የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)

220/349

ባለግርማው የትንሣኤ ማለዳ

በፒትካይርን ደሴት ላሉ ወንድሞች የተላከ መልእክት

የደረሰባችሁን ጥልቅ የሆነ መከራ በመስማታችን በጣም አዝነን ነበር፡፡ በተወደደው ወንድማችን የጄ አር ማክኮይ ቤተሰብ ላይ በደረሰው ሞት ልባችን እጅግ አዝኗል፡፡ በዚህ መከራ ምክንያት ላዘኑት ሁሉ ሀዘኔታችንን እንገልጻለን፡፡ በዚህ ሞት ምክንያት ልባቸው ለቆሰለባቸው ልጆችና ለቤተሰብ አባላት ሀዘናችንን እንገልጻለን፣ ነገር ግን ብቸኛ ተስፋችሁና ማጽናኛችሁ ወደሆነው ወደ ኢየሱስ እናመለክታችኋለን፡፡ በችግር ውስጥ ያለው የውድ ወንድማችን ማክኮይ የትዳር አጋርና እጅግ ትወዳቸው የነበሩ አሁን ግን በሀዘን ላይ ያሉ ልጆች እናት በሞት ጸጥታ ውስጥ ነች፡፡ ነገር ግን ከሚያለቅሱት ጋር እያለቀስን ሳለ ይህቺ የተወደደች እናትና ሴት ልጅ፣ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያናችሁ ሽማግሌ የነበረው ወንድም ያንግ እና ሌሎችም በሞት የተነጠቁት በኢየሱስ ስላመኑና እርሱን ስለሚወዱት በልባችን እንደሰታለን፡፡ Amh2SM 269.1

የሐዋርያው ጳውሎስ ቃሎች ያጽናኑአችሁ፡- «ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፣ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ ሌሎች ደግሞ እንዳታዝኑ፣ አንቀላፍተው ስላሉት ታውቁ ዘንድ እንወዳለን፡፡ ኢየሱስ እንደ ሞተና እንደ ተነሳ ካመንን፣ እንዲሁም በኢየሱስ ያንቀላፉትን እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያመጣቸዋልና፡፡ በጌታ ቃል የምንላችሁ ይህ ነውና እኛ ሕያዋን ሆነን ጌታ እስኪመጣ ድረስ የምንቀር ያንቀላፉትን አንቀድምም፤ ጌታ ራሱ በትዕዛዝ በመላእክትም አለቃ ድምጽ በእግዚአብሔርም መለከት ከሰማይ ይወርዳልና፣ በክርስቶስም የሞቱ አስቀድመቀው ይነሳሉ፤ ከዚያም በኋለ እኛ ሕያዋን ሆነን የምንቀረው ጌታን በአየር ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ እንዲሁም ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን፡፡ ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል ተጽናኑ” (1ኛ ተሰ. 4፡ 13-18)፡፡ Amh2SM 269.2

የሰዎችን ሀዘኔታ ለማነሳሳት በማለት ብቻ ሙታን ምንም ባይሰሙም የማይረባ ሙሾ በማውረድ ቀናትንና ሌሊቶችን ለማሳለፍ እኛ አህዛብ አይደለንም፡፡ ጓደኞቻችንና ዘመዶቻችን ከእኛ ለዘላለም እንደተለዩብን አድርገን የሀዘን ልብስ መልበስ ወይም ያዘነ ፊት ማሳየት የለብንም፡፡ ዮሐንስ እንዲህ ይላል፣ “የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁት ኢየሱስንም በማመን የሚጸኑት ቅዱሳን ትዕግሥታቸው በዚህ ነው፡፡ ከሰማይም፡- ከእንግዲህ ወዲህ በጌታ የሚሞቱ ሙታን ብጹአን ናቸው፡፡ መንፈስ፡- አዎን ከድካማቸው ያርፉ ዘንድ፣ ሥራቸውም ይከተላቸዋል ይላል ብለህ ጻፍ የሚል ድምጽ ሰማሁ” (ራዕይ 14፡ 12፣ 13)፡፡ Amh2SM 270.1

በኢየሱስ አንቀላፍተው ያሉትን እነዚህን የምንወዳቸውን ሰዎች በተመለከተ እነዚህ የዮሐንስ ቃላት ምንኛ ተገቢ ናቸው፡፡ ጌታ ስለወደዳቸው፣ እነርሱ በሕይወት እያሉ የተናገሯቸው ቃላት፣ የሚታሰቡ የፍቅር ሥራዎቻቸው፣ በሌሎች ይደገማሉ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ፈቃደኛ እንዲሆኑና እርሱን የሚያስደስት ነገር እንዲፈጽሙ በውስጣቸው ስለሰራ በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ ከሙሉ ልብ መሳተፋቸው ሌሎች የሚከተሉትን ምሳሌ ትቶ ያልፋል፡፡ Amh2SM 270.2

“ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፣ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው እርሱ በእናንተ በሚኖረው መንፈሱ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወት ይሰጠዋል” (ሮሜ 8፡ 11)፡፡ እነዚህ ቃላት ለእያንዳንዱ በሞት ሀዘን ውስጥ ላለ ሰው እንዴት የከበሩ ናቸው! ክርስቶስ በመከራዎቻችን ሁሉ የሚያጽናናን መሪያችንና አጽናኛችን ነው፡፡ መራራ ጽዋን እንድንጠጣ ሲሰጠን፣ የበረከት ጽዋንም በከናፍሮቻችን አጠገብ ይይዝልናል፡፡ ልብን በመገዛት፣ ከማመን በሚገኝ ደስታና ሰላም በመሙላት፣ ጌታ ሆይ፣ የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይሁን እንድንል ያስችለናል፡፡ «እግዚአብሔር ሰጠ፣ እግዚአብሔር ነሳ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን (ኢዮብ 1፡ 21)፡፡ በዚህ ዓይነት መገዛት ተስፋ ትንሳኤ ያገኝና የእምነት እጅ ዘላለማዊ ኃይል ያለውን እጅ ይይዛል፡፡ “ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሳው እርሱ በእናንተ በሚኖረው መንፈሱ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወት ይሰጠዋል” (ሮሜ 8፡ 11)፡፡ Amh2SM 270.3

በመበስበስ የተዘሩ አካላት የማይበሰብሱ ሆነው ይነሳሉ፡፡ በውርደት የተዘሩት በክብር ይነሳሉ፤ በድካም የተዘራው በኃይል ይነሳል፤ በተፈጥሮአዊ አካል የተዘራው በመንፈሳዊ አካል ይነሳል፡፡ ሟች የሆኑ አካሎች በውስጣችሁ በሚኖረው መንፈሱ ሕይወት ያገኛሉ፡፡ Amh2SM 270.4

ክርስቶስ በስሙ ያመኑትን የራሱ አድርጎ ይቀበላቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ ሟች አካል ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ሰጭ የሆነው የክርስቶስ መንፈስ ኃይል እያንዳንዱን አማኝ ነፍስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያቆራኛል፡፡ በኢየሱስ የሚያምኑ ሕይወታቸው ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ውስጥ ስለተሰወረ ለእርሱ ልብ የተቀደሱ ናቸው፡፡ ሕይወት ሰጭ ከሆነው እንዲህ የሚል ትዕዛዝ ይመጣል፣ «በምድር የምትኖሩ ሆይ፣ ጠልህ የብርሃን ጠል ነውና፣ ምድርም ሙታንን ታወጣለችና ንቁ ዘምሩም» (ኢሳ. 26፡ 19)፡፡ Amh2SM 271.1

ሕይወት ሰጭ የሆነው ራሱ የገዛ ንብረቱን በመጀመሪያው ትንሣኤ የሚጠራቸው ሲሆን የመጨረሻው መለከት ተነፍቶ ብዙ ሰራዊት ወደ ዘላለማዊ ድል እስከሚነሱበት እስከዚያ የድል ሰዓት ድረስ እያንዳንዱ አንቀላፍቶ ያለ ቅዱስ እግዚአብሔር በስሙ የሚያውቀው ስለሆነ እንደ ከበረ እንቁ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ በሕይወት እያሉ በውስጣቸው ባደረው በአዳኙ ኃይል እና የመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች ስለሆኑ ከሙታን እንዲነሱ ተደርገዋል፡፡ Amh2SM 271.2

ክርስቶስ የአብ አንድያ ልጅ እንደሆነ ቢናገርም ባለማመን የተጀቦኑ፣ አግባብ በሌለው ጥላቻ የታጠሩ ሰዎች ቅዱስና ጻድቅ የሆነውን ካዱት፡፡ ተሳድቧል የሚል ክስ ቀርቦበት የጭካኔ ሞት እንዲሞት የተፈረደበት ቢሆንም የመቃብርን የእግር ብረት ሰብሮ ሞትን ድል በማድረግ የተነሳ ሲሆን በተከፈተው የዮሴፍ መቃብር ላይ እንዲህ በማለት አውጆ ነበር፡- «እኔ ትንሣኤና ሕይወት ነኝ” (ዮሐ. 11፡ 25)፡፡ በሰማይና በምድር ላይ ያለው ኃይል ሁሉ ለእርሱ የተሰጠ ስለሆነ ቅዱሳንም በኢየሱስ ከመቃብር ነጻ ሆነው ይወጣሉ፡፡ ያንን ዓለም እና ከሙታን ትንሳኤን ለማግኘት የተገቡ ሆነው ይቆጠራሉ፡፡ “በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግስት እንደ ፀሐይ ያበራሉ” (ማቴ. 13፡ 43)፡፡ Amh2SM 271.3

የትንሣኤ ማግስት እንዴት ያለ ባለግርማ ማግስት ይሆን ይሆን! ክርስቶስ በሚያምኑት ሊደነቅ ሲመጣ እንዴት ያለ አስደናቂ እይታ ይሆን ይሆን! በክርስቶስ ውርደትና ስቃይ ተሳታፊ የሆኑት ሁሉ በእርሱ ክብርም ተሳታፊዎች ይሆናሉ፡፡ በክርስቶስ ከሙታን መነሳት በኢየሱስ አምኖ ያንቀላፋ እያንዳንዱ ቅዱስ አማኝ ከታሰረበት እስር ቤት አሸናፊ በመሆን ይነሳል፡፡ ከሙታን የተነሱት ቅዱሳን እንዲህ በማለት ያውጃሉ፡- “ሞት ሆይ፣ መውጊያህ የት አለ? ሲዖል ሆይ ድል መንሳትህ የት አለ?” (1ኛ ቆሮ. 15፡ 55)፡፡. . . Amh2SM 271.4

ኢየሱስ ክርሰቶስ ሞትን ድል በመንሳት የመቃብርን ብረት ስለሰበረ በመቃብር ያንቀላፉ ሁሉ ድሉን ይጋራሉ፤ ሞትን ድል የነሳው እንዳደረገው ሁሉ እነርሱም ድል በመንሳት ከመቃብር ይወጣሉ፡፡. . . Amh2SM 272.1