለ ይህን ከሞከርሽ ቃሎቼ እውነት መሆናቸውን ታረጋግጫለሽ፡፡ የባሕር ዛፍ ዘይት በተለየ ሁኔታ ሳል ሲኖርና በደረትና በሳንባዎች ውስጥ ሕመም ሲኖር ጠቃሚ ነው፡፡ ይህን ቀላል የሆነ እና ምንም ወጪ የማይጠይቀውን መድሃኒት እንድትሞክሪ እጠይቃለሁ፡፡ Letter 20, 1909 (To the worker addressed in the preceding letter). Amh2SM 300.2
የመድሃኒትነት ባሕርይ ያላቸው ዛፎች፡፡ ብዙ ነገሮችን በተመለከተ እግዚአብሔር ብርሐን ሲሰጠኝ ነበር፡፡ የተሻለ ውጤት ማግኘት እንዲቻል የጤና ተቋሞቻችን ከፍታ ባለው ቦታ ላይ መገንባት እና በአበቦችና በውበት ዛፎች ባጌጠ መሬት መከበብ እንዳለባቸው አሳይቶኛል፡፡ Amh2SM 300.3
በአንድ ቦታ የጤና ተቋምን ለመገንባት የመሬት ምንጣሮ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነበር፡፡ በፈረንጅ ጥድ (ፓይን)፣ ጥድ (ሴደር) እና ፍር በሚባሉ ዛፎች መዓዛ ውስጥ ጤና እንዳለ ብርሐን ተሰጥቶኛል፡፡ የመድሃኒትነት ባሕርይ ያላቸው እና ጤንነትን የሚጨምሩ ሌሎች በርካታ ዛፎች አሉ፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ዛፎች በጭካኔ አይጨፍጨፉ፡፡…እንዲኖሩ ተውአቸው፡፡ Letter 95, 1902 (To workers in the south). Amh2SM 300.4
“የእኔ የቅጠል መጠጥ፡፡» ሻይ ፍለጋ ወደ ቻይና ወይም ቡና ፍለጋ ወደ ጃቫ መሄድ የለብንም፡፡ አንዳንዶች እንዲህ ይላሉ፣ «ሲሰተር ኋይት ሻይ ትጠቀማለች፣ በቤቷም ታስቀምጣለች፤ ቤተሰቧም እንዲጠጣ ታቀርባለች፡፡» እኔ ሻይን ስለማልጠቀም እቤቴም ስለማላስቀምጥ የነገሩአችሁ ነገር እውነት አይደለም፡፡ አንድ ጊዜ ውኃዎችን አቋርጬ እየተሻገርኩ ሳለሁ ታምሜ ስለነበርና ምንም የሚቀመስ ነገር ስላልነበረ ትንሽ ቀጭን ሻይ እንደ መድሃኒትነት ወስጃለሁ፣ ነገር ግን ማናችሁም ብትሆኑ እንደገና «እህት ኋይት ሻይ ትጠቀማለች» እንድትሉ አልፈልግም፡፡ ወደ ቤቴ ከመጣችሁ የቅጠል መጠጤን የያዘውን ከረጢት አሳያችኋለሁ፡፡ ወደ ሚሽጋን፣ ወደ ተራሮች ዳር ሊኬ ሬድ ክሎቨር (red clover) የሚባል የሳር ዓይነትን ጫፍ አስመጣለሁ፡፡ ቡናን በተመለከተ በፍጹም መጠጣት አልችልም፣ ስለዚህ እህት ኋይት ቡናን ትጠጣለች ብለው መረጃ የሰጡት ሰዎች ተሳስተዋል፡፡ Manuscript 3, 1888 (Sermon, Oakland, California). Amh2SM 301.1
የክሎቨር አበባዎች- የመጀመሪያ መከር፡፡ ማቅረብ የምፈልገው ጥያቄ አለኝ፡፡ እነዚህ ሕፃናት ባለፈው ዓመት የሰበሰቡልኝን ያህል ወይም ከዚያም በላይ ሊሰበስቡልኝ ይችላሉን? ይህን ማድረግ ከቻሉ ትልቅ ውለታ ዋሉልኝ ማለት ነው፡፡ እዚህ እኔ መሰብሰብ አልችልም፡፡ በእኛ መሬት ላይ ክሎቨር የለም፡፡ የመጀመሪያው መከር ይመጣል፣ ነገር ግን ይህን ለማድረግ ጊዜ ካለፈበት ሁለተኛውን ምርት መሰብሰብ ይሻላል፡፡ Letter 1, 1872 (To a family in Michigan). Amh2SM 302.1
ሻይን እንደ መጠጥ ሳይሆን እንደ መድኃኒት መጠቀም፡፡ አረንጓዴውንም ሆነ ጥቁሩን ሻይ አልጠቀምም፡፡ አንድ ጊዜ ውቂያኖስ እየተሻገርኩ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እዚሁ ሆኜ ታምሜ እያስታወክሁ ሳለሁ ከወሰድኩት በቀር አንድ ማንኪያ ሻይ አንኳን ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም፡፡ Amh2SM 302.2
ከእኛ ጋር አብረህ በነበርክ ጊዜ ሻይን አልተጠቀምኩም፡፡ እንደ ነገርኩህ የቀይ ክሎቨርን ጫፍ ሁልጊዜ እጠቀማለሁ፡፡ ለአንተም ሰጥቼ ጥሩ፣ ቀላል፣ እና የተሟላ መጠጥ እንደሆነ ነግሬሃለሁ፡፡… Amh2SM 302.3
ለዓመታት የአንዲት ሳንቲም ዋጋ ያለው ሻይ እንኳን አልገዛሁም፡፡ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ስለማውቅ ከባድ ትውከት በሚከሰትበት ጊዜ እንደ መጠጥነት ሳይሆን እንደ መድሃኒትነት ከምወስድ በስተቀር ልጠቀመው አልደፍርም፡፡… Amh2SM 302.4
አንድ ነገር እየሰበክሁ ሌላ ነገር አላደርግም፡፡ እራሴ የማልጠቀምባቸውን የሕይወት ደንቦች ለአድማጮቼ አላቀርብም፡፡… Amh2SM 302.5
ከቀይ ክሎቨር ቀንበጥ ከሚሰራ ሻይ በስተቀር ማንኛውንም ሌላ ሻይ የመጠጣት ወንጀል የለብኝም፤ ወይንን፣ ሻይን እና ቡናን ብወድም ለጤንነት እና በእነዚህ ሁሉ ነገሮች ለጤናማ አኗኗር ምሳሌነት ዋጋ ስለምሰጥ እነዚህን ጤንነትን የሚጎዱትን አደንዛዥ እፆች አልጠቀምም፡፡ ለሌሎች መሻትን የመግዛትና የጥሩ ሥራዎች ምሳሌ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ Letter 12, 1888 (To a minister of a West coast). Amh2SM 302.6
ቡና እንደ መድሃኒት፡፡ አስቀድሜ እንደነገርኳችሁ ታምሜ በነበርኩበት ሰዓት ጥሬ እንቁላል ተሰብሮ የተጨመረበትን በጣም ጠንካራ የሆነ አንድ ሲኒ ቡና ከመጠጣቴ በስተቀር ለሃያ ዓመታት ያህል እያወቅኩ ትክክለኛውን ቡና አልጠጣሁም፡፡ Letter 20, 1882 (To friends). Amh2SM 302.7
የወይን ጭማቂና እንቁላሎች፡፡ ድህነት ባጠቃው አመጋገብህ አካልህን እየጎዳህ እንዳለህ ብርሃን ተሰጥቶኛል፡፡… ይህን ያህል ከፍተኛ ሥቃይ እየደረሰብህ ያለው ተገቢ የሆነ ምግብ ከማጣት የተነሳ ነው፡፡ ደካማ የሆነ የአካል ብርታትህን ለመገንባት አስፈላጊ የሆነ ምግብ አልተመገብክም፡፡ ጥሩና የተሟላ ምግብን ለሰውነትህ መንፈግ የለብህም፡፡ የጤናማ ዶሮዎችን እንቁላል ተጠቀም፡፡ እነዚህን እንቁላሎች ጥሬውንም ሆነ ብስሉን ተጠቀም፡፡ ጥሬ እንቁላሎችን ልታገኝ በምትችለው ያልፈላ ወይን ውስጥ ጨምራቸው፡፡ ይህ ለአካልህ የሚያስፈልገውን ነገር ይሰጣል፡፡ …እንቁላሎች መርዞችን በመከላከል ረገድ የመፈወስ ባሕርያት ያላቸውን ነገሮች ይይዛሉ፡፡ Counsels on Diet and Foods, pp. 203, 204 (To Dr. D. H. Kress, 1901). Amh2SM 303.1