የተመረጡ መልእክቶች (ሁለተኛው መጽሐፍ)

208/349

ምዕራፍ 27—ሰው ሞቶባቸው ያዘኑት

በሞት ምክንያት የሚመጣ ሀዘን ልብን ርህሩህና ለስላሳ ያደርጋል

የመከራን ተግሳጽ መቀበል ዕጣዬ ነበር፣ የደረሰብኝ መከራ ከልቤ ውስጥ ጠላትነትን በማስወገድና በርህራሄና በፍቅር በመሙላት አዛኝና ርህሩህ አድርጎኝ ነበር (ከአራት ልጆቿ መካከል ሁለቶቹ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ሞተውባት ነበር፡፡ የመጀመሪያ ልጇ ሄንሪ በአሥራ ስድስት አመቱ ሲሞት የመጨረሻ ልጇ ሄርቤርት ደግሞ በሶስት ወሩ ሞቶባታል፡፡ ሞት ባለቤቷን ጄምስ ኋይትን የጎበኘው በ1881 ዓ.ም በ60 ዓመት ዕድሜው ከአጭር ህመም በኋላ ነበር፡፡ አሰባሳቢዎች)፡፡ ከሞት የተነሳ የሚመጣ ሀዘን፣ ስቃይና መከራ የአዳኜን ክቡር መገለጥ ሳያሳየኝ ያለፈ አልነበረም፡፡ ዓይኖቼ ከላይ በውበት ወደሚያበራው ሰማይ ተስበው ነበር፤ ስለ ዘላለማዊው ዓለምና እጅግ በጣም ታላቅ ስለሆነው ሽልማት ጭላንጭል አግኝቼ ነበር፡፡ ሁሉም ነገር ጨለማ በመሰለ ጊዜ በደመናዎች መካከል ባለው ክፍተት ከዙፋኑ የሚወጡ የፀሐይ ጮራዎች ሀዘኔን ይበትኑ ነበር፡፡ ማናችንም ብንሆን መሪር በሆነ ሀዘን ውስጥ በቆሰለና በተሰበረ ልብ እንድንቆይ አይፈልግም፡፡ የተስፋውን ቀስተ ዳመና ለማየትና ብርሃንን ለሌሎች እንድናንጸባርቅ ወደ ላይ እንድንመለከት ይፈልጋል፡፡ Amh2SM 257.1

የተባረከው አዳኝ እርሱን ማየት እስኪሳናቸው ድረስ ዓይኖቻቸው በዕንባ በታወሩት አጠገብ ይቆማል፡፡ እርሱ እንዲመራን እየጠየቅን በእምነት በእርሱ ላይ ስንጣበቅ እጆቻችንን አጥብቆ ሊይዝ ይናፍቃል፡፡ በእግዚአብሔር ደስ የመሰኘት ዕድል አለን፡፡ የኢየሱስ መጽናናትና ሰላም ወደ ልባችን እንዲገባ ከፈቀድን፣ ታላቅ በሆነው የፍቅር ልቡ አጠገብ እንጠበቃለን፡፡ --The Review and Herald, Nov. 25, 1884. Amh2SM 257.2